ሰሁር ስበላ ስለሚያመኝ ሰሁር አልበላም አትበል!! በሚስማማህ መልኩ ሰሁር ብላ!።—————
አንዳንድ ወንድምና አህቶች "
ሰሁር ስበላ ስለሚያመኝ ሰሁር አልበላም" ሲሉ ይደመጣሉ፣ እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ሚታመምበትን ምክንያት አውቆ አመጋገቡ ላይ ማሻሻያ ካላደረገ ሊታመም ይችላል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ሰዎች ከተመገቡ በኋላ ሊያቅራቸውና ጨጓራቸውን ሊያሳምማቸው የሚችለው በዋናነት በሁለት ምክንያት ነው።
1ኛ,
እንደተመገቡ ወዲያው መተኛት። ይህ ለጨጓራ በሽታና ለአለስፈላጊ ክብደት (ውፍረት) መጨመር ይዳርጋል። ይህ በየትኛውም ጊዜ ከባድ የሆነ አደጋ ነው። የጤና ባለ ሞያዎች እንደተመገቡ መተኛትን በጥብቅ ይከለክላሉ ያስጠነቅቃሉ!። በመሆኑም አንድ ሰው ሰሁር ከበላ በኋላ ማረፍ (መተኛት) ከፈለገ ቢያንስ ከ30 ደቂቃ በላይ መቆየት አለበት። አንዳንድ ሰዎች እንደበሉ አዛን ሳይጠብቁና ሱብሂያቸውንም ሳይሰግዱ ወዲያው ይተኛሉ፣ ይህ ትልቅ አደጋ ነው። አንድም የሱብሂ ጊዜ ያመልጣቸዋል፣ በተለይ ወንዶች ከሆኑ ደግሞ መስጂድ ሄደው በጀመዓ መስገድ ይጠበቅባቸዋልና ይህን ግዴታም ያስመልጣሉ።
2ኛ,
ከልክ በላይ መመገብ። ከመጠን በላይ መብላት ጨጓራን አጨናንቆ ለመፍጨት እንዲቸገር ያደርገዋል። ከመጠን በላይ መብላት በየትኛውም ጊዜ አይፈቀድም!። ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንድ ሰው ሲመገብ ሆዱን ለ3 ነገር መካፈል እንዳለበት አስቀምጠዋል፣ 1,ለምግብ 2,ለሚጠጣ ነገር 3, ለመተንፈስ። ከልክ በላይ በጣም ጠግቦ ከበላ ጨጓራው ይጨናነቃል፣ ይህ ደግሞ ጤናው ላይ ከሚያሳድረው ተፅእኖ ባሻገር ዒባዳ ለማድረግም ነፃነት አይሰጠውም።
3ኛ,
የተለያየ አይነት ምግብ በአንድ ጀንበር መብላት። ይህ አንድ ሰው ከጨጓራው የሚስማማው ከሆነ ከሁሉም አይነት በትንሽ ትንሹ መብላት ብዙም አደጋ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን የትኛው ምግብ እንደማይስማማው ማወቅ ካልቻለ ይቸገራልና በተቻለ መጠን ቀለል ባለ መልኩ ከሚስማማው አይነት አንዱን መመገብ ነው።
አንድ ሰው ከላይ የተጠቀሱ ጥንቃቄዎችን አድርጎ የማቃርና የህመም ስሜት የማይወገድለት ከሆነ ሌሎች አማራጮችም አሉ። አንድ ሰው ሰሁርን ግዴታ እስኪጠገብ ብዙ መመገብ አይጠበቅበትም። ዋናው ነገር በሰሁር በረካ ስላለበት ተፈላጊውም በረካው ነውና ቀለል ያለ ነገር መጠቀም ይችላል።
ከአነስ ኢብኑ ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“ሰሁርን ተመገቡ በሰሁር በረካ አለ!።” [ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።]
ዋናውና ተፈላጊው ነገር በረካውን ማግኘት ነውና ተምርና ውኃ… መሰል ቀለል ያሉ ነገሮችን በመጠቀም በረካውን ማግኘት ነው።
ከአቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“የአማኝ ምርጡ ሰሁር ማለት ተምር ነው።” [አልባኒ፣ አቢዳውድ 2345 ላይ ሶሂህ ብለውታል።]
ተምር ያላገኘ ሰው በውሃም ቢሆን እንኳን ሰሁር ማድረግ አለበት።
ከአቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“ሰሁርን መመገቡ በረካ ነውና አትተውት!፣ አንዳችሁ አንዴ የሚጎነጯትን ውሃ ቢሆን እንኳን በመጎኝጨት (ይተግብረው)፣ አላህና መላኢካዎች ሰሁር በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ሶለዋት ያወርዳሉ።” [በሶሂህ አት-ተርጊብ 1070 ላይ አልባኒ ሀሰን ብለውታል]
ከነቢዩ ባልደረቦች የሆነ አንድ ሰው ወደ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ቤት ሰሁር እየበሉ ገባ፣ ነቢዩም እንዲህ አሉ:-
“እርሷ በረካ ናት፣ አላህ እርሷን ሰጥቷችኋልና እንዳትተውዋት!።” [ነሳኢይ 2162 ላይ አልባኒ ሶሂህ ብለውታል]
ሰሁርን መብላት ከከሃዲዎች ፆም እና ከእኛው ፆም አንዱ መለያ ነው። ሙስሊሞች ሆይ! ሰሁርን በመብላት ፆማችሁን ከከሃዲዎች ፆም ከመመሳሰል ለዩት!።
ከዐምር ኢብኑል ዓስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“በእኛ ፆምና በመፅሃፉ ባለ ቤቶች ፆም መካከል ያለው መለያ ሰሁር መብላት ነው።” [ሙስሊም 1096 ላይ ዘግበውታል]
ከጠቀስኳቸው ሀዲሶች ውጭ ሌላ ሰሁር ላይ የሚያበረታቱና የሰሁርን ደረጃና ትሩፋት የሚገልፁ በርካታ ሀዲሶች መጥተዋልና ለሰሁር ልዩ ትኩረት እንስጥ!!
የአላህ ባሪያዎች ሆይ! "ተሰሀሩ ፈ ኢንነ ፊ ሰሁሪ በረከ!፣ ሰሁርን ተመገቡ በሰሁር በረካ አለ!።" ✍🏻ኢብን ሽፋ: (
t.me/ibnshifa)
የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ⤵️ #join በማድረግ ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifahttps://telegram.me/IbnShifa