Фильтр публикаций


❤️አ😍ፈ😍ቅ😍ር😍ሻ😍ለ😍 ሁ❤️

አ🥰= አንድ ነገር ቀረኝ ከጥፋት መታቀብ
ፈ🥰= ፈልጌው አደለም አላበዛም ሰበብ
ቅ🥰= ቅንነትሽ ደስታ ስሜትን ይስባል
ር🥰= ርሀብን ያስታግሳል ጥምንም ያስቆማል
ሻ🥰= ሻማ ሁነሽኛል በጨለመው ጎኔ
ለ🥰= ለማንም አልፈቅድም እንዲለዩሽ ከ
#እኔ👈
ሁ🥰  = ሁሌም ወድሻለሁ ትናፍቂኛለሽ እስከማይሽ በ
#አይኔ😢


ብትወድቁ ትነሳላችሁ!

ትምክህት አያሰናክላችሁ፣ ትዕቢት መንገድ አያስታችሁ፣ አጉል ድፍረት ችግር ውስጥ አይክተታችሁ። ለሌላ ለማንም ሳይሆን ለራሳችሁ ጠንቃቃ ሁኑ፣ ሌላ ማንንም ለመጥቀም ሳይሆን ራሳችሁን ለመጥቀም ራሳችሁን ገስፁ። ስህተትና ውድቀት ብርቅ ባልሆነበት ዓለም ላይ እየኖራችሁ አንዴ ስለተሳሳታችሁ ወይም አንዴ ስለወደቃችሁ ሰማይ የተደፋባችሁ ምድር የዋጠቻችሁ አታስመስሉ። እደጉ ስትባሉ ስህተት ወደ ህይወታችሁ ይመጣል፣ መቀየር ካለባችሁ ውድቀት ደጋግሞ ይጎበኛችኋል። "በፍፁም እንዳትሳሳቱ፣ በፍፁም እንዳትወድቁ።" የሚል አስተምህሮ የለም። የስህተት ጥቅም የገባቸው ለመሳሳት ይደፍራሉ፣ የውድቀትን ትርፍ ያገኙ ደጋግመው ለመውደቅ ይዘጋጃሉ። ህይወት እስርቤት ሳትሆን ነፃ ሜዳ ነች። አስሬ ብትሳሳቱ በሰውኛ የሚፈርድባችሁ ሰው ቢኖርም ተጨማሪ እድል የሚሰጣችሁ ፈጠሪ ግን አለ። እድሉ የሚሰጣችሁም እንደገና እንድትሳሳቱና እንድትበድሉ ሳይሆን ከስህተታችሁ ታርማችሁ በትክክለኛው መንገድ እንድትጓዙ ነው። ጥሩ ተማሪ ስህተቱን አይደግምም፣ ብልህ ሰውም ዳግም በወደቀበት መንገድ አይጓዝም።

አዎ! የዓለም ፍፃሜ አታስመስሉት፣ ብትወድቁ ትነሳላችሁ፣ ብትሳሳቱ ትታረማላችሁ፣ ብትጠፉም ትመለሳላችሁ። ባለፈ መጥፎ ትዝታ ራሳችሁን አትሰሩ፣ በቀደመ ጥፋት ራሳችሁን እየወቀሳችሁ አትኑሩ። አዋቂ ሁኑ፣ አንዱን ስህተታችሁን ከቀጣዩ ስህተት መጠበቂያ አድርጉት፣ የአሁን ውድቀታችሁን ለቀጣይ ጉዟችሁ መጀመሪያ አድርጉት። በራሱ የሚያዝንን ሰው ማንም ሊያፅናናው አይችልም፣ ራሱ ላይ የሚጨክንን ሰው ማንም ሊረዳው አይችልም። እርግጥ ነው ፍረሃታችሁ መሳሳት ወይም መውደቁ ሳይሆን በስህታችሁ ወይም በውድቀታችሁ  ምክንያት የሚደርስባችሁ ሰው ትቺትና ፍርጃ ነው። ይሔን አስታውሱ፦ "ብዙ ሰው አዋቂ ሳይሆን ፈራጅ ነው፣ ብዙ ሰው አራሚ ሳይሆን ተቺ ነው።" በሳታችሁ ሰዓት ፈጣሪያችሁን አስቡ፣ ስትወድቁ አምላካችሁን ተመልከቱ። ሁሌም በስህተት መንገድ እንድትመላለሱ የሚፈልግ ፈጣሪ የላችሁም፣ እዛው በወደቃችሁበት ስፍራ እንድትቀሩ የሚፈልግ አምላክ የለም። መነሳታችሁን የሚፈልግ አባት አላችሁና እርሱን ተደግፋችሁ ዳግም ተነሱ፣ የእናንተን በትክክለኛው መንገድ መጓዝ የሚናፍቅ አምላክ አላችሁና መንገዱን እንዲመራችሁ ፍቀዱ።

አዎ! ጀግናዬ..! ከዋጋህ በታች አትኑር፣ በሚያጠፋህ መንገድ አትመላለስ፣ አስኮኙ ምግባር ላይ አትሰየም። አውቀህ አውቀህ ለድህነት ትቀርብ ይሆናል ፍፁም ነፃ የሚያወጣህና የሚያድንህ ግን እምነትህ ነው። አንድም ከስህተት የመውጣት እመነት፣ ሌላም ፈጣሪ ከስህተት እንደሚያወጣህ ማመን። ተስፋህን ቸል አትበለው፣ እምነትህን አትፈትነው፣ ዳግም የመነሳት ሃሳህን አትገዳደረው። አንድ ቀን ከተሳሳተው መንገድ ትወጣለህ፣ አንድ ቀን ካቀረቀርክበት ቀና ትላለህ፣ አንድ ቀን ውድቀትህን ትሽረዋለህ፣ በአምላክህ ፍቃድ ነፃ ሆነህ በሰው ፊት በነፃነት ትራመዳለህ። ሁሉም ሰው የራሱ የውድቀት ታሪክ አለው፣ ማንኛውም ሰው ደግሞ ማንሳት የማይፈልገው የህይወት ከስተት አለው። የተለየውና ልብ ሰባሪው ታሪክ ያንተ ብቻ አይደለም። ታሪክህ ምንም ይሁን እንዲያልፍ ፍቀድለት፣ ትዝታህ ምንም ይሁን እንዲያስርህ አትፍቀድለት። አሁን የትም በምንም ውስጥ ሁን፣ ያለህበት ስፍራ የተሳሳተ እንደሆነ ከተሰማህ ግን ጊዜ ሳታጠፋ ጥለሀው ውጣ፣ ከዳግም ውድቀትም ራስህን አድን።


ከምንም አትጣበቅ!

ለብቻ መሆን፣ እራስን በብዙ ዘርፍ መቻል፣ ለግል አቋም ታማኝና ቆራጥ መሆን፣ ከማንም ምንም ብታጣ እንኳን ከተፅዕኖ ነፃ መሆን መቻል ቀላል አይደለም። ቢሆን ኖሮ ብዙዎች ባደረጉትና ከሰዎች ሲለያዩ እራሳቸውን ባላጡ ነበር። ከአንድ ሰው ወይም ከቁስ ጋር ባለህ ግንኙነት ዘወትር ፈላጊው አንተ፣ ሙሉ ትኩረትህ እርሱ ላይ፣ ደስታና ሰላምህንም ከእርሱ እያገኘህ ከሆነ የአደጋህ ቀይ መብራት በትልቁ እንደበራ አስተውል። የዛፍ ቅርንጫፎች የዛፉ ስር ሲቆረጥ አብረው ይወድቃሉ፣ አንተም እንዲሁ የተደገፍከው፣ የተጣበከው፣ ከልብህ የተማመንክበት ነገር ካጋደለ ያንተም ህይወት ከማጋደልና ከመውደቅ አያመልጥም። እንደ ቀልድ የጀመርከው የትኛውም ግንኙነት ገዢህና መሪህ እንዲሆን አትፍቀድ። ምንም ዘላለማዊ ነገር የለም። ያለን ነገር ሁሉ ጅማሬና ፍፃሜ አለው።

አዎ! ጀግናዬ..! ከፈጣሪህ፣ ከአምላክህ በቀር ከአንዳች ምድራዊ ነገር ለመነጠል እስከሚያስቸግርህ ድረስ አትዋሃደው፤ ከምንም አትጣበቅ፤ ለማንም እራስህን፣ ክብርህን፣ ማንነትህንና ህልውናህን አሳልፈህ አትስጥ። ላንተም ሆነ ለአምላክህ ካንተ በላይ ዋጋ ያለው ነገር የለም። የሚመጡ ሁሉ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሆነ ጊዜ ጥለውህ ይሔዳሉ፤ የማይሔዱም ቢሆን ሊገዙህና እንደፈለጉ ሊነዱህ ስልጣን የላቸውም። የብዙዎች ስብራት፣ የብዙዎች ህመም፣ የብዙዎች ቁስል ዋናው ምክንያት ከልክ ያለፈ መዋሃድ፣ ገደብ የሌለው መጣበቅ ወይም Over Obsession, Over Attachment ነው። ፍቅርና Attachment, ግንኙነትና ጥገኝነት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው። ነፃነትን የሚነሳ ፍቅር ፍቅር ሳይሆን ጥገኝነት ነው፤ "ያለእርሱ መኖር አልችልም፤ ያለእርሷ ህይወት ለእኔ ባዶ ነው" የሚያስብል ግንኙነት ጤነኛ ግንኙነት አይደለም።

አዎ! ምንም አይነት ግንኙነት ውስጥ ብትሆን ትልቁና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አንተ ከእራስህ ጋር ያለህ ግንኙነትና አብራህ ያለችው ወዳጅህ ከእራሷ ጋር ያላት ግንኙነት ነው። ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሁለት ሰዎች ከእራሳቸው ጋር ሰላም ከሆኑ፣ ምንም አይነት የጥገኝነት ባህሪና ሙጭጭ የማለት ፀባይ ከሌለባቸው ግንኙነት ሰላማዊ፣ የተረጋጋና አስደሳች የመሆን እንድሉ እጅግ በጣም ሰፊ ነው። ሰውን ተደግፈህ ሰው ቢጥልህ ካለሰውየው ድጋፍ ለመነሳት ልትቸገር ትችላለህ፤ ፈጣሪህንና እራስህን ተደግፈህ ብትወድቅ ግን በፈጣሪህ ድጋፍ ባንተ ብርታት ድጋሜ ትነሳለህ። እራስን ማክበር እራስን ከልብ የመውደድ አይነተኛ ማሳያ ነው። መገፋትህ እንዳያሳምምህ፣ በመገለልህ እንዳትሰበር፣ ሁሉም ቦታ በመገኘት ዋጋህን እንዳታጣ፣ ጥገኛ በመሆን ስሜትህ እንዳይጎዳ ከምንም በላይ ለእራስህ ቦታ ስጥ፣ ከማንም በተሻለ ከእግዚአብሔር አምላክህና ከእራስህ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይኑርህ። መጪው ቀድሞ ያልነበረ ስላለመሔዱም እርግጠኛ የማትሆንበት ነውና እራስህን በመውደድህ፣ ለእራስህም ቅድሚያ ባለመስጠትህ ምንም ሃፍረት አይሰማህ።


ያልተሰጠህን ለእራስህ ስጥ!

