Meseret Media


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


መሠረት ሚድያ በኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሰሩ ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ በማለም ያቋቋሙት ዲጂታል ሚድያ ነው።

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


#የምርመራዘገባ አለም ባንክ በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ለኢትዮጵያ የሰጠው 200 ሚልዮን ዶላር ምን ላይ እየዋለ ነው?

- በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ስር በግል አማካሪነት በአመት 120 ሺህ ዶላር የሚከፈለው ግለሰብ አለ

(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ይፋ ተደርጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው በ2013 ዓ/ም ነበር። በዚህ ወቅት ነበር የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ብሄራዊ ኮሚቴ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ሆኖ መንቀሳቀስ የጀመረው።

ፋውንዴሽኑ ዋና አላማው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን ማስፋፋት፣ የህዝብ ተቋማት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ዝርጋታ፣ የብሄራዊ መታወቂያ ስራ፣ የግል የቴክኖሎጂ ተቋማትን አቅም መገንባት በስራው ውስጥ የተካተቱ ነበሩ።

እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ በመንግስት በይፋ ቢገለፅም አንዳንድ አነጋጋሪ ድርጊቶች ግን መታየት ጀምረዋል።

ለምሳሌ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ከሚገኙት መሀል ዶ/ር ስሜነው ቀስስ ሲሆኑ የትምህርት መስካቸው የእንስሳት ህክምና ቢሆንም በዚህ የዲጂታል ዘርፍ በአማካሪነት ተቀጥረው በአመት 130,000 ብር በአማካሪነት እንደሚከፈላቸው ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ወይም ኢቢኤስ ቴሌቭዥን ላይ 'ቴክ ቶክ' በሚል ስያሜው የሚታወቀው ግለሰብ በተመሳሳይ በማማከር ቅጥር በአመት 120,000 የአሜሪካ ዶላር መቀጠሩ አነጋጋሪ እንደሆነባቸው ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል፣ ሰለሞን በአመት በርካታ ወራትን በአሜሪካ የሚያሳልፍ መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ እንደሚያደርገው ይገልፃሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "Internet Exchange Point" በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

"አይቲ ፓርክ" ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ እነዚህ ምንጮች ያስረዳሉ።

"በሸገር ከተማ ቡራዩ ውስጥ ለሚገኝ አንድ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 'የቴክኖሎጂ ክህሎት ስልጠና ለመስጠት' በሚል ፋሪስ ለተባለ ድርጅት 21 ሚልዮን ብር በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ተከፍሏል" የሚሉት እነዚሁ ምንጮች ይህም የተከናወነው በጨረታ ስም ሆኖ ሌሎች አቅም ያላቸው ተቋማት ገለል ተደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።

የፋሪስ ድርጅት ባለቤት በቅርቡ የቴስላ 'ሳይበርትራክ' መኪና ካለቀረጥ ወደ ሀገር በማስገባቱ የሚታወቅ ሲሆን የዚህን መኪና ወደ ኢትዮጵያ መግባት ባለቤቱ አቶ ኤልያስ ይርዳው ማህበራዊ ሚድያ ላይ ለሀገሪቱ ትልቅ "የኢኖቬሽን" እምርታ ብሎ የገለፀበት መንገድ ብዙዎችን አነጋግሮ ነበር።

በዚህ ዙርያ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩን ዶ/ር በለጠ ሞላን እንዲሁም የዲጂታል ፋውንዴሽን ሀላፊውን አቶ ተሰማ ገዳን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

20k 0 224 36 670



#Update ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) በዛሬው እለት መፈታቱን መሠረት ሚድያ አረጋግጧል

@MeseretMedia

33.7k 0 23 25 714

ማህበራዊ ሚድያ ላይ ትችት በማቅረብ የሚታወቀው ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) ታሰረ

(መሠረት ሚድያ)- በቅርብ አመታት ማህበራዊ ሚድያ ላይ የሚለቀቁ ቪድዮዎችን መነሻ በማድረግ ትችት እና ሽሙጥ በማቅረብ የሚታወቀው ሰመረ ካሳዬ (ሰመረ ባርያው) በትናንትናው እለት በፀጥታ አካላት አዲስ አበባ ውስጥ ተይዞ እንደታሰረ ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደጠቆሙት ሰመረ ትናንት እኩለ ቀን ገደማ ምሳ ከጓደኞቹ ጋር በልቶ እየወጣ በነበረበት ወቅት በፀጥታ አካላት ተይዞ ተወስዷል።

ሰመረ ብዙውን ግዜ ትችት የሚያቀርበው በማህበረሰቡ ዘንድ ጥያቄ በሚያስነሱ እና አነጋጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሆኖ ሳለ ለእስር መዳረጉ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ስራዎቹን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ከትናንት በስቲያ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በፖሊስ ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ ተብላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተወሰደች መሠረት ሚድያ መዘገቡ ይታወሳል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

41.6k 0 75 22 610

በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሰዎች ተገደሉ

(መሠረት ሚዲያ)- ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እና ጂቡቲ ድንበር አቅራቢያ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ 

ጥቃቱ መጀመሪያ በሁለት አርብቶ አደሮች ላይ የተፈፀመ ሲሆን አንዱ ሲሞት አንዱ መትረፉ ታውቋል። በተጨማሪም 2 ሴቶች እና 5 ወንዶች በሌላ ጥቃት መገደላቸውን የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል፡፡

በኤሌዳአር ወረዳ ሂሉ እና ቲኪቦ ቀበሌ ሲያሪ ጣቢያ ሟቾችን ወደ ቤተሰብ ይዘው ሲመጡ በድጋሜ ህዝብ በተሰበሰበበት ጥቃት ተፈጽሟል ተብሏል።

"ባለን መረጃ መሰረት ጥቃት የፈጸመው የጅቡቲ መንግስት እንደሆነ እናምናለን" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት የመረጃ ምንጫችን ከዚህ ቀደም በጣቢያው ያሉ አርብቶ አደሮችን ከቦታው ለማስለቀቅ የጅቡቲ ወታደሮች ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ተኩስ ይከፍቱ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በአሜሪካ የሚኖሩ የአፋር ዲያስፖራ ማሕበር አባላት ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን "ጨካኝ" በማለት አውግዘውታል።

የዲያስፖራ ማህበሩ ጥቃቱ የተፈጸመው በጂቡቲ መከላከያ ሀይል ድሮን መሆኑን ገልጾ በጥቃቱ ሲያሮ እና ኤሊዳር በተባሉ ቦታዎች 2 ወንድማማቾችን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውንና 3 ሰዎች ደግሞ በከፋ ሁኔታ በጽኑ መቁሰላቸውን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዞ የሰላማዊ ዜጎች ግድያ እንዲቆም በመጠየቅ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ማህበረሰብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟቾችና መገናኛ ብዙሃን ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በኢትጵያም ሆነ በጂቡቲ መንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡

የሰሜኑ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ መሬት ዘልቀው ገብተው ይገባኛል የሚነሳበትን መሬት መያዛቸው የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ ከደቡብ ሱዳን ዘልቀው የሚገቡ የሙርሌ ታጣዊዎችም ድንበር ጥሰው በመግባት በተደጋጋሚ ዝርፊያ እንደሚፈጽሙ ይታወቃል፡፡

የኤርትራ ጦርም ወደ ትግራይ ገብቶ ከፈጸመው ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ ትንሽዋ አገር ጂቡቲም በኢትዮጵያ ምድር በሰላማዊ ዜገች ላይ የፈጸመችው ወታደራዊ ጥቃት አነጋጋሪ ሆኗል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

41.6k 0 20 34 445



ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አዲስ አበባ እንደሚገኙ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ከሁለት ሳምንት በኋላ በአዲስ አበባ በሚጀመረው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ከስብሰባው አዘጋጆች ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው ዶ/ር ቴድሮስ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በመገናኘት እንደ ወባ፣ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና መሰል በሽታዎች ዙርያ የተሰሩ ስራዎችን ይገመግማሉ።

ዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ሆነው የዛሬ ሰባት አመት ገደማ ሲመረጡ በወቅቱ የነበረው መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎላቸው የነበረ ቢሆንም የዛሬ አራት አመት የትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የመንግስት ሚድያዎች እና አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ዘመቻ ከፍተውባቸው ነበር። ዶ/ር ቴድሮስም በጦርነቱ ሲደርሱ ስለነበሩ ጤና ነክ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በተደጋጋሚ ሲፅፉ እና ሲናገሩ ነበር።

ከዛም አልፎ የዛሬ ሁለት አመት ተኩል ገደማ የአለም ጤና ድርጅት ግለሰቡን ለሁለተኛ ግዜ በዳይሬክተር ጀነራልነት ሲመርጥ የኢትዮጵያ ተወካይ በግልፅ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።

የአለም ጤና ድርጅት ሀላፊው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ ከአምስት አመት ወዲህ የመጀመርያቸው ይሆናል።

በዚህ ጉዟቸው ከኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር አመራሮች ጋር ተገናኘተው እንደሚመክሩ ቢጠበቅም ከጠ/ሚር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ያደርጉ እንደሆን እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

31.5k 0 23 40 368

ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ለእስር ተዳረገች

(መሠረት ሚድያ)- ገጣሚ እና የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፕሮግራም አዘጋጅ ምስራቅ ተረፈ ትናንት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በፖሊስ ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ ተብላ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተወሰደች ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደጠቆሙት ምስራቅ ዛሬ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ፖሊስ ምርመራ ለማጣራት ጊዜ እንዲሰጠው ፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አቅርቧት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ እንዲያቀርብ 7 ቀን በመስጠት  ለጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጠሮ ሰቷል፣ ምስራቅ ተረፈ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተመልሳለች።

ምስራቅ የኪነጥበብ ምሽቶችን በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ሀገራት በማዘጋጀት እንዲሁም የራሷን ግጥሞች በማቅረብ በብዛት ትታወቃለች።

እንደ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና ገጣሚ ትእግስት ማሞ ያሉ የደመቁባቸውን ዝግጅቶች በማሰናዳት የምትታወቀው ግለሰቧ ግጥም፣ መነባንብ፣ ዲስኩር እንዲሁም ጥበብ እና ጥበብ ነክ ስራዎች ይበልጥ እንዲለመዱ እንደለፋች ብዙዎች ይናገራሉ።

ገጣሚ ምስራቅ አሁን ላይ የታሰረችበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልፅ እንዳልሆነ ታውቋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

32.2k 0 109 25 673

በዛሬው እለት የታጠቁ ግለሰቦች መቐለ ኤፍኤም 104.4 ሬድዮን ለመቆጣጠር ሙከራ አርገው ነበር ተባለ

(መሠረት ሚድያ)- በትግራይ ክልል ባለስልጣናት መሀል እየተካረረ የመጣውን ውዝግብ ተከትሎ በዛሬው እለት የታጠቁ ግለሰቦች የመቐለ ኤፍኤም 104.4 ሬድዮን ለመቆጣጠር ሙከራ አርገው እንደነበር ታውቋል።

ሙከራው የተካሄደው በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው ቡድን አባላት መሆኑን ምንጮቻችን ጠቅሰው ሙከራው ግን ያልተሳካ ነበር ብለውታል።

"ታጣቂዎቹን ወደ ሬድዮ ጣቢያው ይዞ የገባው በእነ ዶ/ር ደብረፅዮን የተሾመ ዘመንፈስ ቅዱስ ፍስሃ የተባለ ግለሰብ ነው" ያሉት ምንጫችን ድርጊቱ ሲከሽፍ የኤፍኤም ሬድዮ ጣቢያውን ማህተም ይዘው ሲወጡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመዋል።

ምን ያህል ታጣቂዎች ወደ ሬድዮ ጣብያው እንደገቡ እንዲሁም አላማቸው ምን እንደነበር እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

45.6k 0 58 49 350

ከመንግስት ጋር ለመደራደር የተዘጋጀው የፋኖ ክንፍ ንግግሩ በአሜሪካ ወይም በአውሮፓ እንዲሆን ጠየቀ

(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ታዛቢዎች በተገኙበት ከመንግስት ጋር ውይይት እንዳደረገ እና ለድርድር ዝግጁ እንደሆነ የገለፀው በእስክንድር ነጋ የሚመራው የፋኖ ክንፍ ድርድሩ በውጭ ሀገራት እንዲሆን እየጠየቀ መሆኑ ታውቋል።

የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንደተናገሩት ታጣቂ ክንፉ ድርድሩ በአውሮፓ አልያም በአሜሪካ እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።

መንግስት በዋናነት በእስክንድር ከሚመራው የፋኖ  ክንፍ  ጋር በቅርቡ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ እንደተወያየ እስክንድር ከኢትዮ 360 ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ገልፆ ነበር። አክሎም በድርድሩ ላይ የኢጋድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች መገኘታቸውን ገልፆ ነበር።

በውይይቱ ላይ በፋኖ ክንፉ በኩል የተነሱ ነጥቦች መከላከያ አካባቢውን በግዜያዊነትም ቢሆን ለቆ መውጣት፣ ክልሉን ማስተዳደር፣ በፌደራል መንግስቱ በስልጣን መወከል፣ የድሮን ጥቃት ማቆም፣ ለተጎዳው ህዝብ ለህይወት ሳይቀር ካሳ መክፈል እና የመሳሰሉት ናቸው ተብሏል።

በመንግስት በኩል ደግሞ ትጥቅ በመፍታት ወደ ማሰልጠኛ መግባት፣ ጎጃም አካባቢ ላይ ያለውን ነገር ማስተካከል፣ በየከተማው ያለውን አደረጃጀት መረጃ መቀበል፣ ተጠያቂ የሚሆኑ አባላቱን አሳልፎ መስጠት እንዲሁም በምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ መካተት ናቸው ተብሏል።

"በመንግስት ዝግ ስብሰባ ላይ ሲያጨቃጭቅ የነበረው የነእስክንድር ክንፍ አቅም ጉዳይ ሲሆን ግምገማውም በሀገር ውስጥና በውጭ ተቀባይነትን ለማግኘት መነጋገሩ እንደ  አማራጭ ተወስዷል" ያሉን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን ሸዋ ላይ ድርጅቱ የተሻለ አቅም እንዳለው፣ ነገር ግን ጎጃም ላይ የለም የሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጃ ቀርቦ ንግግር ተደርጎበታል ብለዋል።

"ቢያንስ ሸዋን ማቃለሉ እንደ ጥሩ እድል በመታየቱ እና የድርድር ዝርዝር መረጃም የሚቀበሉ አለም አቀፍ ተቋማትም በመንግስት የንግግሩ ቦታ ስለተጓጓዙ ውይይቱ ተደርጓል" በማለት ሂደቱን አስረድተዋል።

"ነገር ግን አሳሳቢው ጉዳይ አሁንም ልክ እንደነ ጃል ሰኒ እንዳይሆን ነው፣ ሙሉ ሰላም ለማምጣት የተወሰነ ቡድን ሳይሆን ሁሉንም አካታች መሆን አለበት" ያሉን ደግሞ በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት የሰጡን ተንታኝ ናቸው።

"መንግስት ነገሮችን ያቀሉልኛል ብሎ እየሄደበት ያለው ይህ ነው። ሁሉም ወደ ንግግሩ መግባት አለበት፣ አልያ እንደ  ኦሮምያ አይነት ሁኔታ ይፈጠራል፣ ይባስ ብሎም በቀረው ፋኖ ታጣቂ እና በመንግስት መካከል የሚኖረው ሁኔታ ይባስ ሊካረር ይችላል" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

57.7k 0 160 190 668



#የህዝብድምፅ ከህዝብ በጥቆማ መልክ ደርሰውን ትክክኝነታቸው የተረጋገጡ 5 መረጃዎች

1. የሲዳማ ክልል አስተዳደር በያዝነው ሳምንት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ላይ ከ100 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አድርጓል፣ ይህም አርሶ አደሩን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከቷል። ዳፕ ማዳበሪያ ከዚህ በፊት በኩንታል 3,980 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ከነበረበት ባሳለፍነው ማክሰኞ በተወሰነው መሰረት ዋጋው እስ 8,047 ብር እንዲሆን ተደርጓል። "ምንም አይነት ገቢ የሌለው አርሶ አደር ለማዳበሪያ 8,074 ብር ከየት ያመጣል? ቢገዛ እንኳ ከምርቱ ምንን ሊያተርፍ ይችላል? የሚለው በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነባቸው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

