ሰበር ዜና


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


Connect with ሰበር ዜና to find daily breaking news as they happen in Ethiopia & around the globe all in one place by providing 24/7 coverage from all sources.
Facebook page link https://m.facebook.com/BreakingNewsEthiopia/?ref=bookmarks

Связанные каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


Видео недоступно для предпросмотра
Смотреть в Telegram
ሙሉውን ቪዲዮ ለማየት ከታች ያለውን ሊንክ tag yargu

https://t.me/catizenbot?start=r_3_1406941

https://t.me/memefi_coin_bot?start=r_e9ff4fb14d


ጋዛ በከባድ ፍንዳታ እየተናጠች ባለበት የእስራኤል እግረኛ ሠራዊት ዘመቻውን እያሰፋ ነው!

አርብ ምሽት ጋዛ ሰርጥን ያናወጡ ከባድ ፍንዳታዎችን ተከትሎ የእስራኤል እግረኛ ሠራዊት የሚያካሂደውን “ዘመቻ እያሰፋ” መሆኑን የጦሩ ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ተናገሩ።

ለዚህ ጥቃት ምላሽ ነው በማለት ሐማስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን መግለጹን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።በተጨማሪም የእስራኤል ሠራዊትን በጋዛ ላይ “ተከታታይ ጥቃቶችን” እየፈጸመ መሆኑ ለኤኤፍፒ ገልጿል።

ሠራዊቱ በጋዛ ላይ የሚያካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እያስፋፋ መሆኑን መግለጹን ተከትሎ፣ የጋዛ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ የጋዛ ክፍል ለቀው እንዲወጡ አዟል።ረቡዕ ሌሊት የእስራኤል ታንኮች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ክፍል ዘልቀው በመግባት የተመረጡ እርምጃዎችን ወስደው እንደወጡ መገለጹ ይታወቃል።

ይህም ጥቃት ሠራዊቱ በጋዛ ላይ ለሚያካሂደው የቀጣይ ምዕራፍ ዘመቻ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የታለመ መሆኑን የእስራኤል ጦር ኃይሎች ባለሥልጣናት ተናግረዋል።ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃትን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ነገ ቅዳሜ ሦስተኛ ሳምነቱን የሚይዝ ሲሆን፣ እስራኤል እግረኛ ሠራዊቷን ወደ ጋዛ ለማስገባት እየተዘጋጀች መሆኑ ሲነገር ቀይቷል።

Via BBC


የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት " ኃላፊነት የጎደለው ነው " በማለት እንደማይቀበለው አስታወቀ።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፤ " የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፈናቃዮች አስመልክቶ ባወጣው ሁለተኛው ዘገባ የፌደራል መንግስት ባደረገው ጥረት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ተጋሩ በብዛት ወደ ቄያቸው እንደተመለሱ፤ ሰብአዊ ድጋፍም እየቀረበላቸው እንደሆነ አስመስሎ ይፋዊ ዘገባ አውጥቷል " ሲል ገልጿል።

" በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጋሩ ከቄያቸው ተፈናቅለው በከፋ ሁኔታ በሚገኙበት ወቅት ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ይመለሱ በማለት ሌተ ተቀን  ቢወተውትም የወገኖቻችን መመለስ በሚመለከት አንዳች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባልተደረገበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን መሰል ሃላፊነት የጎደለው ዘገባ ማውጣቱ ፤ ከአሁን በፊት በትግራይ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረውን በደል የሚያስቀጥል " ነው ብሏል።

የፌደራል መንግስት ይህን መሰል ሃላፊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ሆነ ተብሎ በመዋቅሩ ሲለቀቁ የሰላም ሂደቱ የሚያውኩ ፣ መተማመን የሚያጎድሉ መሆናቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢ እርምጃ ወስዶ እንዲያርም ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥሪ ማቅረቡን በመቐለ የሚገኘው የቲክቫህ ቤተሰብ አባል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከላይ ያለውን መግለጫ ካወጣው በኃላ አጭር መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገፁ አሰራጭቷል።
ኮሚሽኑ " በተፈናቃዮች 2ኛ ዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው የጂኦግራፊ ወሰኑ ትግራይን አልሸፈነም ይህም በዝግጅቱ ወቅት ተደራሽ ስላልነበረ መሆኑን እናረጋግጣለን " ብሏል። ኮሚሽኑ የተሳሳተ መረጃን ለማረም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ (IRA) ጋር መተባበሩን እንደሚቀጥል አመልክቷል።


#Oromia

በኦሮሚያ ክልል እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

CDCB (Center For Development &Capacity Building ) ባወጣው ሪፖርት የቡሳ ጎኖፋን መረጃ ዋቢ አድርጎ በኦሮሚያ ክልል እስከ መስከረም ባለው ጊዜ 1.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ከተመዘገቡት ተፈናቃዮች ውስጥ 859,000 (66%) የሚሆኑት ከምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ብቻ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

በመግለጫው የተጠቀሱት ቁጥሮች ምን ያሳያሉ ?

- የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 1,292,323 መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 29 በመቶው ብቻ (374,448) ወደ መጠለያዎች መድረሳቸውን ያመለክታል። 71 በመቶ (916,606) የሚሆኑት በአካባቢው እና ራቅ ብለው በሚገኙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ።

- 739 ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል።

- ከ210,000 በላይ ህጻናት ከትምህርት ውጪ ሆነዋል።

- 1,117 መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ወደ ሥራቸው አልተመለሱም።

- 208 ጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፤  788 በከፊል ወድመዋል። ( ከእነዚህ ውስጥ 13ቱ ሆስፒታሎች ሲሆኑ የተቀሩት ጤና ጣቢያዎች ናቸው)

በዚህ አጭር መግለጫ በምዕራብ ኦሮሚያ እና መካከለኛው አከባቢ በፌዴራል መንግስት እና በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጭ ብሎ በሚጠራውና መንግሥት " ኦነግ ሸኔ " የሚለው ታጣቂ ቡድን መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ድንበር ላይ በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሰው " ፋኖ " በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ጋር በሚፈጠሩ ግጭቶች ለችግሮቹ መንስዔ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

በእነዚህ ግጭቶች በተለይ ሴቶች እና ህጻናት ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው ያለው ይህ አጭር መግለጫ እናቶቻቸውን እና አባቶቻቸውን በድንገት የሚያጡ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው፤ ባል የሞቱባቸው ሴቶች ለዝርፊያ እና ለ አስገድዶ መድፈር (በፆታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት) እና አካላዊ ጥቃት እየተጋለጡ መሆናቸውን ያነሳል።

"በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ውስብስብ እና አሳሳቢ ሁኔታን ፈጥሯል። ይሄን ግጭት ለማስቆም ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ሰላም ማስፈን ያስፈልጋል። በግጭቱ ወቅት ለተፈናቀሉ እና ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች አስቸኳይ የተቀናጀ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።" ሲል በCDCB የቀረበው የፓሊሲ ብሪፍ ጠይቋል።


" ... ሕገወጡ የድርጅቱ #ኦንላይን_ሲስተም ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ፕሮፌሽናል በሆኑ የሙያ ተቋማት በአዲስ መልክ መልማት ይኖርበታል " - አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ

ከሰሞኑ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ግንበቶ አዋልሶ ጨምሮ 42 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች እና ሠራተኞች ከሙስናና ሕገወጥ ተግባር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው ይታወቃል።

ይህንን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛል።

#የግል አስተያየታቸውን ካጋሩት ውስጥ የቀድሞ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ (UAE) የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ሱሌማን ደደፎ አንዱ ናቸው።

አምባሳደር ሱሌማን ፤ የተወሰደው እርምጃ የዘገየ ቢሆንም የይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

" እነዚህ ሰዎች ዘርግተው የሚጠቀሙበትና በበርካታ ደላሎች የሚሠራበት ሕገወጡ የድርጅቱ #ኦንላይን_ሲስተም ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ፕሮፌሽናል በሆኑ የሙያ ተቋማት በአዲስ መልክ መልማት ይኖርበታል " ብለዋል።

አምባደሩ ፤ " ዛሬም የኢትዮጵያ ፓስፖርት በበርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት በደላሎች ሱቆች ውስጥ በይፋ በመቸብቸብ ላይ ይገኛል  " ሲል ገልጸዋል።

" ዜጎቻችን ፓስፖርታቸውን ለማሳደስ እስከ 60,000 ብር የሚጠየቁበት፣ ከቪዛና ከፓስፓርት እድሳት እያንዳንዱ አገልግሎት ጠያቂ $100 ዶላር ላልታወቀ ግለሰብ ወይም ተቋም የሚከፍልበት አሠራር ዛሬም ስላለ በሥራ ላይ ያለው የኦንላይን ሲስተም scrap ተደርጎ በአዲስ መተካት ይኖርበታል። " ብለዋል።

ኦንላይን የቪዛ ጥያቄ አሁንም ሁለት ሦስት ጊዜ ካልተከፈለበት መልስ እንደማይሰጥ ይታወቃል ሲሉም አክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፤ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ፤ ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉት ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጥብቅ መፈተሽ አለባቸው ብለዋል።

" ካሉን ቁልፍ የደህነት ተቋማት መካከል የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መ/ቤት ምን ዓይነት ውርደት/ውድቀት ውስጥ እንደከተተን አይተናል። " ያሉት አምባሳደሩ " ተቋሙ ብቻውን ለዚህ አልበቃም፤ የባሰም እንዳለ ምንም ጥርጥር የለውም፣ በየዕለቱ የምናየውና የምንሰማው ጉዳይ ስለሆነ። " ሲሉ ገልጸዋል።

" ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ በሕጋዊ መንገድ ለማደስ ሁለት ሚሊዮን ብር ጉቦ የሚጠየቅበት አገር ውስጥ መሆናችንን ስናስብ እጅግ በጣም እንደነግጣለን "ም ብለዋል።

" መንግሥት ብዙ ቅድሚያ የሚሰጣቸው (Priorities) ቢኖሩትም የሥልጣን ብልግናና የአስተዳደር በደሎች፣ በተለይም ሌብነት አሁን ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ጉዳዮች መካከል መሆን ይኖርባቸዋል " ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም ኢሚግሬሽን ብቻውን እንዳልበሰበሰ ታውቆ ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉት ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጥብቅ መፈተሽ አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።


#ብሔራዊ_ፈተና

ባለፉት ሁለት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተፈትነው ያለፉት ግን እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው።

ምን የተቀረ ነገር ኖሮ ነው ? የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሰሞኑን በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው ማብራሪያ ሰጥታዋል።

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፦

" የፈተናው ክብደ እና ቅለት ከሆነ ምንም የተቀየረ ነገር የለም።

የፈተና አሰጣጥ እና ዝግጅት ሂደት አለ፤ እራሱን የቻለ ሳይንስ አለው በጣም እንዳይከብድም በጣም እንዳይቀልም።

እስከ ዛሬ ሲሰራ ከነበረው ምንም የተለየ ነገር የለም። የተለየው ፈተና አሰጣጡ ነው።

ፈተና አሰጣጡ ያመጣው ለውጥ ምንድነው ከተባለ ፤ ከዚህ በፊት ፈተናዎች በየትምህርት ቤት ነው የሚሰጡት ፈተና መታተም ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ፣ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ፈተናዎቹ ይሰረቃሉ።

ፈተና ሲሰረቅ የነበረው በተደራጀ መልክ ነው በክልሎች ፈታኞች በየክልሉ ሲሄዱ ትልቅ ግብዣ ተደርጎ ጉቦ ተሰጥቷቸው ተማሪዎቹ እንዲኮራረጁ ይደረጋል። ውጤቱ ትርጉም ያለው አልነበረም።

