ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ለወራቤ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1 ሚሊየን 2 መቶ ሺ ብር በላይ የሚገመት የመማሪያ ክፍል እደሳት እና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ወራቤ ዩኒቨርሲቲ በወራቤ ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው ወራቤ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የቅድመ አንደኛ ተማሪዎች መማሪያ ክፍል እድሳት እና የህጻናት መጫወቻ እና የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
150 ወንበር እና ጠረጴዛዎች፣ 30 ፍራሾችን፣ መጽሃፍት፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ፣ ለመምህራን የማስተማሪያ ቁሳቁስ እና የመማሪያ ክፍል የግንባታ እደሳቱን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ1 ሚሊየን 2 መቶ ሺ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል ።
በስፍራው ተገኝተው ድጋፉን ያበረከቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር ተውፊቅ ጀማል አሁን የተደረገው ድጋፍ ጊዜያዊ መሆኑንና በቀጣይ ህፃናት የትምህርት ጊዜያቸውን በአግባቡ የሚከታተሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ በተለይ በግንባታ በኩል ተጨማሪ ክፍሎችን ዩኒቨርሲቲው እንደሚገነባ ገልጸዋል።
ህጻናት ላይ በትኩረት መስራት ለሀገራችን ዘላቂ ዕድገትና ለውጥ መሠረት መጣል ስለሆነ ወራቤ ዩኒቨርሲቲ መሠል ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ረ/ፕ አንዋር አህመድ ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ትምህርት ቤቶችን የመደገፍ ተግባር እንደሆነ ጠቁመው ህፃናት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የማድረጉን ስራ እንደተቋም ኮሌጆች ተከፋፍለው በየዘርፋቸው የመደገፍ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።
የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹክራላ አወል በበኩላቸው ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ሁሌም ግንባር ቀደም መሆኑን አውስተው በተለይ ለትምህርት ቤቶች ከመማሪያ ቁሳቁስም ሆነ አቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በርካታ አበረታች ስራዎችን እየሰራ ያለ ተቋም ነው ብለዋል።
በተለይ የዛሬው ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ከታች ጀምሮ ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ የቀጣይ ትውልድንም የሚያነቃቃ ተግባር እንደሆነ ገልፀው ስለተደረገው ድጋፍ ዩኒቨርሲቲውን በማህበረሰቡ ስም አመስግነዋል ።
ቁሳቁሱን የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አካላት ለስልጤ ዞን እና የወራቤ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላት አስረክበዋል።
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news