TGStat
TGStat
Введите текст для поиска
Расширенный поиск каналов
  • flag Russian
    Язык сайта
    flag Russian flag English flag Uzbek
  • Вход на сайт
  • Каталог
    Каталог каналов и чатов Поиск каналов
    Добавить канал/чат
  • Рейтинги
    Рейтинг каналов Рейтинг чатов Рейтинг публикаций
    Рейтинги брендов и персон
  • Аналитика
  • Поиск по публикациям
  • Мониторинг Telegram
አል ሀድራ AL-HADRA Official

6 Mar 2020, 07:43

Открыть в Telegram Поделиться Пожаловаться

‹ማ ጧበ ለሁም መናሙ
መሽረበን ወላ መእከላ
'ለነርሱ መኝታ አላማረም
መጠጥም ቢሆን መብልም'› ጎርፉ-አመዴ!
×××××
.
ራያ ውስጥ ነው - ተወለዱ፣ ከጀማለዲን-አንይ ጋር አደጉ፡፡ በልጅነት፣ በነብዩ ሙሀመድ(ዐሰም) ፍቅር ተያዙ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረውም፣ ትቡዕ ብዕራቸውን መዘዙ፡፡ ቀለም አወዙ፣ ብራና አጓዙ፡፡ ፍቅራቸውን እያዋዙ፣ ናፍቆታቸውን እየነዙ፣ ስስታቸውን እያባዙ፣ ሃሳባቸውን በደርዝ ድርሣን ላይ ሰበዙ፡፡ ንጥሉ አንዱ፣ በኪነ-ፍቅር ጎራ ግን ተብዛዙ፡፡ ነጋ ጠባ በሚያልሙት፣ ሌትና ማዕልት በሚደቁሱት የደግ-ሰው ፍቅር ደበዘዙ፡፡ ህይወታቸውን ሙሉ ተሰዩ፣ መላ ሥጋቸውን አሰቃዩ፣ ላይድኑ ዘንድ በቁራኛነት ተሰቀዙ፡፡ ሀኬተኛ መስለውም፣ ጎመዘዙ፡፡ ሥጋ-ለባሲ ፍጡር፣ ግራ-ቢስ ሰው፣ 'ራያ'ና 'የጁ' ላይ ከትመው፣ 'መዲና' ዘንድ ልብ ሊገዙ - በህልም ዓለም እንደዛበሩ ተጓዙ፡፡ ተድላ የተባለን ሰረዙ፡፡ ምኞትን ሁላ ደለዙ፡፡ የነፍስን ውትዋቴ ገረዙ፡፡ ከአዘቦት ኑሮ ቦዘዙ፡፡ ሥመ-ሙሀመድን ከሥጋቸው ለውሰው፣ ከደማቸው አጋብተው፣ ከህሊናቸው ሰንቅረው፣ ከልባቸው ደንብቀው፣ ከሆዳቸው አረገዙ፡፡ እናም ዕድሜ ልካቸውን ሳሱ፣ ቀጠኑ፣ መረቀዙ፡፡ ፈዘዙ፣ ተከዙ፣ ቀዘዙ፡፡ ላመል ታህል ውልጃ አገኙ፣ እናም ‹ታጁል-ሙርሠላ›ን ለህይወታቸው ክኒን አድርገው ያዙ - "ጎርፉ-አመዴ(1883 ዓ.ኢ ያረፉ)"!
.
ታላቁ፣ የጀማለዲን ዕንቁ የሆኑት - ሼህ ሙሀመድ አህመድ - "ሙሀመድ አመዴ" ይባላሉ፡፡ "ጎርፉ አመዴ" ተብለውም ይታወቃሉ፡፡ ከሁሉም፣ ነብዩ ሙሀመድን ‹የነቢያት ዘውድ፡ የምድባን ጉልላት - ታጁል-ሙርሠላ፡ ቁበቲል ወላ› እያሉ ባዘጋጁት መወድስ ጎልተው ይታወሳሉ፡፡ ባለፈውም ሆነ እስከዚህም ድረስ ይዘከራሉ፡፡ ከታጁል-ሙርሠላ ጋር በጥብቂያ ይታያሉ፡፡ ጎርፉ-አመዴ - ‹ሼህ ሙሀመድ-ኑር› እና ‹ሼህ ሙሀመድ-ያሲን አዩብ(1914፡ ዳንዩ ሣኒ)›፣ የተባሉ ጓደኞች ነበሯቸው፡፡ የሁለቱም ልጆች - "ሼህ ሚስባህ ሙሀመድ-ኑር(1925)" እና "ሼህ ሙሀመድ-አሚን ሙሀመድ-ያሲን(1963)"፣ ስለ ጎርፉ-አመዴ እንዲህ ይመሰክራሉ፦
‹እንዲያው ዝም ብሎ ይወደዋል ሆዴ
የአንይ-ወዳጅ ሙሀመድ አመዴ
ሚስትም አላገባ፣ ልጅም አልወለዴ
በታጁል-ሙርሠላ ጨሶ እየነደዴ› - ይላሉ፣ ሼህ ሚስባህ የዳናው፡፡ ሼህ ሙ/አሚን ጉራ፦
‹እንደ-ዳንይ ያሉ እንደ አህመደል ሃዴ
እንደ አንይ ያሉ እንደ ጎርፉ አመዴ
በርስዎ አጉርፎ ሄደ ይሄ ሁላ ዘውድ› - በማለት፣ በአፍቅሮተ-ነቢ ከትላልቃን ተርታና ጎራ ረድፈዋቸው ይገኛሉ፡፡ እርግጥም ጎርፉ-አመዴ፣ ታጁል-ሙርሠላ ላይ፦
‹ለነርሱ መኝታ አላማረም
መጠጥም ቢሆን መብልም› - ሲሉ፣ የእራሳቸውን መናኒነት በድምስሱ ያበይናሉ፡፡
.
