ነብይ እመስላለሁ እንዴ? 😥
----◉----
ከበርናባስ በቀለበአናስሞስ አሳታሚ (ጸዴ ጅማሮ) የቀረቡልን መጽሐፍት ምረቃ መርሓ ግብር ተካፍለን እየተመለስን ነው። ሰማዩ ጠቋቁሯል፤ ፋኑ እየነዳ ነው። መገናኛ (የቀድሞ ዲያስፖራ አደባባይ) እንደተሻገርን አንድ ትራፊክ ፖሊስ አገኘን። ቆምን፤ ፋኑ "ውይ ይኽ ሰው ይዞናል በቃ" አለ።
#ትራፊኩ፦ "መንጃ ፈቃድ ይዘሃል?"
#ፋኑ፦ "አዎን፤ 'መዥለጥ!' ይኸው።"
#ትራፊኩ፦ "ግን አልታደሰም።"
#ፋኑ፦ "አዎን፤ ልክ ነው። አንድ ወር አልፎበታል፤ በማልችልበት ሁኔታ ውስጥ ስነበርሁ አላደስሁም።"
#ትራፊኩ፦ "ቦሎም አልለጠፍህም!"
#ፋኑ፦ "አዎን! ይኸው" አለና ከዳሽ ቦርዱ ለይ አንስቶ ሰጠው። እስክትሎም "ከቤት ስወጣ መለጠፊያ አላገኘሁም ነበርና ለዚያ ነው፤ ይቅርታ እለጥፈዋለሁ አባ" አለ።
#ትራፊኩ፦ "እሺ፣ ሦስተኛ ወገን ይዘሃል?" እኔ በልቤ፦ ከዚህ አገር ግን ወገናዊነት መቼ ነው የሚገረሰሰው? እያልሁ አጉተመትማለሁ፤ ለካ ነገሩ ወዲህ ነው።
#ፋኑ፦ "ሦስተኛ ወገን! ይዣለሁ" ብሎ መፈላለጉን ቀጠለ...
ፋኑ ግን ምን ሆኖ ነው? ርሱ እኮ ለእኔ ግልጽና ታማኝ ወንድም እንደሆነ ነው የማውቀው። ገና ከEGST ስንነሳ ለምን ይህን ሁሉ አላጫወተኝም? ለምንስ መንጃ ፈቃዴን አላደስሁም፣ ቦሎ አልለጠፍሁም ሲያልፍም 3ኛ ወገኑን ፊት ለፊት አላደረግሁም" አላለኝም? ይህን ሁሉ ከእኔ የሰወረው ለምን ይሆን!? መኪና እንደያዘ ነበር የነገረኝ፤ እነዚህን ካልያዘ ትላንት እኮ ፋኑዬ መኪና አልያዘም፤ ለምን መኪና ይዣለሁ አለኝ!? በውጭ ቆሜ እነዚህ ሃሳቦች በአዕምሮዬ ይመላለሳሉ። ደግሞ እኮ ከሳር ቤት ሳንነሳ ቢነግረኝ እኔ አግዘው ነበር፤ መኪናው ውስጥ ባለመግባት!😊
#ትራፊኩ፦ ፊቱን ወደ እኔ አዞረ፤ "አንተ ነብይ ነህ አይደል?" አለኝ።
#እኔ፦ አይ... ነብይ እንኳን አይደለሁም! ግን አስተማሪ ነኝ፤ እኔም ባለ መንጃ ፈቃዱ ወዳጄም። ከመኪናው ወርጄ ትንሽ ጨዋታ ጀመርን... ፋኑ 3ኛ ወገን ከፋይሎቹ ውስጥ እየፈለገ ነው።
#ትራፊኩ፦ "ከመኪናው ውስጥ ለምን ወረድህ?"
#እኔ፦ ቁጭ ብዬ እንዳላወራህ ብዬ ነው። ሁለታችንም (እኔም በወንጀሉ ተጠርጣሪው ወዳጄም) ቁጭ ብለን ከምናወራህ እኔ በውጭ ቆሜ ርሱን ብታነጋግረው ይሻላል ብዬ ነው (መገሰጽም ካለብህ)።
#ትራፊኩ፦ "ቁጭ ብትል ምን ችግር አለው?"