ብቻህን ትጓዛለህ ቢሆንም አትፈራም፤ ብቻህን ትለፋለህ ቢሆንም አትጨነቅም፤ ብቻህን ትኖራለህ ቢሆንም በእራስህ መቆም አይከብድህም፤ በችግሮችህ መዋል ማለፍ ትችላለህ፤ ብዙዎች ባያምኑብህ በእራስህ ትተማመናለህ፤ ማንም ባይደግፍህ እራስህን ትደግፋለህ፤ ማንም የተሻለ ቦታ ባይሰጥህ ለእራስህ ግሩም ቦታ ትሰጣለህ። ያጣሀውን ለእራስህ አድርግ፤ ያልተሰጠህን ለእራስህ ስጥ። ብቻህን ነበርክ ዛሬም ዳግም ብቻህን መቅረትህ ሊደንቅህ አይገባም። ሰዎች ይመጣሉ በፊት እንደነበርከውም ብቻህን ጥለውህ ይሔዳሉ። ብቸኝነትን ተለማመድ፤ ከሌሎች ስታገኘው የነበረውን ነገር ከእራስህ ለማግኘት ሞክር። በእርግጥ ሰው የሚሰጥህን በሙሉ ከእራስህ ላታገኝ ትችላለህ ከልቡ አምኖበት፣ ፈልጎና ወዶ የሚሰጥህ እስኪመጣ ግን ለእራስህ በፍፁም አንሰህ እንዳትገኝ። ለእራሱ፣ በእራሱ ደስተኛ፣ ጠንካራ ብርቱ የሆነ ሰው ከውድቀቱ እንዴት ማገገም እንዳለበት፣ በምንያክል ፍጥነት ዳግም መነሳት እንዳለበት፣ እንዴት እራሱን ዳግም ማግኘት እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል።

አዎ! ጀግናዬ..! ያልተሰጠህን ለእራስህ ስጥ! ከሌሎች ጠብቀህ ያጣሀውን፣ ስትናፍቀው ያስቀሩብህን፣ እያስፈለገህ የተነፈከውን ነገር ለእራስህ በእራስህ ለመስጠት ቆርጠህ ተነስ። በሰዎች ችግር ምክንያት፣ በሰዎች ፍላጎት ማጣት፣ በሰዎች ፊታቸውን ማዞር ማላዘንህን አቁም፤ እራስህን መውቀስ አቁም፤ እራስህን ተጠያቂ ማድረግ አቁም። ይህ ጊዜ ብቸኝነትህን በሚገባ የምታከብርበት፣ ማየት ለሚገባቸው፣ ማየት ለሚፈልጉ ትክክለኛውን ማንነትህን የምታሳይበት ጊዜ እንደሆነ እወቅ። ብቻውን የፈለገውን ነገር ማድረግ የሚችልን ሰው የትኛውም ጫና ሊያስቆመው አይችልም፤ የትኛውም አይነት በደል ወደኋላ ሊያስቀረው አይችልም። ብቻህን ስትሆን ፍፁም የተለየህ ሰው ትሆናለህ፤ ፍፁም ከዚህ በፊት የማትታወቅ ላንተም ለሌላውም አዲስ ሰው ትሆናለህ።

አዎ! ድጋፍ ማጣትህ ያጠነክርሃል፤ የሚያምንብህ አለመኖሩ በእራስህ እንድታምን ያነሳሳሃል፤ በሰዎች መገፋትህ እግዚአብሔር አምላክህን እንድትጠጋ ያደርግሃል፤ ተቀባይነት ማጣትህ እራስህን ከነድክመቱ እንድትቀበለው ይጠቁምሃል። ብቻህን ስትጓዝ አብሮህ ያለው አምላክህ ነውና መከዳት የለም፤ መገፋት አይኖርም፤ ድራማ የለም፤ በሰዎች ስሜት ምክንያት ዋጋ መክፈል አይኖርም። ብቻህን እራስህ ላይ ትሰራለህ፤ ብቻህን እራስህን ታጠነክራለህ፤ ብቻህን ማን እንደሆንክ፣ ምን ማድረግ እንደምትችል ታሳያለህ። በስተመጨረሻም የእውቁ ደራሲ የዋይኒ ዳየርን ንግግር አስታውስ፡ "ብቻህን ስትሆን አብረሀው የምትሆነውን ሰው ከወደድከው በፍፁም ብቸኛ ልትሆን አትችልም።" ያንን ሰውም አንተ ሁን፤ በህይወትህ በጣም የምትፈልገውን ሰው እራስህ ሁን፤ እራስህ ላይ በመስራትህ የሚያኮራህን አይነት ሰው ሆነህ ተገኝ።


ከሃሳብ እለፉ!

ከሀሳብ እለፉ፣ ከተደጋጋሚ እቅድ ከፍ በሉ፣ ወደ ተግባር ተጠጉ፣ ሩጫውን ተቀላቀሉ፣ የረጅሙን ጉዞ ምዕራፍ ጀምሩ። ከእያንዳንዱ አስባችሁ ካልጀመራችሁት ነገር ጀርባ ከፍተኛ ፀፀት እንደሚጠብቃችሁ አስታውሱ። በሀሳብ ልክ ለመኖር፣ ፍላጎትን ለማሟላት፣ ወደ ላቀው ከፍታ ለመድረስ ጅማሮ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው። እስከ ዛሬ ለነገ የቀጠራቿቸውን ጉዳዮች አስታውሱ፣ ነገ ባላችሁት ቀን ስለማድረጋችሁ መርምሩ፣ በማወላወል ያጠፋቿቸውን ጊዜያት አስታውሱ። ሁሌም እያቀዳችሁ መኖር አትችሉም፣ ሁሌም በሀሳብ ውቂያኖስ ውስጥ ተዘፍቃችሁ አትቀሩም፣ ሁሌም በማወላወልና በማንገራገር እየተጨነቃችሁ አትኖሩም። እፎይታችሁ ያለው ከጅማሬያችሁ ቦሃላ ነው፣ ልባዊ መረጋጋትን የምታገኙት ወደምታስቡት አቅጣጫ መራመድ የጀመራችሁ እለት ብቻ ነው። ነገሮችን ሰፋ አድርጋችሁ ለመመልከት ሞክሩ፣ ከዛሬ ሁኔታችሁ በላይ ማሰብ ጀምሩ። ሀሰሳባችሁን አጠንክሩ፣ አግዝፉት፣ መቋጫውን ተግባር አድርጉት።

አዎ! ቆሞ ቀር አትሁኑ፣ የሀሳባችሁ ባሪያ፣ የጊዜያዊ ስሜታችሁ ተገዢ አትሁኑ። ከሃሳብ እለፉ፣ እቅዳችሁን ፈፅሙት፣ ፍላጎታችሁን ጨብጡት። እናንተ ቆማችሁ እየተጓዙ ካሉ ሰዎች ጋር አትፎካከሩ፣ እናንተ እያሰባችሁ ሀሳባችውን የሚፈፅሙ ሰዎችን አትገዳደሩ። ሰውን ማለፍ ላይ ሳይሆን እቅዳችሁን መፈፀም ጀምራችሁ ብቁ መሆን ላይ አተኩሩ፣ የተሻለ ነገር እንዲከናወንላችሁ ከማሰብ በላይ እንዲከናወንላችሁ የምትፈልጉትን ነገር በራሳችሁ ለማከናወን ሞክሩ። ከሰው ሲጠብቁ የነበሩ ሰዎች ዛሬም እዛው የጥበቃቸው ስፍራ ናቸው፤ በሰው ላይ እምነት የጣሉ ሰዎች ዛሬም ሰውን እየተጠባበቁ ነው፤ የሁኔታዎችን መገጣጠም ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዎች አሁንም የማያባራ ሀሳብ ውስጥ ናቸው። የተቻላችሁን ያህል በትልቁ አስቡ ነገር ግን ሀሳባችሁን በትንሹ ጀምሩት፣ እንደ አቅማችሁ እቅድ አውጡ፣ ግብ አስቀምጡ፣ እቅዳችሁንም መፈፀም ጀምሩ፣ ወደ ግባችሁ ጉዞ ጀምሩ። አስተውሉ፣ ዙሪያችሁን ተመልከቱ፣ መርምሩ፣ አካባቢያችሁ ላይ ያለውን ለውጥ አጢኑ፣ ሀሳባችሁን አዳምጡ በራሳችሁ ያመጣችሁትን ለውጥም እንዲሁ መርምሩ።

አዎ! ጀግናዬ..! ትልቁ ሀሳብህ አብሮህ እስጊያረጅ አትጠብቅ፣ ፍላጎትህ ትርጉም አልባ ቅዠት እስኪሆን አትጠብቅ። እንደማንኛውም የሚያስብ ሰው ሳይሆን የሚያስበውን እንደሚኖር ጥቂት ሰው ለመኖር ሞክር። የሀሳብህ ትልቅነት፣ የፍላጎትህ ግዝፈት አንቅቶህ ወደ ተግባር እንዲያስገባህ አድርግ። የሀሳብህ እንቅፋቶች ምንድናቸው? በትንሹ እንዳትጀምር ያደረጉህ ነገሮች ምንድናቸው? የተግባር ሰው እንዳትሆን አስረው የያዙህ ነገሮች ምንድናቸው? እንቅፋቶችህን እወቅ፣ መሰናክሎችህን መርምር። አሁን መጀመር ባትችልም መሰናክል የሆኑህን ነገሮች መቀነስ ጀምር፣ የእውቀት ደረጃህን ከፍ አድርግ፣ የምትፈልገውን ነገር ግልፅ አድርግ። ማድረግ የምትፈልገውን ትልቅ ነገር ለማድረግም ሆነ ለመጀመር ስለሁሉም ነገር ማወቅ እንደሌለብህ እወቅ። ህልምህ ህልም ብቻ ሆኖ እንዳይቀር፣ ሀሳብህም ሀሳብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ራስህን አደፋፍር፣ ፍላጎትህን አጥራ፣ ፍረሃትህን አስታግስ፣ በሀሳብህ እውንነት እመን፣ ወደ ተግባርም ግባ።


ከእራስህ ተነስ!

"የመውደድ አቅም ካለህ አስቀድመህ እራስህን ውደድ።" - Charles Bukowski

ማንንም ለመውደድ ጅማሬያችን እራሳችንን መውደዳችን ነው፤ ማንንም ለማክበራችን መሰረታችን እራሳችንን ማክበራችን ነው፤ ማንንም አስደሳች ለማድረግ ቀዳሚው እራሳችንን ማስደሰት መቻላችን ነው፤ በማንም ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘታችን ዋስትናው እራሳችንን መቀበላችን ነው። ውጪውን ለማስተካከል ከመሔድህ በፊት አንተ ጋር ምንም መስተካከል የሚገባው፣ መታነፅ ያለበትና መሻሻል የሚኖርበት ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ሁን። አመለካከትህ፣ አረዳድህ፣ የእምነት ደረጃህ፣ እውቀትህ፣ የማስተዋል አቅምህ፣ የመረዳት ችሎታህ ሁሉ እንከን አለባ እንደሆነ እርግጠኛ ሁን። ውጪው ላይ ጣትን ከመቀሰር በተሻለ እራስን መመልከት እራስን መረዳትና ለእራስ እምነት ታምኖ መገኘት ይቀድማል። እድሎች ቢያመልጡህ ተጎጂው አንተ ነህ፤ ከእራስህ ማግኘት የምትችለውንም ከሰዎች እየፈለክ፣ እየጠበክና በየቦታው እያሳደድክ ብትቆይ የምትጎዳው እራስህ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ከእራስህ ተነስ! ከእራስህ ጀምር፣ መውደዱን ከእራስህ ጀምር፣ ማክበሩን ከእራስህ ጀምር፣ ጊዜ መስጠቱን፣ ማዳመጡን፣ መንከባከቡን፣ መደገፉን፣ ማነቃቃቱን ከእራስህ ጀምር። ለእራስህ የማትሰጠውን ፍቅርና ክብር ለማንም መስጠት እንደማትችል እወቅ። በእራስህ ደስተኛ ሳትሆን ሌላውን ደስተኛ አደርጋለሁ ብለህ አታስብ፤ እራስህን ሳትመራ፣ ፍላጎቶችህን ሳትቆጣጠር፣ ስሜትህ ላይ ሳትሰለጥን ሰዎችን እመራለሁ፣ ድርጅትን አስተዳድራለሁ፣ ሀገርን እረከባለሁ፣ ትውልድንም አንፃለሁ ብለህ አታስብ። ማንም ሰው የሌለውን ነገር ሊሰጥ አይችልም። ትርጉም ሰጪው፣ አትራፊውና ውጤታማው ህይወት የሚመጣው ሌላ ከማንም ሳይሆን ከእራሱ ከባለቤቱ ነው። ክፍተትህን እንዲሞሉልህ የምትጠብቃቸው ሰዎች እራሳቸው የእራሳቸው ክፍተትና ድክመት ይኖርባቸዋል። ጫማህ ቢጠብህ እግርህን እንደማታስተካክለው ሁሉ ነገሮች እንዳሰብከው ካለሆኑ ከነገሮቹ በላይ ለነገሮቹ ያለህን አመለካከት መርምረህ አስተካክል።

አዎ! ጊዜያዊ የአመለካከት ስህተትህ የእድሜህን እኩሌታ በጥበቃና በወቀሳ እንዲጨርሰው አታድርግ። ለእራስህ መታመን እየተቸገርክ፣ የግል አቋም መገንባት ላይ እየተንገጫገጭክ፣ ወደፊት የሚመሩህን መርሆችን ወደኋላ እየጣልክ፣ እራስህን የበታች መጪዎቹን የበላይ፣ እራስህን ደካማ ገና ወደህይወትህ የሚገቡ ሰዎችን ጠንካሮች አድርገህ ማሰብ እስካላቆምክ ድረስ የምትጠብቀውን ውጤት በፍፁም ልታገኝ እንደማትችል እወቅ። እራስህን ተቀበል፣ ክፍተቶችህን ሙላ፣ ድክመትህን አርም፣ ወደህይወትህ እንዲገቡ የምትጠብቃቸው ሰዎች ሊያደርጉልህ የሚችሉትን ነገር በጥቂቱም ቢሆን ለእራስህ አድርግ። መውደድ፣ ማፍቀር፣ ማክበር፣ መንከባከብ እችላለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ በቅድሚያ ለእራስህ ከማድረግ ተነስ። 


በክብር ተቀበል!