ጎርፉ-አመዴ - ሚስት አግብቶ፣ ቤት ሰርቶ፣ ፍሬ አፍርቶ፣ ዘር አኩርቶ እንዲኖር - 'እናት ደጓ' በብዙ ትከጅላለች፡፡ ወግና ማዕረግ ለማሳየት ትሻለች፡፡ ሲመሽና ሲነጋ፣ ሲመጡና ሲወጡ እየጠበቀች ‹ልጄ! አግባልኝ፣ ውለድልኝ!› ትላቸዋለች - ለመጠየቅ ከመፍራት፣ ግን ደግሞ ቀልብሳ እየመረቀች፡፡ ሰውዬው ለዘበት ውልፊት አላሉም፡፡ ዴንታ ከመንሳት ብዛት፣ መኖሪያቸው - ምድር ይሁን ሰማይ አልለዩም፡፡ የሥጋቸውን ፍትዎት አልሰሙም፡፡ የሠውነታቸውን ሙቀት፣ ህጋዊ በሆነ ዘዴ ማስተንፈስንም አልባጁም፡፡ እናት ግን፣ በጉልበት ድግስ ደገሰች፡፡ 'ኮረሚ' ውስጥ፣ "ዘይንያ ሁሰይንዬ" የተባለችን እንስት አጨች፡፡ ጎርፉ-አመዴ ሽር-ጉዱን ሰሙ፡፡ ሠርጉን አወቁ፡፡ዕለቱ ቀርቦ ድግሱን ሲያዩ፣ ለአፍታ ተቀየሩ፡፡ ባቡ፣ ተሸበሩ፡፡ ‹‹እንዲህ መደገስና መደ'ገስማ፣ ለሙሀመድ ነው እንጅ›› አሉ፡፡ ሠርጉን፣ ወደ መውሊድ ቀየሩ፡፡ የዚያን ጊዜ ነው ይባላል፣ ‹አሏሁመሶሌ ዓላ ሙሀመዴ፡ አህመድ ኸይሪል-ወራ ዓሩሲል ከማሌ› ብለው አንድ መድብል ያሰናዱት፡፡ ሠርጉን እንደ ፍጥርጥራቸው ሆኑበት፡፡ ትኩሳታቸው ላይ መወድሱን ቸለሱበት፡፡ ሠርጉ፣ የነብዩ ሙሀመድ መወለድ ሆነ፡፡ ድግሱ በሀድራ ቀጠነ፡፡
.
እንዲሁ፣ ድክድክ የምትል አዲስ ህይወት ጀመሩ፡፡ በደንቡ ከሚስታቸው ጋር ሊጋደሙ ወደ አልጋ ያቀናሉ፡፡ የወ/ሮ ዘይንያ ጥሩ ሽታዋ፣ ደግ ማዕዛዋ ሲዘልቃቸው፣ የድንገቴ መከረኛ ሙሀመድን ያስታውሳሉ፡፡ እንደገና በርግገው፣ እርግፍ አድርገው ትተው፣ "ሙሀመድ ሙሀመድ፡ ታጁል-ሙርሠላ" ሲሉ ያድራሉ፡፡ ቀናት እየዞሩ ሲመላለሱ፣ ያንኑ አባዜያቸውን ይደጋግማሉ፡፡ እናም የወሮ ዘይንያን ሥጋ ሳይቀምሱ፣ ብዙ ጊዜ ኳተነ፡፡ ወገን ዘመድ አዘነ፡፡ ቤተሰብ ተስማምቶ፣ የሁለቱን ፍቺ ወሰነ፡፡ ጎርፉ-አመዴ ደስ አላቸው፡፡ ውልቃቸው ፋታ ሰጣቸው፡፡ እናት ‹ዘርህን ተካልኝ ባክህ?› ብትላቸው - ‹የታመሰ ዘር፣ ፍሬ ያወጣል? እኔም እንዲያው ነኝ፡፡ በታጁል-ሙርሠላ ታምሻለሁ፡፡ ፍሬ አላፈራም፣ እርሱን ግን ወልጃለሁ›› ሆነ መልሳቸው፡፡ እንዳሉትም ዘር ሳይተኩ ነበር - ህልፈታቸው፡፡ ብቻ! ዓለምን በቁሟ የከዱ፣ ከንቱ የነፍስ ግፊትን የማገዱ፣ ግን ሥጋ ለብሰው የከበዱ ንጡህ መናኒ ነበሩ፡፡ ጀማለዲን ናቸው፣ የነብዩ ሙሀመድን ፍቅር መጥነው ያጎረሷቸው፡፡
.
