ሕዝቅኤል 33
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦
² የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥
³ እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ሰይፍ ባየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥
⁴ የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል።
⁵ የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር።
⁶ ጕበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ ቢያይ መለከቱንም ባይነፋ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
⁷ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው።
⁸ ኃጢአተኛውን፦ ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።
⁹ ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
¹⁰ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው።
¹¹ እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
¹² አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም።
¹³ እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም።
¹⁴ እኔም ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥
¹⁵ ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ የነጠቀውንም ቢመልስ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።
¹⁶ የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
@onegodonlyjesuss