በገቢው ዘርፍ የሚደረገው የፀረ ሙስና ትግል የተቀናጀ ጥረትን የሚጠይቅ ነው፤ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ፣ የገቢዎች ሚኒስትር
#########################
(ጉምሩክ ኮሚሽን፣ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም)
ለገቢዎች ሚኒስቴር እና ለጉምሩክ ኮሚሽን ዳይሬክተሮች፣ አማካሪዎች፣ ፅ/ቤት ሀላፊዎች፣ ስራ ሂደት መሪዎች እና ቡድን አስተባባሪዎች ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት በሚል መሪ ቃል በፌደራል ስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መድረክ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ የታክስ ስርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መስከረም ደበበ እና የፌደራል ስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ ተገኝተዋል፡፡
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፤ ሙስና ለዘላቂ ልማት፣ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ማነቆ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሚንስትሯ አክለውም በገቢው ዘርፍ የሚደረገው የፀረ ሙስና ትግል የተቀናጀ ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ ገልፀው ከፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በገቢው ዘርፍ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ሥር ከመስደዱ በፊት ተጋላጭነትን የመለየት፣ ክፍተቶችን የመዝጋት እና አሰራሮችን የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩም ነው ብለዋል ሚንስትሯ፡፡
የፌደራል ስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራር የአስተሳሰብ መበላሸት እና የማህበራዊ እሴቶች መሸርሸር ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልእኮ ስኬት በሚል መሪ ቃል እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠናም ዘርፍ ተኮር እና በገቢው ዘርፍ ያለውን የሙስና ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/ecczenaበድረ ገጽ፦
www.ecc.gov.etበቴሌግራም፦
https://t.me/EthiopianCustomsCommission