መክሊቱን በአጋጣሚ ያገኘው ቦክሰኛው መሀመድ አሊ የተሰረቀችበት ብስክሌት የሞያ መነሻው እንደሆነች ያውቃሉ?
**** ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 1954 ነው። መሀመድ አሊ እድሜው ገና የ12 ዓመት ታዳጊ ነው። የቦክስ ሻምፒዮናው መሀመድ አሊ ተጋጣሚዎችን በመዘረር ዓለምን ያስደነቀ፣ የወርቅ ሜዳሊያንም ለሀገሩ በማስገኘት የምንጊዜም አይረሴ ጀግና አሜርካዊ ቦክሰኛ ነው።
ለዚህ ክብር እና መደነቅ የበቃው መሀምድ አሊ ብዙዎች የዛሬ ማንነቱን እና የዓለም የቦክስ ሻምፒዮና መሆኑን እንጂ እንዴት ለዚህ ክብር እንደበቃ የሚያውቁ መኖራቸው ያጠራጥራል። ለዚህም ይመስላል ሰዎች አንዳንድ አጋጣሚዎችን አለመግፋት የእድላቸው በር እንደመክፈት ይቆጠራል የሚሉት።
መሀመድ አሊ ገና የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ የአጎቱ ልጅ የሚያደርገውን የቦክስ ግጥሚያ ውድድር ለማየት ወደ ኮሎሚቢያ ትእይንት በ60 ዶላር የተገዛች ሳይክሉን እየነዳ የሄደው። በዚህ ውድድር ላይ የአጎቱ ልጅ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱን መሀመድ አሊ በአንድ ወቅት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ አስታውሶ ተናግሯል።
ይህ የውድድር እለት ለመሀመድ አሊ ጥሩ የሚባል አጋጣሚ አልነበረም። ምክንያቱም የአጎቱ ልጅ በውድድሩ አላሸነፈም እና ደግሞ መሀመድ ከውድድሩ ሲወጣ በ60 ዶላር የገዛት ሳይክሉ በሌቦች ተሰርቃበት ነበር። እና በወቅቱ መሀመድ አሊ በንዴት ሁኔታውን ጆ ማርቲን ለተባለ ፖሊስ ሪፖርት ያደርጋል። ሳይክሉን የሰረቀው ሌባ ቢያገኘው በቦክስ ዋጋውን እንደሚሰጠውም መሀመድ ለፖሊሱ ይነግረዋል። የፖሊስ አባሉም የቦክስ አሰልጣኝ ስለነበረ “ቦክስ ዝምብሎ መሰንዘርና ማሸነፍ ማለት አይደለም ይልቁንም የቦክስ ስልጠና መውሰድ ብትችል ብዙ ትማርበታለህ” በማለት ለመሀመድ አሊ ምክር ይለግሰዋል። መሀመድም በዚህች አጋጣሚ የጠፋች ሳይክሉን ለመፈለግ ብሎ ጊዜውን ሳያባክን የፖሊሱን ምክር ተቀብሎ የቦክስ ስልጠናውን ጀመረ። በዚህች ቅጽበትም መሀመድ አሊ የህይወት እጣ ፈንታው የሆነውን የቦክስ ስፖረት ሀ ብሎ ጀመረ።
ስለመሆነም ዝነኛውና ዓለም አቀፍ ቦክሰኛው መሀመድ ዓሊ የጠፋችበትን ሳይክሉን የማስታወስ እድል አላገኘም ። ይልቁንም የወደፊት ህይወቱን ለማቅናትና ህልሙን ለመኖር የሚረዳውን የጆ ማርቲንን ምክር ተከትሎ በጠንካራ መንፈስ የቦክስ ልምምድ ስራውን ጀመረ።
መሀመድ ዓሊ ከ6 ሳምንታት ስልጠና በኋላ ለውድድር ብቁ ሆኖ በመገኘቱ የ12 ዓመት ቦክሰኛ ጋር የቦክስ ግጥሚያውን አደረገ። በዚህ ውድድርም መሀመድ ተጋጣሚውን 5 ዙር በማሸነፍ ዘርሮ በመጣል የመጀመሪያ ድሉን አስመዘገበ።
ከዚህ በኋላ መሀመድ የሚወስደውን የቦክስ ስልጠና በተከታታይነት ስራዬ ብሎ ያዘው። መሀመድ ዓሊ የከባድ ሚዛን ቦክሰኞች የሆኑትን እነ ጆ ፍሬዘር፣ ሳኒሊስተር፣ ጆርጅ ፍርማን የተባሉ ተዋቂ ቦክሰኛ ተጋጣሚዎቹን በመፋለም ድንቅ ብቃቱን አስመስክሯል።
