Ethiopia Insider


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


Ethiopia Insider is a digital media that provides news, updates, analysis and features.

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций




በአዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ያጋጠመው አካባቢ፤ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ

ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በትላንትናው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ የእሳት አደጋ ያጋጠመው በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ገበያ የሚገኝ አካባቢ፤ “የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ቧሟላ” መልኩ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ። ምክረ ሃሳቡን ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው።

ትላንት እሁድ ህዳር 8፤ 2017 እኩለ ቀን ገደማ የእሳት አደጋ የደረሰበት የመርካቶ ገበያ ስፍራ፤ በተለምዶ “ድንች ተራ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። ስፍራው ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከነበረው “ነባር የገበያ ማዕከል” በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

የእሁዱ ቃጠሎ የደረሰበት ስፍራ፤ “በነባር የገበያ ማዕከል” ላይ የሚነግዱ ነጋዴዎች ንብረቶቻቸውን የሚያስቀምጡበት መጋዘን እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእሳት አደጋው “ጌሾ ግቢ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከሚገኘው መጋዘን በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙ መደብሮች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ውድመት አድርሷል። 

በትላንቱ የእሳት አደጋ ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሁለት የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14595/

@EthiopiaInsiderNews


የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዲስ የአመራር ምርጫ ሊያካሄድ ነው 

አባል በሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ አዲስ የአመራር ምርጫ ሊያካሄድ ነው። ምክር ቤቱ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢውን እና የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ይመርጣል።

በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በመንግስት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር ለማድረግ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ በአሁኑ ወቅት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 59 አባል ፓርቲዎች የታቀፉበት ነው። የጋራ ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሰረት ሰብሳቢውን እና ምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት የስራ አስፈጻሚ አባላትን በየዓመቱ ይመርጣል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ያለበት ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር። ሁለት ወር የዘገየው የጋራ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ከነገ ቅዳሜ ህዳር 7፤ 2017 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ እርሳቸው የሚመሩት ስራ አስፈጻሚ በ2016 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ለተሳታፊዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል። 

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14592/

@EthiopiaInsiderNews


በ2017 ሩብ ዓመት ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት ተልከዋል?

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ካለፈው ሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በውጭ ሀገራት ለስራ ሊያሰማራቸው ከነበሩ 140 ሺህ ዜጎች ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 62 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ። በሊባኖስ ለስራ የተሰማሩ ዜጎችን ከጉዳት ለመታደግ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቢቀርብለትም፤ አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ጥያቄውን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ህዳር 4፤ 2017 በተካሄደ ስብሰባ ላይ ያቀረበው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የትላንት በስቲያውን ስብሰባ የጠራው፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን የ2017 እቅድ እና የሩብ አመት የስራ አፈጻጸምን ለመገምገም ነበር። 

በዚሁ ስብሰባ ላይ የሚመሩትን መስሪያ ቤት የሶስት ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በተመለከተ ጥቅል አሃዞችን በሪፖርታቸው አካትተዋል። ወደ ውጭ ለስራ የሚላኩ ዜጎችን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት ሩብ ዓመት፤ ሚኒስቴሩ በውጭ ሀገራት ለስራ ያሰማራቸው ኢትዮጵያውያን 87,067 እንደሆኑ ሙፈሪያት ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን በህጋዊ መንገድ ለመቀበል፤ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰሩ ያሉ ስድስት የመካከለኛው ምስራቅ እና ሁለት የአውሮፓ ሀገራት መሆናቸውን ሚኒስትሯ አመልክተዋል። 

🔵 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14579/

@EthiopiaInsiderNews


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ትኩረት የሚያሻው” “የገቢ እጥረት” እንደገጠመው ገለጸ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የሰበሰበው ገቢ፤ በእቅድ ይዞት ከነበረው በ10 ቢሊየን ብር ያነሰ መሆኑን ገለጸ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውጭ እርዳታ እና ብድር የተገኘው ገቢም፤ ከታቀደው ከግማሽ በታች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