እኔ ትምህርት ሚኒስቴር የመጣሁ ጊዜ በሁለተኛው ሳምንት ፈተና ሰጥተን ነበር በድሮው አሰጣት ፎርማት ያኔ ነው የማለፊያ ውጤት 50 በመቶ ነው ብለን ፖሊሲ ያደረግነው ፣በወቅቱ ፈተና አሰጣጡን አልቀየርንም ነበር ያኔ ያለፈው 48% ነው። አንዳንድ ክልሎች 70-80 በመቶ አሳልፈዋል።

በምንም አይነት የተማሪዎቹ ችሎታና ብቃት አይደለም። ... መሰረቅ መኮረጁን ለማወቅ ዳታውን ከተታትሎ ማግኘት ይቻላል፤ ግልፅ ነው።

ፈተናው እራሱ የተማሪዎች ችሎታና ብቃት መለኪያ አልነበረም። ያንን ነው የቀየርነው። ከምንም በፊት የሰራነው በተማሪዎች ጭንቅላት ውስጥ በስርቆት፣ በማጭበርበር  ፣ ሌላ ሰው በማስፈተን ፣ በመኮረጅ የሚገኝ ትምህርት የለም የሚል ነው። ይሄን አውቀው እንደ ችሎታቸው እንዲያጠኑ ነው ያደረግነው።

የዛ ውጤት፣ እንደ ሀገር ያለንበትን ልክ ነው ያሳወቀን። በዚህም ይሄ ነው የትምህርት ስርዓቱ ካልን በኃላ ሪፎርሞችን በተግባር አውለን አንድ ትውልድ ቢበላሽብን ቀጣዩን እንዴት እናድናለን ብለን ነው እየሰራን ያለነው። "

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ፤ በ2014 እና በ2015 በድምሩ 1,741,619 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውስደዋል። ከነዚህ ውስጥ ያለፉት በድምሩ 57,301 ተፈታኞች ናቸው።

በዚህ ልክ ተፈታኝ ተማሪዎች መውደቃቸው ዜጎችን ያስደነገጠ ቢሆንም ከነዚህ ተማሪዎች በፊትም ፈተናው አሰጣጡ በዚህ መንገድ ቢሆን ውጤቱ ከዚህ እንደማይለይና የትምህርት ስርዓቱ ውድቀት ከታች ጀምሮ የመጣ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።

ለዚህ ውድቀት ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነት እንዳለበትና ተማሪዎቹን ከሚያስተምሯቸው መምህራን ብቃት አንስቶ ፣ የትምህርት ቤቶች የጥራት ጉዳይ፣ የግብዓት አቅርቦት ሁሉ ሊፈተሽ የሚገባው እንደሆነ የሚያመላክት መሆኑ ይነሳል።


" የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ርችት መተኮስ አይቻልም "- አዲስ አበባ ፖሊስ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ለ #ኤፍቢሲ በሰጠው ቃል ፤ የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ርችት መተኮስ በፍጹም የተከለከለ መሆኑን አሳውቋል።

ፖሊስ ምን አለ ?

- ህብረተሰቡ በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተከለከሉ ነገሮችን በፍጹም መያዝ አይገባውም። ለሚኖሩ ፍተሻዎችም መተባበር አለበት።

- በየአካባቢው በሚደመሩ ደመራዎች አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

- ከዚህ በፊት ደመራ ተደምሮባቸው የማያውቁ ቦታዎች #የጸብ_መነሻ እንዳይሆኑ የድሮዎቹን መጠቀም ይገባል።

- ርችት መተኮስ በፍጹም ክልል ነው። ክልከላው የተደረገው ርችትን ሽፋን በማድረግ ህገወጦች ህገወጥ የጦር መሳሪያቸውን የሚሞክሩበት ጊዜ በመሆኑ ነው። ርችት ሲተኩስ የተገኘ ግለሰብ ሆነ ተቋም በህግ አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል።


#Update

ኢትዮ ቴሌኮም 630 ሺ ደንበኞቹ ዛሬ ይፋ ያደረገውን የ5G ኔትወርኩን መጠቀም ይችላሉ ብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛውን ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ እንዲሁም በአዳማ ከተሞ በሙከራ ደረጃ ሲያቀርብ ቆይቶ ዛሬ በይፋ በአዲስ አበባ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታውቋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛውን ትውልድ (5G) የሞባይል ኔትወርክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከው በአዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር። በቀጣይም በሙከራ ደረጃ በአዳማ ከተማ አገልግሎቱን ሲሰጥ ቆይቷል።

ይህ የ5G ኔትዎርክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ተደራሽነቱን አስፍቶ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ዛሬ በነበረው ይፋዊ የማብሰሪያ መድረክ ላይ ተናግረዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ በኢትዮጵያ ይህንን አገልግሎት በአዲስ አበባ 145 ሳይቶች ላይ የ5G ኔትዎርክ ማስፋፊያ የተደረገ ሲሆን 630 ሺ ደንበኞቹ ይህንን አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችል ቀፎ (Device) መኖሩን አስታውቀዋል።

ይህ አገልግሎት ከተዘረጋባቸው ቦታዎች መካከል ከመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ኤርፖርት፤ ከመስቀል አደባባይ መገናኛ CMC እንዲሁም ወደ ሰሚት የሚወስደው መንገድ፤ ከመስቀል አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ ድረስ፤ ከመስቀል አደባባይ ሜክሲኮ ሳር ቤት እንዲሁም ልደታ ከመስቀል አደባባይ ለገሀር ቸርቸል ጎዳና ይህ መሰረተ ልማት የተዘረጋላቸው አከባቢዎች ናቸው ተብሏል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በመግለጫቸው ተቋሙ በቀን በአማካይ ወደ 2,087 GB የዳታ ትራፊክ መኖሩን የገለጹ ሲሆን ከዚህ ውስጥም የ4G አገልግሎቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ጠቁመዋል።

በአለማችን ወደ 110  ሀገረት በአፍሪካ ደግሞ 16 ሀገራት ይህንን አገልግሎት የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ 1.3 ቢሊዮን ተጠቃሚዎችን የ5G ኔትዎርክ ተጠቃሚ መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።


#ጅግጅጋ

" እኔ ተጎጂ ነኝ፤ ፍትሕ እፈልጋለሁ " - አባት

በጅግጅጋ ከተማ የተደፈረችው ልጅ አባት ምን አሉ ?