ማንም ሰው የእራሱ መገለጫ፣ የእራሱ እምነትና የእራሱ የህይወት ዘይቤ ይኖረዋል። አስተዳደጉ፣ ባህሉ፣ አመለካከቱና አቋሙ ሁሉ የማንነቱ መገለጫ ነው። እስካመነበትና እስከተቀበለውም ድረስ ለእርሱ ልክ ነውና ከብሩና ኩራቱ ነው። የሌላውን ሰው የክብር መገለጫ፣ የሌላውን ባህልና እምነት ማክበር ደግሞ እራስን እንደማክበር፣ ለእራስም ጥበብን እንደማስተማር ነው። ከጥላቻ በላይ እለት እለት ፍቅርን የሚመግበን፣ መተሳሰብ መከባበርን የሚያስተምረን፣ ሰብዓዊነት ሰውነትን የሚያሳድርብን አምላክ አለን። የጎሪጥ በመተያየት የሚመጣ ነገር ቢኖር ጥላቻና መጠፋፋት ብቻ ነው። መከባበር፣ መፈቃቀር፣ መዋደድ ውስጥ ዋናውን የሰውነት ማንነት እናገኘዋለን። እንደጠዋቷ ጀምበር እንዲሁ እያየናት ለምትጠልቅ አጭር የህይወት ዘመናችን እርስበእርስ ባንገፋፋና ባንጠላላ ጥቅሙ ለእራሳችን ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! በክብር ተቀበል! ማንም የወደደውን ቢያደርግ፣ ማንም የትም ቢገኝ፣ ማንም በእምነት በአመለካከቱ ቢመላለስ አንተን እስካልነካና እስካልተጋፋህ ድረስ በክብር ተቀበለው፤ ወግ ባህሉን፣ አስተምህሮውንና እሳቤውን አክብርለት። ቢሳሳት እንኳ  በቂም በቁርሾ አትመልሰውም፤ ቢያጠፋ እንኳን ፊት በመንሳት፣ የማይሆን ስም በመስጠት አታስተምረውም። ፍቅር ሰውን ይገዛል፤ አክብሮትም ልብን ያቃናል። ጠልቶህ ጠልተሀው፣ ገፍቶህ ገፍተሀው፣ አርሱም ልታይ አንተም ልታይ ብለህ መቼም ደህንነትህን ልታስጠብቅ፣ ቁስልህን ልትሽርና ሰላምህን ልታስጠብቅ አትችልም። አፋፍና አፋፍ ቆመህ እርስበእርስ ብትነታረክ ነገህን ይባስ ታስከፋው፣ መጪውንም ጊዜህን ታጨልመው ይሆናል እንጂ አንዳች ትርፍ አይኖርህም።

አዎ! በፍቅር ግዛ፣ በክብር ተቀበል። ቂም ያነገበ፣ በእልህ የሚጓዝ፣ በጥላቻ የታወረ፣ ሁሌም እኔ ብቻ የሚል ሰው አትሁን። እግዚአብሔር በጊዜ መረብ ሁሉን ሲያነሳ ሌላውንም ሲተካ አይተናል። ትናንት ብዙ የተባለላቸው፣ ትናንት ስማቸው ብቻ የሚያስፈራ፣ ትናንት ደጋግ የነበሩ እንዲሁም ክፉዎች የነበሩ ዛሬ ጠፍተው፣ ተረስተው ከስመዋል። የዛሬውም ሆነ የነገው የህይወት ጉዞ ከዚህ የተለየ አይደለምና በአጋጣሚ ሁሉ እትመካ፤ ከአንተም በላይ ሰው የሌለ እይምሰልህ። በታሪክ እስራት እራስህን አትግረፍ፤ ውዷ ዛሬ ውስጥ ሆነህ በማታውቀው ትናንት ክስተት ጨጓራህን አትታመም፤ ውስጥህን አታቁስል። ወንድምህ ቢሳሳት በጥላቻ ከምትርቀው በፍቅር መልሰው፣ ማስተዋልን ቢያጣ፣ በጭፍን ቢጓዝ ዞር ብለህ ከምትፈርድመት፣ ስሙንም ከምታጠለሽ በክብር ተቀበለው፣ በትህትናም አስተምረህ መልሰው።


ተሸናፊ አትሁን!

ያለህን ሁሉ ሰጥተህ ልትሸነፍ አትችልም፤ የእውቀትህን ጥግ ተጠቅመህ ላይሳካልህ አይችልም፣ የምትችለውን ሁሉ አድርገህ ልትወድቅ አትችልም። እያንዳንዱን እርምጃህን ፈጣሪ ያያል፣ ፍላጎትህን በሚገባ ያውቀዋል፣ ጥልቅ ተነሳሽነትህን ጨምሮ ሁሉንም ጥረትህን ፈጣሪ በእርግጥም ይመለከታል። የሚሰጥም የሚነሳም እርሱ እንደሆነ ታውቃለህ፣ ነገሮችን የሚያሳካልህም እርሱ እንደሆነ ታምናለህ። እንግዲያውስ እምነትህን በእርሱ ላይ ጥለህ ካንተ የሚጠበቀውን ማድረግ ስለምን አቃተህ? እንግዲያውስ የሰጠህን ሁሉ አቅም ሳትጠቀም ስለምን የተሻለ ነገር እንዲሰጥህ ትጠብቃለህ? እንግዲያውስ እንዴት ለስንፍናህ እንዲሸልምህ ትመኛለህ? ዘመንህን በሙሉ ያለህን ሁሉ የማውጣት አቅም አይኖርህም፣ እድሜ ልክህን በፈለከው ሰዓት የምትጠቀመው ጥንካሬና ብርታት የለህም። ሰውነትህ ተጠቀምክበትም አልተጠቀምክበትም የሆነ ጊዜ መድከሙና ከቁጥጥርህ ውጪ መሆኑ አይቀርም። ሁሉም ነገር የሚጠቅምህ በትክክለኛው ጊዜ ስትጠቀመው ነው። አሁን ላይ ያለህን ነገር ሁሉ አውጥተህ እንዳትጠቀም የሚያደርግህ ብዙ ነገር ይኖር ይሆናል። ነገር ግን ሁሉም እንዳለ ሆኖ ምርጫህ ሁለት ነው። አንድም ምክንያትህን አልያም ትልቅ አቅምህን።

አዎ! ማንም የማታምንበትን ነገር እንድታደርግ አያስገድድህም፤ ማንም በግድ አሁን ካለህበት ቦታ አያወጣህም። "ሁሉም ነገር ሲወራ ቀላል ነው።" ከማለትህ በፊት ከወሬው በላይ አንተ በተግባር ያደረከውን ነገር በጥልቀት ተመልከት። ለምትፈልገው ነገር ያለህን ሁሉ ሰጥተሃልን? ቢሆንልኝ ብለህ ለምትመኘው ነገር የምትችለውን ሁሉ አድርገሃልን? የምትመኘውን ህይወት እንዳትኖር የከለከሉህን ነገሮች ለማሸነፍ የሚጠበቅብህን ሁሉ አድርገሃልን? አንድ ሰው ያለውን ሁሉ ከሰጠ፣ እስከ ጥግ ከተፋለመ፣ አንድን ነገር መርጦ እሱ ላይ ለዘመናት ከቆየ፣ የእኔ ነው የሚለውን ነገር ሳያቋርጥ ከሰራው በእርሱ ስኬታማ እንደሚሆን አምኖበታልና ማሳካቱ የማይቀር ነው። ይሔ ነገር ላንተም የማይሰራበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም። አማኝ አይቸኩልምና ፈጣሪ የልፋትህን ውጤት እንደሚሰጥህ ካመንክ፣ ያንተም ምርጫ ነፃ እንደሚያወጣህ ከተማመንክ አትቸኩል፣ አቋራጭ መንገድን አትመልከት፣ ትንሽ ሞክረህ ተስፋ አትቁረጥ፣ ነገሮች እንዳሰብከው ሳይሆኑ ሲቀሩም አታማር። መዋጥ ያለብህን እውነታ ዋጠው። የአቅምህን ሁሉ አውጥተህ ብትሰራ ሁሉም ነገር ይቀየራል።

አዎ! ጀግናዬ..! ራስህን ካልገደብክ፣ በፍቃድህ አቅምህን ካላሳነስክ፣ እምነትህን ካልሸረሸርክ፣ የውስጥ ፍላጎትህን ካልዘጋሀው በእርግጥም ትሸለማለህ፣ የምርም ታሸንፋለህ፣ የእውነትም ውጤታማ ትሆናለህ። "ምክንያት የሚደረድሩ ብፁዓን ናቸው" የተባለ ይመስል ሁሉም ሰው ምክንያት መደርደር ላይ አንደኛ ነው "አምነህ ስራ" ሲባል ግን ፊቱን ያዞራል። አትሸወድ አምነህ ስራ፤ እንዳትበላ የጉብዝናህን ወራት በሚገባ ተጠቀምባቸው። የተለየ ውጤት የሚያመጡት እነዛ የተለየ እምነትና የተለየ አፈፃፀም ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ እወቅ። ተሸናፊ አትሁን ያለህን ሁሉ ስጥ፣ መካከለኛ አትሁን የምትችለውን ሁሉ አድርግ፣ በሰዎች ጥንካሬና ስኬት አትቅና እንዴት ያንን ጥንካሬና ስኬት ወደ ራስህ ህይወት ማምጣት እንደምትችል መርምር። ሰዎች አዝነውልህ ፍርፋሪ እየሰጡህ የዘመናት አገልጋያቸው እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። ራስህን ቻል፣ ራስህን ወደፊት አውጣ፣ በድብቅ አቅምህ እመን፣ ውስጥህ ለሚንቀለቀለው የማያባራ ፍላጎት እድል ስጠው፣ ሳትሰስት አሁኑ በተግባር ግለጠው።


ክፍተቱን አጥብብ!

ከየትኛውም እርምጃህ በፊት የሚመጣ ለምን ይኖርሃል፣ ከየትኛውም ጅማሮህ አስቀድሞ ለምን እንደምትጀምር ታስባለህ፣ ምንም ነገር ከማቆምህ በፊት ለምን እንደምታቆም ለእራስህ አሳማኝ ማስረጃ ታቀርባለህ። ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴ በስተጀርም በጉልህ የሚነገር፣ ግልፅ ሆኖ መታየት ያለበት ለምንህን በአሳማኝ ሁኔታ የሚመልስ ምክንያት አለ። አሁን የምታደርገውን የምታደርገው ለምንድነው? ይህን ፅሁፍ የምታነበው ለምንድነው? እራስህን ለማስተማር፣ እራስህ ላይ ለመስራት የተነሳሀው ለምንድነው? ጠንካራው ለምንህ የውጤትህን ጥራት ይወስናል፤ ከኋላ የሚገፋህ ምክንያት ከመዳረሻህ የማድረስ ሃይል አለው። ህመም፣ ስቃይ፣ መገፋት፣ መከዳት፣ ሱስ፣ ገንዘብ ማጣት፣ ድህነት፣ የቤተሰብ ችግር፣ ውድቀት፣ የማይቋረጠው ፍላጎትህ? የቱ ይሆን የለምንህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው? የቱ ይሆን እስከጥግ እንድትታገል፣ እስከ ተራራው ጫፍ እንድትጓዝ የሚያደርግህ?

አዎ! ጀግናዬ..! ክፍተቱን አጥብብ፤ ርቀቱን ቀንስ፣ ከፍታውን ቁረጠው፣ ፍራሃትን አሸንፈው። ፍላጎትህና የአሁን ያለህበት ቦታ መሃል ያለውን ክፍተት አጥብብ፤ መድረስ የምትመኘው ስፍራና አሁን የቆምክበት ስፍራ መሃላ ያለውን ርቀት ቀንስ፤ እለት እለት አስሮ የሚይዝህን፣ በየሰዓቱ መሰናክል የሚሆንብህን ፍረሃት አሸንፈው። ከጀርባህ ለሚነዳህ ግፊት እድል ስጠው፣ ምክንያትህን በሙሉ ልብህ አዳምጠው፣ ምንለማግኘት እንደምትጥር፣ ለምን ዋጋ እንደምትከፍል፣ ለእራስህን እንደምታሰቃይ ጮክ ብለህ ለእራስህ ተናገር። ምክንያትህ ከምንም እንደሚበልጥ፣ ለምንህን ከየትኛውም ነገር እንደሚልቅ ጠንቅቀህ እወቅ። ከጥረትህ ጀርባ ልምድ አለ፣ በሙከራህ ውስጥ ድፍረት፣ ንቃት፣ ትጋት፣ ጥንካሬ፣ ብስለት አለ።

አዎ! ለምንህ ይነዳሃል፣ ለምንህ ይመራሃል፣ ለምንህ የህይወት አቅጣጫህን ይወስንልሃል። በየጊዜው ምክንያትህን አትቀያይር፣ አቋም አጥ በየሰዓቱ የሚረበሽና የሚታወክ ሰው አትሁን፣ ለምክንያትህ የምትተጋ፣ ለምንህን የምታስበልጥ፣ እራስህ ወደፊት የምትገፋ፣ ለእራስህ የገባሀው ቃልና ተግባርህ መሃል ያለውን ክፍተት (Gap) አጥበብ። ማቆምን እርሳውና እረፍት ለማይሰጥህ የውስጥ ህመምህ መፍትሔ ፈልግለት፣ የገንዘብ ችግርህን ለመቅረፍ ከምንም ጊዜ በላይ ጥረትህን ጨምር፣ ለቤተሰቦችህ ደስታ፣ ለወዳጆችህ እረፍት የምትፈራውን ነገር ፊትለፊት ተጋፈጠው። ለምንህን ባገኘህ ቅፅበት አላርምህን መዝጋት፣ Snooze Button መጫን ታቆማለህ፣ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ ታቆማለህ፣ ወደኋላ ከመመለስ እራስህን ትታደጋለህ በምትኩ ማድረግ ያለብህን እንዴት ልታሳካው እንደምትችል መንገድ መፈለግ ትጀምራለህ።


አስፈሪ ሰው ሁኑ!

አንድ ሰው ጥሩ ሰውም አስፈሪ ሰውም መሆን አይችልም ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተሳስታችኋል። በሚገባ ይችላል። በጥሩነት ማስፈራትን የተካኑ ብዙ ሰዎች አሉ። በብዙዎች የሚከበር የሚፈራና የሚደመጥ ሰው መሆን ከፈለጋችሁ በጣም ብዙ ጥረት አይጠበቅባችሁም። አንድ ወሳኝ ነገር ብቻ አድርጉ። ዝምታችሁ እንዲናገር አድርጉ። የዓለማችን በጣም አስፈሪውና አደገኛው ሰው ጮክ ብሎ የሚያወራና በሰው ፊት ለራሱ የተለየ ቦታ የሚሰጥ ሰው አይደለም። ይልቅ አስፈሪው ሰው ሙኑም የማይታወቀውና ከስንት አንዴ የሚናገረው ሰው ነው። አስፈሪ ሰው ብዙ የማይታይ ሃይል አለው። ብዙ አይናገርም ሲናገር ግን በአንዴ ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል፣ ብዙ ቦታ አይገኝም በሚገኝበት ስፍራ ግን በብዙዎች ይከበራል፣ ስለራሱ ደጋግሞ አያወራም በተግባር ያሳያል። ሰው እንዲፈራችሁ የምታደርጉት ሰውን ለመጉዳት ወይም በሰው ለመጠቀም ሳይሆን የራሳችሁን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ነው። የዋህነትም ሲበዛ እንደ ሬት ይጎመዝዛል። ለራሳችሁ መቆም የማትችሉ የሁሉም ሰው መጠቀሚያና መጫወቻ አትሁኑ።

አዎ! ራሱን የሚጠብቅ አስፈሪ ሰው ሁኑ፤ ራሱን አድኖ ለብዙዎች መትረፍ የሚችል መጥፎ ሰው ሁኑ። ጅብ ካለፈ እንደሚጮሀው ውሻ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ። ከብዙ አቅጣጫ ከተጎዳችሁና ከተበደላችሁ ቦሃላ ዳግም ለመነሳት አትፍጨርጨሩ። አስቀድማችሁ የማይናወጥ ፅኑ ማንነትን ገንቡ፣ ለራሳችሁ ተገን ሁኑ። ምንም አይነት ያለፍቃዳችሁ በህይወታችሁ ውስጥ የሚከናወን ነገር እንዲኖር አትፍቀዱ። አንዳንዴ ባዶ ክብር ያዋርዳል፣ ቀን ቆርጦ ዋጋ ያስከፍላል፣ ሳታስቡት አንገት ያስደፋችኋል። ፍረሃት የታከለበት ክብር ግን ድንበራችሁን ሁሉ ያስጠብቃል፣ ዙሪያችሁን ሁሉ ያፀዳዋል። ሃይላችሁን አሰባስቡ፣ አቅማችሁን አጠናክሩ፣ ደረጃችሁን ጨምሩ፣ የሚያኮራችሁን ስብዕናና ማንነት ገንቡ። በፍረሃት የምታከብሩትን አንድ ሰው አስቡ። ምናልባትም ያን ሰው ትወዱት ይሆናል፣ ትልቅ ቦታ ትሰጡት ይሆናል፣ በዛው ልክም ትፈሩታላችሁ። የምትፈሩት ሊጎዳችሁ ስለሚችል ወይም ልታሸንፉት ስለማትችሉ አይደለም። የምትፈሩት ከእናንተ የላቀ ደረጃን ስላለው ነው፣ በፍረሃት የምታከብሩት ኬት ተነስቶ አንዴት የት እንደደረስ በሚገባ ስለምታውቁ ነው፣ እናንተን ለማስፈራራት ምንም አይነት የተለየ ነገር ስለማያደርግ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ጥሩ ሰው ሁን በዛው ልክም ለሚንቁህና ለሚሳለቁብህ ሰው አስፈሪ መሆንህን እንዳትረሳ። ለሚወድህ ፍቅርን፣ ለሚያከብርህ ክብርን፣ ጊዜ ለሚሰጥህ ጊዜና ትኩረትን፣ ለሚያስደስትህም ሳቅና ደስታን ትሰጣለህ ለሚንቅህ ግን ክብርን ልትሰጥ አትችልም፣ ለሚያንቋሽሽህ ግን ቦታ ልትሰጥ አትችልም፣ ስምህን ለሚያጠፋው ግን ትኩረትህን ልትሰጠው አትችልም። ምንም ያህል መልካም ብትሆን መልካምነትህ በራሱ የማይሰራበት ስፍራ መኖሩን አስተውል። ለሰዎች ጥሩ ነገር አድርግ፣ ሰዎችን ውደድ፣ ሰዎችን አክብር የራስህን ክብር ግን በየቦታው አትጣል፣ በፍፁም ራስህን ባይተዋር አታድርግ። ለሰዎች ተፋለም ለራስህ ግን ከዛ በላይ ተፋለም፣ ሰዎችን ጠብቅ ራስህን ግን ከዛ በላይ ጠብቅ። ስምህ በጥሩነት ይነሳ፣ ምግባርህ በመልካምነት ይታወቅ ድንበርህ ሲታለፍ ግን ዝም እንደማትል አሳይ። ሰውን አትጥላ፣ ተጎድቼያለሁ ብለህ አቅም የሌለውን ሰው ለመጉት አትነሳ፣ በእውነቱ አዛኝ ልብ ይኑርህ። ነገር ግን አቅምህን ሊገዳደር ለሚመጣው በር ሰባሪ እውነተኛ ማንነትህን አሳየው። አስፈሪ ሰው የሚያስፈራው አንዱ በትዕግስቱ ሲሆን ሌላውም በዝምታው ነው። በዙሪያህ ካሉ ሰዎች ሁሉ ዝምተኛውና ታጋሹ ሰው ሁን፣ የአስፈሪነትን ሃይልም ተጎናፀፍ።


እኔ ግን አደረኩት!

ከእራስ ጋር ንግግር፦ "ስለ ገዛ ሰላሜ፣ ስለ ውስጣዊ መረጋጋቴ፣ ስለ እኔነቴ፣ ስለ ማንነቴ ብዙ አሰብኩ፣ ብዙ አወጣው ብዙ አወረድኩ፣ ብዙ ሰማው ብዙ አወራው። በስተመጨረሻም አንድ ነገር አስተዋልኩ የሰላሜ ባለቤት፣ የመረጋጋቴ መሰረት፣ የጤንነቴ ምንጭ፣ የመንፈሴ ገዢ አምላኬ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ ደረስኩበት። ውስጥን በድፍረት ማዳመጥ ይህን ያክል ቀላል ባይሆንም ይጠቅመኛልና አደረኩት፤ አይኖች ሁሉ ውጪውጪውን በሚያማትሩበት፣ ሰው ሁሉ ሃሳቡ በተሰረቀበት ወቀት እራስን መመልከት ቢከብድም፣ ስለ እራስ ማሰብ፣ ስለ እራስ ማሰላሰል ቢከብድም እኔ ግን አደረኩት፤ ዓለም አጀንዳዋ ባያልቅም፣ ዘወትር ኮሽታ ባይጠፋትም፣ ትኩረቴንም አብዝታ ብትፈታተንም እኔ ግን የእርሷን አጀንዳ ትቼ፣ ጫጫታዋን ወደኋላ ገፍቼ እራሴ ላይ ማተኮር ቻልኩኝ። 

አዎ! ዋናው አላማዬ ብዙ ተጉዤ፣ ብዙ ለፍቼ፣ ብዙ ደክሜ፣ ትልቅ ዋጋ ከፍዬ የምደርስበት ስፍራ አይደለም፤ ይልቅ በጉዞዬ መሐል የምገነባው ማንነትና የምፈጥረው ስብዕና ነው። እንደማንኛውም ሰው ጉድለት ቢኖርብኝም እንደማንኛውም ሰውም የተባረኩበት ነገር አለኝ። አምላኬን የማመሰግነው የሚያስፈልገኝን ስለሰጠኝ፣ የሚገባኝ ስፍራ ስላደረሰኝ፣ በጉዞዬ ሁሉ ስለረዳኝ፣ በመውጣት መውረዴ፣ በመውደቅ መነሳቴ፣ በመተቸት መወደሴ ሁሉ አብሮኝ ስለነበረ ብቻ አይደለም። የምስጋናዬ ምክንያት ሰውነቴ ነው፤ የምስጋናዬ ምክንያት እኔን እኔ ስላደረገኝ ነው፤ የአድናቆቴ መንስኤ የአባትነት ፍቅሩ፣ የአምላክነት ስጦታው ነው። እራሴን በማውቀው ልክ ለእራሴ መሆን ባልችልም አምላኬን በማውቀው ልክ ግን እለት እለት በቃሉ ለመመራት፣ ትዕዛዙን ለማክበር፣ ይቅርታውን ለማግኘት የምጥር ምስኪን ልጁ ነኝ። አመስጋኝህ ስላደረከኝ አመሰግንሃለሁ፤ ስጦታህን እንድረዳ በረከትህንም እንድመለከት ስላስቻልከኝ ከልቤ አከብርሃለሁ፤ በደካማው ማንነቴም እወድሃለሁ።

