"ከአባቶችህ ጋር ትኖር ዘንድ ወደ ገዳምህ ተመለስ" የሚል ቃል መጣ፡፡ በተመለሰም ጊዜ አቡነ አክርስጥሮስ በሰላም ዐረፈ፡፡
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቷ_ቅድስት_ጤቅላ፡- ጤቅላ ማለት "ልጅ፣ ለግላጋ" ማለት ነው፡፡ ቅድስት ጤቅላና ከእርሷ ጋር የነበሩ አራት ደናግል ጥር 30 ቀን ፎላ በሚባል ኃጥእ ቄስ እጅ ሰማዕትነታቸውን ፈጸሙ፡፡ ይህም ፎላ የተባለ ቄስ በአመጽ የሰበሰበው ብዙ ገንዘብ እንዳለው በከሃዲው መኰንን ዘንድ ነገሩበት፡፡ ስለዚህም መኮንኑ ገንዘቡን ሁሉ እንዲወርሱ አዘዘ፡፡ ፎላም ወደ መኰንኑ ዘንድ በመሄድ ገንዘቡን ይመልስለት ዘንድ ቢለምነው እምቢ አለው፡፡ ከሃዲው መኰንንም ስለ እነቅድስት ጤቅላ የምግባር የሃይማኖታቸውን ዜናቸውን በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ እንዲያመጧቸው አዘዘና አስመጣቸው፡፡ ጌታችንን አስክዶ እምነታቸው አውጥቶ ለጣዖት እንዲገዙ ግድ አላቸው፡፡ እነርሱ ግን በእምነታቸው በጸኑ ጊዜ መኰንኑ ፎላንን ጠርቶ "እነዚህ ደናግል ለፀሐይ ይሰግዱ ዘንድ እነርሱን ብትሸግልልኝ ገንዘብህን መልሼ እሰጥሃለሁ" አለው፡፡ ፎላንም እነ ቅድስት ጤቅላን ይሸነግላቸው ጀመረ፡፡ ደናግሉም "አንተ የሰይጣን ልጅ የክብር ባለቤት ክርስቶስን እንክው ዘንድ እንዴት ትፈትነናለህ? አንተ ቀድሞ መምህራችን የነበርክ ስትሆን" ብለው ዘለፉት፡፡ መኰንኑም ይህን ቃላቸውን ከአንደበታቸው በሰማ ጊዜ በጅራፍ ጽኑ ግርፋትን አስገረፋቸው፡፡ እነዚህ ቅዱሳት ደናግል ግን ስለ ጌታችን ይመሰክሩ ነበር እንጂ ምንም አልፈሩም ነበር፡፡ መኰንኑም ፎላንን "የበከተ ብትበላ ደምንም ብትጠጣ ገንዘብህን እመልስልሃለሁ" ባለው ጊዜ እንዳለው አደረገ፡፡ ዳግመኛም "እነዚህን ደናግል ብትገድላቸው ገንዘብህን እመልስልሃለሁ" አለው፡፡ ፎላም ይህን በሰማ ጊዜ እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ልቡ በገንዘብ ፍቅር ተነድፏልና ልቡናውን አጽንቶ ቅዱሳት ደናግሉን ሊገድላቸው ሄደ፡፡ እነርሱም እንዲህ አሉት፡- "ከሃዲ ሆይ የመድኃኒታችንን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በእጅህ ታቀበን አልነበረምን? ስለ ገንዘብ ፍቅር ብለህ እኛን የክርስቶስን በጎች ልታርድ መጣህን?" እያሉ በገሠጹት ጊዜ ሰልፍ እንደተማረ አርበኛ ሰው ሆኖ በሰይፍ ራስ ራሶቻቸውን ቆረጣቸው፡፡ መኰንኑም የፎላንን ብላሽነትና ድንቁርናውን አይቶ ወዲያው በሰይፍ ገደለው፡፡ ፎላም ገንዘቡን፣ ሃይማኖቱንና ነፍሱን አጣ፡፡ የእነዚህም ቅዱሳት ደናግል ስማቸው መሪ የሆነቻቸው ጤቅላ፣ ማርያ፣ ማርታ፣ አመታ፣ አበያ ሲሆን ጥር 30 ቀን ሰማዕትነታቸውን በድል ፈጽመው የክብር አክሊልን ተቀዳጅተዋል፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን በአባ ጎርጎርዮስና አቡነ አክርስጥሮስ በቅድስት ጤቅላ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር30 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግል ድኅሬሃ። ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ። ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበኃሤት"። መዝ 44፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 5፥1-7፣ 1ኛ ጴጥ 5፥2-5 እና የሐዋ ሥራ 9፥37-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 23፥26-32። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የማኅበረ ጻድቃን (ዴጔ) በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
@sigewe https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886 https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKwL