የአክሱም የሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሂጃብ ክልከላን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው የትግራይ አጠቃላይ የእስልምና ጉዳዮች ምክርቤት አስታወቀ
ምክርቤቱ የቀረበው ጥያቄ አንድና አንድ መሆኑን እሱም ሴት ተማሪዎቹ ሂጃባቸውን ይለብሳሉ ትምህርታቸውን ይማራሉ የሚል እንደሆነ ገልፆል።
የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት በአክሱም ከተማ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ሂጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ የተጣለው ክልከላ ለማስነሳት ኃይማኖታዊ ብሎም አለም አቀፍ የሰው ልጆች መብት እንዲከበር በሚያስገድዱ አማራጮች ሁሉ ችግሩን ለመፍታት ተሞክሯል ብሏል።
ሆኖም ግን በክልሉ የትምህርት ቢሮ ከተሞከረው ያልተሳካ ሽምግልናና ሊያስፈፅመው ያልቻለውን የትዕዛዝ ደብዳቤ ከመፃፍ ውጭ ምንም ለውጥ ሊመጣ እንዳልቻለ ገልፆል።
የልጆቹ ጥያቄ የሁሉም እምነት ተከታይና የሌሎችን እምነት አክባሪ ትግራዋይ ጥያቄ ሆኖ ሳለ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ከራሳቸው ሃይማኖታዊ ፍላጎት መብት በማደባለቅ ሴት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት መዓድ እንዳይመለሱ አድርጓል ብሏል።
ጉዳዩ የከፋ የሚያደርገው ተማሪዎቹ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ መሆናቸው ነው ያለው ምክር ቤቱ በሂጃብ ምክንያት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የመግባት እድላቸው እየተዘጋ ይገኛል ሲል አክሏል።
ምክር ቤቱ ትላንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫው ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት በሌለበት የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ የማገድ ተግባሩ በአፋጣኝ ካልተፈታ ጉዳዩን በህግ አግባብ እንዲታይ እናደርጋለን ባልነው መሰረት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ወስደነዋል ብሏል።
ምክርቤቱ አክሎም ጉዳዩ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን በሴቶችና በሰው ልጆች የመማር መብትን የሚቃረን ነው በማለት ሁሉም ሰው በፍትሃዊው ጥያቄ ጎን እምዲቆም ጠይቋል።
Facebook.com/EthioTube Twitter.com/EthioTube Youtube.com/EthioTube Instagram.com/EthioTube https://t.me/ethiotubehttps://whatsapp.com/channel/0029VaCq8Gs2kNFzFeZTGh3L