ዐብይ ጾም የሚጀምረው መቼ ነው? ጾሙስ ስንት ቀን ነው ❓
ጾም ዛሬ ገባ፤ ዐቢይ ጾም የሚጀምረው ግን በሚቀጥለው ሰኞ ዕለት ነው። (ዝርዝሩን ዝቅ ብዬ አስረዳለሁ።) የካቶሊክ፣ የአንግሊካን፣ የምስራቅ ኦርቶዶክስ እና የተለያዩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ይህን የ40 ቀናት ጾም (Lent) ያካሄዳሉ። (የኢትዮጵያ ፕሬቴስታንቶች ግን ከኦርቶዶክሳዊነት ጋር የተለያዩ መሆናቸው እንዲያሳይላቸው ነው መሰለኝ ይህን ትውፊት አይከተሉም።) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይህን “ጾመ አርብዓ” (ሁዳዴ) እንዲጾሙ ታዛለች፤ ይህንን ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጓ አድርጋ በተቀበለችው መጽሐፈ ሲኖዶስ (ዘሐዋርያት ተደንግጓል)። 40 ቀናት የተመረጡት ጌታ "በገዳመ ቆሮንቶስ" ለአርባ ቀናት መጾሙንና በብሉይ ኪዳንም ሙሴና ኤልያስ የጾሙት በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ጾም በተግባር ሲታይ ግን የአርባ ቀን ጾም ሳይሆን፣ የ54 ቀናት ነው። (አንዳንዶች 55 ያደርጉታል።) ለምን?
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በግለ ታሪካቸው እንዳሰፈሩት ከሆነ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በ40 ቀናቱ ጾም ላይ “ሁለት ባለሰባት ቀን ጾሞች፣ አንዱ ጾመ አርባ ከመጀመሩ በፊት፣ አንዱ ካለቀ በኋላ ተጨምረው፣ እነዚህ ሦስት ጾሞች ተርታውን ስለሚመጡ ነው። ከጾመ አርባ በፊት የሚመጣው (የመጀመሪያው) ጾም “ጾመ ሕርቃል” ይባላል። ጾመ ሕርቃልና ጾመ አርባ እንዳለቁ የሚመጣው (የመጨረሻው) ጾም ደግሞ “ጾመ ሕማማት” ይባላል። ሦስቱ ጾሞች በተለያየ ጊዜ ከመምጣት ይልቅ ተከታትለው የመጡት በአበው ውሳኔ እንጂ፣ ታሪካቸው ተከታታይ ሆኖ አይደለም። ጾመ አርባ የሚጾመው የጌታን ጾም ለማስታወስና ከጌታ ጋር ተባባሪ ለመሆን ነው፤ ጾመ ሕማማት የሚጾመውና የሚሰገደው የጌታን ሥቃይ ለማስታወስና ስርየት ኀጢአት ለማግኘት ነው። ጾመ ሕርቃል የሚጾመው ሕርቃል ላፈረሰው መሐላ ፍዳ ለመክፈል ነው።”
ሕርቃል ማነው?
ሕርቃል (Heraclius) ከ610-641 ባይዛንታይንን የገዛ ንጉሠ ነገሥት ነው። ዋና ከተማው ቁስጥንጥንያ ነበረች። በግዛቱም ውስጥ ኦርቶዶክሳውያን፣ ካቶሊኮች እና አይሁድ ነበሩ። እነዚህም ሦስት ወገኖች በየጊዜው ጠብ የሚፈጥሩና አዲስ ወራሪ በመጣ ቁጥር ከመካከላቸው አንዱ ወራሪውን አስቀድሞ በመቀበል ሌሎቹን ለማስመታት የሚጥሩ ነበሩ። ሕርቃል በፊት የነበረው ንጉሥ ፎቃ በሚገዛበት ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ቁስጥንጥንያን ከብቦ ማስጨነቅ ጀመሩ። ያኔ ክርስቲያኖቹ የፋሲካን በዓል በሚያደርጉበት ጊዜ በየአገሩ ያሉ አይሁድ ተጠራርተው ወረሯቸውና አብያተ ክርስቲያናትን ዘረፉ። መዘበሩ።
ወዲያው ሕርቃል የጦር መኮንን ነበረና የፋርስን ንጉሥ አሸንፎ ሕዝቡን ነጻ ሲያወጣ የቁስጥንጥንያ ነዋሪዎች የገዛ ንጉሣቸውን ገድለው እርሱን አነገሡት። እርሱም ከአገር አገር በውጊያ እየዞረ ኢየሩሳሌም ሲደርስ በዚያን ወቅት አይሁድም ብዙ እጅ መንሻ አመጡለትና እንዳይገድላቸው ቃል አስገቡት፤ አይሁድ ያደረጉት የማያውቀው ሕርቃልም ቃል ኪዳን ገባላቸው። ኢየሩሳሌም ሲገባ ደግሞ የክርስቲያኖቹ ካህናት በዝማሬ ተቀበሉት። የፈራረሱትን አብያተ ክርስቲያናት ያየው ሕርቃል የሆነውን ነገር ቢጠይቅ የአይሁድን ክፋት አጫወቱትና እንዲበቀልላቸው ጥያቄ አቀረቡለት።
