ችሎት መድፈር(Contempt of court )
ችሎት የፍትህ አደባባይ እንደመሆኑ ሊከበር የሚገባው ነው፡፡ ሆኖም በተለመደው የህብረተሰብ አኗኗር ዘይቤ ስለችሎት ሲነሳ ችሎት እና የችሎት ዳኛን ከማክበር ባለፈ ፍርድ ቤት ገብተው እስኪወጡ ድረስ እታሰር ይሆን ብለው በፍርሀት የሚዋጡ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በአንፃሩ በእውቀት ማነስና ሌሎች ምክንያቶች የችሎትን ክብር የማያከብሩ በዛው ልክ ይኖራሉ፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ የችሎት መድፈርን ምንነትና የሚያስከትለውን ተጠያቂነት እንመለከታለን፡፡
#የችሎት መድፈር ምንነት
ጠቅለል ባለ መልኩ ችሎት መድፈር ማለት ለሕግ ወይም ለፍርድ ቤት አለመታዘዝ፣ ለችሎት ክብር መንፈግ ወይም የፍርድ ቤትን ሥራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለማወክ መሞከር አልያም ደግሞ በዳኝነት ሥራው ጣልቃ መግባት እና መሰናክል መፍጠር ነው፡፡ ለፍርድ ቤት አለመታዘዝ የምንለው በችሎት ሂደት ውስጥ በዳኛው የሚተላለፉ ትዕዛዞችን አለማክበር ወይም መተላለፍ ነው፡፡ ለችሎት ክብር መንፈግ ደግሞ ፍርድ ቤት ማህበረሰቡ ፍትሕ የሚያገኝበት ስፍራ በመሆኑ ሊሰጠው የሚገባውን አክብሮት ለተቋሙና ለዳኛው አለመስጠት ነው። በሌላ በኩል ፍርድ ቤትን ማወክ፣ ፍርድ ቤት ስራውን እንዳያከናውን መሰናክል መሆን፣ የዳኝነት ሂደቱ ሊካሄድ በማይችልበት ሁኔታ እንዲቋረጥ ማድረግ ወይም ለማቋረጥ መሞከር አልያም ደግሞ ዳኛው በነፃነት ተግባሩን እንዳያከናውን መሰናክል መፍጠርን የችሎት መድፈር ልንለው እንችላለን።
በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ችሎት መድፈር ቀጥተኛ ትርጓሜ ተሰጥቶት ባናገኘውም ከአጠቃላይ ስለችሎት መድፈር የሚያነሱት የፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 480፣ 481 እና የወንጀል ህግ ቁጥር 449 መንፈስ ሲተነተን ፍርድ ቤቶች በዕለት ተዕለት ተግባራቸው በፍርድ ቤት ውስጥ እና ከፍርድ ቤት ውጪ ሊፈጠሩ የሚችሉ ከችሎት ሂደቱ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ማንኛውንም የፍትሐብሔርም ሆነ የወንጀል ጉዳይ የዳኝነት ሥራዎችን የሚያውኩ ወይም የሚያደናቅፉ ተግባራትን የሚያካትት ነው፡፡ ይህም በችሎት ውስጥ በተገኘ በማንኛውም ግለሰብ፣ ችሎቱ ከተሰየመበት ጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባለው ባለ ጉዳይ፣ ችሎት በመከታተል ላይ ባለ ወይም ሌላ ከችሎቱ ውጭ በሆነ ግለሰብ ቢፈፀም ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው። በመርህ ደረጃ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ለጥፋት በሕግ የተቀመጠውን የሕግ ሥርዓት ተክትሎ ማስረጃ በማጣራት በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶና ማስረጃ አቅርቦ ቅጣት የሚወሰን ሲሆን በችሎት መድፈር ሁኔታ ግን ጉዳዩ የሚፈጠረው ችሎት ውስጥ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛውን ወዲያው አስቀርቦ ሊቀጣ ይችላል፡፡
#ችሎት መድፈር የሚያስከትለው ተጠያቂነት
በኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ በአንቀፅ 449 መሰረት ማንም ሰው በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም የፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ
ፍርድ ቤቱን ወይም የዳኝነት ሥራ በማከናወን ላይ ያለውን ዳኛ በማናቸውም መንገድ፣ የሰደበ፣ ያወከ፣ በችሎቱ ላይ ያፌዘ፣ የዛተ እንደሆነ ወይም
የፍርድ ቤቱን ሥራ በማናቸውም ሌላ መንገድ ያወከ እንደሆነ የችሎት መድፈር ወንጀል ይፈፅማል።
ይህ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሳያደርግ ወዲያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስን የሚችል ሲሆን ቅጣቱም ከአንድ አመት የማይበልጥ ቀላል እሰራት ወይም ከሶስት ሺ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው ከችሎት ውጭ ሆኖ ዳኛው ሥራውን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ከሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል አስራት ወይም ከአንድ ሺ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል፡፡ ከችሎት ውጭ ስንል መደበኛ ችሎት ውጪ በዳኞች ፅህፈት ቤቶች ላይ የሚሰሩ የዳኝነት ወይም የምርመራ ስራን ሊያካትት ይችላል፡፡
ወንጀሉ የተፈፀመው በችሎት ወይም በማናቸውም ቦታ የዳኝነት ሥርአት በሚካሄድበት ጊዜ ሆኖ በሀይል ወይም በማስገደድ እንደሆነ አግባብ ያለው የወንጀል ህግ አንቀፅ 441 በተደራቢነት ይፈፀማል፡፡ ይህም በዛቻ፣ በማስገደድ ወይም በሀይል ድርጊት የፍርድ ቤቱ ባለሞያዎች ሥራቸውን እንዳያከናውን ወይም ማድረግ የሌለባቸውን እንዲያደርጉ ማስገደድን ወይም ሰራተኛውን መደብደብ የሚያካትት ሲሆን እንደ ጥፋቱ ክብደት፣ እንደተበዳዩ የሥራ ደረጃ እና ወንጀለኛው ወንጀሉን ለመፈፀም እንደተጠቀመው መሳሪያ ሁኔታ ቅጣቱ ከ5 አመት የማይበልት ፅኑ እስራት ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል የፍትሐብሔር ሥነ ሥርአት ህግ ቁጥር 480 የችሎት ሥነ ሥርአትን ለማስከበር ስለሚወሰዱ እርምጃዎች የደነገገ ሲሆን በዚህም መሰረት የማንኛውም ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ የዳኝነት ሥራ አካሄድ ሥነ ሥርአት ለማስከበር ማንኛውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አመልክቷል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ ለችሎቱ ክብር ወይም ለዳኝነት ሥነ ሥርአት መልካም አመራር ተቃራኒ የሆነ ጠባይ በሚያሳይ ማንኛውም ተከራካሪ፣ ጠበቃ፣ ወይም በችሎቱ ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ሰው ተቃራኒ ተግባሩን በሰራበት ጊዜ በያዘው መዝገብ ላይ መቀጮ ሊወስን ይችላል፡፡ አስፈላጊ የሆነው ማናቸውም እርምጃ ሲባል አጥፊውን መገሰፅ፣ ማረም፣ መምከር፣ ማስጠንቀቅ ወይም ከችሎት እንዲወጣ ማዘዝ ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ በተጨማሪም በወንጀል ህጉ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የወንጀል ተግባር በተፈፀመ ጊዜ ጥፋቱ በተደረገበት ጊዜ በያዘው ፍትሐብሔር መዝገብ ላይ ወዲያውኑ የእስራት ቅጣት ሊወስን ይችላል፡፡
በአጠቃላይ ችሎት መድፈር በህጉ የሚታይበት ሁኔታ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ማህበረሰቡም የችሎት መድፈርን ምንነት በአግባቡ ተረድቶ ሊያስቀጡ ከሚችሉ አላስፈላጊ ተግባራት እስከታቀበ ድረስ የለምንም ፍርሀት ችሎት መታደም የሚችል መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