በወንጀል ተጠርጥሮ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ የነበረና በእስር ምክንያት በስራው ላይ ያልተገኘ ሰራተኛ ከቀረበበት ክስ ነፃ ቢባልም ደመወዝ ሊከፈለው የማይችል ስለመሆኑ፤
(ሰ/መ/ቁ፡ 201933)ጥቅምት 04/2014
===============================
ለሰበር የቀረበው ጉዳይ በአጭሩ ተጠሪ የስራ ሂደት መሪ ስሆን በሙስና የወንጀል ክስ ተመስርቶብኝ ስከራከር ቆይቼ ከቀረበብኝ ክስ በነፃ ብሰናበትም በእስር ምክንያት በስራዬ ላይ ላልተገኘሁባቸው ጊዜያት ተጠሪ ደመወዝ ሊከፍለኝ አልቻለም በማለት ክስ አቅርቧል፡፡ ተጠሪም በበኩሉ አመልካች በመታሰሩ ምክንያት የተቋረጠበት ደመወዝ ሊከፈለው አይገባም በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሠበር ችሎቱም ተጠሪ በእስር ምክንያት ላልሰራው ስራ ደመወዝ ወደ ኋላ ተመልሶ ሊከፈለው ይገባል ? ወይንስ አይገባም? የሚለውን በጭብጥነት ይዞ ጉዳዩን መርምሯል፡፡
በመሰረቱ ደመወዝ ለተሰራ ስራ በአሰሪው አካል የሚከፈል የድካም ዋጋ በመሆኑ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ የሚከፈለው በመስሪያ ቤቱ በስራ ላይ ሁኖ በተመደበበት ስራ ለሰጠው አገልግሎት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ መርህ ሲሆን በስራ ላይ ባልነበረበት ጊዜ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ የሚከፈለው በህግ በልዩ ሁኔታ የተመለከተ ግልፅ ድንጋጌ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 በክፍል አራት ስር አንድ ሰራተኛ ስራ ሳይሰራ ደመወዝ ሊከፈለው የሚችለው በህዝብ በዓላት፣ በዓመት እረፍት ፍቃድ፣ በሳምንት እረፍት ፣ በወሊድ ፍቃድ፣ በህመም ፍቃድ፣ ለግል ጉዳይ በሚሰጥ ልዩ ፍቃድ ምክንያት ብቻ ስለመሆኑ ከአንቀፅ 36 እና ከተከታዮቹ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ሰራተኛው በወንጀል ተጠርጥሮ በፍርድ ሂደት ላይ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ቢሆንም በዚህ እና በመሰል ሁኔታዎች ምክንያት ሰራተኛው ከስራ የቀረ እንደሆነ በስራው ላይ ባይገኝም መስሪያ ቤቱ ደመወዝ የመክፈል ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አይደነግግም፡፡ ስለሆነም በመርህ ደረጃ ደመወዝ የሚከፈለው በስራ ገበታው ላይ ተገኝቶ ተገቢውን አገልግሎት ለሰጠ የመንግስት ሰራተኛ በመሆኑ እና ስራ ሳይሰራ ደመወዝ የሚከፈለው በአዋጁ የተመለከተ ድንጋጌ ሲኖር ብቻ ስለሆነ እና ይህም ለመርሁ ልዩ ሁኔታ በመሆኑ በጠባቡ መተርጎም የሚገባው ስለሆነ በእስር ምክንያት በስራ ገበታው ላይ ላልተገኘ ሰራተኛ መስሪያ ቤቱ ደመወዝ ለመክፈል የሚገደድበት የህግ ምክንያት የለም በማለት አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
@LawStudentsUnion @LawStudentsUnion