አዎ! ጀግናዬ...! ከእራስህ ገር የምታደርገው ንግግር በአስተውሎት አድርገው፤ ከአምላክህ ጋር ስትወያይ ጉዳይ ከልብህ ተወያይ። ሰው አይኘን አላየኝ፣ ሰማኝ አልሰማኝ፣ ስም አወጣልኝ ፈረደብኝ ብለህ አትፍራ። እራስህ ከእራስህና ከአምላክህ በላይ የሚያቅስህ አካል የለም። እራስህ ላይ ብትፈርድ፣ ለእራስህ የግል አቋም ብታበጅ፣ እምነትህን ብትፈትን፣ መንገድ ብትስት፣ ብትሳሳት ቀዳሚው ሃላፊነት የእንደሆነ አስተውል። ከእራስህና ከደጉ አባትህ በቀር ማንም ስለማይሰማህ የልብ ንግግር አትጨነቅ፤ ከእራስህና ከህያው አምላክህ በቀር ማንም በማያይህ መንፈሳዊ ተግባርህ አትሸማቀቅ። ከእራስህ ጋር ለመነጋገር ነፃ ሁን፤ ከአምላክህ ለመማከር ዘወትር መንፈሰ ጠንካራ ሁን።


ትግልህን ምረጥ

ከሕይወት የምትፈልገው ምንድነው?” ብዬ ብጠይቅህና “ደስተኛ መሆን፣ ታላቅ ቤተሰብ መመስረትና የምወደው ስራ እንዲኖረኝ፡፡” ብለህ ብትመልስልኝ፣ መልስህ የተለመደና የሚጠበቅ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ትርጉም የሌለው ይሆናል፡፡

ሁሉም ሰው ጥሩ በሆነው ይደሰታል፡፡ ሁሉም ሰው ጭንቀት የሌለበት፣ ደስተኛና ቀላል ሕይወት መኖር፤ በፍቅር መውደቅ፣ በጣም ደስ የሚል ወሲባዊ ግንኙነትና የፍቅር ጓደኝነት፣ ዘናጭ መሆንና ገንዘብ መስራት፣ ታዋቂና የተከበረ መሆን፣ በጣም የተደነቀ ከመሆን የተነሳ ወደ አንድ ቦታ ሲራመድ ሰዎች እንደ ቀይ ባህር የሚከፈሉለት ቢሆን ይፈልጋል፡፡

ሁሉም ሰው ያንን ይፈልጋል፤ ያንን መፈለግ ቀላል ነው፡፡

በጣም ደስ የሚለውና ብዙ ሰዎች በጭራሽ የማያስተውሉት መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ግን “በሕይወትህ ውስጥ ምን አይነት ስቃይ ትፈልጋለህ? ልትታገል የምትፈልገው ምንድነው?” የሚል ነው፡፡ምክንያቱም ህይወታችን እንዴት እንደሚሆን የሚወስነው ትልቁ ነገር ያ ነውና፡፡

ለምሳሌ ብዙ ስዎች አሪፍ ቢሮ እንዲኖራቸውና ብዙ ገንዘብ መስራት እንዲችሉ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በሳምንት ስልሳ ሰዓት በመስራት፣ በረጅም ጉዞዎችና አሰልቺ በሆኑ የወረቀት ስራዎች መሰቃየት የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ አይደሉም፡፡

ብዙ ሰዎች አሪፍ ወሲብ፣ ጥሩ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ወደዚያ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ንግግሮችን፣ አሳፋሪ ሁኔታዎችንና የስሜት መጎዳቶችን ለማለፍ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ከዚያ ይረጋጉና፣ ጥያቄው ከ “ቢሆንስ?” ወደ “ከዛስ?” እስኪለወጥ ድረስ ለአመታት ያስባሉ፡፡

ደስታ ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ የሚነሳው ከችግር እንጂ ልክ እንደ አበባና ቀስተደመና ከመሬት የሚነሳ አይደለም፡፡ እውነተኛ የእድሜ ልክ እርካታና ትርጉም የሚገኘው ትግሎቻችንን በመምረጥና ማስተዳደር በኩል ነው፡፡

አሪፍ የሰውነት አቋም እንዲኖርህ ትፈልጋለህ እንበል፡፡ ነገር ግን ለብዙ ሰዓታት ጂም ውስጥ በመስራት የሚያጋጥምህን ህመምና አካላዊ ጭንቀት በፅናትና በደስታ ካልተቋቋምክ፣ የምትመገበውን ምግብ መመጠን እና ማስተካከል ካልወደድክ፣ የምትፈልገውን በስፖርት የተገነባ ሰውነት አታገኝም፡፡

ሰዎች የራሳቸውን ስራ መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ያንን ለማድረግ በሚደረግ ሙከራ የሚያጋጥማቸውን አደጋ፣ እርግጠኛ ያለመሆን፣ ተደጋጋሚ ውድቀት ካልተቋቋሙ፣ ምንም ነገር ጠብ ለማይል ነገር ያጠፏቸውን ጊዜያት በደስታ ካልተቀበሉ፣ስኬታማ ስራ ፈጣሪ መሆን አይችሉም፡፡

ሰዎች የትዳር አጋር፣ ወይም የፍቅር ጓደኛ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ከሚያጋጥሙህ ተደጋጋሚ አለመፈለጎች የተነሳ የሚመጣብህን የስሜት መዋዠቅ በትዕግስት  ካላለፍክ፣ ማስተንፈስ የማትችለውን ወሲባዊ ውጥረት ካልተቋቋምክና የማይደወል ስልክ ላይ ማፍጠጥን ካልተጋፈጥክ ማራኪ አጋር ማግኘት አትችልም፡፡ ይህ የፍቅር ጨዋታ ክፍል ነው፡፡ ካልተጫወትክ ማሸነፍ አትችልም፡፡

ያንተን ስኬት የሚወስነው “በምን መደሰት ትፈልጋለህ?” በሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ወደ ደስታ የሚወስደው መንገድ በሚያንሸራትቱ ነገሮችና በእፍረት የተሞላ በመሆኑ ተገቢ የሚሆነው ጥያቄ “ምን አይነት ስቃይን መቋቋም ትፈልጋለህ? የሚል ነው፡፡ ሕይወት ሁልጊዜ በፅጌረዳ ያሸበረቀ ሊሆን አይችልም፡፡ ስቃይ አልባ ሕይወት ሊኖርህ የማይችል ከሆነ ደግሞ የሆነ ነገር መምረጥ አለብህ ፡፡

በአብዛኛው በጉርምስናና በወጣትነት ዘመኔ ሙዚቀኛ በተለይም የሮክ ሙዚቃ ኮከብ ስለመሆን አልም ነበር።የትኛውንም በጊታር የታጀበ ሙዚቃ ስሰማ አይኖቼን ጨፍኜ በምናቤ ራሴን መድረክ ላይ በአድናቆት
ለሚጮኹ ብዙ ሰዎች ጊታር ስጫወት፣ ሰዎች በእኔ ጊታር አጨዋወት ተማርከውብ ራሳቸውን ሲስቱ እመለከት ነበር፡፡ ሀሳቡ ለእኔ ቢሆንስ? የሚል ጥያቄ ስላልነበረ ይህ ህልም ለሰአታት ይዞኝ ይቆይ ነበር፡፡ በአድናቆት በሚጮኹ ተመልካቾች ፊት እንደምጫወት እርግጠኛ ነበርኩ፤ ግን መቼ? ሁሉንም ማቀድ ነበረብኝ፡፡ እዚያ ደርሼ አሻራዬን ለማሳረፍ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን ኃይልና ጥረት መስጠት ከመቻሌ በፊት ጊዜዬን መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ በመጀመሪያ ትምህርቴን መጨረስ፣ ከዚያ ጊታር ለመግዛት ተጨማሪ ገንዘብ መስራት፣ ከዚያ ደግሞ ለመለማመድ በቂ ነፃ ጊዜ ማግኘት፣ ቀጥሎ የመጀመሪያ ፕሮጀክቴን ማቀድ ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ከዚያ... ከዚያ. . . በቃ፡፡

ይህንን ነገር የእድሜዬን ግማሽ ያህል ሳልመው የኖርኩ ቢሆንም ምኞቴ ግን ለፍሬ አልበቃም፡፡ በመጨረሻ ለምን ለፍሬ እንዳልበቃ እስክረዳ ድረስ ረጅም ጊዜና ረጅም ትግል ወስዶብኛል፡፡ ለካ ለፍሬ ያልበቃው ከልቤ ስላልፈለግኩት ነበር፡፡

በምናቤ ራሴን መድረክ ላይ ሆኖ ሳየው፣ ሰዎች በአድናቆት ሲጮሁ፣ እኔ ፍፁም ከልቤ ሆኜ ጊታር ስጫወት ሳልም ፍቅር የወደቅኩት ከውጤቱ ጋር እንጂ ከሂደቱ ጋር አልነበረም፡፡

ያልተሳካልኝም በዚያ ምክንያት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ወድቄያለሁ፡፡ በበቂ ሁኔታ አለመሞከር ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አልሞከርኩም ማለት ይቻላል፡፡ የየእለቱ አሰልቺ ልምምድ፣ የሙዚቃ ቡድን መፈለጉና አብሮ መለማመዱ፣ ሰዎችን የመጠበቁ ስቃይ፣ የጊታሬ ክሮች መበጠስ፣ እቃዎቼን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የመኪና አለመኖር ህልሜን ተራራ የሚያክል አድርጎብኝ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ለመድረስ ደግሞ ተራራውን መውጣት ያስፈልግ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የወደድኩት ውጤቱን በምናቤ ማየት ብቻ ስለነበር፣ ብዙም ተራራ መውጣት እንደማልወድ ለመረዳት ብዙ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡

የተለመደው ባህላዊ ትረካ ያቋረጥኩ ወይም ተሸናፊ መሆኔ፣ “ያላገኘሁ” መሆኔ፣ ህልሜን በመተው እና ምናልባትም በህብረተሰቡ ጫናዎች እንድሸነፍ በማድረግ በሆነ መንገድ ራሴን እንድወድቅ ያደረግኩ እንደሆንኩ ይነግረኛል፡፡

እውነቱ ግን ከእነዚህ ገለፃዎች በተሻለ ደስ የሚል አለመሆኑ ነው፡፡ እውነቱ የሆነ ነገር እንደምፈልግ አስቤ ነበር፡፡ ግን አልፈለግኩም ነበር፡፡ አለቀ፡፡ የፈለግኩት ሽልማቱን እንጂ ትግሉን አልነበረም፤ የፈለግኩት ውጤቱን እንጂ ሂደቱን አልነበረም፡፡ ፍቅር የያዘኝ ከድሉ እንጂ ከትግሉ አልነበረም፡፡

ሕይወት ደግሞ በዚያ መንገድ አይመራም፡፡ማንነትህ የሚታወቀው ልትታገልለት ፈቃደኛ በሆንከው ነገር ነው፡፡ ስፖርት የመስራትን ትግል በደስታ የሚቀበሉ ሰዎች የሚፈልጉትን ስፖርታዊ አቋም ያገኛሉ፡፡ ረጅም የስራ ሳምንትንና ቢሮክራሲ መቋቋም የሚችሉ ሰዎች የአመራር መሰላል ጫፍ ላይ መድረስ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡

ይህ ስለ ቆራጥነት ወይም ጥርስን ስለመንከስ አይደለም፡፡ ይህ “ህመም ከሌለ ማግኘት የለም” የሚለው አይነት ሌላ ግሳፄ አይደለም፡፡ ይህ ትግላችን ስኬታችንን ይወስናል፡፡  ችግሮቻችን የደስታዎቻችን መፈጠሪያ ናቸው የሚል የሕይወት በጣም ቀላሉና መሰረታዊ አካል ነው፡፡

አየህ ይህ መጨረሻ የሌለው ቀጥ ብሎ የቆመ ጠመዝማዛ ብረት ነው፡፡ የሆነ ነጥብ ላይ መውጣት ማቆም እንደሚፈቅድልህ ካሰብክ፣ ነጥቡን ስተሃል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም ደስታው ያለው በራሱ በመውጣቱ ላይ ነውና!!


ጠንካራ ሁኑ!