2. የኢሚግሬሽን ባህር ዳር ቅርንጫፍ በርካታ ሰዎችን ለአሻራ እየቀጠረ ተስተናጋጆች ሲሄዱ "አዲስ አሰራር ስለመጣ ተቃጥሏል፣ ከእንደገና ለአዲስ 5,000 ብር እና የሚያስቸኩል ጉዳይ ካላችሁ ደግሞ 20,000 ብር ከፍላችሁ መመዝገብ ትችላላችሁ" እየተባሉ መሆኑን ለሚድያችን ጠቁመዋል። የከፈሉት ገንዘብ እና ያቃጠሉት ግዜን በተመለከተ ሲጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

3. በኦሮሚያ ክልል "ሚዛን ጀምረናል" በሚል ምክንያት ከ12 ሜትር ኪዩብ በላይ የሆኑ እንደ ሲኖ ያሉ መኪናዎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ታውቋል፣ ይህም የኮንስትራክሽን ግብዐት የሆኑት እንደ ጠጠር እና አሸዋ ዋጋቸው በእጅጉ እንደጨመረ መሠረት ሚድያ ሰምቷል። ይህ የሰሞኑ "ሚዛን" የተባለ አሰራር የተወሰኑ የአሸዋ እና ጠጠር አምራቾችን ለመጥቀም እንደሆነ የተናገሩት ምንጮች ከዚህም በተጨማሪ በየቦታው የኬላ ክፍያ እንዳሰለቻቸው ጠቁመዋል።

4. በሀዋሳ ከተማ የሚስተዋለው የቤንዚን እጥረት ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል። ማደያዎች አሁንም ቤንዚን መሸጥ ያቆሙ ቢሆንም አሽከርካሪዎች እስከ 300 ብር ከጥቁር ገበያ ከመግዛት እየተገደዱ መሆኑን ያስረዳሉ። "ብዙ ማደያ አለ፣ ነገር ግን ቤንዝን የለም። የሆነ ቀን አንዱጋ አለ ከተባለ አዳር ተሠልፈን ሳናገኝ እንበተናለን። በየመንገዱ ከየት እንደሚያመጡ የማይታወቁ አንድ ሊትር 300 ብር እየሸጡልን ነው" ብለው ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

5. በመጨረሻም፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለበዓል የወጡ በርካታ ወጣቶች የፋኖን ስም ጠርታችሁ ጨፍራችኋል ተብለው እየታደኑ በመታሰር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል። ወጣቶቹ አሁን ላይ የታሰሩበት ቦታ እንደማይታወቅ የጠቆሙት ምንጮቻችን ቁጥራቸው በርካታ በመሆኑ ፖሊስ ጣብያ ስለማይችለው ምናልባት ወደ ወታደራዊ ካምፕ ተወስደው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። "ሚካኤል ታቦቱ ወደ ማደሪያ ሲመለስ ጨፍራችሀል የተባሉት ወጣቶች እስከዛሬ ቀን ድረስ ታፍሰው የት እንደታሰሩም አይታወቅም፣ በየፖሊስ ጣቢያውም የሉም፣ በቁጥር በጣም ብዙ ናቸው" ያሉን በስፍራው ያሉ ምንጮቻችን ናቸው።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

51.9k 0 31 29 445

• ታኅሣሥ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ገነተ-ማርያም ቀበሌ አርክን በተባለ ልዩ ጎጥ ሲያመርቱ የዋሉትን የጤፍ ምርት ለመጠበቅ አውድማ ተኝተው የነበሩ 5 የአንድ ቤተዘመድ አባላት የሆኑ አርሶ አደሮች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የተጎጂዎች ቤተሰቦች ለኢሰመኮ አስረድተዋል። በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቀደም ብለው ከአካባቢው በመሸሻቸው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሲገቡ አውድማው ላይ ተኝተው ያገኟቸውን በግጭት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸውን አርሶ አደሮች እንደገደሏቸው ጨምረው ገልጸዋል።  

• ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ደብረ ኤልያስ ወረዳ በጭነት መኪና ተሳፍረው በመጓዝ ላይ የነበሩ የደብረ ኤልያስ ወረዳ የመንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት 2 ሴት ሠራተኞች ጎዛመን ወረዳ ውግር ቀበሌ ሲደርሱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከመኪና አስወርደው ከወሰዷቸው በኋላ በማግሥቱ ታኅሣሥ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ተገድለው እንደተገኙ የሟች ቤተሰቦች አስረድተዋል።

• በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሸካ ዞን አጎራባች ቀበሌዎች መካከል አልፎ አልፎ በወሰን አለመግባባት ምክንያት ግጭቶች የሚከሰቱ ሲሆን፣ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት ድረስ በዘለቀ ግጭት በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን፣ መንገሺ ወረዳ፣ የሪ ቀበሌ ጂፎር ንኡስ ቀበሌ ውስጥ 5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል። እንዲሁም የተወሰኑ ነዋሪዎች የቤት ውስጥ ዕቃዎችን እና የእርሻ ሥራ መሣሪያዎችን ጨምሮ ንብረት  ተዘርፏል።

• በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጃ ወለል ወረዳ፣ የላሎ ገለታ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ዳግም ኢገዙ እና አቶ ጸጋ ተክሌ የተባሉ 2 ሰዎች ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ጋር “ግንኙነት አላችሁ፤ ስንቅ እና መረጃ ታቀብላላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ  በዚያው ዕለት ማለትም መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።

• መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣  አመያ ወረዳ ኢተያ ገምባ ጀቴ፣ ኢላላ እና ጢሮ ኢላላ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች “በአካባቢው ላለው የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል አቶ አለኸኝ አባተ፣ አቶ ተመቸው አርቄ፣ አቶ በለጠ ከበደ፣ አቶ ተመስጌን ተፈራ እና አቶ አስፋ ርቀው የተባሉ 5 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፡፡

• መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ኢተያ ገምባ ጀቴ ቀበሌ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አቶ ሙሳ ኑሩ፣ አቶ ኢብራሒም መሐመድ፣ አቶ ኢብራሒም ኡመር እና አቶ ጉልማ (ከ5 ቤተሰቦቹ ጋር) በአጠቃላይ 9 ሰዎችን ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል ገድለዋል።

• ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቤጊ ወረዳ፣ የኮበሬ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ መሐመድ ሀጂ ጀማል የተባሉ ሰው ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) “ድጋፍ አድርገሃል” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች  ከተያዙ በኋላ በዕለቱ በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።

• ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ የወንዲ ዶች ቀበሌ ነዋሪ የነበሩት አቶ ምናለ ቃስም የተባሉ ሰው “ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ድጋፍ ታደርጋላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙ በኋላ  በጥይት ተገድለው አስክሬናቸው መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል።

• ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ንጋት ላይ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ ብርቢሣ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት “የመንግሥት አካላትን ተባብራችኋል” በሚል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ 17 ወንዶች እና 21 ሴቶች በአጠቃላይ 38 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። 78 መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል። 

• ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ መጃ ላሉ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት በቀበሌው በሚኖሩ የጉራጌ ብሔር ተወላጆች ላይ በምሽት ቤታቸውን በላያቸው ላይ በማቃጠል እና ጥይት በመተኮስ በአጠቃላይ 12 ሰዎችን ገድለዋል።

• ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ በመቂ ከተማ 02 ቀበሌ ማንነታቸው በውል ባልታወቀ ነገር ግን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) አባላት መሆናቸው በተጎጂዎችና በተጎጂ ቤተሰቦች የተጠረጠሩ የታጠቁ አካላት በፈጸሙት ጥቃት 3 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን አንድ የ12 ዓመት ሕፃንን ጨምሮ 4 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል።

• ኅዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በአርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌሳ ረከታ እና መከና ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከሌሎች ነዋሪዎች ለይተው በፈጸሙት ጥቃት 13 ሰዎችን ከመኖሪያ ቤቶቻቸው በማስወጣት በጥይት ገድለዋል።

ምንጭ ኢሰመኮ

መረጃን ከመሠረት!

43.3k 0 25 16 299

• መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል ከተደረገ የተኩስ ልውውጥ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የደጋ ዳሞት ወረዳን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ወደ ወረዳው መቀመጫ ፈረስ ቤት ከተማ በመግባት በርካታ የወረዳ አመራሮችን፣ ሥራ ኃላፊዎችን እና “የመንግሥት የመረጃ ምንጭ ናቸው” ያሏቸውን ቢያንስ 80 ሰዎች አስረዋል። እንዲሁም የወረዳ አስተዳዳሪውን ጨምሮ 3 መኖሪያ ቤቶችን በእሳት እንዳቃጠሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ከመስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት ሰዎች መካከል 38 ሰዎች ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ልዩ ቦታው ፈረስ ቤት ሚካኤል 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) እንደተገደሉ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች አስረድተዋል። ሁሉም ሟቾች ሲቪል ሰዎች (የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች) ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 22ቱ ሰዎች ኢሰመኮ በስም የለያቸው ናቸው።

• ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በደቡብ ሜጫ ወረዳ፣ ገርጨጭ (መሃል ገነት) ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ አባላት አቶ ገብሬ ሙሉዬ እና አቶ መሀሪው መኩሪያ የተባሉ 2 ሰዎችን “ከፋኖ ጋር በመሆን ስትዋጉን ቆይታችሁ ነው ወደ ቤታችሁ የገባችሁት” በማለት ከቤታቸው አውጥተው እንደገደሏቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

• ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡20 አካባቢ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በደጋ ዳሞት ወረዳ፣ ፈረስ ቤት ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አማን እንየው የተባለ 1 የ4 ዓመት ሕፃን ልጅ ሲገደል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፈረስ ቤት ቅርንጫፍ የሚገኝበት ሕንጻ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል። የድሮን ጥቃት በተፈጸመበት ወቅት ፈረስ ቤት በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደነበረ እንዲሁም በጥቃቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

• ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 3፡20 ሰዓት በሰሜን ሸዋ ዞን፣ መንዝ ማማ ባሽ ንኡስ ወረዳ፣ “ጦስኝ አፋፍ” በተባለ አካባቢ በሚገኝ አንድ የመንገድ ተቋራጭ ድርጅት ሲጠቀምበት የነበረ ካምፕ ላይ በተፈጸመ የአየር (ድሮን) ጥቃት 2 ሕፃናትና 1 ሴት የተገደሉ ሲሆን በ5 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን እማኞች ገልጸዋል። ተጎጂዎቹ ከ5 ዓመታት በፊት በመሬት መንሸራተት ምክንያት ባሽ ቀበሌ “ወራና ጨታ” ከተባለ ጎጥ ተፈናቅለው በዚሁ ካምፕ ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ ናቸው። የድሮን ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት አካባቢው በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ሥር የሚገኝ እንደነበርና ጥቃቱ ከመድረሱ በፊት ታጣቂዎቹ የመጠጥ ውሃ ለመቅዳት፣ ለመታጠብ እና ምግብ ለማብሰል ወደ ካምፑ ይመጡ እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።

• ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ ዞን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከወልድያ ከተማ ወደ ቃሊም ከተማ በተከታታይ የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ በሰው ሕይወትና አካል እንዲሁም በመኖሪያ ቤቶች እና የቤት እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ኢሰመኮ ያሰባሰባቸው መረጃዎች ያስረዳሉ። በወቅቱ ቃሊም ከተማ በታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር ብትሆንም የጦር መሣሪያ በሚተኮስበት ወቅት በአካባቢው ምንም ዐይነት የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበረ ነዋሪዎች አስረድተዋል።

• ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. አቶ ተግባሩ ሽፌ አበበ የተባሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ የእህታቸውን ባል ተዝካር (የ“ፋኖ” አባል የነበረ) ታድመው ከደባይ ጥላትግን ወረዳ ሲመለሱ፣ በቁይ ከተማ አሰንዳቦ ፍተሻ ኬላ ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። ግድያው የተፈጸመባቸው ሲፈተሹ የሟችን ፎቶግራፍ ይዘው በመገኘታቸው “ለምን ፎቶውን ይዘህ ተገኘህ?” በሚል እንደሆነና እስከ ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. እኩለ ቀን ድረስ አስከሬናቸው እንዳይነሳ ከልክለው እንዳቆዩት የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።

• ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በማእከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ለምባ አርባይቱ ቀበሌ፣ አርባ ተንሳይ ጎጥ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመግባት በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኝ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ ከሰበሰቡ በኋላ አቶ ነጋ ያለው (75 ዓመት)፣ አቶ አጉማሴ አዱኛ (45 ዓመት) እና አቶ ታእት ታከለ (34 ዓመት) የተባሉ 3 ሰዎችን ሕዝብ በተሰበሰበበት እንደገደሏቸው የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች አስረድተዋል።

• ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ሌሊት በሰሜን ወሎ ዞን ላስታ ወረዳ ብልባላ ከተማ በተፈጸመ የድሮን/የአየር ጥቃት እማሆይ ደስታ ካክራው የተባሉ የ83 ዓመት አረጋዊት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገድለዋል። በዚሁ ግቢ ውስጥ ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ 2 የብልባላ ጤና ጣቢያ ባለሙያዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ። ጥቃት ከመድረሱ በፊት እና ከደረሰ በኋላ በአካባቢው የድሮን ድምጽ ይሰማ እንደነበር ለማወቅ ችሏል።

• ኅዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ እናርጅ እናውጋ ወረዳ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የተከሰተውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ኅዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ቡሽት ኮኛ ቀበሌ፣ ግራርጌ ሰፈር በመጫወት ላይ ከነበሩ ሕፃናት መካከል ባንችግዜ አዲስ በተባለች የ5 ዓመት ሕፃን ላይ ሞት እና እባብሰው ጌቴ በተባለ የ6 ዓመት ሕፃን ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በተመሳሳይ ቀን በዚሁ ቀበሌ በሌላ መንደር በተፈጸመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት ወይዘሮ መደሰት ሞኜ የተባሉ የ42 ዓመት ሴት የሞቱ ሲሆን 1 ወጣት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኝ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

• ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ ፋግታ ለኮማ ወረዳ፣ ፋግታ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች (በተለምዶ “ፋኖ”) ቁጥጥር ሥር የነበሩ 12 የመንግሥት የጸጥታ አባላት እና ለጸጥታ አባላቱ ምግብ አቅራቢ የነበሩ 2 ሴቶች (ወይዘሮ ፈንታነሽ መላኩ እና ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም) በድምሩ 14 ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም 9 በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ይገኙ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ አባላት፣ 1 ሕፃን (ከላይ በስም የተጠቀሱት የሟች ወይዘሮ ይመኙሽ አንዱዓለም የ2 ዓመት ሴት ልጅ) እና በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሻይና ቡና በመሸጥ የምትተዳደር 1 ሴት በአጠቃላይ 11 ሰዎች በጥቃቱ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የዐይን እማኞች አስረድተዋል።


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በየቦታው የሚፈፀሙ ግድያዎች ተባብሰው መቀጠላቸውን ጠቆመ

(መሠረት ሚድያ)- ኢሰመኮ በዚህ የሩብ ዓመት ሪፖርቱ ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. አጋማሽ ያለውን ጊዜ የዳሰሱ ግድያዎችን እና አስገድዶ ስወራዎችን ዳስሷል። በቀጥታ እንዲህ ይቀርባል:

• በአማራ ክልል ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ፣ ቀበሌ 18፣ አዲስ ዓለም፣ ገንፎ ቁጭ፣ ቆሸ ሰፈር፣ ፋሲል ካምፓስ፣ አማኑኤል፣ ሎዛ ማርያም፣ አጣጥ እና አዘዞ በተባሉ የከተማው አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረው የትጥቅ ግጭት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተጸፈመ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ ጥቃት እንዲሁም በሁለቱም ወገን በነበረው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሕፃናትን እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 10 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉና  በአካል እና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች እና የዐይን እማኞች ለማወቅ ተችሏል። ከአንድ ሆስፒታል  በተገኘ  መረጃ  ብቻ በግጭቱ ምክንያት 6 ሴቶች እና 6 ሕፃናትን ጨምሮ በአጠቃላይ 32 ሲቪል ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 1 ሰው ሆስፒታሉ ውስጥ ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

