🚨 " አሁንም በርካታ የታመሙ ተማሪዎች ወደ ህክምና ተቋሙ እየሄዱ ነው "- ተማሪዎች
➡️ " በሽታው የተከሰተው ከምግብ ወይም ከውሃ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገና እየተጣራ ነው " - አብርሃም ዘገየ የተማሪዎች ዲን
በጎንደር ዩንቨርስቲ የፋሲል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፋክሊቲ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች መታመማቸውን ተገልጾዋል።
ከባለፈው እሮብ ጀምሮ በግቢው " በውሃና በምግብ ብክለት ነው " ብለው በጠረጠሩት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች መታመማቸውን ህክምና ላይ ያሉ ተማሪዎች አመልክተዋል።
ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን በግቢው ተማሪ መሆናቸውን እና አሁን በህክምና ላይ መሆናቸውን የገለፁልን ተማሪዎች ግቢው ውስጥ ባለው የህክምና ተቋም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች እየታከሙ መሆኑን ገልፀዋል።
ለተሻለ ህክምናም ወደ ጎንደር ዩንቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል የተላኩ እንዳሉም ተማሪዎች ተናግረዋል።
የሁለተኛ አመት የኬሚካል እንጂነሪንግ የሆነ አንድ ተማሪ ባለፈው እሮብ ምሳ ላይ የተመገቡት ፓስታ እርሱን ጨምሮ በርካቶችን ለህመም እንደዳረጋቸው ይጠረጥራል።
የትኩሳት፣ የተቅማጥ እና እጅና እግር የመቆረጣጠም ምልክት እንዳለው የሚናገሩት ታማሚዎች ወደ ህክምና ተቋም የሄዱ ተማሪዎች በሙሉ " ታይፎድ " ነው እንደተባሉ ተማሪው ተናግሯል።
ሌላው የሶስተኛ አመት የኤሌክትሪካል እንጂነሪንግ ተማሪ መሆኑን የነገረንና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን ተማሪ ደግሞ ምግቡ፤ የሚጠጣው ውኃም ተበርዟል ይላል። ህክምና ተደርጎለት መድሃኒት እየወሰደ እንደሆነ የሚናገረው ይህ ተማሪ የውሃ እጥረት በግቢው ስር የሰደደ ችግር ነው ብሏል።
ከየት እንደሚመጣ የማይታውቅ ውኃ በቦቴ ተጭኖ ይመጣል በጥራቱ ሁሌ እንጠራጠር ነበር። በተለይ ሰሞኑን ከተማሪዎች መታመም ጋር በተያያዘ አብዛኛው ተማሪ የታሸገ ውሃ ገዝቶ እየጠጣ ይገኛል ብሏል።
ተማሪዎቹ ለተማሪዎች ህብረት ተወካይ ችግሩን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
የኢንጅነሪግ ተማሪዎች ብቻ በሚማሩበት በጎንደር ዩንቨርስቲ የፋሲል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፋክልቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳት የሆነውን ተማሪ ተመስገን ችግሩ መከሰቱንና እርሱን ጨምሮ በርከት ያሉ ተማሪዎች መታመማቸውን ገልጾ፥ ችግሩ ከውሃው ነው በመባሉ ትላንት በታንከሩ ያለው ውሃ ተቀይሮ በኬሚካል በታከመ ውሃ መቀየሩን ተናግሯል።
በጎንደር ዩንቨርስቲ የፋሲል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ፋክልቲ የተማሪዎች ዲን አብርሃም ዘገየ በግቢው ከመቶ በላይ ተማሪዎች ወደ ክሊኒክ ታመው መሄዳቸውን ጠቅሰው ከመጡት ውስጥ 84 ተማሪዎች ብቻ " ባክቴሪያ " ተገኝቶባቸው መድሃኒት ተሰጥቶቸው እያገገሙ ነው ብለዋል።
ከዚህ ህመም ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጎንደር ዩንቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል የሄዱት ከ5 እንደማይበልጡና ከእነዚህ ውስጥ ተጏዳኝ የጨጏራና ሌሎች ችግሮች ያለባቸው ናቸው ተብለው ታክመው የተመለሱ ናቸው ሲሉ አስረድተዋል።
ቀለል ያለ ስሜት ላላቸው ተማሪዎችም ኦ አር ኤስ እየተሰጣቸው ነው፤ ከዩንቨርስቲው አመራር ጋር በመሆን የመድሃኒት ችግር እንዳያጋጥምም ወደ ክሊንኩ አስገብተናል ያሉት አብርሃም የውሃና የምግብ ችግር ነው የሚለውን ምክንያት እየተጣራ መኦኑን ተናግረዋል።
@Zena_Adis_Ethiopia