EBS TV NEWS


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Образование


BREAKING NEWS ABOUT WORLD!!!

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Образование
Статистика
Фильтр публикаций


#ATTENTION🚨

“ የካንሰር ሕመም እየጨመረ ነው ” - ዶክተር አስቻለው ወርቁ

በኢትዮጵያ የካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን፣ በተለይም ማኀበረሰቡ ትንቦሆ፣ አልኮል ነክ ነገሮችን ከመጠቀም እንዲታቀብ ጥሪ ቀረበ።

ለካንሰር ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም በተለይ በኢትዮጵያ በኩል የፋይናንስ እጥረት ችግር እንደፈተነው ማቲዎስ ወንዱ ገልጿል።

ተቋሙ የ20ኛ ዓመት ምስረታውን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ካንሰር #በኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ? በበሽታው የተጠቂ ሰዎች ቁጥር ቀነሰ ወይስ ጨመረ ? ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

የተቋሙ የቦርድ አባልና የውስጥ ደዌ ባለሙያው ዶክተር አስቻለው ወርቁ ምን አሉ ?

“ በጣም እየጨመረ ነው ያለው። ለመጨመሩ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ። በአጠቃላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽዎች እየጨመሩ ነው። የካንሰር ህመምም እየጨመረ ነው።

ለምሳሌ፦ የሳንባ ካንሰርን ብናዬው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ነው ያለው። የምንመረምረው ጥቂት ሰዎችን ስለሆነ በዚያችው ዳታ ተመርኩዘን ነው የምንገልጸው። ማኀበረሰቡን ያማከለ የዳሰሳ ጥናት ካልሰራን ቁጥሩን በትክክል መግለጽ ከባድ ነው።

10 ሰዎችን መርምሮ 5 ሕሙማን ቢገኝ 50 በመቶ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ያልተመረመሩ ብዙ ስለሚኖሩ። እንደ አጠቃላይ ካየነው ግን ፦
- የሳንባ፣
- የአንጀት፣
- የጉበት፣
- የማህፀን፣
- የደም ሴል ካንሰር ታማሚሞች ቁጥራቸው እጅግ ባጣም እየጨመረ ነው ያለው። ” ብለዋል።

ካንሰር ዋነኛ የሞት እና የስቃይ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ቁጥሮች እንደሚያመላክቱ ተገልጿል።

ለአብነት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሞቱ ሰዎች ካንሰር የመገኘት እድሉ ከፍ ብሏል። ምክንያቱም የሳንባ ካንሰር ካሉት የካንሰር ዝርዝሮች ወደ 6ኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው ተብሏል።

የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዱ በቀለ ምን አሉ ?

“ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትንባሆ መሸጥም መግዛትም እንዳይችል የሚነገርበት ጊዜ መቼ ነው ?

ትንባሆ ነክ ነገሮች፣ አልኮል በሽታውን እያስፋፉት ነው።

ከ3,000 በላይ የካንሰር ሕሙማንና ቤተሰባቸውን እረድተናል። በአሁኑ ወቅት 175 ለካንሰር ሕሙማንና ለቤተሰባቦቸው፦

° ከአገራቸው የሚመጡበት ሙሉ የትራንስፖርት፣
° ከውጪ የሚገዙ መድኃኒቶች፣
° በሆስፒታል ውጪ በግል ተቋማት ለሚሰሩ የላብራቶሪ ምርመራ፣
° ሆስፒታል ለተኙት ሕሙማን ለአንዳንድ ነገር መሸፈኛ በወር 1,000 ብር፣
° እየታከሙ ለሚማሩ ተማሪዎች በወር 1,000 ብር፣
° 24 አልጋ ባለው የካንሰር ሕክምና ማዕከል በየዕለቱ ለቁርስ፣ ምሳ፣ በክሰስና እራት ወጪዎችን እየሸፈንን ነው። ”

NB. ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የአቶ ወንዱ በቀለ የ4 ዓመት ጨቅላ ልጃቸው በካንሰር በሽታ ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎ ቤተሰቦቹ የደረሰባቸውን መሪር ሀዘን “ ማቲዎስ ቢሞትም ብዙ ማቲዎሶችን ማዳን እንችላለን ” በሚል መልካም አስተሳሰብ በመቀየር በ15 መስራች አባሎች ሚያዚያ 9 ቀን 1996 ዓ/ም የተመሠረተ ለካንሰር ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው። @EBS_TV_NEWS


እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ አይገባም " - ብፁዕ አቡነ አብርሃም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፥ የዲጀታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የራሷን ሕግና መመሪያ እንደምታዘጋጅ አሳወቀች።

ይህ የተሰማው " ኦርቶዶክሳውያን ብዙኃን መገናኛ ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን " በሚል በቤተክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መመሪያ በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ነው።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፥ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ ወሬ ባለመቀበል እና ባለማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