➡️ በከተማይቱ እየተተገበሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ሆነው ሳለ፤ በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ መቀነሱ “ትኩረት የሚያሻው” መሆኑ ተገልጿል።

➡️ ይህ የተገለጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት አመት አንደኛ የሩብ አመት የስራ አፈጻጸሙን ትላንት ማክሰኞ ህዳር 3፤ 2017 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በገመገመበት ወቅት ነው።  

➡️ በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ የአስፈጻሚ አካላት የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል። በስራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል የዕለቱ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ሁኔታ ነው።

➡️ በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 54.9 ቢሊየን ብር እንደነበር በትላንቱ የግምገማ መድረክ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ጊዜያት ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 83.3 በመቶ እንደሆነ አቶ አደም ተናግረዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14568/

@EthiopiaInsiderNews


ለቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የምስጋና መርሃ ግብር ሊደረግ ነው 

ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ከፕሬዝዳንትነታቸው ለተሰናበቱት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፤ በኃላፊነታቸው ላይ ሳሉ ላከናወኗቸው ስራዎች የምስጋና መርሃ ግብር ሊደረግላቸው ነው። ከነገ በስቲያ አርብ ህዳር 6፤ 2017 የሚደረገውን ይህን መርሃ ግብር ያዘጋጁት በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሰባት ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው ታዬ አጽቀ ስላሴ ያስረከቡት፤ የስድስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ከመገባደዱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ነበር። የቀድሟዋ ፕሬዝዳንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ፤ የመክፈቻ ንግግር እንዲያቀርቡ አስቀድሞ ተይዞ የነበረው መርሃ ግብር ተሰርዞ በምትኩ አምባሳደር ታዬ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። 

በፌደራል መንግስት ደረጃ ይፋዊ የሽኝት ስነ ስርዓት ላልተደረገላቸው ሳህለ ወርቅ፤ የምስጋና መርሃ ግብር የተዘጋጀው በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል ነው። የምስጋና መርሃ ግብሩ ዋና አላማ የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት በሴቶች አመራር ረገድ ላከናወኗቸው ስራዎች በሴቶች አማካኝነት ምስጋና ለማቅረብ መሆኑን ፕሮግራሙን የማዘጋጀት ኃላፊነት የወሰደው የመቅዲ ፕሮዳክሽን ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ በሃይሉ ተከተል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

🔵 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14559/

@EthiopiaInsiderNews


በአዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ላይ የትውልደ ኢትዮጵያውያን መብት በግልጽ አለመቀመጡ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ 

አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል፤ በባንክ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ውስጥ ወይም ከውጭ ሀገር ኢንቨስተርነት አንዱን መምረጥ እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

▶️ በ2000 እና በ2011 ዓ.ም. የወጡትን የባንክ ስራ አዋጆችን የሚሽረው አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ፤ ለፓርላማ የቀረበው ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ነበር።

▶️ በተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ሰኞ ህዳር 2፤ 2017 በጠራው የውይይት መድረክ ላይ፤ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ጨምሮ በአዲሱ “የባንክ ስራ አዋጅ” የሰፈሩ ድንጋጌዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

▶️ በፓርላማ ውይይት እየተደረገበት ያለው አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ የባንክ ስራን በተመለከተ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የወጡ አዋጆችን ቁጥር አራት ያደረሰ ነው።

▶️ የኢትዮጵያ መንግስት የባንክ አገልግሎትን ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚከፍት ፖሊሲ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅ፤ “ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው” የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል።

▶️ ጥያቄውን በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የፓርላማ የአስረጂ የውይይት መድረክ ላይ ያቀረበው፤ በተወካዮች ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት ነው። አዲሱ አዋጅ በዋናነት ትኩረት ያደረገው “የውጭ ሀገር ዜጎች በባንክ የስራ መስክ” መሰማራት እንደሚችሉ መሆኑን ዳይሬክቶሬቱ በጥያቄው ላይ ጠቅሷል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14555/