በ18 ዓመቱ በጠንካራ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ተጋጣሚዎቹን በከፍተኛ ልዩነት በመርታት ለሀገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት ችሏል። ይህ ክስተት ደግሞ የመሀመድ ሌላ አስደናቂ አጋጣሚ ሆነ። የዓለም ሻምፒዮናው መሀመድ አሊ ውድድሩን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ባገኘ ጊዜ ሜዳሊያውን በአንገቱ አንጠልጥሎ ነጮች ከሚዝናኑበት አንድ ሬስቶራንት ጎራ ይላል። መሀመድ አሊ ወርቁን በአንገቱ ላይ አንጠልጥሎ ሬስቶራቱ ውስጥ አንደኛው ወንበር ለይ ቁጭ ብሎ አስተናገጇን አንድ ሲኒ ቡና እንድታመጣለት ያዛታል። አስተናጋጇም ጥቁሮች በዚህ ሬስቶራንት መስተናገድ እንደማይችሉ ለመሀመድ ትነግረዋለች። በዚህ ጊዜ መሀመድ ተናደደ።
በዚህም ምክንያት እንደውም 2 ሲኒ ቡና ካልሰጠሽኝ አልጠጣም ማለቱን አሊ አስታውሶ ተናግሯል። ለሀገሬ የወርቅ ሜዳሊያ አምጥቼ እንዴት በዜጎች አልከበርም የሚለው ጥያቄ የተፈጠረበት መሀመድ ይህ ሁኔታ ስሜቱን እንደጎዳውና በወቅቱ እንደተበሳጨም ገልጿል። እናም ብስጭቱ ለውሳኔ ያደረሰው መሀመድ ኦሀዮ ወንዞ በመውረድ ያገኘውን የወርቅ ሜዳሊያ ከወንዙ ላይ መጣሉን በግለ ታሪኩ ላይ ተጽፏል።
ይህ ሁኔታ ከተፈጸመ ከ36 ዓመታት በኋላ በአትላንታ በተካሄደ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ መሀመድ አሊ ለሀገሬ ያመጣሁት የወርቅ ሜዳሊያ እንዴት አያስከብረኝም ብሎ ወንዝ ውስጥ የጣለውን ምትክ ሜዳሊያ ተሰጥቶታል። መሀመድ አሊ የዓለም ከባድ ሚዛን የቦክስ ውድድሮችን በማሸነፍ የ3 ጊዜ ሸምፒዮና በመሆን ሪከርዱን ማስጠበቅ የቻለ ጀግና ነው።
በ2024 ዓለም አቀፉ የቦክስ ፌዴሬሽን ማህበር ጉባዔ በዱባይ ሲካሄድ ለመሀመድ አሊ ቤተሰቦች ክብር እና እውቅና ተሰጥቷል። በዚሁ ጊዜም ልጁ ረሺዳ አሊ የአባቷ ስራዎች ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ተናግራለች።
በርግጥ መሀመድ አሊ ከፕሮፌሽናል ቦክሰኛነቱ ባሻገር ለሰው ልጅ እኩልነት የታገለ እና የሚታገል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደሆነ የሚመሰክሩለት ብዙዎች ናቸው። መሀመድ አሊ የነበረበት ወቅት የጥቁሮች እና ነጮች እኩልነት ያልተረጋገጥበት ጊዜ በመሆኑ ይህን በብዙ መንገድ ታግሏል።
የዓለም የምን ጊዜም ታላቅ ሰው የሚባለው መሀመድ ከዘመናት የስኬት ጉዞ በኋላ በ74 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በአጋጣሚ የብስክሌቱ መጥፋት የፈጠረበትን ብስጭት ለማስታገስ እሰነዝረዋለሁ ያለው ቦክስ በህይወቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣበት እሱም እንደኮኮብ የሚያበራበት አጋጣሚ የሆነለት ታላቅ ሰው ከዝናው ባለፈ ህይወቱም ለብዙዎች አስተማሪ ሆኖ ተመዝግቧል።
በመሀመድ ፊጣሞ
⛵️⛵️⛵️
"ማንበብ ፋሽን ነው።"
Join us
@noahbookdelivery