" ቤተክርስቲያንን ሳያውቁ ተገቢው ሙያና እውቀት ሳይኖራቸው የሃይማኖት አስተምህሮ ለማስተላለፍ እና በየማኅበራዊ ሚዲያው እና ዲጂታል ሚዲያው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ አሉ " ሲሉ የጠቆሙት ብፁዕነታቸው " እውቀቱ ሳይኖራቸው ቤተክርስቲያንን ወክሎ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ አይገባም " ሲሉ አሳስበዋል።

" ማኅበራዊ ሚዲያውና ዲጀታል ሚዲያው ከቤተክርስቲያን ይልቅ ለግለሰቦች እና ለቡድን ፍላጎቶች የመቆም ዝንባሌ በሰፊው ይታያል " ያሉ ሲሆን " ቅድሚያ ለቤተክርስቲያን መስጠት ይገባል ፤ ገንዘብ መስብሰብን ዓላማ ያደረገ የዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ ሥራ በመንፈሳዊ ቅኝት ያልተቃኘ በመሆኑ እርምት የሚሻ ነው " ሲሉ ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው በዲጂታል ሚዲያ እና ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያገለግሉ እና የሚገለግሉ የቤተክርስቲኒቱ ልጆች ለቤተክርስቲያን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ መክረዋል።

በዲጂታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በሕሙማን እና በቤተክርስቲያን ስም የሚከናወኑ ልመናዎች ለተባለው ዓላማ ስለመዋላቸው ማረጋገጥ ከእያንዳንዱ እርዳታ ሰጪ ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን በጣስ መልኩ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን እና ሥርዓተ አምልኮ በዲጂታል ሚዲያ የሚያስተላልፉ አገልጋዮች እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።

" በቀጣይ የዲጀታል ሚዲያና ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የቤተክርስቲያኗ የራሷን ሕግና መመሪያ እንዲዘጋጅ ይደረጋል " ሲሉ አሳውቀዋል። @EBS_TV_NEWS


ኢራን እስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት ከፈተች።

ከዛሬ 12 ቀናት በፊት እስራኤል በሶሪያ የኢራን ቆንስላ ጽ/ቤት ላይ እንደፈፀመችው በተነገረ የአየር ጥቃት ከፍተኛ የኢራን ጄኔራልን ጨምሮ 13 ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል ለግድያው ኃላፊነቱን ባትወስድም ኢራን እሷ እንደሆነች ነው የምታምነው። ይህን ተከትሎ ኢራን የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቆይታለች። መዛት ብቻ ሳይሆን ዝግጅትም ስታደርግ ነበር።

እስራኤልም " እኔ እራሴን ለመከላከል ዝግጁ ነኝ " ስትል ከርማለች።

ገና የእስራኤል እና የፍልስጤም ሀማስ ጦርነት ይህ ነው የተባለ መቋጫ ባላገኘበት ሁኔታ ኢራን እና እስራኤል የለየለት ጦርነት ውስጥ ይገባሉ በሚል ፍራቻ ሀገራት ሲያስጨንቃቸው ቆይቷል።

እንደ አሜሪካ ያሉ የእስራኤል እጅግ ጠንካራ ወዳጅ ሀገራት ኢራንን " አርፈሽ ተቀመጪ ጥቃት እንዳትፈጽሚ " ሲሉ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ዛሬ ለሊቱን በተሰማው ዜና ግን ኢራን እንደዛተች አልቀረችም እስራኤልን በድሮን (ሰው አልባ አውሮፕላን) ማጥቃት ጀምራለች። የሚሳኤል ጥቃትም እንደሚኖር ኢራን ገልጻለች።

እስካሁን ድረስ ከ100 በላይ የድሮን ጥቃቶችን እንደሰነዘረች ተሰምቷል።

የእስራኤል ጦርም የኢራን ድሮኖች ወደ እስራኤል እየተላኩ መሆኑን አረጋግጧል። በትንሹ ከ100 በላይ ድሮኖች የእስራኤል አየር ክልል ሳይደርሱ መከላከል እንደተቻለ ገልጿል።

የአሜሪካ ጦርም እስራኤልን እየተከላከለ ሲሆን እስራኤልን ለማጥቃት የተላኩ ድሮኖችን መቶ መጣሉን አመልክቷል። የዩኬ አየር ኃይልም እስራኤልን እንዲያጠቁ የተላኩ ድሮኖችን መቶ ጥሏል።

እስራኤል ለማንኛውም የኢራን ቀጥተኛ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እንደተዘጋጀች አሳውቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌባኖስ ያለው ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል የሚሳኤል ጥቃት እየፈፀመ ሲሆን የየመኑ ሁቲ ደግሞ እስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት ከፍቷል። @EBS_TV_NEWS


