በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁርጠኝነታቸን አንዱ ማሳያ የሆነውን መሶብ የአንድ መዐከል አገልግሎትን ዛሬ መርቀናል።
ይኽን አዲስ ማዕከል የሚገልጡ ሶስት ቁልፍ አላባውያን አሉ። የቆየ እና የተጎዳ ህንፃን ወደ ዘመናዊ እና ሥነውበታዊ ደረጃው ለሥራ ከባቢ አስደሳች ወደ ሆነ ህንፃ መለወጡ አንዱ ነው። አገልግሎቶችን ለመሰተር እና ለማቀናጀት በሀገር ውስጥ የለማ ሶፍትዌር በሥራ ላይ መዋሉ ብሎም በታደሰ አመለካከት ብቁ እና ክብር የሞላበት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች መዘጋጀታቸው ሌሎቹ አላባውያን ናቸው። 12 ተቋማት በአንድ ጣሪያ ሥር 40 የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የጀመሩ ሲሆን ይኽም ዜጎች ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና አገልግሎቶችን በተሻለ ውጤታማ መንገድ ለማግኘት ያግዛል።
እንደዚህ ያሉ ሥርዓቶችን ማበልፀግ ለዜጎች የተለያዩ የአገልግሎት ርካታ መታጣቶች ምላሽ በመስጠት በሂደት ለሰፊው ማኅበረሰብ ርካታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። የዛሬው ምረቃ ትልቅ ርምጃ መራመዳችንን ያሳያል። ኢትዮጵያ በዚህ ማዕከል ላይ ጨምራ እና አስፋፍታ ለዜጎች ሁሉ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥን ታረጋግጣለች።