#ሳይጨመር
የብዙ ነገር ድምር እና ክምችት ሙላት ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ሰዎች አሁን ባለኝ እዚህ ነገር ላይ ይሄ ቢጨመር፣ ይሄ ደግሞ ቢታከል ሙሉ ነኝ ሲሉ መስማት የተለመደ ነው። ሙላትን ሰው እንደየጎድለቱ ሊተምነው ይችላል። ጤና ኖሮት ገንዘብ የጎደለው ጤናው ብቻ ሙላት አይሆንለትም፣ ገንዘብ ኖሮት ጤና ያጣ ደግሞ ገንዘብ ምን ይሰራልኛል ይላል።
ሰው እንደየ ክፍተቱ ለሙላት ያለው ምልከታም የተለያየ ነው። አንድ ጥያቄ ግን ላንሳ .. በእርግጥ ሰው የፍላጎቱ ሙላት ላይ ሊደርስ ይችል ይሆን? አለኝ ያለው ሌላ እንዲኖረው ሲተጋ እንጂ ሲያመሰግን አይታይም። ለዚህም ሰው ሙላቴ የሚለው በህይወቱ ካሉት ነገሮች በመነሳት እንደሆነ የሚታመን እና ቅቡልነት ያለው ሃሳብ ነው።
እስኪ አለኝ ከምትሉት ነገር ሁሉ ውጡና አንዱን እግዚአብሔርን አስቡት። ያላችሁን ሁሉ አጥታቹ እግዚአብሔርን ብቻ ስላላችሁ ሙሉ እንደሆናችሁ ይሰማችኋል? ይህ በጣም መሰረታዊ ነገር ነው። በእርግጥ ይህ ይሰማችኋል? እግዚአብሔር ብቻውን ሙላት ከልሆነላችሁ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋችኋል።
በእኛ ህይወት የትኛው ስሌት ልክ ሊሆን ይችላል ?
እግዚአብሔር ሲደመር ገንዘብ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ጤና = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ክብር = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ዝና = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር እውቅና = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ውበት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ስኬት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ከፍታ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ስልጣን = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር የሰው ፍቅር = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ትዳር = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ጉልበት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ዕድሜ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ስራ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ሃብት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ተወዳጅነት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ተሰሚነት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ቤተሰብ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ልጅ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ዘመድ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ጎረቤት = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ጥሩ ጓደኛ = ሙላት ነውን?
እግዚአብሔር ሲደመር ወዳጅ = ሙላት ነውን?
ነውን? በእርግጥ እነዚህ ሁሉ ሙላት የሚመስሉ ነገር ግን በፍጹም ያልሆኑ ናቸው። ትክክለኛው ቀመር ይሄ ነው። እግዚአብሔር + ምንም = ሙላት። ምንም ባይኖረኝ እግዚአብሔርን ብቻ ስላለኝ ሙሉ ነኝ ማለት ከፍተኛ የእምነት ብርታት እና አስተውሎት ይፈልጋል። እግዚአብሔርን ማንም ሳይጨመር ሙላቴ ነህ፣ ምንም ሳይጨመር ሙላቴ ነህ ማለት ትችሉ ይሆን?
ከእቃ እና ከአይነት ምንም፣ ከሰው እና ከፍጥረት ማንም ሳይጨመር እግዚአብሔር ሙላት የሚሆን አምላክ ነው። እጅግ የጎደለው እግዚአብሔርን ያለው ሰው ሳይሆን እግዚአብሔርን ሳይኖረው ሁሉን ያለው ነው። ምክንያቱም እርሱን የሌለው ምንም ቢኖረው ያለው ነገር ሁሉ ምንም ስለሆነ ነው። ያለ እግዚአብሔር ሁሉ ምንም ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ምንም ግን ሙላት ነው።
አስተውሉ በሲደመር መርህ የምትመላለሱ ከሆነ እጅግ ከባድ ነው። ምንም ሳይደመር፣ አንዳች ሳይጨመር እርሱ እግዚአብሔር ሙላታችሁ ይሁን። ይህን እምነት ያለው ሰው በምንም ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን አይተውም። በሲደመር መርህ የሚመላለስ ሰው ግን ያንን የሚደመረውን ፍላጋ መባዘኑ አይቀርም። እና ምንም አትደምሩ ምንም።
እግዚአብሔር ሙላት ያልሆነው ሰው የቱምንም የስኬት ጣራ ቢመለከት አያርፍም። ምክንያቱን ሁሉን ባለው በእግዚአብሔር ስላለረፈ። እግዚአብሔር ላይ ተደምሮ ሙላት የምንለው ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን የመተካት (በእኛ ላይ ጣዖት የመሆን) አቅሙ ከፍተኛ ነው። በማስተዋል ያለምንም ተደማሪ እና ተጨማሪ ነገር እግዚአብሔርን ሙላቴ ማለት ይብዛልን። አሜን
✍ ዲያቆን ተስፋ መሠረት
📆 የካቲት 18 2017 ዓ.ም ተጻፈ
ይቀላቀሉ 👇👇 ለሌሎች ያጋሩ
@orthodox_new_mezmur@orthodox_new_mezmur