ከተለያዩ ክልሎች ለተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች የተቀናጀ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየተሰጠ ነው
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የወባ በሽታ በስፋት ከሚታይባቸው ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተወጣጡ የወባ ፕሮግራምን ለሚያስተባብሩ የጤና ባለሙያዎች /Malaria focal person/ ከጥር 19/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ሥልጠና /Comprehensive Malariology Training/ በመስጠት ላይ ነው፡፡
የወባ ምርመራና ሕክምና፣ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ የሚሰጥበት ሂደት፣ የፕሮግራም አስተዳደርና ዕቅድ፣ ወባ ላይ ያለው አመራር ምን መምሰል አለበት የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮችን ሥልጠናው በስፋት ይዳስሳል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ም/ፕሬዝንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በመክፈቻ ንግግራቸው የወባ በሽታን ለማጥፋት ለበርካታ ዓመታት ሲሠራ የቆየ ቢሆንም በሽታውን መግታትና ገዳይነቱን ማስቆም አንዳልተቻለና እንደ ሀገሪቱ ተጫባጭ ሁኔታ የዝናብ ወራትን ተከትሎ ከፍተኛ የወባ ስርጭት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ የአካባቢ ሁኔታ፣ የእርሻ ቦታ ውኃ አጠቃቀም ያለመዘመን የመሳሰሉ ችግሮች በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት አዳጋች እንዳደረገው የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ መድኃኒቱን የሚቋቋም ተሕዋሲ መምጣቱና የወባ ትንኟ ባሕርይ መለዋወጥ ችግሩን ይበልጥ እንዳወሳሰበው እና የኅብረተሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ የተጋረጠውን ተግዳሮት ተጋፍጦ የማኅበረሰቡን ጤና ለማስጠበቅና የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሥልጠናው ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙና ያላቸውን ዕውቀት እንዲያዳብሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡
በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር የወባ እና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ጥላሁን ከበደ እንደ ሀገር የወባ ሕሙማን ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ከፍተኛ የወባ ስርጭት በታየባቸው ክልሎች ላይ በማተኮር ከየክልሉ ለተወጣጡ የወባ በሽታ መሪ ተጠሪ የጤና ባለሙያዎች የተቀናጀ የወባ ሥልጠና ለመስጠት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በዩኒቨርሲቲው ቅንጅት ሥልጠናው መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡ አቶ ጥላሁን ሥልጠናውን ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ42 ቀናት ለአፍሪካ ሀገራት ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰው ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በማምጣት ለፕሮግራሙ አፈጻጸም የሚረዱ አምስት ክፍሎች ያሉት ሥልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ለረዥም ጊዜያት በወባ በሽታ የሚያዙ ሕሙማንና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ እንደነበር ያስታወሱት ኤክስፐርቱ ከሦስት ዓመታት ወዲህ ባልተጠበቀ ሁኔታ የበሽታው ስርጭት የጨመረ በመሆኑ በዚሁ ዓመትም ለወረርሽኙ ምላሽ የመስጠት ዘመቻ ላይ መቆየታቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በዘመቻ ሥራው የበሽታው ስርጭት መቀነስ እያሳየ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ሠልጣኞቹም አስፈላጊውን ሥልጠና ሲያጠናቅቁ ወደ ሥራ የሚሠማሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ እና ሥልጠና ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር አባይነህ ቱንጄ ማእከሉ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመንና በባለሙያዎች ምክንያት የሚፈጠሩ የዕውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት ለጤና ባለሙያዎች ሥልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለሥልጠናው ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ሞጁሎች የተዘጋጁ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር አባይነህ ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ የሚመዘኑ መሆኑን፣ መመዘኛውን ላለፉ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ እና በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀትና ክሂሎት በሥራ ላይ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ ማዕከሉና የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ክትትል እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-ድረ-ገጽ -
https://www.amu.edu.et/ቴሌግራም -
https://t.me/arbaminch_universityፌስቡክ -
https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/ዩቲዩብ -
https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት