🎅 የገና አባት (ቅዱስ ኒቆላዎስ) ለድሆች ሥጦታ ይለግስ የነበረ ቅዱስ አባት ነው። ታሪኩም በስንክሳር ታኅሣሥ 10 ላይ ተጽፎአል። "የገና ዛፍ ባሕላችን አይደለም እነርሱ ክረምታቸውን የሚያስታውሱበት ነው ከእኛ ጋር አይገጥምም" "የተወለደውን ክርስቶስ የበዓሉ ማዕከል እንዳናደርግ ያደርገናል" ማለት ትክክለኛ ነገር ነው። Pagan Origin (የባዕድ አምልኮ መነሻ) አለው ብሎ ጣዖት አምልኮ ነው ማለት ግን ከገደብ ያለፈ ድምዳሜ ነው። በከዋክብት ያመልኩ የነበሩት የጥበብ ሰዎች በሚያመልኩት ነገር ወደ ክርስቶስ ተጠርተዋል ፣ የዙሐል ጣዖት ይከበርበት የነበረውን ዕለት ከክርስትና በኋላ በእስክንድርያ የቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን ሆኗል።
➡️ የራሳችንን የገና ባሕላዊ አከባበሮች የገና ጨዋታን ፣ ቀጤማ መጎዝጎዝ የመሳሰሉትን ማክበር ይገባናል። ከዚያ ውጪ በክርስትና መንፈስ እስከተቃኘና የጌታን በበረት መወለድ ፣ የሰብአ ሰገልን ጉዞ ፣ ከዋክብቱን ፣ የመላእክትን ዝማሬ ፣ የእረኞችን ደስታ ፣ የሰብአ ሰገልን እጅ መንሻ የሚያሳይ እስከሆነ ድረስ የኛ ባሕል ያልሆነውን ሁሉ ጣዖት ነው ብሎ ማንቋሸሽ ፣ የሚያምር ነገርን ሁሉ ማውገዝ ያስመስላል። ቅዱስ ኒቆላስም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምትዘክረው ቅዱስ ስለሆነ አጋጣሚውን ጻድቁን ለማስተዋወቅም ልንጠቀምበት ይገባል። ሥጦታም የምንሠጣጠው የሰብአ ሰገልን ሥጦታ መነሻ አድርገን ሲሆን ልግስናውን ለነዳያን ብናደርገው የበለጠ በረከት እንቀበልበታለን።
ጌታችን ስለተወለደባት ምሽት {ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም} አንዲህ አለ :
‹‹ይህች ምሽት ንጹሕ የሆነውና እኛን ሊያነጻን የመጣው (አምላክ) የተገለጠባት ንጽሕት ምሽት ናት፡፡ ጆሮአችን ንጹሕ ይሁን ፤ ዓይኖቻችንም ወደ ንጹሕ ነገር ይመልከቱ ፤ የልባችን ስሜት ቅዱስ ይሁን! ንግግራችንም አክብሮትን ይሞላ!
➦ ይህች ምሽት የዕርቅ ምሽት ናት ፤ ስለዚህ ማንም ሰው ወንድሙን ተቆጥቶ እንዳያስቀይም! ይህች ምሽት ለዓለም ሁሉ ሰላምን ያስገኘች ምሽት ስለሆነች ማንም ሰው አይሸበርባት፡፡ ይህች ምሽት የደግነት ምሽት ስለሆነች ማንም ሰው ክፉ አይሁን! ይህች ምሽት የትሕትና ምሽት ናትና ማንም ሰው እንዳይታበይባት!
➦ ይህች ምሽት የደስታችን ቀን ስለሆነች የበደሉንን አንበቀልባት! የበጎ ፈቃድ ቀን ናትና የጭካኔ ቀን አናድርጋት! የጸጥታ ቀን ናትና በቁጣ የምንነድባት ቀን አናድርጋት! ዛሬ እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች የመጣበት ቀን ነው ፤ ስለዚህ ጻድቅ ሰው በኃጢአተኞች ላይ አይኩራባቸው! ዛሬ እጅግ ባለጠጋ የሆነው አምላክ ስለ እኛ ደሃ የሆነበት ቀን ነው፤ ስለዚህ ሀብታም ሰው ድሆችን ወደ ገበታው ይጥራቸው፡፡
➦ ዛሬ ያልጠየቅነውን ሥጦታ የተቀበልንበት ዕለት ነው፡፡ ስለዚህ እጆቻቸውን ዘርግተው እየጮኹ ለሚለምኑን ሰዎች የእርዳታ እጃችንን እንዘርጋ! የዛሬዋ ዕለት ለጸሎቶቻችን የሰማያትን በር ከፍታልናለች ፤ እኛም ይቅርታን ለሚጠይቁን ሰዎች በራችንን እንክፈት! ዛሬ አምላክ የሰውነትን ማኅተም በራሱ ላይ አተመ ፤ ሰውም የአምላክነትን ማኅተም ተጎናጸፈ!››
ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
💚
@maedot_ze_orthodox💛
@maedot_ze_orthodox❤️
@maedot_ze_orthodox