አባት ኡጋስ አረብ በጅግጅጋ ከተማ ወረዳ 13 ተብሎ በሚጠራው ቦታ ልጃቸው በራሳቸው ሰራተኞች ከተደፈረች በኃላ መገደሏን ገልጸዋል።

ለቢቢሲ ሶማሊ ክፍል አባት ኡጋስ አረብ ፦

" እኔ ተጎጂ ነኝ፤ ፍትሕ እፈልጋለሁ። እለኔ ልጅ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በዚህ መንገድ ሕይወታቸው ለጠፋ ሁሉ ፍትሕ እንዲሰፍን እጠይቃለሁ።

በወቅቱ መኝታ ቤቴ ውስጥ ተኝቼ ነበር። ቤት ውስጥም ከእኔ ውጭ ትልልቅ ሰዎች አልነበሩም።

ልጄ ጋር ሄጄ ሳያት እየተነፈሰች አልነበረም ደረቷንም በመጫን እንድትተነፍስ ለማድረግ ሞከርኩ።

አንገቷንም ሳየው ገመድ ተጠምጥሞባት ታንቃለች። ገመዱን ቆርጬ ወደ ሐኪም ወሰድኳት።

ለሕክምና ወደ ሆስፒታል አፋፍሰን ብንወስዳትም ሕይወቷ አልፏል።

በሞባይል ጥገና ሱቄ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ አራቱ ሠራተኞቼ በድርጊቱ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል። አንደኛው ሠራተኛዬ ጠፍቷል። " ሲሉ ተናግረዋል።

Via BBC Somali


#ኢትዮጵያ

" ደም አፋሳሽ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ "

በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚታዩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲቆሙ ጥሪ ቀረበ።

ይህን ጥሪ ያቀረበው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው።

ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ፥ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች በንግግርና በምክክር መፍታት ሲገባ በተለያዩ አካባቢዎች እና በተለያዩ ወገኖች እየተወሰዱ ያሉ የኃይል እርምጃዎች የሀገራችን ኢትዮጵያን ደህንነትና ህልውና በመፈታተን ላይ መጥተዋል ሲል አሳውቋል።

ኮሚሽኑ " የተቋቋምኩበትን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረኩ ባለሁበት በዚህ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሥራዬን አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ " ብሏል።

የኮሚሽኑ ምክር ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ/ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ በመላው ሀገራችን የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ ቆመው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አሉን የሚሏቸውን ልዩነቶች ወይም ጥያቄዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በምክክር እንዲፈቱ አስቸኳይ ሀገራዊ ጥሪ አቅርቧል።

ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለድርሻ አካላትን በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየትና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን ያ
አሳውቋል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)


#Amhara

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለት 8 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት " የሰላም እና ዘላቂ መፍትሄ ጥሪ " መግለጫ አቀረቡ።

ጥሪውን ያቀረቡት ፦

👉 የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) 
👉 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል 
👉 የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር 
👉 የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት 
👉 አዲስ ፓወርሀውስ 
👉 የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት 
👉 የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች 
👉 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት 
👉 ሴታዊት ንቅናቄ ናቸው።

ድርጅቶቹ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው ግጭት እጅግ አሳስቦናል ብለዋል።

በመሆኑም  የሚመለከታቸው አካላት፦

- ግጭቶች በሰላማዊ ዘዴዎች የሚፈቱባቸውን መንገዶች ለማግኘት የሲቪል ማኅበራት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የእምነት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃንና የአገር ሽማግሌዎች የተከሰተው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶችና ሥምምነቶች በአማራ ክልልም በሚንቀሳቀሱ ወገኖች እና በፌዴራሉና የክልሉ መንግሥታት መካከል መደረግ የሚችልበት ዕድል እንዲፈለግ ፤

- ትጥቅን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በሰብዓዊ መብቶች እና በሰብዓዊ ሕግጋት (humanitarian laws) እንዲመሩ እና የንፁኃን ደኅንነት እንዲጠበቅ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ እና ሌሎችም ጉዳቶች በክልሉ እንዳይፈፀሙ ከፍተኛ የመከላከል ሥራዎች እንዲከናወኑና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ ፤

- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ወቅት የፀጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙ ፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎች እና ጥቃቶች እንዳይስፋፉ እና የጅምላ እስሮች (indiscriminate mass arrests) እንዳይከናወኑ ፤

- የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና ብዙኃን መገናኛዎች ግጭት አገናዛቢ አዘጋገብን እንዲተገብሩ፣ የሐሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት እንዲገቱ፣ እንዲሁም ሐቁን የሚያንፀባርቁ መረጃዎችን ብቻ ለዜጎች በማድረስ ከግጭት አባባሽነት እንዲቆጠቡ ፤

- ዝርዝር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ለዜጎች ተዳራሽ በሆኑ አማራጮች በተከታታይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)




ጾመ ፍልሰታ እና የቅዱስ ፓትርያርኩ መልዕክት !

በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ " የጾመ ፍልሰታ " መልዕክት አስተለልፈዋል።

ከመልዕክታቸው የተወሰደ ፦

" . . . እንደ እግዚአብሔር ቃልም እንደ አባቶቻችን ትውፊትም የጾመ ፍልሰታ ጾም ሲጾም የበደለ ይቅርታ ጠይቆ፤ ተገቢውንም ካሣ ከፍሎ፣ ቂም በቀሉን አሰርዞ፣ ፍቅርን መሥርቶ ነበረ፤ የተበደለም በበኩሉ ዕርቅን አውርዶ፣ ይቅርታን ሰጥቶ የአእምሮ ማለስለሻና ማስረሻ የሆነውን ካሣውን ተቀብሎ ቂሙንና በቀሉን ከአእምሮው አውጥቶና አጽድቶ፣ ለእግዚአብሔር ሲል ከልብ ይቅር ብያለሁ ብሎ፤ ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ በፍቅር #ይታረቃል ! በዚህ ሁኔታ ፍጹምና ልባዊ ፍቅር ተይዞ ሲጾም ሁሉም ዓይነተ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ይደመሰስለታል። እግዚአብሔርም ይቅርታ ጠያቂውንም፣ ይቅርታ ሰጪውንም አሸማጋዩንም ይባርካል።

ማኅበረቡ በዚህ ቅዱስና ሃይማኖታዊ ባህልና ትውፊት ተጠብቆ ለብዙ ዘመናት አንድነቱንና ሃይማኖቱን ወንድማማችነቱንና ነጻነቱን አስጠብቆ እስከ ዛሬ ደርሶአል፤ ይህ ለሀገራችን ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔር በረከት ነበረ፤ ይህ እውነተኛ በረከት በአሁኑ ጊዜ ቸል በመባሉ ፈተናችን በዝቶአል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ ጥልና መገዳደል በየትኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ሀገር በየትኛውም ማኅበረሰብ ይከሠታል፣ ዛሬም በሀገራችን በተፈጠረው አለመግባባት ከባድ ችግር ተፈጥሮአል፣ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር እንዴት እንደባህላችንና እምነታችን በቀላሉ በዕርቅና በይቅርታ ማስተካከል አቃተን የሚለው ነው ፤ የዘመናችን ልዩ ነገር ይህ ነው ፤ ለዚህም ብዙ የተለያየ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፤ በሃይማኖት ዓይን ሲታይ ግን ለእግዚአብሔር ቃል የምንሰጠው ክብር በእጅጉ ስለተቀነሰ ነው የሚል ሆኖ ይገኛል፣ ይህ ዝንባሌ አሁን ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ አደገኛ ስለሆነ የኦርቶዶክስ ሕዝበ ክርስቲያንም ሆነ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህንን በጥልቀት ሊያጤኑትና ሊያርሙት ይገባል፡፡

ሽማግሌ የሀገር በረከት ነው፤ አስታራቂ ሽማግሌ የችግር ሐኪምና ፈዋሽ ነው፤ የፍቅርና የተግባቦት መሐንዲስም ነው፤ በእግዚአብሔርም ' የሚያስታርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ' ተብሎ ውዳሴ ተችሮአቸዋል፣ እነዚህን ሽማግሌዎች ተጠቅመን ችግሮቻችንን መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው አስገዳጅ ጉዳይ ሆኖአል።

ሁሉም ታየ፤ ሁሉም ተሞከረ ዘላቂ መፍትሔ ሲያመጣ ግን አልታየም፤ እንዲያውም ችግሩ ወደ ሃይማኖት ተዛምቶ ቤተ ክርስቲያንም የገፈቱ ቀማሽ ለመሆን ተገዳለች፡፡

በተጨባጭ እንደሚታወቀው ሕዝብንና ሃይማኖትን ነጣጥሎ ሰላምን ማረጋጋጥ ከቶውኑ ሊታሰብ አይችልም፤ ምክንያቱም ሕዝብ የሃይማኖቱ ቤተሰብ ነው፣ ሃይማኖቱም በሕዝቡ መንፈስ ውስጥ ነግሦ የሚኖር መለኮታዊ ኃይል ነውና፣ ከዚህ አንጻር ' ወልድ ሲነካ አብ ይነካ ' እንደሚባለው ሕዝቡ ሲነካ ሃይማኖቱ ይነካል፤ ሃይማኖቱ ሲነካ ደግሞ ሕዝቡ ይነካል፤ በመሆኑም በተካሄደው ግጭት ብዙ ነገሮች መመሳቀላቸው የማይካድ ቢሆንም ችግሩ በዕርቅና በካሣ በይቅርታና በመተው ካልተዘጋ ለማንም ስለማይበጅ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለዕርቅ ዝግጁ እንዲሆኑ ፤ የበደሉም እንዲክሱ የሀገር ሽማግሌዎችም የማስታረቅ ስራን በሐቅ በገለልተኝነትና ዕንባን በሚያደርቅ ስልት እንዲሸመግሉ መንግሥትም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ "

(የቅዱስ ፓትርያርኩ ሙሉ መልዕክት ከላይ ተያያዟል)


" ከቅርብ ጊዜው ተሞከሯችን መማር አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝ ነው " - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

" ጦርነት መፍትሄ አይኾንም፤ ከትናንት እንማር፤ ችግሮችን በውይይት እንፍታ " ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ምክር ቤቱ ባወጣው የ " ሰላም ጥሪ " መግለጫ ፤ በሃገራችን አንዳንድ አከባቢዎችና በተለይም በአማራ ክልል ከዕለት ወደ ዕለት ተባብሶ የቀጠለውን የፀጥታ መደፍረስ ሁኔታ በአንከሮ እየተከታተለው እንደሚገኝ ገልጿል።

" በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ካደረሰብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ገና በቅጡ እንኳ ባላገገምንበት በዚህ ወቅት፣ ዳግም ወደ ሌላ መጠነ ሰፊ የእርስ በርስ ግጭት መግባት በሕዝባችን ላይ የሚያደርሰው ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቡናዊ ጉዳት በእጅጉ የሚያሳስብ ነው " ብሏል።

ምክር ቤቱ ፤ " ጦርነት ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብኣዊ እልቂትን እና ቁሳዊ ውድመትን ከማስከተል በቀር፣ ለችግሮቻችን መፍትኄ እንደማያስገኝ ከቅርብ ጊዜው ተሞከሯችን መማር አለመቻላችን እጅግ አሳዛኝ ነው " ሲል ገልጿል።

በሀገር ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት የሀገር አንድነት ፀንቶ የቆመባቸውን የእሴት አምዶች በማፍረስ የሕዝባችንን እንድነት የሚንድ በመኾኑ፣ ሁሉም አካላት ሁኔታውን ከማባባስ እንዲቆጠቡና ወደ ውይይት መምጣት የሚቻልበትን መላ እንዲያፈላልጉ ምክር ቤቱ አጥብቆ አሳስቧል።

ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ እጅግ አውዳሚና አክሳሪ ከኾነው ጦርነት የችግር መፍትኄን ከመጠበቅ ይልቅ፣ በአስቸኳይ ወደ ውይይት እንዲመጡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ የሰላም ጥሪ አቅርቧል።

ይህ እንዲሳካ ምከር ቤቱ አስፈላጊውን ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ገልጿል።


#Tigray

በትግራይ ክልል ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች በረኀብ እንደሞቱ ተገለጸ።

በትግራይ ክልል የሰብአዊ ርዳታ ምግብ በይፋ ከተቋረጠ 90 ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች በረሀብ እንደሞቱ፣ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

በተለይ ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕፃናት እና የዕድሜ ባለጸጋ አረጋውያን፣ ይበልጥ እየተጎዱ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረመልስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገ/እግዚአብሔር አረጋዊ መቼ ሞቱ፣ የት አከባቢ፣ እድሜያቸው የሚሉት የሟቾች መረጃ ከተለያዩ አከባቢዎች፤ ከተፈናቃይ አስተባባሪዎች፤ ከዞንና ከክልል አስተባባሪዎች እየደረሳቸው እንደሆነ አንስተዋል።

በዚህም እስካሁን በተሰበሰበው መረጃ የሟቾች ቁጥር ከ1000 ከፍ ማለቱን አስታውቀው አሁንም ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።

ዳይሬክተሩ ፥ ተመዝብሯል ከተባለው የእርዳታ እህል ጎን ለጎን ምርመራው እየተካሄደ የህይወት አድን ሥራው እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የእርዳታ ሰጪ ተቋማት በሚፈልጉት መልኩ መረጃዎችንና ተረጂዎችን የመለየት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ገ/እግዚአብሔር እርዳታው እስካሁን ባለመጀመሩ በተለይ ተፈናቃዮች በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል እያካሄደው ባለው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ ማኅበረሰቡ እና ተፈናቃዮች ዋነኞቹ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሥራቸውን በማቋረጣቸው ከአራት እስከ ሰባት ወራት ለቆየ ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ያለማግኘታቸውን እና በዚህም ቀደም ብሎ የነበረው የሰብአዊ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

የኢሰመኮ የክትትልና ምርመራ ዳይሬክቶሬት ሰላማዊት ግርማይ እንደገለጹት፥ " ከህክምና ተቋማት እንዲሁም በአካል በመገኘት ባለሞያዎች የተለያዩ መረጃዎች ሰብስበዋል። ነገር ግን ክትትሉና ምርመራ ሂደት ላይ ስለሆነ ቁጥሩን መግለጽ አንችልም፤ ሆኖም ባደረግናቸው ክትትሎች ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ታዝበናል " ብለዋል።

ኮሚሽኑ፥ መንግሥትና የእርዳታ ሰጪ ተቋማት ወቅቱን የጠበቀና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ወይም ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ የሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት መልሰው እንዲጀምሩ አሳስቧል።

#ቪኦኤ


በጉራጌ ዞን በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ!

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በምስራቅ መስቃን ወረዳ፤ ሐሙስ ሐምሌ 13/2015 እና ዕሁድ ሐምሌ 16/2015 የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።በወረዳው በቼ እና ዲዳ በተባሉ የቀበሌ ከተሞች፤ ምሽት 3 ሰዓት ላይ ጥቃቱ እንደተሰነዘረ እና ግድያዎች እንደተፈጸሙ ምንጮች ከስፍራው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ ከአካባቢው መሰወራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ አካል አለመኖሩ ተጠቅሷል።በተጠቀሰው ምሽት ላይ ሦሰት ሰዓት አካባቢ በቼ ቀበሌ ውስጥ በተሰነዘረ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው የታወቀ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ዕሁድ ሐምሌ 17/2015 ምሽት ኹለት ሰዓት ገደማ አንድ አባውራ ከነባለቤታቸው እና ጎረቤታቸው ከሆኑ ግለሰብ ጋር መገደላቸውን አዲሰ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በመስቃንና ማረቆ ብሔረሰብ መካከል ባለው የቆየ አለመግባባት በተደጋጋሚ የሚፈጸም ማንነት ተኮር ጥቃት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ለአካባቢው ማህበረሰብ በነጻነት መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑ ተመላክቷል።እንደ ነዋሪዎች ገለጻ፤ በአካባቢው ባለው የሰላም እጦት ሳቢያ አብዛኛውየመንግሥት ሠራተኞች ለደኅንነታቸው በመስጋት በሥራ ገበታቸው ላይ እንደማይገኙ እና ብዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ብሎም የተከፈቱትም አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ተነግሯል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ ከሐሙስ ሐምሌ 13/2015 እስከ ሐምሌ 17/2015 ድረስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቅሰው፤ “በቂ የጸጥታ አካላት ወደቦታው ልከናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም፤ ግድያውን በሚመለከት ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው ወይም አይደለም? የሚለውን ጉዳይ በሚመለከት በመጣራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በጊዜው ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በዞኑ ኹለቱ ወረዳዎች መካከል ዓመታትን ያስቆጠረው ግጭት ዕልባት ሳያገኝ የቀጠለ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ በርካታ አካላት ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት ሙከራ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት ከአራት ዓመታት በፊት ሰላም ሚኒስቴር ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ሰፊ ሥራዎችን ይሰራ እንደነበር ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ችግሮች ተባብሰው መቀጠላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