@EthiopiaInsiderNews


የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለመምራት ዕጩ የሚሆኑ ግለሰቦችን የሚያቀርብ ኮሚቴ ተቋቋመ

የስራ ዘመናቸውን ከአራት ወራት ገደማ በፊት አጠናቅቀው የተሰናበቱትን የህዝብ ዋና ዕንባ ጠባቂ የሚተኩ ዕጩዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቋመ።

▶️ በኮሚቴው ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ) የፓርላማ ተመራጮች እንዲካተቱ ተደርጓል። 

▶️ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፤ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ዋና ዓላማ ያለው ነው። ተቋሙ የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ፤ “ስልታዊ ምርመራ” የማካሄድ ኃላፊነትም በአዋጅ ተሰጥቶታል። 

▶️ይህን ተቋም ላለፉት ስድስት ዓመታት በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ናቸው። ዶ/ር እንዳለ በድጋሚ ተሹመው፤ ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት በኃላፊነት መቀጠል የሚችሉበትን ዕድል የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቢሰጣቸውም፤ ከዋና እንባ ጠባቂነታቸው መሰናበትን መርጠዋል።

▶️ ያገለገሉበት የስራ ዘመን “ከበቂ በላይ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ዶ/ር እንዳለ፤ “አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ እና ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት አስቸጋሪ” ስለሆነ በኃላፊነት ላለመቀጠል መወሰናቸውን አስረድተዋል።

▶️ ለስራቸው ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ አነስተኛ መሆን፤ በዋና እንባ ጠባቂነት ለሁለተኛ ዙር ላለመሾም ካስወሰኗቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14549/


ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የምታበድረውን ገንዘብ፤ በድፍድፍ ነዳጅ ለማስከፈል የሚያስችል አማራጭ የያዘ ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ 

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ለምትበደረው 738.26 ሚሊዮን ዶላር፤ ወደፊት የምትፈጽመውን ክፍያ በድፍድፍ ነዳጅ እንድትመልስ አማራጭ የሚሰጥ የብድር ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ።

➡️ በብድር ስምምነቱ የሚገኘው ገንዘብ፤ በደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ከምትገኘው ፓጋክ ከተማ በመነሳት እስከ ፓሎች ከተማ ድረስ ያለውን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት የሚያስችል ነው።

➡️ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል የተደረገው የብድር ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በቀረበበት ወቅት፤ ማብራሪያውን በንባብ ያሰሙት በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪው ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

➡️ ዶ/ር ተስፋዬ የብድር ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱም የተለያዩ የዝግጅት እና የትብብር ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። 

➡️ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ብድር የምትሰጥበት የስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ለፓርላማ ይቀርብ እንጂ፤ ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በግንቦት 2015 ዓ.ም ነበር።

➡️ ደቡብ ሱዳን በብድር የምታገኘው ገንዘብ፤ በጋምቤላ በኩል ካለው የኢትዮጵያ ድንበር በመነሳት በነዳጅ ሀብት ወደ በለጸገው ፓሎች አካባቢ የሚዘረጋውን መንገድ ወደ አስፋልት ለማሳደግ የሚውል ነው።

➡️ የመንገድ ፕሮጀክቱ የሲቪል እና የአማካሪ ስራዎች የሚከናወኑት በኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።

🔵 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14540/

@EthiopiaInsiderNews


ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ መክፈያ እና ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ቦንድ ለሽያጭ ሊቀርብ ነው

የገንዘብ ሚኒስቴር 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲያወጣ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። ገንዘቡ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ለመክፈል እና ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ነው።

ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ አዋጅ፤ “የመንግስት እዳ ሰነድ” የሚል ስያሜን የያዘ ነው። አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበት “ከፍተኛ ዕዳ” በባንኩ የፋይናንስ ገጽታ ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላስከተለ” መሆኑ በረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስት ለልማት ድርጅቶች ካበደረው ውስጥ እስካሁን ያልተሰበሰበው የገንዘብ መጠን፤ ከ846 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። የልማት ድርጅቶቹ ብድሩን ከመንግስታዊው ባንክ የወሰዱት፤ ለተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ነው።