ታጋችዋን ታዳጊ ለማስለቀቅ ከከተማ እስከ ክልል የተቀናጀ የክትትልና ምርመራ ስራ እየሰራን ነው። በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችም አሉ " - የዓድዋ ከተማ ፓሊስ

የዓድዋ ከተማ ፓሊስ በታጋቿ ታዳጊ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ማብራሪያ ሰጥቷል።

መጋቢት 10/2016 ዓ.ም በዓድዋ ከተማ ልዩ ቦታ ዓዲ ማሕለኻ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ የተሰወረችው ታዳጊ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ከታገተች 24 ቀናት ተቆጥሯል።

የዓድዋ ከተማ ፓሊስ ዋና አዛዥ ተስፋይ ኣማረ ለ104.4 የመቐለ ኤፍኤም በስልክ በሰጡት መረጃ ፥ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታግታ ለማስለቀቂያ 3 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባትን የተማሪ ማህሌት ተኽላይ አጋቾችን በቁጥጥር ስር ለመዋል ፓሊስ ጥረት እንያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

የታዳጊዋ መታገት በማስመልከት በተሰቦችዋ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም ሪፓርት ካደረጉበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ ፓሊስ ጉዳዩ ለደቂቃ ያህል ችላ እንዳላለው የገለፁት የፓሊስ ዋና አዛዡ ፥ " ' ፓሊስ ለእገታው ትኩረት አልሰጠውም ' ተብሎ በማህበራዊ የትስስር ገፆችና በሚድያዎች የሚሰራጨው መረጃ ልክ አይደለም " ብለዋል።

" ይህን ያህል ከባድ የውንብድና ወንጀል ተፈፅሞ ፓሊስ እንዴት ችላ ይለዋል ? " ሲሉ የጠየቁት ዋና አዛዡ ተስፋይ አማረ ፥ ከከተማው እስከ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን በመቀናጀት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ለመያዝ ሌት ተቀን እየተሰራ ነው ብለዋል።

" ታዳጊዋን ያገቱ ሰዎች ከእገታው በፊት ለረጅም ጊዜ ሲከታተሉዋት የቆዩ መሆናቸው ከቤተሰቦችዋ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል " ያሉት ዋና አዛዡ ፥ " የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውለናል። ለሚድያ መግለጫ ስላልሰጠን ብቻ ስራችን እየሰራን እንዳልሆነ ተደርጎ መውሰድ አግባብነት የለውም " ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በታዳጊዋ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ጉዳይ በተደጋጋሚ መረጃ ያደረሰ ሲሆን ከቀናት በፊት ቤተሰቦቿ በሰጡት ቃል ፥ አጋቾች ለማስለቀቅያ 3 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው በጠየቁበት ዕለት ድምጿን ከሰሙ በኃላ ዳግም እንዳላገኟት እነሱም እንዳልደወሉ ፣በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች እንኳን እንደማያውቁ ፤ በዚህም መላው ቤተሰብ በከፍተኛ ጭንቅና ሃዘን ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረው ነበር። @EBS_TV_NEWS


" በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእስር እና ለእንግልት ቢዳረግም የበቀል ሰው አልነበረም " - አቶ ጃዋር መሀመድ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር አቶ ጃዋር መሀመድ በአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ ምን አሉ ?

" የትኛው እጅ ነው ጨክኖ በቴ ኡርጌሳን በለሊት ከእንቅልፋቸው አስነስቶ የሚረሽነው ? እንዴትስ በቴን የሚያውቅ ሆዱ አስችሎት አይኑ እያያ ሊገድለው ቻለ ? ወገኖች ይህ ምን ይባላል አሁን ?

በቴን ቢያንስ አውቀዋለሁ ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ አቋም ቢኖረውም ለማንም ሆነ ለየትኛውም ቡድን ክፉ የሚያስብ ሰው አልነበረም።

እ.ኤ.አ ነሀሴ 2016 በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተይዞ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞበት ሞተ ተብሎ ለረጅም ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ ቆይቷል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእስርና ለእንግልት ቢዳረግም የበቀል ሰው አልነበረም። ይህ ለበቴ አይገባም ነበር። " ሲሉ የአቶ በቴን ግድያ አውግዘዋል።

የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ትላንት ለሊት በትውልድ ከተማቸው መቂ ካረፉትበት ሆቴል ተውስደው ተገድለው መንገድ ላይ ተጥለው ተገኝተዋል።

ወደ መቂ ያቀኑት የእርሻ ስራቸውን ለመመልከት እንደነበር ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የቅርብ ጓደኛቸውን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።

እስካሁን ድረስ ፓርቲያቸው ኦነግ በይፋ መግለጫ አልሰጠም። በመንግስት በኩልም የተባለ ነገር የለም። @EBS_TV_NEWS


አቶ በቴ ኡርጌሳ ተገደሉ።

የተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር / የፖለቲካ ኦፊሰር የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ትላንትና ለሊት በመቂ ከተማ መገደላቸው ከቅርብ ወዳጆቻቸው ተሰምቷል።

