ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ ነሐሴ 17/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች
1፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው በሚል የቀረበበትን ውንጀላ አዲስ ባወጣው መግለጫ አጣጥሎታል። ቡድኑ ሁለት ደቡብ ኮሪያዊያን ዜጎችን ከሰሜን ኬንያ አፍኖ ለአልሸባብ አሳልፎ ሰጥቷል በማለት የኢትዮጵያና ኬንያ የደኅንነት ተቋማት ያቀረቡበትን ውንጀላም ውድቅ አድርጓል። በኮሪያዊያኑ አፈና ዙሪያ የገለልተኛ ምርመራ ውጤት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የገለጠው ቡድኑ፣ ኾኖም የአልሸባብን አቅም ለማጎልበትና ቱርክ-መራሹ ኢትዮጵያና ሱማሊያ በባሕር በር ውዝግባቸው ዙሪያ ከሚያደርጉት ንግግር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሱማሊያ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲል ራሱ ለአልሸባብ አሳልፎ ሰጥቷቸው ሊኾን ይችላል ብሏል። አልሸባብ ሙስሊሞች በብዛት የሚኖሩባቸውን የኦሮሚያ ክልል ግዛቶች የሱማሊያ ግዛት አድርጎ የሚቆጥር ኾኖ ሳለ፣ የትኛውም የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይል ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ሊመሠርት አይችልም በማለት ቡድኑ አቋሙን ገልጧል።
2፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን የሰገን ዙሪያ ወረዳ አስተዳደራዊ መቀመጫ ሰገን ከተማን ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የተቆጣጠሩ ታጣቂዎች ረቡዕ'ለት ከከተማዋ እንደወጡ ተነግሯል። ታጣቂዎቹ ከከተማዋ የወጡት፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ከተማዋ መግባት መጀመራቸውን ተከትሎ ነው። የዞኑ አስተዳደር፣ በታጣቂዎቹ ጥቃት ስምንት ፖሊሶችና አምስት ሲቪሎች እንደተገደሉ እንዲሁም ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት እንደወደሙ ገልጧል።
3፤ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ ትናንት በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 62 የንግድ መደብሮች እንደታሸጉና 326ቱ ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ በጨመሩና ሸቀጦችን ባከማቹ 67 ሺሕ 158 የንግድ መደብሮች ላይ ርምጃ እንደተወሰደ ገልጧል። የማሸግ ርምጃ ከተወሰደባቸው 31 ሺሕ 384 የንግድ ድርጅቶች መካከል 29 ሺሕ 162 የንግድ ድርጅቶች የውል ስምምነት ፈጽመው ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል ተብሏል። በነጋዴዎች ላይ የተወሰዱትን ተከታታይ ርምጃዎች ተከትሎ፣ በበርካታ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ መረጋጋት እንደታየም ሚንስቴሩ ጠቅሷል።
4፤ ራይድ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ኩባንያ የደንበኞቹንና የአሽከርካሪዎቹን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችለውን ስምምነት ከፌደራል ፖሊስ ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱ፣ በራይድ አሽከርካሪዎችና ታክሲዎች ላይ ወንጀሎች በሚፈጸሙበት ወቅት በፍጥነት እልባት ለመስጠት የሚያስችል የድንገተኛ የስልክ ጥሪ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የወንጀል ክትትልና ፍትሕ አሰጣጥን በጋራ ለማጎልበት፣ የወንጀል ሰለባዎች እንዲያገግሙ ለማገዝ እና በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ እንዲወሰድ ለመከታተል እንደሚያስችል ተገልጧል።
5፤ ብሪታንያ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠሉት ግጭቶች በሲቪሎች ላይ ያስከተሉት ከባድ ተጽዕኖ እንደሚያሳስባት ገልጣለች። ብሪታንያ ይህን ስጋቷን የገለጠችው፣ የዓለማቀፍ ልማት ሚንስትሯ አኔሊሴ ዶድስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አገራቸው ለኢትዮጵያ ሰላምና ጸጥታ በምትሰጠው ድጋፍ ዙሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው። ሚንስትሯ፣ ሁሉም የግጭቶች ተሳታፊ ወገኖች ግጭቶችን እንዲያበርዱና በሰላማዊና አካታች ንግግር ግጭቶችን እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ሚንስትሯ፣ በሱማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል። [ዋዜማ]