• ከመስከረም 6 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ዳባት ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት መካከል ከነበረው የተኩስ ልውውጥ ጋር በተያያዘ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ዒላማን ባልለየ የጦር መሣሪያ ምክንያት ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 3 ሕፃናትን ጨምሮ በ5 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ድርሷል። በተጨማሪ ቢያንስ 6 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።

• መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከዓለም በር ወደ ወረታ ሲጓዙ ወጅ የተባለ ቦታ ላይ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ጋር የተፈጠረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በመንገድ ላይ አግኝተው እንዲሁም ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥተው የያዟቸውን በአጠቃላይ 10 ሲቪል ሰዎች ገድለው እንደሄዱ የዐይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።

• መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ስናን ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ አቶ ጌታ እንዳለ አንማው እና አቶ አትንኩት ሁነኛው የተባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራንን ከመኖሪያ ቤታቸው በመውሰድ የገደሏቸው ሲሆን በሌሎች 4 መምህራን ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። በመምህራኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና ድብደባ በ2017 ዓ.ም. ትምህርት ለማስጀመር ካደረጉት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የመረጃ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

• ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ቢቡኝ ወረዳ፣ ወይንውሃ ቀበሌ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ “ፋኖን ትደግፋላችሁ” እና “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” ያሏቸውን 11 ሲቪል ሰዎች በመያዝ ወይንውሃ ቀበሌ ወደሚገኘው የመከላከያ ካምፕ በመውሰድ እንደገደሏቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አስረድተዋል።

• መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሊቦ ከምከም ወረዳ፣ አግድ ቀበሌ፣ ውሻ ጥርስ በተባለ ጎጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል የነበረውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቤት ለቤት በመግባት “የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ” እንዲሁም “ፋኖን ትደግፋላችሁ” በሚል በ8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል።

• መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ጉና በጌምድር ወረዳ፣ ክምር ድንጋይ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተተኮሰ ወታደራዊ ዒላማን ያልለየ የጦር መሣሪያ አቶ ገደፋው አለሜ በተባሉ ሰው መኖሪያ ቤት ግቢ ላይ በማረፉ 2 የቤተሰቡ አባላት (ወ/ሮ ፍቅረዓለም አለበልና ሕፃን ዮርዳኖስ ገደፋው) ሲገደሉ ሌሎች 2 ሕፃናት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ኢሰመኮ  ለማረጋገጥ ችሏል።

• በምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ በደባይ ጥላትግን ወረዳ፣ በቁይ ከተማ እና በዙሪያ ቀበሌዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) መካከል በነበረ ውጊያ በሲቪል ሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። በተለይ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት መጽሔት ልንገረው የተባለች የ3 ዓመት ሕፃን በተባራሪ ጥይት ተመትታ ቁይ ጤና ጣቢያ የሕክምና እርዳታ ከተደረገላት በኋላ ለከፍተኛ ሕክምና “ሪፈር” ብትባልም መንገድ በመዘጋቱ እና በወቅቱ ሕክምና ባለማግኘቷ ሕይወቷ ማለፉን ከቤተሰቦቿ ማረጋገጥ ተችሏል። መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. በውጊያው የሞቱ ሰዎችን ሥርዓተ ቀብር ሲፈጽሙ የነበሩ 3 ሲቪል ሰዎች “ለምን ትቀብራላችሁ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሲሆን፣ አንዱ መስማት የተሳነው አካል ጉዳተኛ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

• መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ በቋራ ወረዳ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት ይካሆ እና ገለጉ (አሶል) ቀበሌዎች በመግባት ነዋሪዎችን “የብልጽግናን መንግሥት ትደግፋላችሁ” እንዲሁም “ከመከላከያ ጋር ሆናችሁ ፋኖን ተዋግታችኋል” በሚል 8 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል። በተጨማሪም 60 የሚሆኑ ሰዎችን ገለጉ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለቀናት እንዳሰሩ እንዲሁም በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን እንደዘረፉ ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። ጥቃቱን በመፍራት በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበረ ሲሆን ከቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል።

• መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሰዓት አካባቢ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በሰሜን ሜጫ ወረዳ፣ ዳጊ ቀበሌ ላይ በመንግሥት ኃይሎች በተደጋጋሚ በተፈጸመ የአየር ጥቃት አቶ ሞገስ ደፈርሻ የተባሉ የ70 ዓመት አረጋዊ እንደተገደሉና 2 ሴቶች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም ዳጊ ጤና ጣቢያ ላይ ጉዳት እንደደረሰ እና 4 መኖሪያ ቤቶች ተመተው እንደፈራረሱ ኢሰመኮ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው ነዋሪዎች አስረድተዋል። በዕለቱ የአየር ጥቃት በተፈጸመባቸው ቦታዎችም ሆነ በቅርብ ርቀት ላይ ግጭት እንዳልነበረ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (በተለምዶ “ፋኖ”) አባላት በቦታው እንዳልነበሩ ጨምረው ገልጸዋል።

39k 0 15 5 101



የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ያስከተለው ምስቅልቅል እና ምሬት

(መሠረት ሚድያ)- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ በተለይ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻ ከተደረገ ወዲህ የኑሮ ውድነት ተባብሶ ቀጥሏል።