" ካረፉበት ሆቴል ውስጥ ትላንት ለሊት ተወስደው ተገድለው ነው አስክሬናቸው መንገድ ላይ የተገኘው " ተብሏል።

አቶ በቴ ኡርጌሳ በተደጋጋሚ ጊዜ ለእስር ሲዳረጉ የቆዩ ሲሆን በቅርቡም " ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት " ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ታስረው በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ተለቀው ነበር።

ትላንትና በመቂ ከተማ ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተገኝቷል።

ፓርቲያቸው እስካሁን ስለግድያው በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም። @EBS_TV_NEWS


ኢድ ሙባረክ! ✨🌙

የደስታ፣ የሰላም እና የብልጽግና በዓል እንዲሆንላችሁ እንመኛለን።

መልካም በዓል🙏🏻


" 38 #ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ህይወታቸው አልፏል " - በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ

በጅቡቲ የባህር ዳርቻ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ #የመን በመጓዝ ላይ በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰ የመስጠም አደጋ 38 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ህይወታቸውን እንዳጡ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቋል።

ትላንትና ሰኞ በጅቡቲ ሰሜን ምስራቅ " #ጎዶሪያ " በሚባል የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ስልሳ (60) ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ #የመን ትጓዝ የነበረች ጀልባ ላይ በደረሰው የመገልበጥ አደጋ የ38 ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ሚሲዮንም አደጋው ከደረሰ በኋላ ወደ ስፍራው በመጓዝ የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ኤምባሲው ፥ በየዓመቱ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ፍልሰተኞች ከጅቡቲ ባህር ዳርቻ የኤደን ባህረ ሰላጤ በመነሳት መካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመድረስ በየብስና በባህር አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ ብሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት #በጀልባ_መስመጥ አደጋ ብቻ የ189 ዜጎቻችን ሕይወት እንዳለፈ ጠቁሟል።

በየጊዜው የሚደርሰው አደጋ እንዳለ ቢሆንም የፍልሰተኞቹ ቁጥር ግን አሁንም #እየጨመረ እንደሆነ ገልጿል። @EBS_TV_NEWS

ዜጎች በህገ ወጥ #ደላሎች የሀሰት ስብከት በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።

የፍትህ አካላት ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን #ከገጠራማ የአገራችን አካባቢዎች ዜጎችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳስቧል።


የዒድ አልፈጥር በዓል ረቡዕ ነው።

ዛሬ የሸዋል ወር ጨረቃ አልታየችም ፤ በመሆኑም የዒድ አልፈጥር በዓል ረቡዕ ይከበራል።

ነገ ማክሰኞ የረመዷን #የመጨረሻው ሰላሳኛ ቀን ይሆናል።


ታግታ ከተወሰደች በኃላ ለማስለቀቂያ 3 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባት ታጋዲዋ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ታግታ ከተወሰደች 20 ቀናት ሆኗታል።

ቤተሰቦቿ " ልጃችንን አፋልጉን " ሲሉ በፈጣሪ ስም ተማጽነዋል። መላው ኢትዮጵያ ህዝብ እና የፀጥታ ኃይል ልጃቸውን እንዲፈልግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የታዳጊ ተማሪ ማህሌት ቤተሰቦች ከትግራይ ዓድዋ ከተማ ያስተላለፉት የአፋልጉን የተማፅኖ ጥሪ ምን ይላል ?

የማህሌት ተኽላይ ቤተሰቦች ፦

" ታዳጊ ልጃችን ተማሪ ማህሌት ተኽላይ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም ከ 11:00 ሰዓት በኃላ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት በመሄድ ሳለች በትግራይ ዓድዋ ከተማ ዓዲ ማሕለኻ ተብሎ ከሚጠራ ልዩ ቦታ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍና ተወስዳለች።

አጋቾቹ በወሰዱዋት ቀን በራስዋ ሞባይል ስልክ ወደኛ በመወደወል ለማስለቀቅያ 3 ሚሊዮን ብር እንድንከፍላቸው ጠይቀውናል።  ከዛ በኃላ ግን በደውሉበት የልጃችን የሞባይል ቁጥር ብንደውልም አናገኛቸውም፤ በሌላ የሞባይል ቁጥር ደውለውም ያሉን ነገር የለም።

ስለሆነም እኛ የታዳጊ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ወላጆች በከፍተኛ ጭንቅና ሃዘን ውስጥ እንገኛለን። ስለዚህ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና የፀጥታ አካላት የአፋልጉን የተማፅኖ ጥሪ እናቀርባለን። "