መንግስት የልማት ድርጅቶቹ ውስጥ ያልተከፈለ ከፍተኛ ብድር ያለበት፤ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል ይገባው የነበረው ብድር ከእነ ወለዱ 191.79 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት በቀረበ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል።

ከመንግስት ተቋሟት መካከል ባልተከፈለ ከፍተኛ የብድር መጠን ሁለተኛውን ቦታ የያዘው፤ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ነው።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14532/

@EthiopiaInsiderNews


በወላይታ ሶዶ ነዳጅ ማደያዎች የማይገኘው ቤንዚን፤ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ እንዴት እንደ ልብ ሊገኝ ቻለ?

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ በሰባት በሮች እንግዶቿን ትቀበላለች። የህዝብ ትራንስፖርት እና የግል ተሽከርካሪዎችን የሚጠቀሙ ተጓዦች፤ በአረካ፣ ቦዲቲ፣ ኡምቦ እና ገሱባ ከተሞች አድርገው ወደ ወላይታ ሶዶ መግባት ይችላሉ። በጭዳ፣ ሆቢቻ፣ በዴሳ ከተሞች በኩል ያሉ መንገዶችን ለተጓዦች በአማራጭነት ያገለግላሉ።  

ከአዲስ አበባ ከተማ 332 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በወላይታ ሶዶ፤ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በዋናነት የሚጠቀሙት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩትን ባለ ሶስት እግር ታክሲዎችን ሲሆን ሞተር ሳይክልም በነዋሪዎቹ ዘንድ ይዘወተራል። በከተማይቱ ከ12 ሺህ በላይ ባጃጆች እና ሞተር ብስክሌቶች  እንደሚንቀሳቀሱ ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ደም ስር የሆኑት እነዚህ መጓጓዣዎች በዋነኛነት የሚጠቀሙት ቤንዚን ቢሆንም፤ በአቅርቦት ረገድ ያለው ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ለከፍተኛ ምሬት ዳርጓል። ላለፈው አንድ ሳምንት በሶዶ ቆይታ ያደረገው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በከተማይቱ ውስጥ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ከፍተኛ የቤንዚን እጥረት መኖሩን አስተውሏል። 

ካለፈው ረቡዕ ጥቅምት 20 ጀምሮ ደግሞ፤ የከተማይቱ ነዳጅ ማደያዎች “ቤንዚን የለም” የሚሉ ጉልህ ማስታወቂያዎችን መለጠፋቸውን ታዝቧል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት፤ በከተማዋ የነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን አለመኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14522/

@EthiopiaInsiderNews


የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ሁለተኛ ዓመት ሲታሰብ፤ ማን ምን አለ?

አቶ ሬድዋን ሁሴን የፌደራል መንግስትን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ህወሓትን ወክለው፤ ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመው፣ እጅ ለእጅ ከተጨባበጡ፤ ትላንት ቅዳሜ ጥቅምት 23፤ 2017 ድፍን ሁለት ዓመት ሞላቸው። ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል ያጓሩትን ጠመንጃዎች ጸጥ በማሰኘቱ፤ በአቶ ጌታቸው አገላለጽ “ስኬታማ” ነው። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በመሾም ውጊያው እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ትላንት ምሽት ባወጣችው መግለጫ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቃለች። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት ያመጣቸውን “ጠቃሚ መሻሻሎች” አሜሪካ በአዎንታ እንድምትመለከት ገልጸዋል።

ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው “ከምንም በላይ በትግራይ የአፈሙዝ ላንቃ ዝም ብሎ መቆየቱን” አድንቀዋል። በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እና ሰብአዊ እርዳታ መጀመራቸው፣ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዎንታዊ ለውጥነት ጠቅሰዋል። 

ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን መልሶ ከማህበረሰቡ ለማዋሃድ የተያዘው ዕቅድ በዚህ ወር ተግባራዊ እንደሚሆን የጠቆሙት ብሊንከን፤ ይህ እርምጃ “ሰላምን ለማጠናከር” “ወሳኝ” እንደሆነ ገልጸዋል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እና የትግበራ ፍኖተ-ካርታ፤ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅ ለማውረድ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውንም አስገንዘበዋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14517/

@EthiopiaInsiderNews


የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል በመፈጸም እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ የተከሰሱት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ላይ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ። በቀድሞው ከንቲባ እና አብረዋቸው በተከሰሱ ሁለት ተከሳሾች ላይ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 19፣ 2017 ብይኑን የሰጠው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ በአቶ ጸጋዬ እና ሁለት ተከሳሾች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረተው፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በአንድ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል፤ የሲዳማ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ ይገኙበታል።

የክልሉ ዐቃቤ ህግ በአቶ አበራ እና በአቶ ጸጋዬ ላይ የመሰረተው የመጀመሪያ ክስ፤ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ የተቀመጠን ድንጋጌ በመተላለፍ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” የሚል ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የመጀመሪያው ክስ፤ በሀዋሳ ከተማ ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ጎን የተወሰደ ቦታ ምትክ መሬት እንዲሰጥ ከቀረበ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው።

የምትክ ቦታ ጥያቄ ቀርቦ የነበረው፤ ከአቶ ጸጋዬ አስቀድሞ በነበሩት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ የአመራር ጊዜ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል። አቶ ጥራቱ የምትክ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ ቢያስተላልፉም፤ የመሬት ርክክብ ከመፈጸሙ በፊት ከኃላፊነታቸው በመነሳታቸው ጉዳዩ ለተተኪያቸው ተላልፏል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14503/

@EthiopiaInsiderNews


ኢትዮጵያ ከተነካች “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያ ጦርነት ባትፈልግም፤ ከተነካች ግን “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣን ወረራ ለመመከት የሚያስችል “በቂ አቅም አለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ በውጊያ ላይ የገጠሟትን ክፍተቶች የሚያሟሉ “ነገሮች” ማምረት መጀመሯን ገልጸዋል።

ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በተካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስደመጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ ትችላለች” በሚል “አልፎ አልፎ” ስለሚቀርቡ ስጋቶች ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር እንደሚያያዙት፤ ሌሎች ደግሞ “ሀገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። 

ከኤርትራም ይሁን ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያም ይሁን ከኬንያ፤ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት “ሰላማዊ ጉርብትና” እንደሆነ አብይ በማብራሪያቸው አስገንዘበዋል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ላልጠቀሷቸው ሀገራት፤ ከእንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያን “እየመዘበሩ” እና “በሰፈር እያባሉ መኖር” እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።  

“እኛ ቅጥረኞች አይደለንም። ለሆነ ቡድን ተቀጥረን፣ በስሙ ተገዝተን፣ የሆነ ቡድን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች ሳንሆን፤ አርበኞች ነን። ይሄን አምኖ ካከበረ ማንኛውም ሀገር [ጋር] በከፍተኛ ደስታ አብረን መስራት እንፈልጋለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14492/

@EthiopiaInsiderNews


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ሐሙስ በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ፤ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ካብሯሯቸው ጉዳዮች ሰላም እና ጸጥታን የተመለከቱት ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ “ሰላምን የማይመርጡ” ስላሏቸው ሰዎች አንስተዋል።

“መቶ ፐርሰንት ሰው አመዛዛኝ ስለሆነ ሰላም ይፈልጋል ማለት አይደለም” ያሉት አብይ፤ በዚህም ሳቢያ በአለም ላይ ያሉ መንግስታት፤ ለዜጎቻቸው መኖሪያ ቤት እንደሚገነቡ ሁሉ ማረሚያ ቤት እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል። ሆኖም መኖሪያ ቤት መገንባት ብቻውን “ሰላምን አያረጋግጥም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለደሃ ዜጎች የሚሆኑ 248 ሺህ ቤቶች መገንባቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚያው ልክ ማረሚያ ቤት አለመገንባቱን ተናግረዋል። “ቁጥሩ ቢያንስም” ማረሚያ ቤት መገንባት እንደሚያስፈልግም ማብራሪያቸውን ለተከታተሉት የፓርላማ አባላት አስገንዝበዋል።

