እርስዎ ምን ይላሉ?
የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣናቸው ቀናት «አሜሪካ ትቅደም» በሚል መርሃቸው መሰረት የውጭ እርዳታ መርሃ ግብሮችን ለመገምገም በሚል የውጭ እርዳታ ለ90 ቀናት እንዲቆም ወስነዋል።ይህም በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ/ም ብቻ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ ላገኘችው ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና መሆኑ ይነገራል።
በየዓመቱ ሥር የሰደደ የምግብ እጥረት የተጋረጠባቸው የገጠር ድሆች እንደ ከባቢ አየር ለውጥ ያሉ አደጋዎች እንዲቋቋሙ፣ ጥሪት እንዲቋጥሩ እና ራሳቸውን እንዲችሉ ለማገዝ ለተዘረጋው የኢትዮጵያ የፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም አሜሪካ 114 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች።
የትራምፕ ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖውን ማጥላት መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ። በጋምቤላ ከልል “አክሽን አጌይንስት ሃንገር” የተባለ የግብረ-ሰናይ ድርጅት በስደተኛ መጠለያዎች ለሚገኙ በተመጣጠነ ምግብ እጦት ለተጎዱ ሕጻናት የሚያቀርበውን እገዛ በዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ምክንያት መግታቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ድርጅቶች ባለሥልጣን ይህን ውሳኔን ተከትሎ ከአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት (USAID) ድጋፍ የሚያገኙ ተቋማት ንብረታቸውን እንዳይሸጡ አልያም ለሦስተኛ ወገን እንዳያስተላልፉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርም በአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት የሚደገፉ ወደ 2.4 ሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አደጋ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።
የትራምፕ ውሳኔ በርካታ ተፈናቃዮችና የሰፍቴኔት ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ላሉባት ኢትዮጵያ ተፅዕኖው ምንድነው? የመውጫ መንገዱስ? ተወያዩበት።አስተያየት ለመስጠት ይኽን ቦት ይጠቀሙ 👉🏾
@dwamharicbot