ጎንደር ላይ ለተገደሉት ሙስሊም ወንድሞቻችን እናዝናለን፣ ድርጊቱንም እናወግዛለን። ነገር ግን ጎንደር ላይ ለተገደሉት ሙስሊሞች አዝነናል ማለታችን ጎንደር ላይ በተገደሉት ክርስቲያኖች ተደስተናል ማለታችን አይደለም። በአንጻሩ የመስጊድ መቃጠልን እናወግዛለን ስንል ደግሞ የቤተክርስቲያንን መቃጠል ለበጎ ነው እያልን እንደግፋለን ማለታችን አይደለም።እንደ ዜጋ ሁላችንም በሀገራችን ላይ እኩል የመኖር መብት አለን።ክርስቲያኑ ሲሞት ለበጎ ነው፣ከጥንት የበረ ነው፣ አዲስ ነገር አይደለም፣ እያሉ ማለባበስ፣የሌላው ወገን ሲሆን ደግሞ ነገሩን ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና በመግለጫ ብዛት ጉዳዩን ማጮህ ፍትሀዊ አይደለም።በሁሉም ወገን የሞተው ሰው ነው።ሙስሊሙም፣ክርስቲያኑም፣መገደል የለባቸውም:: መስጊዱም፣ቤተክርስቲያኑም፣መውደም የለባቸውም።ወይብላ ማርያም ላይና አቃቂ ቃሊቲ ላይ ለተገደሉት ክርስቲያኖች እና ጎንደር ላይ ለተገደሉት ሙስሊሞች ሀዘናችን እኩል ይሁን።ሞጣ ላይ ስለተቃጠለው መስጊድ የጮህነውን ያህል፣ዛሬ ወራቤ ላይ ስለተቃጠሉት፣ አንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ሶስት የፕሮቴስታንት ቤተ አምልኮ እኩል መጮህ ካልቻልን፣አሁንም ፍትህ ወዴት ናት ያስብላልና።የአንዱን በኡኡታ የሌላውን በዝምታ፣ማስተናገድ ይቅር።ገዳይም፣አቃጣይም፣የሃይማኖት ጦርነት ቀስቅሶ፣ሕዝቡን ለማጫረስ፣ኢትዮያንም ለማፍረስ፣ወይንም ርካሽ የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት፣ከዛም አልፎ በሃይማኖት ሽፋን ብሄር ተኮር ጥቃት ለመፈጸም ያቀደና የቌመጠ ሁሉ አደብ የሚገዛው፣መልካም የሠራን የሚሸልም፣ጥፋተኛውንና ወንጀለኛውን፣ደግሞ ለህግ አቅርቦ የሚቀጣ፣ፍትህ ሲሰፍንና የህግም የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።