‹‹እኔ እንጃ ...እሱን በምን አውቃለሁ? ላገኛት በፈለኩ ጊዜ አጥቼያት አላውቅም፤ ስንገናኝም ከልቧ በሆነ በተፍለቀለቀ ስሜት ነው አብራኝ የምታሳልፈው..በቃኝ ብዬ እሰክለያት በቃህ ብላ ገፍትራኝ አታውቅም፡፡››
ጽዮን ትንፋሽ እያጠራት‹‹ያ ማለት እኮ በጣም ታፈቅርሀለች ማለት ነው››አለችው ፡፡
‹‹ይመስለኛል፡፡››አላት፡፡ በተሰበረ ልብ ‹‹ገባኝ፡፡ ››አለችው፡፡
‹‹ምኑ ነው የገባሽ?››
‹‹ያው የእኔ እና የአንተ ጉዳይ ተስፋ የሌለው መሆኑ ነዋ፡፡ ችግር የለውም ያው ምርጥ ጓደኛዬም መሆንህ አንድ ነገር ነው..ታዲ የእውነት ልንገርህ አንተ በጣም ድንቅ ሰው ነህ፤ አንተን የቀረበች ማንኛዋም ሴት በፍቅር የመውደቅ እድሏ ከፍተኛ ነው..ስለዚህ በተቻለህ መጠን ሴት ባትቀርብ ደስ ይለኛል..ካለበለዚያ አፍቅረው ሲያጡህ ይጎዳሉ፡፡››
‹‹እኔ እኮ አሁን መልሱን የመለስኩልሽ ከእኔ እና አንቺ ጉዳይ ጋር አያይዤው ሳይሆን በቀጥታ ያለውን ነገር ነው፡፡››
‹‹እኔ ደግሞ አያይዤ ተረዳሁታ፡፡››
‹‹ፂ ትንሽ ላብራራልሽ መሰለኝ.. አሁን የነገርኩሽ ልጅ ርብቃ ትባላለች፡፡ አዲስአበባ ነው የምትኖረው፡፡ እንደነገርኩሽ ከአስር አመት በላይ
አብረን ቆይተናል፡፡በየወሩ ወደ አዲስ አበባ የምሄደው ጉዳይ ኖሮኝ ሳይሆን እሷን ለማግኘት ነው፡፡ይሁንና የእኔ እና የእሷ ጉዳይ ትንሽ ለየት ያለ ነው፡፡ እንገናኛለን፣እንዝናናለን፣ብዙ ብዙ ነገር እንጫወታለን፣በፈለግነው መንገድና መጠን(ፍቅር መጠን ባይኖረውም)ፍቅር እንሰራለን፣እንደሰታለን፣ ስለጋብቻ፣ቤት ስለመመስረት፣ልጆችን ስለመውለድ የመሳሰሉትን ጉዳዬች ግን በስህተት እንኳን ርዕሱ ተነስቶ አያውቅም፡፡››
‹‹ይገርማል!! ያንተስ ይሁን አንደኛ በብዙ ነገር የተለየ ባህሪ ነው ያለህ ፤ያም ባይሆን ወንድ ነህ የእሷ ግን::
‹‹ቆይ ቆይ.. ወንድ ነህ ስትይ?›.
‹‹የዘመኑ ወንድ 99 ፐርሰንቱ ስለጋብቻ ሲነሳበት ያጥወለውለዋል፤ አግባ ከምትለው ጦርነት ሂድ ብትለው ይቀለዋል..እያሉ ብዙ ሴቶች ሲያማርሩ ታዝቤያለሁ..የእሷ ግን ይገርማል!!ማንኛውም ሴት አንድ አመት ቢበዛ ሁለት አመት የፍቅረኛዋን ነባራዊ ሁኔታ አይታና አገናዝባ ዝምልትል ትችል ይሆናል.... ከዛ በላይ ግን የወደፊት ህይወታችን እንዴት ነው?› ብላ መጠየቋ አይቀርም ፡፡ቢያንስ በቃል እንኳን ቢሆን ካፈቀራት ወንድ ስለወደፊቱ መተማመኛ ትፈልጋለች፡፡አንዳንዷ ሴት እንደውም አንድን ወንድ በተዋወቀች በአንድ ሳምንትም ‹እንዴት ነው አንጋባም?› ብላ ብትጠይቅ የሚያስገርም አይደለም.. ይህቺኛዋ ግን ያንተ ቢጤ ሳትሆን አትቀርም፡፡››
‹‹ይሆናል .እኔ ግን ሳስበው እሷ ጋብቻ አምርራ የምትጠላ ይመስለኛል፡፡ አንድ ቀን በጨረፍታ እንደነገረችኝ በአባት አና እናቷ መካከል የነበረው የተበላሸ የጋብቻ ታሪክ የማይድን ጠባሳ ጥሎባት ያለፈ ይመስለኛል፡፡በወላጆቾ መካከል በነበረው የዘወትር ጠብና ድብድብ እሷም ሆነች ቀሪ ወንድምና እህቶቾ አሰቃቂ የልጅነት እና የወጣትነት ህይወት እንዲያሳልፉ ሳያረጋቸው አልቀረም፤ በዛም የተነሳ በአለም ላይ የሚመሰረተው ጋብቻ ሁሉ የእናትና የአባቷን አይነት የተበላሸ ጥምረት እንደሆነ አድርጋ የምታስብ ይመስለኛል፡፡››
‹‹አንተስ... ?ማለቴ ስለጋብቻ ያለህ አመለካከት፡፡››