Via Addis Maleda


" ሱተን ዙሪያ ቀበሌ ድረስ ተከታትለው በመምጣት ነው የገደሉት ፤ ... ይሄን ለማን አቤት ልበል ? " - ወላጅ አባት

በኦሮሚያ ክልል፤ ምዕራብ ሸዋ ዞን  የትራፊክ ፖሊስ አባላት የጠየቁትን ያህል ጉቦ አልሰጥም ያለን አንድ አሽከርካሪ በጥይት ደብድበው መግደላቸውን የሟች ቤተሰቦችና የሥራ ባልደረቦች መግለፃቸውን ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዘግቧል።

ድርጊቱ የተፈፀመው ባለፈው ዓርብ ዕለት ሲሆን በትራፊክ ፖሊስ አባላቱ በጥይት የተገደለው እና ትላንት ስርዓተ ቀብሩ ተፈፀመ የተባለው የ33 ዓመት እድሜ ያለው ሳሙኤል መረተ ነው።

ሳሙኤል መረት ነዋሪነቱ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡

ጓደኞቹ እንዳሉት ሳሙኤል ከረጅም ጊዜ አንስተቶ የአሽከርካሪነት ሥራውን ሲያከናውን የቆየው ከአዲስ አበባ ቡታጅራ በተዘረጋው መስመር ላይ ነበር።

በመስመሩ በሰበብ አስባቡ ካልቀጣንህ የሚሉትን የትራፊክ ፖሊስ አባላት ለማባበል ዝርዝር የ " ሃምሳ ብር " ኖቶችን በእጃቸው እያስጨበጠ ማለፍ የሁልጊዜ ተግባሩ እንደነበር  ጓደኞቹ ይናገራሉ።

ይህ የሃምሳ ብር ጣጣ ታዲያ  " አንሷል ጨምር አልጨምርም " በሚል ከትራፊክ ፖሊስ አባላት ጋር የገባበት እሰጥ አገባ ለህይወቱ መጥፋት ምክንያት መሆኑን ነው በሥፍራው ነበርን ያሉ ገልጸዋል።

የሳሙኤል ረዳት ምን አለ ?

የሳሙኤል መረተ ረዳት ሆኜ ሥሠራ ነበር የሚለው አንዱዓለም ሁሴን ፦

" መንገደኞችን አሳፍረን ከአዲስ አበባ ቡታጅራ በመጓዝ ላይ እያለን በኦሮሚያ ክልል ፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ስንደርስ ሦስት ትራፊኮች ያስቆሙናል።

ሳሙኤል የመውጫ ወረቀት እና ሃምሳ ብር ሲሰጥ ከትራፊኮቹ አንዱ ሀምሳውን ቀይረህ መቶ አድርግ ሲለው ሰምቻለሁ።

ሳሙኤል አሁን የለኝም አልተዘጋጀሁም ሲለው ትራፊኩ አለበለዚያ የተሸከርካሪውን ሠሌዳ እፈታለሁ በማለት በቦክስ መታው፡፡

ይሄኔ በንዴት ተሽከርካሪውን አስነስተን ወደፊት መሄድ ስንጀምር ተከትለው መተኮስ ጀመሩ፡፡

ጥቂት እንደተጓዝን ተሸከርካሪውን በማቆም እኔም ሆንኩ ሌሎች መንገደኞች ደንግጠን ወረደን መሮጥ ጀመርን፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እሱን በጥይት መትተው ጣሉት " ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

የሟች ሳሙኤል አባት አቶ መረተ ለማ በበኩላቸው ፤ ከትራፊክ ፖሊስ አባላቱ ጋር አለመግባባቱ የተነሳው በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ተሬ ወረዳ ላይ ቢሆንም ግድያው የተፈጸመው ግን በጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ሱተን ዙሪያ ቀበሌ ድረስ ተከታትለው በመምጣት  አንደሆነ ገልጸዋል።

" ይህን ለማን አቤት ልበል ? " ሲሉም ጠይቀዋል ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደ/ምዕራብ ሸዋ ዞን የተሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ፈይሳ ደበላን ጉዳዩን በተመለከተ ከሬድዮ ጣቢያው ተጠይቀው ፤ ወንጀሉ የተፈጸመው እሳቸው ከሚመሩበት የተሬ ወረዳ አልፎ ጉራጌ ዞን ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ " በዚህ ላይ እኔ የምለው ነገር የለም ፤ ባይሆን የደቡብ ክልል ፖሊስን ጠይቁ " ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሀመድ ፤ የወንጀሉ አድራሾች በኦሮሚያ ክልል ፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ ድርጊቱን በመፈጸም የተጠረጠሩ ሦስት የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

" የተከሰተው ነገር አሳዛኝ ነው " ያሉት ኮማንደር ጠጄ " የወንጀሉ ተጠርጣሪዎች ወዲያው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ጥሩ ነገር ነው፡፡ አሁን ምርመራውን ከኦሮሚያ ክልል የሥራ ሃላፊዎች ጋር አብረን እየሠራን እንገኛለን ፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው በጉራጌ ዞን ውስጥ በመሆኑ ምርመራውን ወደ ዞኑ ለማዛወር በሂደት ላይ ነው ያለነው " ብለዋል፡፡

#ዶቼቨለ


#ጋምቤላ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የጋምቤላ ክልል አካባቢዎች ሲከሰቱ የቆዩ የትጥቅ ግጭቶችን፣ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶችንና አጠቃላይ የጸጥታ ችግሮችን እና በዚህ ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ተጎጂዎችን፤ የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች እንዲሁም የክልሉን የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎችን በማነጋገር ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በላከልን መግለጫ አሳውቋል።

