ከዩሱፍ ታሪክ ከምንማራቸው ቁም ነገሮች ውስጥ አንዱ እነሆ
~
የዩሱፍ ወንድሞች ዩሱፍን ለመገላገል ብዙ በደል አድርሰውባቸዋል። ይሁን እንጂ የአላህ ድንቅ ስራ ሆኖ ከዘመናት በኋላ የደረሰው ደርሶ፣ ያለፈው አልፎ ዩሱፍን አንግሶ እነሱን ደግሞ በችግር ፈተኖ አገናኛቸው። ዩሱፍ ለይተዋቸዋል። እነሱ ግን አላወቁም። የንጉሱ መስፈሪያ ዋንጫ በ"ቢኒያሚን" ጓዝ ውስጥ ሲገኝ ዩሱፍን በነገር የሚወጋ እንዲህ የሚል ቃል ተናገሩ:-
{إِن یَسۡرِقۡ فَقَدۡ سَرَقَ أَخࣱ لَّهُۥ مِن قَبۡلُۚ}
"ቢሰርቅ ከአሁን በፊት የርሱው ወንድም በእርግጥ ሰርቋል።"
ዩሱፍን ማለታቸው ነው። ዩሱፍ ዛሬ ስልጣን ላይ፣ ሃብት ላይ ናቸው። እርምጃ መውሰድ፣ እሱ ቢቀር የሚወስዱት እህል ላይ ማእቀብ መጣል ይችላሉ። ቢሆንም እዚያ ሊደርሱ ቀርቶ ለውንጀላቸው ግልፅ ምላሽ እንኳን አልሰጧቸውም። ዋጥ አደረጉት።
{ فَأَسَرَّهَا یُوسُفُ فِی نَفۡسِهِۦ وَلَمۡ یُبۡدِهَا لَهُمۡۚ قَالَ أَنتُمۡ شَرࣱّ مَّكَانࣰاۖ وَٱللَّهُ أَعۡلَمُ بِمَا تَصِفُونَ }
"ዩሱፍም (ይህችን ንግግር) በነፍሱ ውስጥ ደበቃት፡፡ ለእነሱም አልገለጣትም፡፡ 'እናንተ ሥራችሁ የከፋ ነው፡፡ አላህም የምትሉትን ሁሉ ይበልጥ ዐዋቂ ነው' አለ" በምላስ ሳይሆን በልብ። [ዩሱፍ: 77]
ዩሱፍ ከራሳቸው ለመከላከል አልቸኮሉም። ባይሆን የኋላ ኋላ ምን አሏቸው?
{ قَالَ هَلۡ عَلِمۡتُم مَّا فَعَلۡتُم بِیُوسُفَ وَأَخِیهِ إِذۡ أَنتُمۡ جَـٰهِلُونَ }
"እናንተ የማታውቁ በነበራችሁ ጊዜ በዩሱፍና በወንድሙ ላይ የሰራችሁትን ግፍ ዐወቃችሁን?' አላቸው፡፡'' [ዩሱፍ: 89]
በዚህን ጊዜ ነበር የሚመላለሱት ከዩሱፍ ጋር እንደሆነ የገባቸው።
{ قَالُوۤا۟ أَءِنَّكَ لَأَنتَ یُوسُفُۖ قَالَ أَنَا۠ یُوسُفُ وَهَـٰذَاۤ أَخِیۖ قَدۡ مَنَّ ٱللَّهُ عَلَیۡنَاۤۖ إِنَّهُۥ مَن یَتَّقِ وَیَصۡبِرۡ فَإِنَّ ٱللَّهَ لَا یُضِیعُ أَجۡرَ ٱلۡمُحۡسِنِینَ }
" 'አንተ በእርግጥም ዩሱፍ ነህንዴ?' አሉት። 'እኔ ዩሱፍ ነኝ፡፡ ይህም ወንድሜ ነው። አላህ በኛ ላይ በእርግጥ ለገሰልን። እነሆ! የሚጠነቀቅና የሚታገስ ሰው (አላህ ይክሰዋል)። አላህ የበጎ አድራጊዎችን ዋጋ አያጠፋምና' አለ።" [ዩሱፍ: 90]
እዚህ ላይ የሚያሳቅቅ ነገር እንደገጠማቸው ገባቸው። "በአላህ እንምላለን፡፡ አላህ በኛ ላይ በእርግጥ አበለጠህ፡፡ እኛም በእርግጥ አጥፊዎች ነበርን አሉ።"
ዩሱፍ ግን በበደል ላይ በደል ቢደራረብባቸውም ጥፋታቸውን ባመኑት ወንድሞቻቸው ላይ ሆደ ሰፊ ነበር የሆኑት። እንዲህ ሲሉ ያለፈውን ሁሉ አለፉት:-
{ قَالَ لَا تَثۡرِیبَ عَلَیۡكُمُ ٱلۡیَوۡمَۖ یَغۡفِرُ ٱللَّهُ لَكُمۡۖ وَهُوَ أَرۡحَمُ ٱلرَّ ٰحِمِینَ }
«ዛሬ በናንተ ላይ ወቀሳ የለባችሁም፡፡ አላህ ለእናንተ ይምራል፡፡ እርሱም ከአዛኞች ሁሉ ይበልጥ አዛኝ ነው» አላቸው፡፤
[ዩሱፍ: 92]
ይህን ትምህርት ያዙና የበደሏችሁን ሰዎች እና ይቅር ለማለት የሚተናነቃችሁን ስሜት አስቡት። የምንማረው ለመለወጥ ነው አይደል? ስሜታችንን ረግጠን፣ እልሃችንን ውጠን ስለ አላህ ሁሉን ይቅር እንበል። ከዩሱፍ ታሪክ እንማር።
~
የቴሌግራም ቻናል:-
https://t.me/IbnuMunewor