፨። ቅበላ ።፨
_________
መቼም "ቅበላ" የሚለው ቃልን ስንሰማ ኹላችንም ጆሮአችን ላይ አንድ ነገር ያቃጭላል፤ እሱም ጾም ከመግባቱ በፊት የምናደርገው ተግባር ነው።
በመሠረቱ "ቅበላ" ማለት በእንግድነት ለሚመጣው እንግዳ፣ ለእንግዳው የሚመጥነውን ያህል፣ ክብር ለመስጠት አዘጋጅቶ እና ተዘጋጅቶ መቀበል ነው፤
ስለዚህ ለአንድ ነገር 'ቅበላ' ስናደርግ ያንን የምንቀበለውን ነገር በሚመጥን መልኩ መኾን አለበት ማለት ነው።
ለምሳሌ አንድ መንፈሳዊ መነኩሴ ወደ ቤታችን በእንግድነት ቢመጣ፣ ለመነኩሴው ቅበላ የምናደርግለት እሱን ሊመጥን በሚችል መልኩ ነው፤ የጸሎት ቤት አዘጋጅተን፣ እግሩን አጥበን፣ ጉልበት ስመን፣ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ቅዱሳት ሥዕላትን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ አስቀምጠን. . . የመሳሰሉትን ነገሮች፣ እንደ እኛ አቅም አዘጋጅተን ልንቀበለው እንችላለን።
ወይም ደግሞ አንድ ሕፃን ልጅ ወደ ጎጆአችን በእንግድነት ቢመጣ፣ መኝታ ክፍል አዘጋጅተን፣ የተረት መጻሕፍትን አሰናድተን፣ የሕፃናት ፊልም ከፍተን፣ የሕፃናት መጫወቻ አዘጋጅተን ቅበላ ልናደርግለት እንችላለን።
ልክ እንደዚሁ ኹሉ፣ "ጾምን"ም ስንቀበል ከጾም ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ አለብን እንጅ፣ ፍጹም ተቃራኒ የኾነ ተግባር ማድረግ ትልቅ ስሕተት ነው።
"ጾም" ሊገባ ነው ብለን፣ ሆዳችን እስኪተረተር የምንበላ፣ ጨጓራችን እስኪላጥ የምንጠጣ፣ ዝሙት የምንፈጽም፣ በየጭፈራ ቤቱ የምንዞር ከኾነ፣ ይኽ "የጾም ቅበላ" ይባላልን? በጭራሽ አይባልም።
እንደውም ይኽ የሚያሳየው ጾሙን ሳንፈልግ እንደምንቀበለው ነው፤ "ነብይን በነብይ ስም የሚቀበል የነብይን ዋጋ ይወስዳል" እንዳለ ጌታችን፣ ጾምን ስንቀበል በጾም ስም፣ በጾም ተግባር መኾን አለበት።(ማቴ ፲፥፵፩)
እንደውም አንዳንድ የበቁ አባቶች፣ የዐቢይ ጾም ሊገባ ሲል ጾሙን በጾም ይቀበሉታል፤ በርግጥ ይኽ ለእኛ ሊከብደን ይችላል፤ ቢኾንም ጾሙን በጾም መቀበል ቢያቅተን እንኳን፣ ጾሙን ከጾም ጋር በሚስማሙ መልካም ተግባራት መቀበል እንችላለን።
ጾም ከመግባቱ በፊት ንስሐ መግባት፣ የበደሉንን ይቅር ማለት፣ የበደልናቸዉን ይቅርታ መጠየቅ፣ የተጣላናቸዉን መታረቅ፣ መመጽወት፣ ጾሙ የበረከት እንዲኾንልን መጸለይ፣ መንፈሳዊ ምግባራትን መላበስ፣ ከመጠን ያለፈ ደስታን ከራስ ማራቅ እና የመሳሰሉትን፣ ከእኛ ጋር የሚስማሙትን መንፈሳዊ ተግባራት፣ ከንስሐ አባታችን ጋር ተመካክረን ተግባራዊ በማድረግ "ቅበላ" ማድረግ ይኖርብናል።
በዚህ መሠረት የሚፈጸም ቅበላ፣ ጾሙ ከመግባቱ በፊት መንፈሳችን እንዲዘጋጅ ከማድረጉም ባለፈ፣ እግዚአብሔር ከጾሙ በፊት አስቀድሞ እንዲባርከን ያደርጋል።
ወዳጄ ኾይ የአንተ "ቅበላ" ከየትኛው ነው? መቼም በስካር፣ በከርስ መሙላት፣ በጭፈራ እና በዝሙት፣ ቅዱሱን እንግዳ ""ጾምን"" እንደማትቀበል ተስፋ አደርጋለኁ።
አበው "ከምግብ ብቻ በመከልከል እንጾማለን አትበሉ .. ከክፉ ግብር መራቅ፣ ጾማችንን ትክክል ታደርጋለች" ይላሉ፤ በዚኽም የአባቶቻችን 'ልጆች' እንባላለን፤ አባቶቻችን የወረሷትን መንግሥት በእውነት እንወርሳለን።
ጾሙ የበረከት እና የፍሬ እንዲኾንልን ከወዲሁ እመኛለኁ፨
© ማኅበረ ሥላሴ © ሐራ ዘተዋሕዶ