እርሱ ግን ለአይሁድ ቃል ኪዳን እንደገባላቸውና ቃል ኪዳኑን ቢያፈርስ እግዚአብሔር እንደሚቀጣው ነገራቸው። ካህናቱ ግን “አይሁድን ተበቀልልን እንጂ ቃል ኪዳኑ አያሳስብህ፤ ንስሓ እንዲሆንህ እኛ ክርስቲያኖቹ ዓለም እስክታልፍ ድረስ ስላንተ በየዓመቱ አንድ ሳምንት እንጾምልሃለን” አሉት። በዚያ ጊዜ ሠራዊቱ አይሁድን እንዲገድሏቸው ትእዛዝ ሰጠ። ብዙዎቹን ፈጇቸው። እነዚያም ኤጴስ ቆጶሳት ስለ ሕርቃል መሓላ መጣስ በየዓመቱ አንድ ሳምንት የንስሓ ጾም እንዲጾሙ ለክርስቲያኖች ሁሉ ላኩባቸው።
እናም “ጾመ ሕርቃል” የንሥሐ ጾም ነው። Encyclopaedia Aethiopica ይህን አሳምሮ ይገልጸዋል፤ “Heraclius was also the Emperor whose repentance for the massacre of Jews in Jerusalem in 630/31 became the alleged reason for adding an (eighth) extra week to the Lent.” በማለት። ጾሙ ራሱን የቻለ ሳምንት ስላስፈለገው፣ በሰባቱ ሳምንታት ጾም ላይ ተጨምሮ ጾሙን የስምንት ሳምንታት አድርጎታል። “ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው” የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ መጽሐፍም፣ “ከዐቢይ ጾም አስቀድማ የምትሆን የሕርቃል ጾም ናት” ይላል (ገጽ 150)።
እናላችሁ የዚህ ሳምንት ጾም ከዐቢይ ጾም ቀድማ የምትመጣ ጾመ ሕርቃል ናት። ጾመ ሕርቃልን ፍትሓ ነግሥቱ ቢጠቅሰውም ዝርዝሩን አይናገርም። ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትም መንፈሳዊ አንድምታው ላይ ያተኩራል እንጂ ታሪኩን አይናገርም፤ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው አገላለጽ። እሳቸውም ታሪኩን ያገኙት አባቶች ወደ ግዕዝ ከተተረጎመው የጊዮርጊስ ወልደ ዓሚድ የዓለም ታሪክ መጽሐፍ ላይ ነው። ስለዚህም አብዛኛው ጿሚ የዐቢይ ጾምን የመጀመሪያ ሳምንት ጾም ታሪክ ሳያውቅ ነው የሚጾመው። ለኢትዮጵያ ጾሙን የሰጠችው የግብፅ ቤ/ክ ታሪኩ በሕይወት ያሉ ወገኖችን የሚያቃቅር ሆኖ ስላገኘችው ታሪኩን መካድ ወይም ለጾሙ ሌላ ምክንያት መስጠትን የተሻለ ሆና ያገኘችው ይመስላል። በእኔ ውስን ንባብ መሠረት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያን የዚህን ሳምንት ጾም “የዝግጅት ሳምንት” በሚል ስያሜ ነው የምትጾመው፤ የዐቢይ ጾም ዝግጅት መሆኑ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደ ታዘብሁት ከሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ግን ይህ ታሪክ በቅጡ የሚታወቅ አይመስለኝም።
ጾመ ሕርቃል የአንድ ሳምንት ጾም ነው፤ ከዚያ የ40 ቀን ዐቢይ ጾም ይቀጥላል። ከዚያም የጌታን ሕማማት መነሻው የሚያደርገው የሐዋርያት ጾም ለአንድ ሳምንት ይቀጥላል። ስለዚህ 7 + 40 + 7 = 54። ከዚያም ይፈሰካል!
ዛሬ ዛሬ ዐቢይ ጾምን የሚጾሙ ጥቂት ወንጌላውያን ክርስቲያኖችን ዐውቃለሁ፤ እኔም ስተባበራቸው ነበር። ታዲያ ከአርባው ቀን በፊት (በዚህ ሳምንት) የሚካሄደውን “ጾመ ሕርቃል” መጾም አለባቸው? ይህስ ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው?
© ጳውሎስ ፈቃዱ
@christian_mezmur🤔