ማህሌት ተኽላይ የሚመለከት ማንኛውም አይነት መረጃ ለመስጠት ፦
+251938819844 ሙሴ ተኽላይ
+251992733943 ደጀን ተኽላይ 
+251935036100/
+251962529287 ሚልዮን ተኽላይ
በሚሉ የሞባይል ቁጥሮች እንድትጠቀሙ በትህትና እንጠይቃለን። "

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሁኔታውን እንዲያብራሩ የታዳጊ ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ቤተሰቦችን ጠይቆ ፥ " የዓድዋ ፓሊስ እኛን መልሶ ምን አዲስ ነገር አለ ብሎ ይጠይቀናል ? " ሲሉ መልሰዋል።
@EBS_TV_News






በሩዋንዳው #ጄኖሳይድ ወቅት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን አደረገ ?

ከ800 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ባለቁበት የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ወቅት የዓለም መሪዎች ምንም እንኳን ስለ ዘር ጭፍጨፋው (ጄኖሳይድ) ቢያውቁም ጣልቃ አልገቡም ነበር።

ለረጅም ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ' ጄኖሳይድ ' የሚለውን ቃል ከመጠቀም ተቆጥቦ ነበር ፤ ይህም #በአሜሪካ ጫና እንደሆነ ይነገራል።

አሜሪካም ወታደሮቿን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያልፈለገች ሀገር ናት።

የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ሃላፊ ባን ኪሙን በ20ኛው ዓመት የዘር ጭፍጨፋው መታሰቢያ ወቅት " ድርጅቱ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ መከላከል ባለመቻሉ አሁንም ድረስ ያፍራል " ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጭፍጨፋው ከመጀመሩ በፊት (እኤአ በ1994 መጀመሪያ ላይ) ተመድ ወደ ሩዋንዳ የላከው ኃይል UNAMIR አዛዥ ጄኔራል ሮሜዮ ዳላይር ስለ ግድያው / ጭፍጨፋው በቂ የደህንነት መረጃ ደርሶት ነበር። በሁቱዎቹ የተከማቸ ሚስጥራዊ የጦር መሳሪያ (እንደ ገጀራዎች) እንዳለ አውቆ ነበር።

ከጥር እስከ መጋቢት ወር ድረስ 5 መልዕክቶችን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ልከዋል።

በዚህም በሩዋንዳ ያላቸው ተልእኳቸው እንዲሰፋ ሁቱዎች ያከማቿቸው መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እና የተመድ የሰራዊት ቁጥር እንዲጨምር ቢጠይቁም እዛ ያሉት ሰዎች ግን ማስጠንቀቂያዎቹን ችለ ብለው ትተዋቸዋል።

ግድያው ሲጀመር ተመድ እና የቤልጂየም መንግሥት የUNAMIR ሰላም አስከባሪዎችን አስወጡ።

የፈረንሳይ እና የቤልጂየም ሰላም አስከባሪዎች ቱትሲዎችን ለመርዳት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረት በተሽከርካሪ የነበሩ የሌላ ሀገር ዜጎችን አስወጥተዋል።

ሳይወጡ የቀሩና ትንሽ የተረፉ የተመድ ኃይሎች በኪጋሊ ውስጥ እንደ " ሆቴል ዴ ሚሌ ኮሊንስ " እና " አማሆሮ ስታዲየም " ባሉ ቦታዎች የተሸሸጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ጥበቃ አድርገዋል።

በአንድ አጋጣሚ ግን በኪጋሊ ኢኮሌ ቴክኒክ ኦፊሴሌ (የቴክኒክ ት/ቤት) የተጠለሉ 2,000 ሰዎችን የሚጠብቁ ወታደሮች ቦታቸውን የውጭ ዜጎችን ለማስወጣት ሲሉ ቦታቸውን ለወቀው ሲወጡ በትምህርት ቤቱ እልቂት / ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።

ቱትሲዎችን ለማጥፋት እቅድ እንዳለው እያወቀች የፕሬዝዳንት ሃብያሪማናን መንግሥት ስታስታጥቅ የከረመችው ፈረንሳይ በግድያዎቹ የመጀመሪያ ቀናት ጭምር ከሁቱ መንግስት ጋር መተባበሯን ቀጥላ ነበር። RPFንም ለፍራንስ አፍሪካ ግንኙነት ጠንቅ ነው ብላ ታስብ ነበር።

በመጨረሻ ተመድ ግንቦት 17/1994 በሩዋንዳ ላይ የጦር መሳሪያ እገዳ ጣለ፣ UNAMIRን ለማጠናከር ውሳኔ አሳለፈ። እስከ ሰኔ ድረስ ግን አዲስ ወታደሮች ሩዋንዳ መግባት አልጀመሩም ነበር።

