ት/ቤቶቻችን እና መስተጋብራቸው
***
በቤተ ክርስቲያን የአብነት ት/ቤት ወጥ የሆነ ዘመናትን የተሻገረ ርቱዕ ትምህርት ይሰጣል፤ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ይወጡበታል። እነዚህ መምህራን የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ በዚህ የአብነት መሠረታቸው ይመለከታሉ፤ ያብራራሉ።
ቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ ቅርጽ ያላቸው የሥነ መለኮት ት/ቤቶችም አሏት። እነዚህ ት/ቤቶች ሰፋ ያሉ የጥንት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ታሪክ፣ የአበው ድርሳናት (ወደ ግእዝ ተተርጉመው የማናገኛቸውን ወይም ቀድሞ ኖረው በኋላ የጠፉትን ጨምሮ)፣ ንጽጽራዊ ሥነ መለኮት እና ነገረ-መለኮትን ለመረዳት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጥንታውያን ቋንቋዎች ይሰጡባቸዋል። ምርምር እንደሚያስፈልጋቸው በሚታመንባቸው ጉዳዮች ላይ ጥናቶችም ይሠሩባቸዋል።
ቤተ ክርስቲያን አብነቱን እንደያዘች ሥነ መለኮት ት/ቤቶች እንደሚያስፈልጓት አምና ሁለቱንም ይዛለች። ይህ የሌሎች ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት እውነታም ነው።
ለወደፊቱ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ተግዳሮት ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ የሁለቱ ት/ቤቶች መስተጋብር ነው። መፈራረጅ እና መቆሳሰል ብዙ ጉዳት አድርሶ የግለሰቦች መጣያ እና መጠላለፊያ ከመሆኑ በፊት በትልቁ ምሥል ላይ በቂ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። በጉዳዮች ላይ በቂ ውይይት ሳይደረግ ሲቀር ጉዳይ ግለሰባዊ መነቃቀፊያ ወደ መሆን ይወርዳልና።
ጤናማው የአካሄድ መሥመር የቱ ነው? በአብነቱ የማናገኛቸውን ነገር ግን በዘመኑ ለሚነሡ ጥያቄዎች አስፈላጊ የሆኑ የአበው ድርሳናት እና የታሪክ ምንጮች እንዴት እንጠቀም? ተቃርኖ የሚመስሉ ነገሮች ሲገጥሙ እንዴት እንፍታ? የሌሎች ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንት መጻሕፍት ስናነብ የሚያስፈልገው ጥንቃቄ ምንድር ነው? የሚሉት እና መሰል ጉዳዮች ሳይረፍድ እና ችግሮች ሳይገነግኑ ለውይይት መቅረብ ይኖርባቸዋል።
የእኔን አጭር እይታ ላስቀምጥ። በሥነ መለኮት ት/ቤቶች የሚማሩ ሰዎች የአብነቱን ትምህርት ትልቅ ዋጋ ሰጥተው ማጥናት ይገባቸዋል፤ የአብነቱን ት/ት ዜማውን ለመማር ቢከብድ እንኳ ይዘቱን (መልእክቱን) አክብሮ ማወቅ እና መረዳት ግዴታ ይመስለኛል። በአብነት ት/ቤት ያሉ ሊቃውንት ደግሞ የሥነ መለኮት ት/ቤት ውስጥ የሚገኙ ተጨማሪ እውቀቶች እና ምንጮች ቢያገኙ የአብነቱን የበለጠ በጥልቀት ለመረዳት እና ለማብራራት ይረዳቸዋል። ነገሮችን ከታሪካዊ ዳራቸው ለመረዳት እና ታሪካዊ ዓውዳቸውን ለመረዳት የሥነ መለኮት ምንጮች ጠቃሚ ናቸው። በመሆኑም ሳይጠራጠሩት በበጎ ኅሊና ሊያዩት፣ እድሉ ከተገኘም ሊማሩት ይገባል። በተለይ ደግሞ የአብነት መሠረት ያላቸው ሊቃውንት የሥነ መለኮት ት/ቤቶች ውስጥ መኖራቸው ሁለቱንም በአግባቡ የመያዝ ሕያው ምስክሮች ስለሚሆኑ በእጅጉ ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መንገድ ለቤተ ክርስቲያን የሠመረ አገልግሎት ትልቅ መመጋገብ ሊኖራቸው ይችላል።
✍️ዲያቆን በረከት አዝመራው