🚩 ክርስቶስ ሰው መሆኑ ፍጡር መሆኑን ያሳያልን?
ሙስሊም ወገኖቻችን ክርስቶስ ፍጡር ነው ለማለት የማይፈነቅሉት መሬት፥ የማይደረምሱት ተራራ የለም። እነዚህ ወገኖች፥ ለዚህ እይታ ዋነኛ ነጥባችን የሚሉት የክርስቶስ ሰውነት ነው
"ሰው ፍጡር ነው። ኢየሱስ ደግሞ ሰው ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነው" ከሞላ ጎደል ሀሳባቸው ይህንን ይመስላል። ከመጽሐፍ ቅዱስም፥ ክርስቶስ ሰው ተብሎ የተጠራባቸውን ስፍራዎች በመጥቀስ ፍጡር ነው ለማለት ይሞክራሉ
▶ ነገር ይህ ድምዳሜ የክርስትናን አንኳር አስተምህሮዎች ካለማወቅ የመነጨ ሲሆን፥ መሰረታዊ የሆነ የአመክንዮ ችግር አለበት
በመጀመሪያ ደረጃ፥ አንድ ነገር ፍጡር መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከመነሳታችን በፊት፥ የፍጡርን (creation) ትርጉም ማወቅ አለብን
ፍጡር ማለት ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ ነገር ማለት ነው። አንድ ነገር በህልውና ያልነበረበት ጊዜ ካለና በሆነ ጊዜና ወቅት ላይ ወደ ህልውና (existence) ከመጣ፥ ያ ነገር ፍጡር ይባላል
Create:- To bring into #existence out of #nothing, without the prior existence of the materials or elements used.
[ English Dictionary 2.0 ]
✒ መጽሐፍ ቅዱስም ፍጡር ማለት ቀድሞ በህልውና ያልነበረ ማለት እንደሆነ ያስተምራል
" ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት #ነበርህ?
(መጽሐፈ ኢዮብ 38:4)
" እርሱም። ለብዙ አሕዛብ አባት አደረግሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ለሙታን ሕይወት በሚሰጥ #የሌለውንም እንዳለ አድርጎ በሚጠራ ባመነበት በአምላክ ፊት የሁላችን አባት ነው።"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 4:17)
ስለዚህ አንድ ነገር ፍጡር ሊባል የሚችለው፤ ካለመኖር ወደመኖር መምጣቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በሆነች ጊዜ እና ቅጽበት ላይ ወደ ህልውና መምጣቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ፍጡር ነው የሚያስብል ምንም ነገር የለም
▶ የፍጡርን ትርጉም በዚህ መልኩ ካየን ዘንድ ወደ ክርስቶስ እንምጣ። ክርስቶስ ሰው የተባለው ለምንድነው?
ክርስቶስ ሰው የተባለው ፍጡር ስለሆነ አይደለም። ክርስቶስ ሰው የተባለው ስለተሰገወ (incarnate) ስለሆነ ነው። ስጋዌ (incarnation) ማለት ቀድሞ ሰው ያልነበረ ነገር በሆነ ጊዜና ወቅት ላይ ሰው ሲሆን ማለት ነው።
Incarnate:- invested with bodily and especially human #nature and form
[ Merriam-Webster Dictionary ]
♦ አስተውሉ! አንድ አካል ተሰገወ ማለት፥ ያ ነገር ሰው ከመሆኑ በፊት በህልውና ነበር ማለት ነው። ሰው ሲሆን አይደለም የእርሱ ህልውና የጀመረው፥ ቀድሞውንም በህልውና ነበር
መጽሐፍ ቅዱስም ነገረ ስጋዌን በተመለከተ ብጥር ያለ ትምህርት አለው። ክርስቶስ ሰው የተባለው ስለተሰገወ እንጂ ካለመኖር ወደ መኖር ስለመጣ አይደለም
" ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ #ልጁን በኃጢአተኛ #ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤"
(ወደ ሮሜ ሰዎች 8:3)
" #ቃልም #ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።"
(የዮሐንስ ወንጌል 1:14)
" እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ #በሥጋና_በደም እንዲሁ #ተካፈለ።"
(ወደ ዕብራውያን 2:14-15)
" ነገር ግን የባሪያን #መልክ #ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥"
(ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2:7)