ከዚያ ሁነት ጀምሮ ምንም ዓለም አልነበራቸው፡፡ እህል አልታይህ አላቸው፡፡ ሳይበሉ ውለው ቢያድሩ፣ ወስፋቶቻቸው ቢንጫጩ አይደንቃቸው፡፡ የእርሳቸው ርሃብ፣ የነብዩ ሙሀመድ ፍቅር፣ ወይም ስም ነው፡፡ ‹ታጁል-ሙርሠላ› የዚህ ሁሉ ግፊትና ንጠት ውጤት ነው፡፡ "በአንድ ቀን፣ አንድ-ዛፍ ሥር" ተጨምተው የገጠሙት አይደለም፡፡ በ'ራያ'፣ በ'የጁ'፣ በ'ወረባቦ'ና በተለያዩ ቀዬዎች - በየተራራና በየዛፎች ሥር ታጁል-ሙርሠላን ከማንጎራጎርና ከመግጠም፣ ቦዝነው አያውቁም፡፡ እርግጥ ነው፣ በተለያየ ጊዜና በተለያየ ቦታ፣ ግን በተመሳሳይ መልኩ የተሰነኟቸው ግጥሞች አልተቋጠሩም፡፡ በተለምዶ ‹ተራ-መንዙማ› ተብሎ፣ የሊቃውንትን ግጥሞች ሰብስቦ፣ በ1997 በተጠረዘ 'ተውሦላት' ውስጥ - ታጁል-ሙርሠላ ባለ 112 ስንኝ ሆኖ ይገኛል፡፡ "ይሄ ብቻ ነው" ለማለት ባይደፈርም፣ 'ጎርፉ-አመዴ' ግን እዚሁ ውስጥም መሽገው ከትመዋል፡፡ ጥበብን፣ ፍቅርን፣ ናፍቆትን፣ እምነትን፣ ክህሎትን፣ ዕውቀትን፣ ማንነትን፣ ችሎታንና እምርታን ሁሉ ደጋግሰው በዓረብኛ ቋንቋ ቀልሰው ደርድረዋል፡፡
.
በታጁል-ሙርሠላ የራሳቸውን ቦይ ቀድደዋል፡፡ የግላቸውን ብትሊያ ክበዋል፡፡ በዝውርውሩ፣ አታካቹን ማንነታቸውን በይነዋል፡፡ የሚለዩበትን ዘዴ፣ የፍርቂያቸውን ክባዴ፣ አልቀውና አይለመዴ አድርገው ወዝፈዋል፡፡ ምናብ የቱንም ያክል ይጓዝ ይሆናል፡፡ ምኞት፣ ሩቅ ተጉዞ ምስል ሊከስት ይችላል፡፡ አያል ድርሳናት፣ መሰል ክስተትና ሰብዕናዎችን፣ አፍቃሪና ሊቃውንትን ሰንደው አስቀምጠዋል፡፡ ኢማም አሸዕራንይ('ጦበቃቱል ኩብራ')፣ አቢ ዓብዱረህማን-አሲልምይ('ጦበቃቱ ሱፍያ')፣ ኢማም አህመድ አል-አስፈሃኒ('ሁልየቱል አውልያእ፡ ወተራጁሙል አስፊያእ') እና ሌሎችም ክቡራን ጸሐፍት - ዓለም-አቀፍ ቀደምት የሱፍያ ሊቃውንትን መንፈሳዊ-ህይወት ሰንደዋል፡፡ እንደ-እውነቱ! ጎርፉ-አመዴን የሚመስልና የሚማዘን፣ ወይም ማነፀሪያ ንመሞና ማግኘት ግና፣ ምኞትና ተምኔት ሆኖ ቀርቶብናል፡፡ ቢሆንም፣ እርሳቸው ገና አልተወሩም!
Credit to mohamed nesim
@alhadra1

5.3k 0 0
Каталог
Каталог каналов и чатов Подборки каналов Поиск каналов Добавить канал/чат
Рейтинги
Рейтинг каналов Telegram Рейтинг чатов Telegram Рейтинг публикаций Рейтинги брендов и персон
API
API статистики API поиска публикаций API Callback
Наши каналы
@TGStat @TGStat_Chat @telepulse @TGStatAPI
Почитать
Академия TGStat Исследование Telegram 2019 Исследование Telegram 2021 Исследование Telegram 2023
Контакты
Справочный центр Поддержка Почта Вакансии
Всякая всячина
Пользовательское соглашение Политика конфиденциальности Публичная оферта
Наши боты
@TGStat_Bot @SearcheeBot @TGAlertsBot @tg_analytics_bot @TGStatChatBot