“አብዛኛው መኖሪያ ቤት፣ አብዛኛው የንግድ ቦታ፣ አብዛኛው ለውጥ የሚያመጣ [ቢገነባም]፤ ትንሽም ቢሆን ግን ማረሚያ ቤት ደግሞ ያስፈልጋል። ይሄንን balance መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ‘ሰው ሁሉ ሰላም ይፈልጋል፤ ሰው ሁሉ ለሰላም ይሰራል’ ብሎ በጥቅሉ ማየት ያስቸግራል። ባለፉት አመታት ያየነው ልምድም የሚያሳየው እንደዚያ አይደለም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


“አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ኢትዮጵያን “መዝረፍ”፤ “መብት እንደሆነ” የሚያስቡ “አንዳንድ ሀገራት አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሱ። የኢትዮጵያን ሀብት “የመዝረፍ” እና “የውጭ ምንዛሬ ቢዝነስ የሚሰሩ” ኤምባሲዎች አሉ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጅለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፤ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። በሁለት ክፍል በተከፈለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቅድሚያውን ያገኙት፤ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች ናቸው። 

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፍ፤ በገቢ፣ በሬሚታንስ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት፣ በወርቅ እና በቡና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) “እድገት ማስመዘገቡን” በቁጥር በማስደገፍ ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች” ያሏቸውን ጉዳዮችንም ለፓርላማ አባላት ዘርዝረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አብይ በተለይ በአጽንኦት ያነሱት፤ በባንኮች፣ በኤምባሲዎች እና በኩባንያዎች ይፈጸማሉ ያሉትን “የጥቁር ገበያ” ንግድ ነው። 

በሀገሪቱ ያሉ ባንኮች በህጋዊ መንገድ ከሚሰራው ይልቅ፤ “በትይዩ” የውጭ ምንዛሬ ገበያ በመሳተፍ “ኮሚሽን ማግኘት” እንደለመዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “ባንክ በህጋዊ መንገድ የሚወዳደሩበት እንጂ በህገ ወጥ መንገድ በኮሚሽን ሀብት የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም” ሲሉም ተደምጠዋል።  

🔴ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14474/

@EthiopiaInsiderNews


የከተማ መሬትን በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው

የከተማ መሬትን ከጨረታ እና ከምደባ በተጨማሪ በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው።

አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት መጠን ውስጥ፤ ቢያንስ 20 በመቶውን ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል። 

“የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ” እንደወጣ የተገለጸው ይህ አዋጅ፤ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 19፤ 2017 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ አጀንዳ ተይዞለታል።

በ2004 ዓ.ም የጸደቀውን “የከተማ ቦታን ስለመያዝ የወጣ አዋጅን” የሚተካው አዲሱ የህግ ረቂቅ፤ በስድስት ክፍሎች እና በ49 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው።

በአዋጅ ረቂቁ ከተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች መካከል “መሬትን በድርድር በሊዝ ለማስተላለፍ” የሚፈቅደው ድንጋጌ ይገኝበታል።

አስራ ሶስት ዓመት ያስቆጠረው ነባሩ አዋጁ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ እንዲያዝ የሚፈቀደው በጨረታ ወይም በምደባ ስልት ብቻ ነበር።

በአዲሱ አዋጅ የተካተተው “የድርድር” ስልት፤ “በጨረታ እና በምደባ አግባብ” ለተጠቃሚ ሊተላለፉ በማይችሉ የከተማ መሬቶች ላይ፤ አንድ አልሚ “ለተለዩ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው አገልግሎቶች” መሬት በሊዝ ይዞ ማልማት የሚፈቀድበት ነው። 

በፌደራል መንግስት ለሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለከፍተኛ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ለምርምር ዘርፍ ፕሮጀክቶች የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተዘርዝሯል።   