በምድር ላይ በክብር ትመላለሱ ዘንድ፣ ዓለም ቦታ ትሰጣችሁ ዘንድ፣ ሰዎች ይፈልጓችሁና ይመርጧችሁ ዘንድ፣ የህይወትን ፈተናንም በድል ትወጡ ዘንድ ጠንካራ ሁኑ። ከአለት የጠነከረ ጠንካራ፣ በእሳት ተፈትኖ ከሚወጣው ብረት በላይ ጠንካራ፣ ልቡ የደነደነ፣ ውስጡ የረጋ፣ ለምንም ለማንም የማትበገር ብርቱ ጠንካራ ሰው ሁኑ። በዚህ ዓለም ለደካሞች ቦታ የለም፣ ምድር ሰነፎችን ሸልማ አታውቅም። ህይወትን እስከኖራችሁ ድረስ የጀብደኛ ህይወትን ኑሩ። በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ ምንአይነት ከባባድ ነገሮች እንደሚፈጠሩ አናውቅም። ነገር ግን የምናውቀው አንድ ነገር አለ እርሱም "ጠንካራ ካልሆንን በእነዛ ከባባድ ክስተቶች ምክንያት አሳዛኝ ህይወት መኖራችንን ነው።" ተስፋችሁ የመከነ ቢመስላችሁም በፍፁም ተስፋ አትቁረጡ፣ ህይወት ከባድ ብትመስላችሁም በፍፁም እጅ እንዳትሰጡ፣ ሰዎች እንደገፏችሁ ቢሰማችሁም ለራሳችሁ ብርቱ ወዳጅ ሁኑ። ደካማ መሆን ለውድቀት ያመቻቻችኋል፣ ስንፍና በቀላሉ እንድትሸነፉ ያደርጋችኋል፣ ልፍስፍስ መሆን ተስፋን ያሳጣችኋል። ከልባችሁ አስባችሁ አቅማችሁን መዝኑት፣ ጥንካሬያችሁን ለኩት፣ ከፊትለፊት የሚጠብቃችሁን ፈተና ለማለፍ ያላችሁን ብርታት መርምሩት።

አዎ! ጠንካራ ሁኑ፣ በጨለማ መሃል ብረሃንን የምትመለከቱ፣ በማጣት ሰዓት ማግኘትን የምታምኑ፣ በረሃብ ወቅት ጥጋብም እንደሚኖር የምታስተውሉ፣ በብቸኝነት ሰዓት የፈጣሪ አብሮነት እንዳለ የምትረዱ፣ በመገፋት ወቅት ማራኪ ፍቅር እንደሚመጣ የምታስቡ ጠንካራ ሰው ሁኑ። በምንም መንገድ ለራሳችሁ የደካማነት አማራጭ አትስጡ፣ ፈተና ቢበዛ፣ ችግር ቢፈራረቅ፣ ዓለምም ፊቷን ብታዞርባችሁ እንዴትም በህይወታችሁ ተስፋ እንዳትቆርጡ። አስቀድማችሁ ያያችሁት ብሩህ ቀን ከጨለማው ማግስት ይጠብቃችኋል፣ ከልባችሁ ከምትፈልጉት መንፈሳዊ ደሴታችሁ በችግራችሁ በኩል ትደርሱበታላችሁ፣ ደጋግማችሁ ያሰባችሁት ለውጥና እድገት በጥረታችሁ ልክ እጃችሁ ይገባል። በማጣት ውስጥም ብትሆኑ፣ ለጊዜው ስኬት ቢርቃችሁ፣ በሰዓቱ የምትፈልጉበት ቦታ ባትደርሱ፣ ውስጣችሁ መረጋጋት ቢሳነው፣ መቋጫ የሌለው ሀሳብ ፋታ ቢነሳችሁ እንኳን መኖር የሚያምርባችሁ ጠንካራ ስትሆኑ ብቻ እንደሆነ እወቁ፣ ዓለም እጇን ዘርግታ በፍቅር የምትቀበላችሁ አሸናፊዎች ስትሆኑ ብቻ እንደሆነ ተረዱ።

አዎ! ጀግናዬ..! የልብህን እምነት መደበቅ አትችልም፣ ምግባርህን ሸሽገህ አትዘልቀውም፣ ስንፍናህን ልትሰውረው አትችልም። እምነትና አስተሳሰብህ ሳይውል ሳያድር በውጤትህ ይገለጣል፣ ለራስህ የምትሰጠው ቦታና በራስመተማመንህ በተግባርህ ይታያል። ጠንካራ፣ ለዓለም ፈተና የማይበገር፣ በምድራዊ ችግር ተስፋ የማይቆርጥ፣ ልቡን በአምላኩ ፍቅር ያደነደነ፣ ረዳት ደጋፊውን እያሰበ የሚፀና ሰው መሆን ከፈለክ ስቃይን አትሽሽ፣ ፈተና በመጣ ቁጥር አታማር፣ ችግር ሲደራረብብህ ቶሎ አትብረክረክ። በቀላሉ የሚገኝ ጥንካሬ የለም፣ እንደ ቀልድ የሚገኝ ብርታት የለም። "በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።" እንዳለ ቅዱስ መፅሐፍ ዓለምን ያሸነፈላችሁን ፈጣሪ እያሰባችሁ ጠንክሩ፣ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ እያሰባችሁ በመከራ መሃል ፅኑ። ተስፋ የማይቆርጥ ትውልድ እርሱ በስተመጨረሻ አስደሳቹን የድል ፅዋ እንደሚጎነጭ እመኑ።


ብቸኝነቴ አይሰብረኝም!

ከእራስ ጋር ንግግር፦ "ብቻዬን ብሆንም ያሰብኩበት ሳልደርስ አላቆምም፤ ቢደክመኝም ከሙከራዬ አልገታም፤ ጫናዎች ቢበዙብኝም፣ ተስፋዬ ቢጨልምም፣ ደጋፊ ባጣም፣ የሚረዳኝ ባይኖርም፣ ደጋግሜ ብሰበርም፣ በሰዎች ዘንድ ዋጋ ባይኖረኝም ለእራሴ ብዬ በከባዱ መንገድ እጓዛለሁ፣ ለቤተሰቦቼ ብዬ መክፈል ያለብኝን ዋጋ እከፍላለሁ፣ ለምወዳቸውና ለሚወዱኝ ስል እስከ ጥግ እፋለማለሁ፣ በእኔ በኩል እንዲጠቀሙ የምፈልጋቸው ሰዎች እንዲጠቀሙ፣ ፈጣሪዬ በእኔ እንዲደሰት፣ ለላቀው ክብርም እንዲያጨኝ ስል እርሱ በሚወደው መንገድ እራሴን እሰራለሁ፣ ለብዙዎችም ብቁ አድርጌ እገኛለሁ። ብዙ የማይመቹ ሁኔታ ውስጥ እራሴን ባገኝም እለት እለት ሁኔታዎች ለእኔ እንዲመቹ ለማድረግ መትጋቴን እቀጥላለሁ።

አዎ! ብቸኝነቴ አይሰብረኝም፤ መገፋቴ እራሴን እንድጠላ አያደርገኝም፤ መጠላቴ ለእራሴ የምሰጠውን ቦታ አያሳንሰውም፣ መውደቅ መሰበሬ ተስፋቢስ ሰው አያደርገኝም፣ ብቻዬን መቅረቴ፣ የሚያምንብኝ ማጣቴ፣ የሚደግፈኝ፣ የሚያግዘኝ፣ የሚያበረታኝ ማጣቴ ከጉዞዬ አይገታኝም፣ ፍፁም ወደኋላ አያስቀረኝም፣ መቼም በእራሴ እንዳዝንና ተሰብሬ እንድቀር አያደርገኝም። እራሴን አውቃለሁ፣ ፍላጎቴን አውቃለሁ፣ ወዴት እንደምሔድ፣ ምን እንደማደርግ፣ በእያንዳንዱ እርምጃዬ ውስጥ ማን አብሮኝ እንዳለ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ተፈጥሮዬን አከብራለሁ፣ ማንነቴን እወደዋለሁ፣ በእኔነቴ እኮራለሁ፣ በአምላኬ ሃይል፣ በፈጣሪዬ መንፈስ እተማመናለሁ፣ በተሰጠኝ ፀጋ፣ በታደልኩት መክሊት ከልቤ አምናለሁ። የምኖረው ለማንም ሳይሆን ለምወደው ሰውነቴ ነው፣ የምኖረው ለማንም ሳይሆን በእኔ ለሚደሰቱ፣ በእኔ ለሚያርፉና በእኔ ምክንያት ፈጣሪያቸውን ለሚያመሰግኑ ነው። እግዚአብሔር አምላኬ ያለምንም ቅድመሁኔታ እንደሚወደኝ አውቃለሁ።

አዎ! ጀግናዬ..! "ብቸኝነቴ አይሰብረኝም፤ ማጣት ዋጋዬን አያሳንስም፤ ስብራቴ ህይወቴን ጥላሸት አይቀባው፤ በሰዎች የሚሰጠኝ መጥፎ እስተያየት ከጉዞዬ አያደናቅፈኝም፤ ከእራሴ በላይ በሚያስብልኝ አምላኬ የማይሸረሸር መተማመን አለኝ።" ብለህ ለእራስህ ንገረው። ከእራስህ መምጣት ላለበት ብርታት፣ ከውስጥህ መመንጨት ላለበት በእራስመተማመን፣ በማንነት ሊገለፅ ለሚገባው ጀግንነትህ ማንንም አትጠብቅ፣ ማንም እርሱን እንዲልህ አትጠብቅ፣ ማንም የልብ ትርታህን እንዲያወራልህ አትጠባበቅ። እራስህን በማበርታት ህይወትህን በከፍታው ላይ ምራው፣ ለአንተነህ ተገን ሁን፣ ለምትፈልገው ነገር እራስህን በመስጠት፣ ለምርጫህ እስከመጨረሻው በመታገል የምትመኘውን ሰው ሁን። አስደናቂው አዕምሮህ፣ አስገራሚው የአምላክህ መንፈስህ የማይቻለውን እንዲያስችልህ ፍቀድ፣ የማይታመን የሚመስለውን አምኖና በተግባር አድርጎ በገሃድ እንዲገለፅ አድርግ።


ወደፊት ሂዱ!

አሁን የት ናችሁ? እናንተ ጋር ያለው እውነት ምንድነው? ቆም ብላችሁ በጥልቀት ስታስቡ ምን ጎልቶ ይታያችኋል? በአስተሳሰብ እስራት አትታሰሩ፣ በሰዎች አመለካከት አትገደቡ፣ ፍረሃት መረማመጃ እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ። ለማንም የማይታየው፣ ማንም ሊረዳው የማይችለው እውነት እናንተ ጋር አለ። እውነታውም ወደፊት መሔድ ነው፤ እውነታው ዝም ብሎ መጓዝ ነው፤ እውነታው ትርጉም ባለው መንገድ ህይወትን መኖር ነው። ለማንም ብላችሁ አትሳቀቁ፣ ለማንም ብላችሁ አትሸማቀቁ፣ በምንም ነገር ላይ ተስፋ አትቁረጡ። ልባችሁ ውስጥ ጥልቅ ፍላጎት ካለ፣ ከማንነታችሁ ጋር የተዋሃደ ብርቱ ሀሳብ ካለ ለማን ብላችሁ ሳትኖሩት ትቀራላችሁ? ለማን ብላችሁ ሳታደርጉት ትቀራላችሁ? ማን ደስ እንዲለውስ ነው ሄዳችሁ የማታገኙት? አሁን ከምትኖሩት የተለየ ህይወት እንዳለ የምታምኑ ከሆነ ያለምንም ግፊትና ጫና ራሳችሁን ወደፊት ግፉት፣ ማንም ሳያስገድዳችሁ ጉዟችሁን ጀምሩ። በእርግጥ ፈልጋችሁ ባላችሁበት ቦታ ለረጅም ጊዜ አትኖሩም። ነገር ግን እንዳልፈለጋችሁት ለማሳየት የግድ መሞከር ይኖርባችኋል።

አዎ! ወደፊት ሂዱ፣ ተንቀሳቀሱ፣ ሁሌም ራሳችሁን ለተሻለ ነገር ለማብቃት ትጉ። ያሰሯችሁ ብዙ ነገሮች ይኑሩ፣ በብዙ ነገር ተያዙ፣ ማንም ምንም ይበላችሁ እናንተ ግን ጉዟችሁ ላይ ብቻ አተኩሩ፣ እናንተ ግን ስለአሁኑና ስለቀጣይ እርምጃችሁ ብቻ አስቡ። ሁሌም ቢሆን አንድ የተለየ መንገድ እንዳለ አትርሱ። ብዙ ሰው የሚመለከተውንም የማይመለከተውንም ለመረዳት ይታገላል፣ ሁሉም ነገር እንዲገባው ይፈልጋል። እውነታው ግን አዕምሮው የሚቀበለውና የሚረዳው በአቅሙ ልክ መሆኑ ነው። ለአዕምሯችሁ ሰላም፣ ለውስጥ መረጋጋታችሁ፣ ለለውጥ ተነሳሽነታችሁ፣ ህልማችሁን ለመኖር፣ የአላማ ሰው ለመሆን ብላችሁ ሁሉንም ነገር ለመረዳት አትሞክሩ። አዕምሯችሁ በዚህም በዛም ጉዳይ ተወጥሮ እንዴትም በትክክል ሊያስብና ሊያስተውል አይችልም። ሄዳችሁ ሄዳችሁ ለብቻ የምትቀሩት እናንተ እንደሆናችሁ አስተውሉ። በፍፁም እዚም እዛም የሚገባ፣ ይሔም ያም የሚያሳስበው ብኩን ሰው እንዳትሆኑ። የራሳችሁ ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሩ፣ ወደፊት ፍሬ የሚያፈራላችሁን ተግባር ብቻ ፈፅሙ፣ የሚመለከታችሁና የሚጠቅማችሁ ቦታ ብቻ ተገኙ።

አዎ! ጀግናዬ..! ድካም በማንኛውም ሰዓት ይመጣል፣ ስንፍና ሁሌም ከበርህ አፋፍ ሆኖ ይጠብቅሃል፣ መቼም ከችግር የፀዳ ህይወት ልትኖር አትችልም። ዋናው ቁብነገር ግን በዚህ ሁሉ መሃል ወደፊት መራመድ መቻልህ ነው። ለማንም ብለህ ለዘመናት አንድ ቦታ ቆመህ አትቅር፣ ማንም እንዲደሰት ወይም ያዝንብኛል ብለህ ፍረሃትህን አትኑረው። ከታጠረልህ አጥር ውጣ፣ ከገባህበት አዘቅት ራስህን መንጭቀህ አውጣ፣ እስራትህን ፍታ፣ በገዛ ሰማይህ ላይ በከፍታ መብረሩን እወቅበት። ጉዞ የሌለው ህይወት ይሰላቻል፣ ለውጥ የሌለው ኑሮ አያጓጓም። ለውጥን አማራጭ አታድርገው፣ ወደፊት መጓዝን መብት አታድርገው። እየተለወጥክ ካልሆነ፣ እያደክ ካልሆነ፣ ሌላው ቢቀር እንኳን እንደ አቅምህ እየጣርክ ካልሆነ ስለህይወት ክፉና ደግ ለማውራት ብቁ እንደሆንክ አታስብ። ነገሮችን አታወሳስብ፣ ችግርና መሰናክሉ ላይ ብቻ አታተኩር። አንቂ ሳትፈልግ በራስህ ንቃ፣ አበረታች ሳትፈልግ ራስህ በርታ፣ ሁሌም ወደፊት ወደ ግብህ አቅጣጫ መጓዝህን ቀጥል።


ፍቅርን ብለሽ...!

ፍቅርን ብለሽ ብታቀረቅሪ፣ አንገትሽን ብትደፊ፣ ብትታዘዢ፣ ዝቅ ብትይ፣ እራስሽን ብትሰዊ፣ እራስሽን ብትሰጪ ምንም ክፋት የለውም። ክፋቱ ፍቅርን ብለሽ ባቀረቀርሽበት ስትረገጪ ነው፤ ፍቅርን ብለሽ እራስሽን በሰጠሽበት ስትሰቃዪ ነው፤ ፍቅርን ብለሽ ብትታዘዢ እንደባሪያ ስትቆጠሪ ነው። ሁሌም ያንቺ ፍቅር በመልካም ሃሳቦች፣ በቅን ተግባሮችና በበጎ ሁነቶች የተደገፈ ሊሆን ይችላል፣ የተቀባዩ ግን በበደልና በክፋት ከታገዘ፣ በጭካኔ ከተሞላ፣ ርህራሄ ከራቀው፣ ፍቅርን ካልታደለ ያንቺ ፍቅርን መምረጥ፣ በፍቅር መመላለስ፣ ፍቅርን ማለት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም። ፍቅር እንዲገባው የሚፈልግ ሰው ይገባዋል፤ ካልፈለገ ግን ሊገባው ቀርቶ ምንም ለመረዳትና ለማስታወስ አይፈልግም።

አዎ! ጀግኒት..! ፍቅርን ብለሽ ፍቅርን አትግፊ፤ ያተረፍሽ መስሎሽ አታጉድይ፣ ያገኘሽ መስሎሽ አትጪ፤ ባንቺ ውስጥ ባለው ስሜት ብቻ እየተመራሽ አንቺን ብሎ ከመጣው አትሽሺ። በፍቃድሽ ሰዶ ማሳደድ ውስጥ አትግቢ። ለእውነተኛ ስሜትሽ፣ ለጥልቅ ፍቅርሽ ዋጋ ብትከፍይም፣ ብትሰቃይም፣ ብትወጪም ብትወርጂም ይህ ሁሉ መሱዓትነት ለፍቅርሽ ዋስተና፣ ላንቺም ደህንነት ጠበቃ ሊሆንሽ እንደማይችል አስታውሺ። ስትወጂው የማይወድሽን፣ ጊዜ ስትሰጪው ጊዜ የማይሰጥሽን፣ ስትከተይው የሚሸሽሽን፣ ስትደግፊው የሚጎዳሽን፣ ስታክሚው የሚያሳምምሽን እያሳደድሽ ተንከባካቢሽን፣ ውድ አፍቃሪሽን፣ ጠባቂሽን እንዳታጪ፣ በምላሹም ከረፈደ ወደማሳደድ እንዳትገቢ ተጠንቀቂ።

አዎ! ጀግናዬ..! የሚያለቅስልህ፣ የሚያስብልህ፣ የሚራራልህ እያለ ለሚስቅብህ፣ ለሚያፌዝብህ፣ ለሚቀልድብህ አታልቅስ። ላንተውን ጊዜን የሚያመቻች እያለ በትፍ ጊዜ ከሚያስታውስህ ጋር አትታገል። ፍቅርህን ከረገጠው ባላይ በፍቅር የሚያነግስህ አለ፤ መውደድህን ካኮሰሰው በላይ በፍቃዱ የሚንከባከብህ አለ። ለፍቅርህ ብለህ ብቻህን ዋጋ ብትከፍል፣ ብትሰበር፣ ብትጋጣ፣ ብትላላጥ፣ ብትገፋ፣ ብትረሳ እራስህን ታጣለህ እንጂ ፍቅርህን አታተርፍም፤ ማንነትህን ታሳንሳለህ እንጂ ለክብር አትበቃም፤ በስቃይ ትሞላለህ እንጂ ሰላምን አታገኝም። ዋጋ መክፈልህ ድጋፍ ይፈልጋል፤ መሱዓትነትህ አጋዥ መሶዓትነት ይጠበቅበታል። ብቻህን ጥረህ፣ ግረህ የእራስህን ቤት ልትገነባ ትችላለህ ነገር ግን ብቻህን ለፍተህና ደክመህ እኩልነት የሰፈነበት፣ በነፃነት የተሞላ፣ በፍቅር የታነፀ የጋራ ቤት መገንባት እንደማትችል አስታውስ። ቢያንስ የጋራ ጥረትና ልፋት ምሰሶውን ማቆሙ የግድ ነው።


መጠጊያ አለህ!

በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ፣ በየትኛውም ከባድና ቀላል አጋጣሚ ውስጥ የአምላክ መንፈስ አለ። ሽብር፣ ስብራት፣ ስጋት፣ ፍረሃት፤ ጭንቀት ቢገጥምህ የምታመልጥበት፣ የምታልፍበት መጠጊያ አምላክ አለህ። ነገሮች በምክንያት ይሆናሉ፣ ሁነቶች ሌላ ውጤት አስከትለው ይመጣሉ፣ ውጤትም ወደ ሌላ ውጤት ይመራል። አምላክም በህይወታችን የሚከሰቱትን አጋጣሚዎች በምክንያት ዝም ይላቸዋል፤ እነርሱን ከማሳለፍ ወይም ከማስቀረት ይልቅ እኛን ያበረታናል፣ በጥንካሬያችን እንድናልፈው ያደርገናል። ቢያስቀራቸው ለእርሱ እጅጉን ቀላል ነው፤ እኛ ግን በምትክቱ ማግኘት የሚገባንን ጥንካሬ እናጣለን፣ ብርታታችን ይሸሸናል፣ እድገታችን ይገታል፣ ከለውጥ እንርቃለን።

አዎ! ጀግናዬ..! መጠጊያ አለህ! ከጭንቀትህ የምታመልጥበት፣ ፍራቻህን የምትሻገርበት፣ ስጋትህን የምትቀርፍበት በማንነቱ አሳራፊ የሆነ፣ ከለላ የሆነ፣ መጋቢ የሆነ ደንቅ መጠለያ፣ ግሩም መጠጊያ አለህ። በአለማዊ ጫናዎች አትሸበር፤ በሰዎች ጫጫታ አትጨነቅ፣ በምድራዊ ውጣውረድ አትበገር። አላማህን ያዝ፣ አምላክህን አስቀድም፣ ህይወትህን ትርጉም ስጠው፣ ብትደገፍ የማይጥልህን፣ ብታምነው የማይከዳህን፣ ብትከለልበት የማያስጠቃህን ቸር አምላክ፣ ሩህሩህ ፈጣሪ ያዝ። አምላክ ምንም ቢያደርግ ምክንያት አለው፤ ምንም ቢፈጥር ከእኛ የሚልቅ ሰበብ አለው። የሆነው መሆን ስላለበት ሆነ፤ እየሆነ ያለውም መሆን ስላለበት እየሆነ ነው፣ መሆን ያለበትም መሆን ስለሚገባው ይሆናል።

አዎ! ሁሉም ለበጎ ሆኗል፤ በበጎ ያልፋል። የሚቀየር ነገር ይቀየራል፤ የሚስተካከል ይስተካከላል፤ የሚታረም ይታረማል፤ ለውጥም ይመጣል፣ እድገትም ይከሰታል፤ አንዳች ሁነት ግን ላይታለፍ፣ ላያልፍ አይመጣም። የዛሬ ጭንቀቶች ነገ ተረት ናቸው፤ የዛሬ ስጋቶች ነገ ብርታት ናቸው፤ የዛሬ ከባዶች ነገ ሃይል ናቸው። ህያው መጠጊያ ባለበት፣ ዘላለማዊ መሸሸጊያ፣ ማምለጫ ባለበት በጊዜያዊ ጭንቀት፣ በአላፊ ስብራት እራስህን አትጉዳ፤ ከየትኛውም ምድራዊ ፈተና የሚከልልህ፣ የሚጠብቅህ ድንቅ አባት እንዳለህ አስታውስ። በድካምህ ተደገፈው፣ በህመምህ ተጠጋው፣ ጭንቀትህን አዋየው፣ ስጋትህን አስረዳው፣ የማያልፍ የሚመስለውን በእርሱ እለፍ፣ የማይሻገሩት የሚመስለውን በእርሱ ተሻገር፤ በእርሱ ከለላነት፣ በእርሱ መጠጊያነት ከጊዜያዊ ፈተናዎችህ አምልጥ።


ቅድሚያ እራስህን አድን!