ይህ ሁሉ እስኪሆን አብዛኛው ግድያ ተፈጽሞ ነበር።

የምዕራቡ ዓለም የሚዲያዎችም ጭፍጨፋውን “ የእርስ በርስ ” ወይም “ የጎሳ ” ጦርነት በማለት ነው ሲገልጹ የቆዩት። @EBS_TV_NEWS


የሴራሊዮን መንግሥት በአገሪቷ በተንሰራፋው ‘ #ኩሽ / Kush ’ እየተባለ በሚጠራው የአደንዛዥ እፅ ምክንያት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።

' ኩሽ ' የተለያዩ ሱስ የሚያስይዙ ግብዓቶችን በመደባለቅ የሚሰራ አደገኛ እፅ ሲሆን ለዓመታት በአገሪቷ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

በአደንዛዥ እጹ ውስጥ ከሚጨመሩ ግብዓቶች መካከል አንዱ የተፈጨ #የሰው_አጥንት ነው።

በዚህም ምክንያት #ከመቃብር ውስጥ አፅም ለማውጣት የሚቆፍሩ #ሱሰኞችን ለማስቆም የጸጥታ አካላት በመካነ መቃብር ሥፍራዎች የሚያደርጉትን ጥበቃዎች አጠክረው ቆይተዋል።

የሴራሊዮን ፕሬዚደንት የሆኑት ጁሊየን ማዳ ባዮ አስተዳደራቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ያስገደደውን ይህንን እፅ / ኩሽ “ የሞት ወጥመድ ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን በአገሪቷ ላይም የህልውና ቀውስና ስጋት ፈጥሯል ብለዋል።

ፕሬዚደንት ባዮ ፤ በእፁ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እንዳሻቀበ ተናግረዋል።

በመሆኑም በ ' ኩሽ ' እፅ ምክንያት የሚደርሰውን ቀውስ ለመከላከል በሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል ፤ ብሔራዊ ግብረ ኃይል እንዲቋቋምም መደረጉን ቢቢሲ አስነብቧል። @EBS_TV_NEWS


ነገ በአዲስ አበባ መንገዶች ይዘጋሉ።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ነገ #ቅዳሜ ከሚደረግ የድጋፍ ሰልፍ ጋር በተያያዘ መንገዶች እንደሚዘጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

በዕለቱ ከንጋቱ 11፡ 00 ሰአት ጀምሮ የድጋፍ ሰልፉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ፦

- ከቴዎድሮስ አደባባይ በብሄራዊ ቴአትር ወደ ወደ መስቀል አደባባይ ሚወስደው መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ፡

- ከኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል አደባባይ ላይ

- ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ

- ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ ላይ

- ከጎተራ ማሳለጫ ወደ መስቀል አደባባይ አጎና ሲኒማ

- ከቅ/ቂርቆስ ቤ/ክርስቲያን በአዲሱ መንገድ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚሄዱ ለገሀር መብራት

- ከሜክሲኮ ወደ መስቀል አደባባይ ቴሌ ለሚጓዙ ለገሀር መብራት

- ከጌጃ ሰፈር አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ሰንጋተራ ትራፊክ መብራት ላይ

- ከሃራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት ላይ

- ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ

- ከካዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ከዛንቺስ ሼል አጠገብ

- ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA ሚወሰደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ ተብሏል።

አሽከርካሪዎች መንገዶቹ እንደሚዘጉ አውቀው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ ባለፈ በተጠቀሱት መንገዶች ላይ ከዋዜማው ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰልፉ ፍፃሜ ድረስ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ወይም ማሳደር ተከልክሏል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የነገው የመስቀል አደባባይ ሰልፍ #መንግሥትን የሚደግፍ ሰልፍ መሆኑን ለማወቅ ችሏል። @EBS_TV_NEWS


የኤርትራ ሰራዊት ከሶስት የኢትዮጵያ የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ወረዳዎች ' 93 ወጣቶች ' አግቶ መሰወሩን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ገልጹ።

እገታው የተፈፀመው ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል ከኤርትራ ከምትዋሰንባቸው የዛላንበሳ ከተማ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች ላይ ነው ተብሏል።

ይህን የተገለፀው የከተማ እና የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች ከኤርትራ ድንበር በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው የዓዲግራት ከተማ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች (AU military attaches) ባካሄዱት ውይይት ነው።

የዛላአንበሳ ከንቲባ መምህር ብርሀነ በርሀና ፣ የጉሎመኻዳ ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቶም ባራኺ በጋራ ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኃላ :-

➡ በአከባቢያቸው የተለወጠ የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩ ፤

➡ ጦርነቱ ተከትሎ የተፈጠረው ችግር እንዳልተፈታ፤

➡ የኤርትራ ሰራዊት የዛላአንበሳ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ፤

➡ ከዛላኣንበሳ ከተማ መግብያ በቅርብ ርቀት ዝባን ሑፃ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ኬላ አቋቁሞ ፍተሻ እንደሚያካሂድ ፤

