በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 343 መሠረት ውሳኔ ክርክሩ ሲመለስ በክርክሩ ጣልቃ መግባት ይቻላል?
በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክር መኖሩን በሚገባ ያወቀ ወገን ጉዳዩ ወደ በላይ ፍርድ ቤት ደርሶ ክርክሩ በነጥብ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 343 መሰረት ወደ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲመለስ ጠብቆ የሚያቀርበው የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም።
በክርክሩ ውስጥ ተካፋይ መሆን የሚገባው ወገን በፍብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 41 መሠረት ጣልቃ መግባት የሚችል መሆኑ የተመለከተ ቢሆንም የጣልቃ-ገብ ማመልከቻውን በየትኛው የክርክር ደረጃና እስከመቼ ጊዜ ድረስ ማቅረብ እንደሚችል በሕጉ በግልጽ የተመለከተ አይደለም፡፡ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ መብቱ ሊነካ የሚችል ወገንን በክርክሩ የሚሳተፍበት ሥርዓት በመፍጠር መብትና ጥቅሙ የሚከበርበትን ዕድል የፈጠረ ሲሆን መብቱን ለማስከበር የሚፈልግ ወገንም መብቱን በምክንያታዊ ጊዜ እንዲያቀርብና አላስፈላጊ የክርክር አቀራረብ ሥርዓት እንዳይፈጥር ግዴታ የሚጥል መሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ክርክሩ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሆነ በሰበር ችሎት ደረጃ ታይተው ወደሥር ፍርድ ቤት እንደገና እንዲወሰኑ ከተመለሱ ክርክሩን መኖሩን ያወቀና በክርክሩ መሳተፉ ጥቅሙን ለማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ያሳየ ወገን በክርክሩ ጣልቃ እንዳይገባ ሕጉ የመከልከል ሀሳብ አለው ሊባል አይችልም፡፡ በክርክሩ እውነተኛ ጥቅሙ የተነካበት ወገን ክርክሩ መኖሩን ባወቀ በምክንያታዊ ጊዜ የጣልቃ-ገብ ማመልከቻውን ሊያቀርብ እንደሚችል ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ ከሥነ-ሥርዓት ሕጉ ክርክርን ውጤታማ፣ ወጭና ጊዜ ቆጣቢ በሆነ አግባብ የመምራት ዓላማዎች የምንገነዘበው በምክንያታዊ ጊዜ ውስጥ ያልቀረበና የዘገየ የክርክር አቀራረብ ተቀባይነት እንደሌለው ነው፡፡
በተያዘው ጉዳይ አመልካች የ2ኛ ተጠሪ ወኪል በመሆን ክርክሩ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ እስኪመለስ ድረስ ሲሳተፉ የነበረ መሆኑን የሥር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ፍሬ ነገር ነው፡፡ ክርክሩ እንደገና እንዲታይ ከተመለሠ በኋላ በ1ኛ ተጠሪ የቀረበው ክስ የተሻሻለ ወይም ጭብጡ የተለወጠ ባለመሆኑ ጉዳዩ ከተመለሠ በኋላ አመልካች መብታቸው የተነካ መሆኑን ክርክሩ አያሳይም፡፡ አመልካች የ2ኛ ተጠሪ ወኪል ሆነው ተከራክረው ክርክሩ ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ሲመለስ ክርክሩን መኖሩን ካወቁ በኋላ ዘግይተው በክርክሩ ጣልቃ ለመግባት ማመልከታቸው የክርክሩን አቅጣጫ በመመልከት ክርክርን እያረፉ ለማድረግና ወደኋላ ለመመለስ የተደረገ ነው ከሚባል በስተቀር እውነተኛ ጥቅማቸውን ለማስከበርና የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ሦስተኛ ወገኖች በክርክሩ ጣልቃ እንዲገቡ የፈቀደበትን ዓላማ ጠብቆ የቀረበ ማመልከቻ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ሆኖ አላገኘነውም፡፡ በመሆኑም አመልካች በመሬቱ ላይ ያለኝ መብትና ያቀረብኩት ማስረጃ አልተመረመረልኝም በማለት ያቀረቡትን የሠበር አቤቱታ አልተቀበልነውም፡፡
Join👇👇
https://t.me/ethiolawtips