◍➾ወር በገባ በ23 የቅድስት መሪና ሰማዕቷ በዓሏ ነው🌹
📕 ◍➾#ቅድስት_መሪና_ሰማዕት◍➲📘
❖ የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር፤ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት፤ ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።
❖ ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የጌታ ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች፤ በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና ከወዴት ነሽ አላት ክብር ይግባውና ከጌታ ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው አለችው፤ ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት፤ እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።
❖ ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ፤ ያን ጊዜም ወደ ጌታ እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳናት፤ ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት፤ በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ አዳናት።
❖ በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት፤ ያን ጊዜም እጆቿ በመስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።
❖ ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር፤ ፊቷንም በመስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው፤ በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም ክብር ይግባውና የጌታ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት መሪና ሆይ የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ።
❖ በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ፤ በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።
❖ መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ፤ ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ ጌታችን ጸለየች፤ ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።
❖ ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት መሪና ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም ለመሪና ገባሪተ ኃይል ወመንክር። ለእለ ይጼውዑ ስማ ውስተ ገጸ ኲሉ ብሔር። ኃይለ ሰማያት ነሢኣ እንዘ ይእቲ እምድር። እስከ ፈጸመት ጸሎታ ለሰይጣን ኅሱር። ከመ አሣዕን ኬደቶ በእግር።
https://t.me/Orthodoxtewahdoc