🔵ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14466/

@EthiopiaInsiderNews


የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያዎች “የታጠቁ አካላት ሰርገው በመግባት” ጥቃት እንደሚፈጽሙ ኢሰመኮ አስታወቀ

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው ጣቢያዎች “ተገቢ ጥበቃ ስለማይደረግላቸው”፤ የታጠቁ አካላት “ሰርገው በመግባት ጥቃት እንደሚፈጽሙ” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በዚህ ሳቢያ ተፈናቃዮች “አስጊ በሆነ የደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ” ኮሚሽኑ ገልጿል።

➡️ ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 18፤ 2017 ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ነው።

➡️ ኮሚሽኑ ለሶስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ  2016 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው። 

➡️ በስምንት ክልሎች የተፈናቃዮቹን ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን በሪፖርቱ የገለጸው ኢሰመኮ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ቡድኖች በየጊዜው በሚያደርሱት ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ዜጎች እንደሚፈናቀሉ አመልክቷል። በመንግስት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

➡️ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለው የጸጥታ ችግር፤ ዜጎችን እንዲፈናቀሉ ከማድረግ ባሻገር ለተፈናቃዮች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ “አስቸጋሪ” እንዳደረገው በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14460/

@EthiopiaInsiderNews


የፎቶ ዘገባ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስረኛ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩን፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል።

በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፤ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚደረገው በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ምክክር መድረክ ላይ፤ የ32 ብሔረሰብ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሏል። ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተወከሉት ተሳታፊዎች የተውጣጡት ከ96 ወረዳዎች መሆኑን በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።

የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩን ለማስተናገድ እንግዶችን መቀበል የጀመረችው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጀምሮ ነበር።

በወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የሀገራዊ ምክክሩን የተመለከቱ ግዙፍ “ቢልቦርዶች” በየቦታው ተሰቅለው ሁነቱን ለማስተዋወቅ ሞክረዋል። ሆኖም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተሳታፊዎች ምክክር በሚደርጉበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለው ድባብ ግን ከከተማይቱ የተለየ ነው።

በግቢው ውስጥ ዛሬ ስለተጀመረው የምክክር መድረክ የሚያስረዳ አንዳችም ነገር የለም። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም እንደ ወትሮ ሁሉ የዕለት ተዕለት ስራውን በመስራት ተጠምዷል።

በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ “ምን እየተከናወነ እንደሆነ” ያውቁ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አራት ተማሪዎች፤ የመርሃ ግብሩን ምንነት እንደማያውቁ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔵 ለተጨማሪ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14451/

@EthiopiaInsiderNews


የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት በነገው ዕለት በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙትን ጨምሮ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ሊያያጸድቅ ነው። ፓርላማው በዚሁ ስብሰባው፤ የከተማ መሬትን የተመለከቱትን ሁለት የአዋጅ ረቂቆችን ጨምሮ አራት አዋጆችን ለሚመለከታቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል።

መደበኛ ስብሰባዎቹን ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ለነገ ጥቅምት 19፤ 2017 ሰባት አጀንዳዎችን ይዟል። በህዝብ ተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የሚቀርብ “የድጋፍ ሞሽን” ማድመጥ የሚለው ከአጀንዳዎቹ መካከል አንዱ ነው።

አቶ ታዬ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት፤ በመስከረም ወር መጨረሻ በተካሄደው በዚሁ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ስነ ስርዓት አንድ ሳምንት በኋላ፤ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ አቶ ታዬን በመተካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

በነገው የፓርላማ ስብሰባ፤ የዶ/ር ጌዲዮን፤ በፍትህ ሚኒስትርነት እርሳቸውን የተኳቸው የወ/ሮ ሃና አርአያ ስላሴ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ሹመት ይጸድቃል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ የተሾሙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካም፤ በነገው ዕለት በፓርላማ በመገኘት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።

🔵 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14448/

@EthiopiaInsiderNews

Показано 20 последних публикаций.