በተለይ ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር መነሻ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተወሰነ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት መሆነ ማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ይሄው አለመግባባት በፍጥነት ወደ ብሔርን መሠረት ያደረገ ውጥረት እንደተሸጋገረ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

ይህንኑም ተከትሎ የተለያየ ብሔር ታጠቂ ቡድኖች በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ፤ በጋምቤላ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሰፈሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በርካታ ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት ደርሷል።

ኢሰኮ በጸጥታው ችግር ምክንያት ገና ወደ አካባቢዎቹ በአካል ደርሶ ምርመራ ለማድረግ ያልቻለ ቢሆንም፣ ነዋሪዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የወደሙ መሆናቸውን አስረድተዌ።

ጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን በሚመጡ ታጣቂ ቡድኖች በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ በክልሉ በሚኖሩ ብሔሮች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርስ መሆኑ እንደሚታወቅ ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል።

ክልሉ ወደ 350 ሺህ የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በስምንት የተለያዩ ካምፖች ያስተናግዳል።

ከሁለት ወራት በላይ ለዘለቀው የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ችግር እና በክልሉ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመድረስ ላይ ያሉ ግጭቶች ተሳታፊዎችን በተመለከተ ተጎጂዎችም ሆነ የክልሉ የጸጥታ እና የአስተዳደር ኃላፊዎች የተለያዩ ብሔር ታጣቂ ቡድኖችን ኃላፊነት ይጠቅሳሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የክልሉ ኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ በሌላ አካባቢ የአኝዋ ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች እና በአንዳንድ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ አንደሚኖሩ የተገለጸ ሰዎች ጭምር በግጭቶቹ ተሳታፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

እነዚህ ጥቃቶች እና ግጭቶች በአብዛኛው ብሔር ተኮር ሲሆኑ በሌላ በኩል ግጭት የሚደርስባቸውን አካባቢዎች ያለ የብሔር ልዩነት ሁሉንም ነዋሪዎች አካባቢውን ሸሽቶ ለመፈናቀል፣ ለንብረት ውድመት እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያጋለጠ ነው ሲል ኢሰመኮ አመልክቷል።

የክልሉ ጸጥታ ሁኔታ በነዋሪዎች ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰትም የመንግሥትን ተጨማሪ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስገንዝቧል።

(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)




" ታጣቂዎቹ በለሊት ከነ #መሳሪያቸው ወደ ጫካ ገብተዋል " - ከንቲባ አቶ ጊሳ ዙፋህ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፤ ግልገል በለስ " የሰላም ጥሪ ተቀብለው መጡ " የተባሉ ታጣቂዎች ከነትጥቃቸው ወደ ጫካ ተመልሰው ገብተዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ የግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጊሳ ዙፋህ ለዶቼ ቨለ ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።

ከንቲባው ፤ ከሚያዚያ 24 ጀምሮ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ የሰላም ተመላሾች በከተማው ለ2 ወራት ያህል መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዛሬ ሁለት ቀን በፊት ወደ ተሀድሶ ስልጠና እንዲገቡ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ባለበት ሰዓት ባልታወቀ ምክንያት ታጣቂዎቹ በለሊት ከነ መሳሪያአቸው ወደ ጫካ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ለማደረግ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ፤ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በመተከል ዞን ውስጥ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን እና የታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ከፓርቲው ጋር ለማገናኘት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እቃወማለሁ ብሏል።

ፓርቲው ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሀይል እንደሌለው ገልጿል።

በቅርብ " የሰላም ተመላሽ " ተብለድ በመተከል ዞን ግልገል በለስ የነበሩ ታጥቂዎችን የጉህዴን ታጣቂዎች ናቸው በማለት " በድርጅቱ ስም መነገድ የሚፈልጉ " አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፓርቲው አሳስቧል።

በካምፕ ውስጥ የነበሩ ከአንድ መቶ የሚበልጡ የሰላም ተመላሽ የተባሉ ታጣቂዎች ወደ ጫካ መመለሳቸውን ፓርቲው ገልጿል።
 
ፓርቲው፤ ከጥቅምት 9/2015 ዓ.ም አንስቶ ከመንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በስሙ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎቹን በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረጉን አስረድቷል።

በተቀመጠው ስምምነት መሰረት በተዘጋጁ  ዘርፎች ወደ ስራ መሰማራታቸውንም አመልክቷታ።

በአሁኑ ጊዜ በፓርቲው ስም ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ሐይል አለመኖሩን አሳውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፓርቲያቸው ጋር ግንኙነት የሌላቸው በርካታ ታጣቂዎች ከመንግስት ጋር በመስማማት በሰላማዊ መንገድ ወደ ካምፒ መግባታቸውን ያሳወቀው ጉህዴን " በሚያዚያ ወር መጨረሻም ወደ ግልገል በለስ ከተማ የገቡ ታጣቂዎች ከፓርቲው ጋር ግንኙነት የለላቸው እና መንግስት ያደረገላቸውን ሰላማዊ ጥሪ የተቀበሉ  ታጣቂዎች ናቸው " ብሏል።

በዞኑ እና ሌሎች ስፍራዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ከፓርቲው ጋር ለማገናኘት የሚደረጉ ጥረቶችን ተቀባይነት የላቸውም ያለው ጉህዴን " በታጣቂዎች ለሚደርሱት ጥቃቶችም ድርጅቱ ኃላፊነት አይወስድም " ሲል አስረግጧል።

በግልገል በለስ ከተማ ሰነ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት ጸጥታ ሐይሎችን ጨምሮ 11 ሰዎች ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

#ዶቼቨለ

Показано 20 последних публикаций.