የመገበያያ ዋጋቸው እጅግ እየጨመሩ ከመጡ ምርቶች አንዱ ነዳጅ ነው። የዛሬ ሁለት አመት በዚህ ወቅት ቤንዚን በሊትር 61 ብር ነበር፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 67 ይሸጥ ነበር፣ ኬሮሲንም በሊትር 67 ብር ነበር።

አሁን ላይ ቤንዚን 101 ብር ከ47 ሳንቲም ገብቷል፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 98 ብር ከ98 ሳንቲም ሆኗል፣ በሌሎች የነዳጅ ምርቶች ላይም በትንሹ ከ8 ብር በላይ ተጨምሯል።

ታድያ የዚህ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ የህዝብ ትራንስፖርቱ ዋጋም በእጅጉ እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል። በተለይ በተለይ በአዲስ አበባ ዳርቻ አካባቢዎች በሰፈሮችና በኮንዶሚኒየምዎች የሚኖሩ ዜጎች ለትራንስፖርት የሚያወጡት ወጪ እጅግ በጣም ጨምሮ ኑሮን እንዳከበደባቸው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

ለምሳሌ በኮዬ ፈጬ፣ በአራብሳ፣ በቂሊንጦ፣ በቱሉዲምቱ ወዘተ... የሚኖሩ ዜጎች ከነዚህ መኖሪያ መንደሮች እስከ መገናኛ እንኳን ለመድረስ በአውቶብስ 20 ብር፣ በታክሲ ደግሞ 50 ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

"ወቅታዊ ታሪፉ ደርሶ መልስ በአውቶቡስ 40 ብር፣ በታክሲ 100 ብር ነው መገናኛ ድረስ ብቻ። እኛ ግን አልፈን ሄደን መሀል ከተማ ነው የምንሰራው፣ ለትራንስፖርት ብቻ በቀን እስከ 130 ብር በትሹ እናወጣለን" በሚል አስተያየት የሰጡት እነዚህ ዜጎች ይህንንም ለማግኘት ብዙ ተሰልፈው እና ተንገላተው እንደሆነ ያስረዳሉ።

"ይሄ እጅግ በጣም ኑሮአችንን አክብዶብናል፣ ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል። አቤቱታችንን በሚዲያችሁ አስተላልፉልን፣ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል" የሚሉት እነዚህ ዜጎች የነዳጅ ድጎማ ቀስ በቀስ መነሳት ላልተጠበቀ እና እጅግ አቅምን ለሚፈታተን ከባድ ወጪ እንደዳረጋቸው በምሬት ይናገራሉ።

"በአንድ ቤት ውስጥ ብቻ ስራ ለመሄድ፣ ልጆችን ት/ቤት ለማድረስ እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን እንቅስቃሴ ሳይጨምር ለአንድ ሰው  ይሄን ያህል ወጪ በቀን እያወጡ እንዴት መኖር ይቻላል?" በማለት አስተያየታቸውን በጥያቄ ቋጭተዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

47.3k 0 26 38 451



"ክሱን የያዙ ጠበቆች ለሚድያዎች የክሱን ሒደት እንዳያስረዱ ዛቻና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው ነው"- የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ቤተሰቦች

(መሠረት ሚድያ)- ጥቅምት 2016 ዓ/ም በብልሹ አመራር እና በአፈፃፀም ድክመት ምክንያት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ቤተሰቦች 'በፖለቲካ ሴራና በጥቂት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጥላቻ' ስቃይ እየደረሰበት ነው በማለት ተናገሩ።

የቤተሰብ አባላቱ ለመሠረት ሚድያ በሰጡት ቃል "ያለፍትሕ ከታሰረ አንድ ዓመት ከአራት ወር ያህል ሆኖታል፣ አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት በዳኞች ላይ በሚያደርሱት ፖለቲካዊ ጫና ዙርያ መረጃ ይፋ ማድረግ እንፈልጋለን" ብለዋል።

አክለውም "ምንም እንኳን በቀረበበት ክስ ላይ በተገቢዉ መልኩ የተከላከለ ቢሆንም የክልሉ መንግስት የፍትህ ስርአቱን ለማዛባት ከሚያደርጉት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በተጓዳኝ ክሱን  የያዙ ጠበቆች ለሚድያዎች የክሱን ሒደት እንዳያስረዱ ዛቻና ማስፈራርያ በማድረስ ላይ ነው" ያሉት እነዚህ የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ቤተሰቦች የመከላከያ ምስክር ተደርገዉ የተቆጠሩ የመንግስት ስራ ሀላፊዎቾ ፍርድ ቤት ቀርበዉ ቃል እንዳይሰጡ ዛቻና ማስፈራራት፣ በሰበብ አስባብ ቀጠሮዎችን ማራዘምና በቂ የህክምና ክትትል እንዳያገኝ ከማድረግ አንስቶ ቤተሰቡን እና ልጆቹን ለችግር እንዲዳረጉ አስርገዋል ብለው ከሰዋል።

"ኢትዮጲያ ህዝብና መላዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ድምጽ እንድትሆኑት ስንል በማክበር እንጠይቃለን" ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ በከንቲባነት ዘመናቸው ህዝብን የሚጎዳ ጥፋት እንዳልሰሩ እና እሳቸውን ማሳደዱ 'የስልጣን ፍላጎትና የእዉቅና ሽሚያ' በማለት ከዚህ በፊት በሚድያዎች በኩል ተናግረው ነበር።

የቀድሞ ባለስልጣኑ በህግ ሲፈለጉ ከቆዩ በኋላ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በዚህ ዙርያ ከሲዳማ ክልል አመረሮች ምላሽ ለማግኘት ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia

50.2k 0 17 27 214


Показано 20 последних публикаций.