➡ የኤርትራ ሰራዊት ከዛላኣንበሳ ከተማ 15 ፣ በቁጥጥሩ ስር ከሚገኙ የጉሎመኻዳና የኢሮብ ወረዳዎች የተለያዩ ቀበሌዎች 78 ባጠቃላይ 93 ወጣቶች አግቶ የወሰዳቸው ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ አብራርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች 10 ቀበሌዎች የሚኖር ህዝብ እርዳታ ጨምሮ የጤና የትምህርት እንዲሁም ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶች እንደማያገኝ አስተዳዳሪዎቹ ለአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በዝርዝር አስረድተዋል።

በስብሰባው ወቅት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች መሳተፋቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የሀገር መከላከያ ሚንስትሩ ዶክተር አብራሃም በላይ በየካቲት 2016 ዓ.ም የመጨረሻው ሳምንት ላይ በትግርኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ፥ " የሻብዕያ ሰራዊት " ብለው የገለፁት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መሬት ስለመውጣት ጉዳይ ፤

" ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በፊት በበርካታ የትግራይ አከባቢዎች የሻዕብያ ሃይል ገብቶ ነበር ፣ ከስምምነቱ በኋላ እንዲወጣ ተደርጓል ፣ አሁንም የተቀሩ ቦታዎች ካሉ ቦታዎቹ እና ቀበሌዎች ከፌደራልና ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ቡድን በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብና መፍትሄ እንዲሰጠው እየሰራን ነው ሁሉም ልክና መስመር ይይዛል " ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

መረጃው በመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው የተዘጋጀው። @EBS_TV_NEWS


የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6 / 2016 ዓ/ም ለሊት ችግር በገጠመው ጊዜ " የህዝብን ገንዘብ ያለአግባብ ወስደው እስካሁን #አልመለሱልኝም " ያላቸው ግለሰቦች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ፎቷቸውን እያሰራጨ ይገኛል።

ከሚዲያዎች በተጨማሪ በየባንኩ ቅርንጫፎች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋም በር ላይ ለህዝብ በሚታይ መልኩ " ገንዘቡን አልመለሱም " ያላቸውን ግለሰቦች ፎቶግራፍ በትልልቅ ባነር በማሰራት ለጥፏል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ " ብር ተመላሽ አድርገን እስካሁን ፎቷችን በሚዲያዎች እንዲሰራጭ እየሆነ ነው " ያሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ባንኩ ገንዘብ የመለሱትንም በፎቶግራፍ ማውጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

" የወሰድነውን ብር ተመላሽ አድርገን ሳለ ባንኩ ብር ካልመለሱት ጋር አደባልቆ ፎቶግራፋችንን ማሰራጨቱ ተገቢ አይደለም በመሆኑንም ህዝብ በሚያውቀው መንገድ መመለሳችንን ሊያሳውቅ ይገባል " ብለዋል። @EBS_TV_NEWS


" 480 ስደተኞች #በሊቢያ የባህር ጠረፍ ላይ ተይዘዋል " - IOM

ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ 480 ስደተኞች በሊቢያ የባህር ጠረፍ ላይ መያዛቸው ተነግሯል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት/IOM ሰኞ'ለት ባወጣው መግለጫ 480 ስደተኞች በባህር ላይ ጠባቂዎች መያዛቸውን አስታውቋል።

ድርጅቱ "ከመጋቢት 24 እስከ 30,2024 ውስጥ 480 ስደተኞች ተይዘው ወደ ሊቢያ ተመልሰዋል " ነው ያለው።

ከተያዙት ስደተኞች ውስጥ 26 ሴቶች እንዲሁም 5 ህፃናት እንደሚገኙበትም ተነግሯል።

የስደተኞች 2 #አስክሬንም ተገኝቷል።

በዚህ ዓመት በጠቅላላ 3,791 ስደተኞች የተያዙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 120ዎቹ #ሲሞቱ ፣ ሌሎች 250 የሚሆኑት #ጠፍተዋል መባሉን MDN ዘግቧል። @EBS_TV_News


“ ከ9 ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈለንም ”- ከ200 በላይ የጤና ባለሙያዎች

➡ “ የትርፍ ሰዓት በየወሩ እየተከፈለ አይደለም እሱ ትክክል ነው። የከተማ አስተዳደሩ ለመክፈል ቃል ገብቷል ” - የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ጋሞ ዞን ፤ በሰላምበር ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች ከ9 ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ የትርፍ ጊዜ ሰዓት ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ፣ ደመወዝም የሚገባላቸው እየተቆራረጠ መሆኑን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎችን ወክለው ቃላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የሰጡ አንድ የጤና ባለሙያ ተከታዩን ብለዋል።

