#ETA84 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ድረስ ተማሪዎቻቸውን ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዘዋውሩ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ትዕዛዝ አስተላለፈ።
ባለሥልጣኑ ባወጣው “አዲስ ስታንዳርድ” መሰረት ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ባለፈው መስከረም ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥሪ አቅርቦ ነበር። በዚህም በድጋሜ ምዝገባ ሳያደርጉ የቀሩ እና በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለማቋረጥ የወሰኑ ኮሌጆች እስከ ጥር ወር ድረስ ተማሪዎቻቸውን ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዘዋውሩ ባለሥልጣኑ አዟል፡፡
84 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “ከከፍተኛ ትምህርት የፈቃድ ስርዓት እንዲወጡ” የሚያደርጋቸውን ውሳኔ ባለስልጣኑ ከሁለት ሳምንት በፊት አስተላልፏል። ዘጠኝ በሚሆኑ የትምህርት ተቋማት ላይም ተመሳሳይ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚተላለፍ ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በባለልጣን በመስሪያ ቤቱ የፈቃድ አሰጣጥ እና ጥራት ኦዲት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ ፊርማ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ለ84ቱ የትምህርት ተቋማት የተላከ ደብዳቤ፤ ውሳኔው የተላለፈው በተሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ባለመመዝገባቸው እንደሆነ ይጠቅሳል። የዳግም ምዝገባው ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ “ያልጠራ መረጃ” ያላቸው እና “ባለቤትነታቸው የማይታወቁ ተቋማት” በመኖራቸው” ምክንያት እንደሆነ አቶ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማቱ በዳግም ምዝገባ እንዲያሟሉ ከተጠየቋቸው ጉዳዮች መካከል፤ የ500 ሺህ ብር ተመጣጣኝ ዋስትና፣ የታደሰ የንግድ ፈቃድ እና በአምሮዓዊ ንብረት የተመዘገበ የንግድ ሎጎ ይገኙባቸዋል። የጤና ትምህርት ለሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ከእነዚህ ጉዳዮች ተጨማሪ መስፈርት ተቀምጦላቸዋል።
ባለስልጣኑ የሰጠው ቀነ ገደብ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲጠናቀቅ፤ ትዕዛዙን ተግባራዊ ባላደረጉ የትምህርት ተቋማት ላይ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ክስ እንደሚመሰርት አቶ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ከላከላቸው 84 የትምህርት ተቋማት መካከል እስካሁን ድረስ ሂደቱን አጠናቅቀው ከፈቃድ ስርዓቱ መውጣታቸው የተረጋገጠው አምስት ብቻ ናቸው። #ኢትዮጵያኢንሳይደር
https://t.me/fresh_handoutshttps://t.me/fresh_handouts