‹‹እኔ እንኳን እንደ እሷ ድፍን ያለ የጥላቻ አቋም የለኝም፤ባይሆን እንደዘመኑ ወንድ እንዳልሽው ኃላፊነቱ በመጠኑ ያስፈራኛል፡፡ ጋብቻ እንደ መፋቀር ቀላል አይደለም፣ኢኮኖሚ ዋስትና ያስፈልገዋል፣የልጆች መጠን መወሰን ያስፈልገዋል፣እነሱን በእንክብካቤ ለማሳደግ የሚያስችል ትዕግስት እና አቅም ያስፈልጋል፣በየጊዜው በባልና ሚስት መካከል ያለውን ፍቅር ማደስ ያስፈልጋል…አረ ጣጣው ብዙ ነው፡፡››
‹‹ቆይ የፍቅር ማደስ ስትል አልገባኝም?››
‹‹እንደእኔ ምልከታ ብዙ ትዳሮች ሚፈርሱት በዚህ ጉዳይ ነው፤ጥንዶቹ ይፋቀራሉ ይጋባሉ..አንድ ቤት መኖር አንድ አልጋ ላይ በየቀኑ መተኛት ሲጀመር መሰለቻቸት የሚባለው ነገር ይመጣል ...አዲስ ክስተት የማጣት ጉዳይ ይከሰታል፤ከዛ ቀጣዩ ሂደት ጭቅጭቅ ይሆናል፡፡ ታዲያ እንደ እዚህ አይነት ምልክቶች በጋብቻ
ውስጥ ሲታዩ ‹‹ጠልቶኝ ነው፡፡›› ...‹‹ሌላ አፍቅራ ነው›› ብሎ እጣት ከመጠቋቆም ችግሩ ተፈጥሮዊ መሆኑን በመረዳት ተጋግዞ መፍትሄ መፈለግ ነው የሚበጀው፡፡ የፍቅር ተሀድሶ ማድረግ ማለቴ ነው፡፡ለምሳሌ በሳምንት አንድ ቀንም ቢሆን አብሮ ከቤት ወጥቶ እራት መብላት ..በወር ካልተቻለ በስድስት ወር አንዴም ቢሆን ከከተማ ወጣ ብሎ ዘና ማለት…ብቻ እንደ አቅምና እንደ ሁኔታው የግል ዘዴን እየፈጠሩ ፍቅርን በየጊዜው ማደስ ያስፈልጋል.....የተዳፈነውን የፍቅር እሳት ጊዜ እየጠበቁ ከመጥፋቱ በፊት መቆስቆሱ የግድ ነው፡፡አየሽ ፍቅር ሽንቁር ገንቦ ነው ይባል የለ.. ለምን ይመስልሻል እንደዛ ሚባለው?ሽንቁር ገንቦ ከላይ ውሀውን ስትጨምሪበት ከስር በሽንቁሩ ያፈሳል፡፡ከላይ መጨመር ያቆምሽ ቀን ውስጥ ያለው ወሀ ፈሶ ያልቅና ባዶ ሽንቁር ገንቦ ብቻ ታቅፈሽ ትቀሪያለሽ ማለት ነው፡፡ፍቅርም ልክ እንደዛ ነው፡፡››
ሌላ የምትለው ነገር ስለሌላት‹‹አይ ጥሩ ነው፡፡›› አለችው ፡፡
‹‹ጽዮን አሁን የሚሰማኝን ስሜት እውነቱን ነው?>>
>
‹‹ርብቃን በጣም ለምጄያታለሁ ...የወደፊቱን ላማክራት እፈልጋለሁ፤የእኔ እና ያንቺን ሁኔታ በእሷ መልስ ላይ የተመሰረተ ነው...››
‹‹እሺ ታዲዬ...ደስ የሚል ሀሳብ ነው፡፡እኔም አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ...አንተ የእኔ መሆን ባትችል እንኳን አይዞህ አታስብ ብቸኛ ሆኜ አልቆራመድም ፤ አንድ ከሶስት አመት በላይ የፍቅር ጥያቄ እያቀረበልኝ ያለ ሰው አለ፤ እኔ አንተን ስላፈቀርኩ ነው እምቢ ያልኩት፡፡ልጁ በጣም ጓደኛዬ ነው፡፡ባላፈቅረውም ማንነቱን በጣም አውቃዋለሁ በዛ ላይ እወደዋለሁ፡፡ ስለዚህ ከእሱ ጋር ቀሪ ህይወቴን ለመኖር ሞክራለሁ፡፡ አንዳንዴ ፍቅር በመላመድ ሊመጣ ይችላል ማለቴ ከቆይታ አብሮ ከመኖር የምፈልገውን አይነት ፍቅር ከእሱ ሊይዘኝ ይችላል ፤ ካልሆነም የምወደውን እና የሚያፈቅረኝን ሰው ማግባት መቻሌም ያን ያህል
የሚያስከፋ አይደለም፤ስለዚህ ነፃ ሆነህ ያለምንም ይሉኝታ እና ተጽዕኖ መሆን ያለበትን ትክክለኛውን ነገር አድርግ፡፡››
‹‹እሺ አመሰግናለሁ… ደህና እደሪ ፡፡››ብሎ ብርድልብሱን ተሸፋፈነና ፊቱን እንዳዞረ ተኛ፡፡
እሷም በመካከላቸውን የነበረውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ አጥፍታ ይተጠቀለለውን አንሶላ ሰርስራ ወደ ውስጥ ገብታ ..ጅርባው ላይ ልጥፍ ብላ አቀፈችውና ተኛች ...በመካከላቻው ትንሽ የሙቀት ጎመራ መንቀልቀል ጀመረ፡፡ >>
✨ይቀጥላል✨
#Share #like and #subscribe my #YouTube
👇
SebscribeYouTube link👇
@atronose' rel='nofollow'>
https://www.youtube.com/@atronose