- “ ከ9 ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈለንም። ሳይከፈለን 10ኛ ወር እየሰራን ነው ያለነው። ”

- “ በሌላ በኩል ደግሞ ዋና ደመወዝ ሁሌም እየተቆራረጠ ነው የሚገባው። ግማሹ ብቻ ያስገቡና ግማሹ ደግሞ ሳይገባ ወሩ ያልቃል። ”

- “ የደመወዝ ሆነ የትርፍ ሰዓት ክፍያ በተመለከተ ቅሬታ ያለን 113 ጤና ባለሙያዎች (የትርፍ ሰዓት ያልተከፈላቸው) ፣ 103 ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች (የትርፍ ሰዓት ክፍያ የማይመለከታቸው) ናቸው። ”
- “ ያልተከፈለው የክፍያ መጠን እንደ ጤና ባለሙያው ፤ አሁን ለምሳሌ የእኔ 5,000 ነው በወር የሚሆነው። 15 ሺሕ የሚከፈለው አለ። 30 ሺሕ የሚከፈለው አለ እንደ ስፔሻሊቲ ከሆነ። ” አቶ ሰይፉ ዋናካ ምን አሉ ?

° “ ቅሬታ ሲቀርብ ወርደን እናወያያለን። ከሁለት ወራት በፊት ወርደን አወያይተን፣ አግባብተን የትርፍ ሰዓት በየወሩ እየተከፈለ አይደለም እሱ ትክክል ነው። ግን ያው የተወዘፈም እየተከፈለ ነው ያለው። ”

° “ ችግሩ ካለ ወርደን እናስከፍላለን። የደመወዝ፣ የትርፍ ሰዓት ጉዳይ ከእኛ አቅም በላይ አይደለም። ”

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጉዳዩ ካቅማችሁ በላይ ካልሆነ ከ9 ወራት በላይ ለምን ዘገዬ ? ሲል ጠይቋል።

ምላሽ ፦

° “ የከተማ አስተዳደሩ ችግርም ፣ አገራዊ ችግሮችም አለ። ሁሉ ወጥ አይሆንም። የከተማ አስተዳደሩ ለመክፈል ቃል ገብቷል። ስለዚህ የ10 ወራቱም ቢሆን ይከፈላል። ”

ጤና ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፣ ከወራት በፊት ፒቲሽን ሰብስበው የትርፍ ሰዓት ሥራ እንደማይሰሩ አቋማቸውን ሲገልጹ ኃላፊዎች ቢያወያዩአቸውም ክፍያው እንዳልተሰጣቸው አስረድተዋል። @EBS_TV_NEWS


በአዲስ አበባ ከአሁን በኋላ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች ከዋና ከመንገድ በ10 ሜትር ርቀት መሆን እንደሚገባቸው ውሳኔ ተላለፈ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ 3ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ በ3 ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ከውሳኔዎቹ አንዱ ግንባታዎችን የሚመለከት ነው።

በዚህም የከተማዋን ስታንዳርድ እና መዋቅራዊ ፕላን ለማስጠበቅ እንዲሁም መልሶ ማፍረስ እንዳይገጥም ፤ ግንባታዎች ከመንገድ ያላቸው ርቀት ከዚህ በኋላ ወጥነት ያለው የከተማ አሰራር አንዲኖር በማሰብ ከመንገድ መራቅ ያለባቸውን 3 ደረጃዎች ወጥተዋል።

ከአሁን በኋላ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች ፦
➡ ከዋና ከመንገድ በ10 ሜትር ርቀት መሆን እንደሚገባው ፤
➡ ከንዑስ ዋና መንገድ 5 ሜትር ርቀት፤
➡ ሰብሳቢ መንገድ ደግሞ 3 ሜትር ርቀት
➡ በተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገድ 2 ሜትር ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸው ካቢኔው ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ሌለው ውሳኔ የተላለፈበት ጉዳይ የከተማዋን የተሽከርካሪ አስተዳደር ህግ እና ሥርዓት ለማስከበር የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ ደንብን ላይ ሲሆን ለአሰራር በሚያመች መልኩ ሀሳብ ተሰጥቶበት ደንቡ ፀድቋል።

ከዚህ በተጨማሪ " የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል " ማቋቋሚያ ደንብ ማዕከሉን በተለይም ፦
- ለጎዳና ህይወት ፤
- ለፆታዊ ጥቃት ሰለባ እና ለወሲብ ንግድ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ፣ መጠለያ፣ ማገገሚያ እና የተመሰቃቀለ ህይወታቸውን እንደገና ለማደስ የሚያስችል የሙያ እና ክህሎት ሥልጠናዎች የሚያገኙበትን እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያግዝ አቅም ያለዉ ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል በሚያግዘው ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ካቢኔው ተወያይቶ አጽድቋል። @EBS_TV_NEWS

Показано 20 последних публикаций.