ስለ ትንሽ መሳይ ትልቅ ጉዳዮች
(ኤልሳ ሙሉጌታ)
ማን ከመንገድ ዳር ቡና ጠጡዎች የምንቀበላት ብጣሽ ጤናዳም የሚንሳፈፈባት በስሱ የምትጤስ አንድ ሲኒ ቡና ጠረን ተረጋግቶ ከመንገድ ዳር ትእይንቶች ጋር መማግ ብርቅ ይሆንብኛል ብሎ አሰበ?
በምሽት መገናኛ አያት ለመምጣት ከዘላለም የሚዘልግ ረጅም ሰልፍ ተሰልፈን ወደቤቲ ከሚያዘግም ህዝብ ጋር በአንድ ሚኒባስ ታጭቄ ስጓዝ የየሰውን የቀን ውሎ ድካምና ውጣ ውረድ ሊያስረሳ የመሰለ ዋዘኛ ተሳፋሪ መንገዱን ሙሉ ሲለፈልፍ ተሳፋሪው ሲያውካካ ሲስቅለት " ምን ያስለፈልፈዋል ዝም ብሎ አይሄድም " ብዬ የበገንኩበት ችኮ ሰውዬ ቀልድ በዚህ ፍጥነት ይናፍቀኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር ።
ጧት ስነቃ ታላቅ ድብታ ይከበኛል ሰው በመንቃቱ ይናደዳል ? እኔ ግን እላለሁ ስድሳ አመታት ዛፍ ጥላ ስር እንደዘበት ባንቀላፋው አቤሜሌክ እቀናለሁ ። የልጅነታችን ማለዳዎች በመንቃት ደስታ የተኳሉ ነበሩ በርግጥ በፍርፍር ጠረን ላይ የተንሳፈፉም ናቸው ። እና ዘንድሮም ማልዳ ምትወጣው ጀንበር ያቺ ልጅ ሆነሽ የምታውቂያት ተግተሽ የምናፍቂያት ታትረሽ የምትሞቂያት ናት ቢሉኝ ግራ ይገባኛል ። ማለዳ ሳያት አስባለሁ እያልኩ ለምን ለዘዘች እንዲህ? ? ጀንበር እንደሰው ያረጃል?? ቀትሯ ከቀትር ቀድሞ እሳቷን ይዞ ሲመጣ ረመጥ ወላፈኗ ሲወርድ ጠሃይቱን ግን ምን ነክቷታል?? ብርሃን ስ በምን ተአምር ከእቶን ብሶ ይፋጃል?? አመሻሽ በውሪዎች ድምፅ በወፎች ሰልፍ መሸኘቷስ ለምን ቀረ?? ሌላው ቀርቶ መጥለቂያዋ በስተ ምዕራብ በየት በኩል ተመተረ?? ለዚህ ሁሉ መልስ የለኝም እርሷም ያላት አይመስለኝም ።
ድንገት በህይወቴ ሙሉ ትልልቅ ህልሞቼ ምንድን ነበሩ ብዬ ሳስብ ወንድ ልጅ መውለድ እና ውቅያኖስ ማየት መሆናቸውን ደረስኩበት ።
ወንድ ልጅ ወልጄ ስሙን "ፒያንኪ" እለዋለሁ ያ ከአክሱም እስከ ግብፅና የመን አገሩን ቀጥ አርጎ የገዛ የአሞን ልጅ የሚሉት የምወደው ንጉስ ነው ፒያንኪ ።
ውቅያኖስ ሲባል ስለ ጥልቅ ሰማያዊነት አስባለሁ ሰማያዊ የህይወት ቀለም ነው ሰማያዊ ሰላም ነው ሰማያዊ ውቅያኖስ የአለምን ሃዘንና መከራ ሁሉ አጣጥቦ የሚወስድላት ይመስለኛል ። አለ አይደል የሆነ ውቅያኖስ ላይ ብንቦጫረቅ ከላይ ሰማይን ደርቤ ከስር ውቅያኖስ አንጥፌ አለሜ በምወደው ቀለም ተከቦ ( በሰማያዊ መለከፌን ያየ አንዱ የወንዶች ቀለም እኮ ነው አለኝ ፣ የማርያም መጎናፀፊያ ሰማያዊ ነው አለው አልኩት ። ያኔ ዝም ያለ ይኸው አለ። ) እና እዛ ለደቂቃም ቢሆን መሆን እፈልግ ነበር ።
ስጋት እንደ መርግ በተጫናቸው በኒህ ቀናት መሃል የተገለጠልኝ ነገር ቢኖር የእግዜር ታላቅነት ነው ። የሰው ልጅ ባለፉት ጊዜያት ሁሉ በተለይም ባለፈው መቶ አመት በአለም ላይ ያለውን ሁሉ በቁጥጥሩ ስር ያደረገ መሰለው ። ማንም እና ምንም ከሰውልጆች ቁጥጥር ውጪ ሊወጣ እንዳማይችል ገመተ ምናምን እንኳን ይቺ መከረኛ ምድር ሌሎች ፕላኔቶችንም ካልገዛሁ ካልተቆጣጠርኩ አለ እና በዚህ ሁሉ መታበይ መሃል የዘነጋነው እግዜር ከፅረአርያም መንበሩ ቁልቁል እያየን ተገረመ ተገርሞ ሲያበቃ መንጠራራታችንን ለመቅጣት ቀለል ያለች ጉንፋን ላከ .... ማለት እርሱ እኮ እንደ ስራችን በአሰቃቂ ደዌ ሊመታን ይችል ነበረ ፣ ማዕበል ወጀብ ነጎድጓድ ሁሉን አስተናብሮ አሳቅቆ ሊያሸብረን ይችል ነበር ። ግን ትንሽነታችንን ሊያሳየን ትንሽ መሆናችንን ሲነግረን በትንሽ ጉንፋን ፈተነን ። እንዲህ ይሰማኛል እኔ ።
የሚናፍቁኝ ቀኖች አሉ ። ስለሚናፍቁኝ ነገሮችም አስባለሁ ስለ አመሻሽ የመንገድ መብራቶች አስባለሁ አሁን ላይ ፣ ስለ ክረምት ቀዝቃዛ ነፋሶች ስለ ዝናብ ጠሎች ስለ ጃንጥላ ቀለማት ፣ ስለ ትኩስ አፈር ጠረን ስለ ክረምት አግቢዎች ስለ አደይ አበባ ስለ መንገድ ዳር ኩሬዎች ፣ ስለ ልጃገረዷች ሳቅ ስለ ጎረምሶች ደረት ስለ እናቶች ምርቃት ስለ አባቶች ተግሳፅ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ስለ ጣሪያው ዙሪያ ክሽሽልታዎች ስለ መስኪድ አዛን ፣ ስለ ብዙ ብዙ ነገሮች።
ብዙ ትንሽ የምመስሉ ሁነቶች ግዙፍ እንደሆኑ የምንረዳው ዳግም እናገኛቸው ዘንድ ሁለተኛ እድል ለማግኘት ስንጥር ነው ።