ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሊሰጡ ነው ተባለ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር እንዲዘጋ የሚያደርገውን ትዕዛዝ በፊርማቸው ሊያፀድቁ መሆኑን እየተነገረ ነው።
የትምህርት እና የሲቪክ መብት ተከራካሪዎች እንዲሁም ዴሞክራት ፓርቲን የወከሉ እንደራሴዎች ትዕዛዙ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ለማፈራረስ ያለመ ነው ሲሉ ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ስለመሆኑም ተነግሯል።
የጥቁሮች መብት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ‘NAACP’ የተባለ ተቋም ፕሬዚዳንት ዴሪክ ጆንሰን፣ “የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በፌዴራል መንግሥት ድጎማ ላይ ጥገኛ ለሆኑ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የአሜሪካ ሕፃናት የዛሬ ቀን ጨለማ ቀን ነው” ብለዋል።
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተር ፓቲ ሙሬይ በበኩላቸው፣ “ትራምፕ እና ኢሎን መስክ ትምህርት ሚኒስቴርን ለማፍረስ የማይሆን ጨዋታ እየተጫወቱ እና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ግማሽ የሰው ኃይል እያባረሩ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
የሀገሪቱ ብሔራዊ የወላጆች ኅብረት ደግሞ “እየተደረገ ያለው የትምህርት ሥርዓቱን ማስተካከል ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የሚገባቸውን ነገር እንዳያገኙ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው፤ እኛ ግን ይህ እንዲሆን በፍፁም አንፈቅድም” ብሏል።
እንደ ሚዲያዎች ዘገባ ከሆነ ትራምፕ የሚፈርሙት ትዕዛዝ የትምህርት ሚኒስትሯ ሊንዳ ማክማሆን የትምህርት ሚኒስቴሩ እንዲዘጋ አስፈላጊውን ሒደት እዲያመቻቹ እና ሥልጣኑን ለግዛቶች አንዲያስተላልፉ ያዝዛል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የትምህርት ሚኒስቴሩን አባካኝ እና በሊበራል ርዕዮተ ዓለም የተበከለ ነው ብለው እንደሚያስቡ አልጀዚራ ዘግቧል።
@Ethio_fastnews🤩
@Ethio_fastnews🤩