#እኔ፦ አንተ ፊት ስቆም ሕግ ፊት እንዳለሁ ነው የማስበው፤ አንተንና ይህን ኃላፊነት የሰጠህን ሕዝብ ማክበር ነበረብኝና ነው የቆምሁት፤ ይህን ስልህ ታዲያ ሁሉም ሰው ይህን ማድረግ አለበት እያልሁህ አይደለም፤ እኔ በዚህ ሰዓት በጥፋት ፊትህ ስንቆም የተሰማኝን ነው ያደረግሁት። ጭንቅላቱን ነቀነቀ...(ነቢያት ግን ከመቼ ነው እንዲህ ሥርዓት የያዙት እያለ ያለ ይመስላል😊)
ልብ አድርጉ አሁንም ፋኑ የ3ኛ ወገን ዶክመንቱን እየፈለገ ነው። የፋኑ ችግር መኪናው ውስጥ የሚነበቡ ማቴሪያሎች (መጽሐፍት) ያበዛልና "የትኛው መጽሐፍ ውስጥ ተሰግስጎ ይሆን!?" እያለ ፍለጋውን ተያይዟል፤ እኔና ትራፊኩ በውጭ ሌላ ታሪክ ውስጥ ገብተናል...
#ትራፊኩ፦ "የሚገርምህ፤ አንተን የሚመስል ነብይ እዚህ ከተማ አለ። ብቻ ግን አገልጋይ ነገር ነህ። አስተማሪ ነኝ አልኸኝ? "ከነቢያቱ ጋር አገናኙማ (አትስማሙማ)!"
#እኔ፦ ምናልባት አንዱን መጽሐፍ ይዘን የተነሳን መሆናችን ያገናኘን ይሆናል፤ ፈገግ አለ። ፋኑ 3ኛ ወገኑን አግኝቷል። "ይኸው!" ብሎ ጨዋታችንን አቋረጠ! ይህን ስታነቡ ትራፊኩ እንዳይቀጣን በውጭ ቆሜ እየጀነጀንሁ ያለሁ መስሏችሁ ይሆናል (ድሮም እናንተ)!😊 ግን በፍጹም እንደርሱ አይደለም ሃሳቤ፤ ሲጀመር ፋኑ እንደምንቀጣ አውቆ ክፍያውን ሁሉ ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር።
በመጨረሻም፦ መንጃ ፈቃዱን መለሰልን! "ይኸው! ቶሎ አድሱ። ቦሎውንም ለጥፉ!" እናመሰግናለን ብለን ጉዟችንን ቀጠልን።
ከዚያ ከፋኑ ጋር መንገዳችን ላይ ነገር ተጀመረ! አንተ ይህን ሳትይዝ እንዴት ትወጣለህ? ስንት ራዕይ ያለኝን ሰው መንገድ ላይ አስቀርተኸኝ ነበር እኮ (ማለቴ መሽቶ ነበርና ወደ ሰፈር ታክሲ አላገኝማ!) እያልሁ መጠነኛ ግሳጼ ቢጤ ሰጥቼዋለሁ። 😊
ቀጥዬም ጠየቅሁት፦ ፋኑዬ ምኔ ነው ግን ነብይ የሚመስለው?😥 እርሱም "ሁሉ ነገርህ" እኔም ታዲያ አንተና ወንድሞችህ ለምን አልተገዛችሁለኝም!? (መቼስ ትራፊኩ ያመሳሰለኝ ያለው ሕዝቡን ለጥቅማቸው አስጨንቀው ከሚገዙ ነቢያት ጋር መሆኑ ግልጽ ነውና)።
ከሰማነው ነገር ዋናው ቁም ነገር፦ በቃ እዚህ አገር "ነቢያቱ" እና "የቃሉ አስተማሪዎች" ሊስማሙ እንደማይችሉ በሁሉም ዘርፍ ባለሞያዎች ጭምር ተረጋግጧል ማለት ነው!? ሌላው፦ ቆይ እኔ ምኔ ነው ነብይ የሚመስለው!? እሺ፣ ነብይ ማንን?
ለአስተያየትዎ፦ @barnica Join ➘ & Share ➝ ◊
@barnabasism ◊
◊
@barnabasism ◊
◊
@barnabasism ◊