ለሰዎች ጊዜ ከመስጠት በፊት፣ ለሰዎች ትኩረት ከመስጠት በፊት፣ ለእነርሱ ብሎ ብዙ ከማሰብ፣ ከመጨነቅ፣ ከማሰላሰል በፊት፣ በእነርሱ ምክንያት መልካምና የዋህ ከመሆን በፊት አንድ አቋምን መመዘኛ፣ እውነተኛውን ስሜት ማወቂያ ጥያቄ አለ " በእርግጥ ይህን የማደርገው አምኜበት ነው ወይስ በእነርሱ ለመወደድ፣ ለመደነቅና ተቀባይነት ለማክኘት ነው? " ሰዎች እንዲወዱን ብቻ፣ እንዲቀበሉን ብቻ፣ እንዲደሰቱብን ብቻ የእኛ ያልሆነውን፣ የማይገልፀንን፣ ክብራችንን የሚያወርደውን፣ በእራሳችን ላይ ጨካኝ የሚደርገንን ተግባር የምንፈፅም ሰዎች ቀላል አይደለንም። ሰው ከሞት አፋፍ እንኳን ብትመልሰው ውለታህን ሊረሳ እንደሚችል አስታውስ፣ አድነሀውም እንደ ጠላት ሊያሳድድህ እንደሚችል አስብ።

አዎ! ጀግናዬ..! ባልሆንከው፣ በምታስመስለው አንተና በሆንከው አንተ መሃከል ትልቅ ልዩነት አለ። ያልሆንከው አንተ መገለጫህ አይደለም፣ አይወክልህም፣ አይገልፅህም፤ የሆንከውና እራሱን ለማስደሰት የመረጠውን የሚያደርግ፣ ለእራሱ ስሜት የታመነ፣ በእራሱ ጥረት የሚበረታታና እራሱን የሚያስቀድም ሰው እውነተኛው መገለጫህና ማሳያህ ነው። ሳታምንበት ለሰዎች ዋጋ በከፈልክ ቁጥር፣ ሳይመችህ እንዳይቀየሙህ እንደተመቸህ ብታስመስል፣ እየተጎዳህ እንዳይርቁህና እንዳይለዩህ ጉዳትህን ብትሸፍን፣ እነርሱን ለማነቃቃትና ለማበረታት የማይገልፅህን ስብዕና ብትላበስ፣ ማንነትህን ብትቀይር፣ አንተነትህን ብትከዳ አንድ ቀን ይህን ተግባርህን የምትረግምበት፣ በፀፀት የምትሰቃይበት፣ በስራህ የምታፍርበት፣ የምትሳቀቅበት ጊዜ ይመጣል።

አዎ! ቅደመው! የእራስህን ስሜት ረግጠህ፣ ማንነትህን ጥለህ፣ ፍላጎቶችህን ገፍተህ ሰዎችን ለማስደነቅ፣ ሰዎችን ለማስደመም፣ በሰዎች ለመወደድ በምታደርገው ጥረት ከመፀፀትህና ከመሰቃየትህ በፊት ለሰዎች ብለህ መጎዳትን ቅደመው። በእራስህ ተነሳሽነት ስራ ጀምር፣ በእራስህ ፍላጎት (desire) መንገድህን ምረጥ፣ እራስህን ለማስደሰት ያመንክበትን አድርግ። ለእራስህ ጥሩ ባልሆንክበት ሁኔታ ለማንም ጥሩ ሰው ለመሆን ብትጥር ውሸት እንደሆነ ተገንዘብ፣ እያስመሰልክ እንደሆነ ይግባህ። በቅርበት እርዳታ የሚፈልግ የእራስ ማንነት እያለህ ሌላውን ለማዳን ብትሯሯጥ፣ ብትጋጋጥ በእርግጥ ከልብህ ስለመሆኑ ደጋግመህ አስብ። ሰዎችን ለማዳን ከመሮጥህ በፊት ቅድሚያ እራስህን አድን፣ እንደሻማ እየቀለጠ ያለውን ማንነትህን ታደገው፣ ለሰዎች ስሜት ሲል እራሱን የጣለውን፣ እራሱን የከዳውን አንተነትህን ድረስለት። ለእራስህ በምትውለው ውለታ ሰዎችን አግኝ፣ ለእራስህ በምትፈፅመው ተግባር ለሰዎች ድረስ፣ ሰዎችን አስደስት፣ በእነርሱም የፈለከውን ትልቅ ቦታ አግኝ።


አስቀድመህ ተማር!

የዛሬ አሸናፊነትን ትልቅነት ማወቅ ከፈለክ የነገውን ቁጪት ጠብቀህ ተመልከት። የዛሬ ልፋትህን ዋጋ መረዳት ከፈለክ ከዓመታት ቦሃላ የት እንደሆንክ እራስህን ተመልከት። በጊዜዎችህ ውስጥ ዋጋ የሌለው ነገር የለም። ያደርሰኛል ብለህ የመረጥከው እርምጃ ሳታቋርጥ ስትጓዝ በእርግጥም ያደርስሃል። ዛሬ ነገ እያልክ ስታስተላልፈው የነበረው እቅድህ ዛሬ ነገ ሳይል ያስቆጭሃል፤ ዋጋ ያስከፍልሃል፤ ያሳምምሃል። እያንዳንዱ ተግባርህ ትልቅ ዋጋ አለው። ስታሸንፍ ብቻ ህይወትን በፈለከው መንገድ ትመራለህ፤ ህይወትህን ስትቆጣጠር ብቻ የተሻልክ ሰው እየሆንክ ትመጣለህ፤ ሁሌም የተሻልክ ስትሆን ብቻ የተሻሉ ነገሮችን ታገኛለህ። ሁሉም የጥረትህ ውጤት ነው። በእራስህ ላይ ሃላፊነት በወሰድክ ቁጥር ማንነትህን ታሳድጋለህ፣ ስብዕናህን ትገነባለህ፣ ትሻሻላለህ፣ ትበለፅጋለህ።

አዎ! አስቀድመህ ተማር! ከቅጣቱ በፊት ተማር፣ ከመከራው በፊት ይግባህ፣ ከችግሩ በፊት ችግሩን ተረዳ፣ ሳይደርስብህ ከደረሰባቸው ትምህርት ቅሰም፣ እራስህን አንድ እርምጃ አስቀድም። ዛሬ የሚያስቡትን በማድረግ ከሚገኘው ድል በላይ ለነገ የሚቀመጠው የቁጪት ሸክም ይበልጣል። ምክንያቱም ድሉ ባለህ ላይ ሲጨምር ቁጪቱ ግን ህመም ይሆንብሃል፣ እራስህን ያሳጣሃል፣ ዋጋህን ያሳንሰዋል፣ ለበታችነት ይዳርግሃል። ህይወት ብዙ አማራጭ ስታቀርብልህ፣ እድሎችን ስትፈጥርልህ በጋፋሃቸው ልክ የግፊቱን ዋጋ፣ የቸልተኝነቱን ውጤት ሳይውል ሳያድር ትከፍላለህ። ከዛሬ የተሻለ ነገ የሚያመጣልህ እድል የለም፤ ከዛሬ በላይ ነገ የምታገኘው አጋጣሚ አይኖርም። የሁሉም ነገር ጠዓም በዛሬ ውስጥ፣ በአሁን ውስጥ ነው። The real feeling is only NOW. እውነተኛው፣ የሚጨበጠው፣ የሚዳሰሰው፣ የሚኖረው ስሜት አሁን ብቻ ነው። ቀሪው ጉም መሳይ የሚበተን ሃሳብ ነው፣ አይጨበት፣ አይዳሰስ፣ አይኖር።

አዎ! አሁንን ከመኖር፣ አሁንን ከመምረጥ በላይ አዋጭና ስኬታማ ምርጫ የለም። ከምንም፣ ከማንም በፊት በአሁንህ ላይ ንገስ፣ አሁንን ተቆጣጠር፣ አሁን ላይ ሰልጥን፣ አሁን በሙላት ኑር፣ የአሁን ዋጋ አሁን ይሰማህ። ብልህ ከጊዜ ሳይሆን ጊዜ ከእርሱ እንዲማር ያደርጋል። የእያንዳንዱ ተግባሩ ዋጋ ከውጤት ቦሃላ ሳይሆን ከውጤቱ በፊት ይገባዋል። "ምን ባደርግ ከምን እድናለሁ? ምንስ አተርፋለሁ? ለማንስ እተርፋለሁ?" የሚለውን ቀድሞ ያውቀዋል። የሚጨበጠውን አሁን መጨበጥ፣ የሚኖረውን አሁን መኖር ለድርድር የሚቀርብ ጥልቅ ሃሳብ ሳይሆን በስሜት የሚኖርና ከልብ የሚደረግ ነው። ከዚህች ቅፅበት በላይ ልዩ ቅፅበት በፍፁም አይኖርም። ባለንበት እንዳለን አሁንን እናጣጥም፤ አሁንን እንኑር፤ ዋጋ እንስጣት፤ ለተሻለና ለላቀ ውጤት እንብቃባት፤ አስደናቂውን የህይወት አቅጣጫም እንያዝባት፤ ከቅጣት በፊት እንማርባት።


ትሻሻላለህ፣ ትቀየራለህ!

የአየር ሁኔታውን መቀየር አትችልም ነገር ግን አለባበስህን መቀየር ትችላለህ፣ ችግሮችህን ማስቀረት አትችልም ነገር ግን እራስህን ማበርታት ትቸላለህ፣ ጊዜውን ማስተካከል አትችልም ነገር ግን ከጊዜው ጋር መራመድ ትችላለህ፣ በአንዴ ተነስተህ መንግስት መቀየር፣ አሰራሩን ማሻሻል አትችልም ነገር ግን እራስህን በፈለከው መንገድ መገንባትና ማሻሻል ትችላለህ። ከአቅም በላይ የሆኑ፣ የማንቆጣጠራቸው፣ በእነርሱ ላይ ስልጣን የሌለን፣ እኛ ሳንሆን እነርሱ የሚመሩን ምድራዊ ጌቶችና በእግዚአብሔር ፍቃድ የሚዘወሩ ነገሮች አሉ። ከዚህም አንፃር በእነርሱ ከማማረርና ከመናደድ ይልቅ እራሳችንን መመልከት ይኖርብናል። እውነት ነው ህይወት ከባድ ነች፣ የክብደቷ ልኬት ግን ሚዛኑ በእኛ እጅ ላይ ነው። "ሁሉም ነገር ይቻላል" ሲባል በሰው አቀምና እውቀት የሚገደብ መሆኑንም መረዳት ተገቢ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ቀላሉን መመኘት አቁመህ ለከባዱ መዘጋጀት ስትጀምር፣ ምቾትን መጠበቅ አቁመህ በማይመች ሁኔታ ውስጥ እራስህን ለማመቻቸት ስትጥር፣ ከምታየውና ከምትሰማው በላይ በእራስህ ተስፋ ከተመራህ፣ የአምላክን መልካም ፍቃድ ከጠበክ በእርግጥም ትሻሻላለህትቀየራለህታድጋለህ። ሃሳብና ምኞትህ ሁሉ ገደብ አላቸው፣ ከገደባቸው የማለፍ አቅሙ ግን ይኖርሃል። ማውጣት ማውረዱ፣ ማሰብ ማሰላሰሉ አይቀርልህምና ማድረግ ስለምትችለው ብታስብ፣ መቀየር ስለምትችለው ብታሰላስል ደግሞ ብዙ ነገር የመቀየር እድሉ ይኖርሃል። ከቢሆነ ኖሮ ሃሳብ ተላቀቅ፣ ቅዠት ከተቀላቀለበት ሃሳብ ውጣ፣ ከአቅምህ በላይ የሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር አቁም። ነፃ ፍቃድ አለን ፍቃዳችን ግን በገዛ ፍላጎትና ምርጫችን የተገደበ ነው፤ ማንም የተሰጠው የተለየ ክህሎት አለው፣ የክህሎቱ ውጤት ግን በእራሱ ውሳኔና ተግባሩ ላይ የተመሰረተ ነው።

አዎ! ልክን አውቆ መኖር፣ እንደ አቅም መራመድ፣ የሚችሉት ላይ ማተኮር ትልቅ ስጦታ ነው። ምንም ማድረግ አልችልም ከማለታችሁ በፊት የምትችሉትን ሁሉ ስለማድረጋችሁ እርግጠኛ ሁኑ። ነገሮች ከአቅማችሁ በላይ መሆናቸውን የምታውቁበት ብቸኛ መንገድ ሙከራችሁ ስታዩ ብቻ ነው። እጅን አጣጥፎ ተቀምጦ ከህይወት ክብደት ማምለጥ አይቻልም፤ ንግግርን ችላ ብሎ፣ ለመግባባት ዝግጁ ሳይሆኑ ቀርቶ የሰመረ የፍቅር ህይወት መመስረት አይቻልም፤ እራስን ገድቦ፣ ማንነትን አሳንሶ፣ እራስን ወደኋላ እየገፉ ለውጤት መብቃትና እራስን ማሻሻል አይቻልም። ከአቅምህ ጋር የሚሔድ ምርጫን ምረጥ፣ በመረጥከው ምርጫ ደስተኛ ስለመሆንህ እርግጠኛ ሁን፣ ባሰብከው ሰዓት ያሰብከው ስፍራም እንደሚያደርስህ ተማመንበት።

Показано 20 последних публикаций.