▶ ክርስቶስ ሰው መባሉ ስጋዌን ያስይዛል እንጂ በፍጹም ፍጡር ነው አያስብለውም። ከላይ ያየናቸው ጥቅሶች በሙሉ፥ ሰው ከመሆኑ በፊት ህልው እንደ ነበር የሚያሳዩ ጥቅሶች ናቸው።
ስለዚህ ኢየሱስ ፍጡር ነው ለማለት ካለመኖር ወደ መኖር መምጣቱን የሚያሳይ ማስረጃ ማምጣት የግድ ይሆናል። ሰው ተብሏልና ፍጡር ነው የሚለው ትርክት ማስረጃ የሌለው ስሁት አመክንዮ ነውና
✒ ስለ ክርስቶስ የቅድመ ስጋዌ ዘመን፥ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድመ ስጋዌ ዘመኑ ዘላለማዊው እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል
1. " እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት #ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።"
(ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:15-16)
✒ በዚህ ስፍራ ክርስቶስ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ ፈጣሪ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። #ሁሉን ፈጠረ ማለት ፍጡር የተባለ ነገር ሁሉ (ቀድሞም በህልውና ያልነበረ፥ በሆነ ጊዜ ላይ ወደ ህልውና የመጣ) ሁሉ በእርሱ ነው የተፈጠረው ማለት ነው።
ይህ ደግሞ እሱን ከፍጥረት ውጪ ያደርገዋል። ምክንያቱም ፍጥረትን ሁሉ እሱ ፈጥሮ፥ እሱ ራሱ ፍጡር ነው ከተባለ ራሱን ፈጥሯል ማለት ሊሆን ነው። ይህ ደግሞ ኢ-አመክንዮአዊ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ፍጡር አይደለም ማለት ነው
2. “እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ #ትክክለኛ_ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፤ የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።”
— ዕብራውያን 1፥3 (አዲሱ መ.ት)
✒ በዚህ ስፍራ ወልድ የአብ ባህሪ ትክክለኛ ምሳሌ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። "ትክክለኛ ምሳሌ" የሚለው የግሪክ ቃል karakteir የሚል ሲሆን "exact imprint: exact representation" ማለት ነው። ማለትም የአንድ ነገር ቁጭ አምሳያ ማለት ነው። ያ ነገር የሆነውን በሙሉ አንድም እንኳ ሳይሸረፍ፥ ሳይቀነስ የሆነ ማለት ነው
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን፥ አብ በባህሪው ዘላለማዊ ነው። (ሮሜ 1:20) ማለትም አብ በባህርይው ፍጡር አይደለም። ይህ ማለት የእርሱ ባህርይ ትክክለኛ ምሳሌ የሆነው ወልድም፥ ፍጡር አይደለም ማለት ነው
3. “ኢየሱስም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ፣ እኔ ነኝ” አላቸው።”
— ዮሐንስ 8፥58 (አዲሱ መ.ት)
✒ በዚህ ስፍራ ጌታ ኢየሱስ አብርሃም ሳይወለድ በፊት እሱ እንደነበር ሲናገር እንመለከታለን። "ሳይወለድ" የሚለው የግሪክ ቃል "genesthai" ሲሆን "ወደ ህልውና መምጣት" ማለት ነው። "እኔ ነኝ" የሚለው ቃል ደግም "eigo emi" ሲሆን በimperfect tense ነው የገባው
ይህ ቃል "የክርስቶስ ህልውና የጀመረው በድንግል ማርያም ማህጸን ነው" የሚለውን ሀሰት ከማፈራረስ ባሻገር የክርስቶስን ዘላለማዊነት የሚያጸና ነው። ምክንያቱም ጌታ፥ እያነጻጸረ ያለው የአብርሃምን ካለመኖር ወደ መኖር መምጣት ከእሱ ጅማሬ አልባነት ጋር ነው። አብርሃም ሳይወለድ እርሱ ነው። ይህ አተራረርክ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሲተረክበት የነበረው አተራረክ ነው። (መዝ 90:2)
▶ መደምደሚያ
ክርስቶስ ሰው የተባለው ስለተሰገው እንጂ ወደ ህልውና ስለመጣ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው፥ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘላለማዊ ነው። ሰው መባሉ ፍጡር መሆኑን አያሳይምና
ስለዚህ ፍጡር ነው የምትሉ ከሆነ፥ ካለመኖር ወደ መኖር መምጣቱን የሚያሳይ ማስረጃ ይዛችሁ መቅረብ ይኖርባችኋል።
ጌታ ይርዳን!