ረቢ ወዴት ትኖራለህ
ከመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች መካከል ሁለቱ "የእግዚአብሔር በግ እነሆ" የሚለውን የመምህራቸውን ስብከት ሰምተው ጌታን ተከተሉት::
"ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ" ዮሐ. 1:37-39
ጌታን ተከትለው የሚኖርበትን ካዩት ደቀ መዛሙርት አንደኛው ስም እንድርያስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የራሱን ስም በወንጌሉ ላይ እኔ የማይጽፈውና ቤተ ክርስቲያን ግን የራሱን ነገር ሲገልፅ በሚጠቀመው ቋንቋ የምታውቀው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነበረ::
"ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ መጥታችሁ እዩ፡ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ" የሚለው ቃል በእርግጥ በጣም አስገራሚ ነው:: የክርስቶስን መኖሪያ ማየት መፈለጋቸው ፈልገው እንዳያጡት አድራሻውን ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ነበረ::
ሆኖም ክርስቶስ በምድር ላይ ሲኖር ቋሚ አድራሻ አልነበረውም:: ራሱ እንደተናገረ :-ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም" (ማቴ. 8:20)
እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት የጠየቁት "ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ?" የሚለው ጥያቄ አድራሻ ከመጠየቅ ከፍ ያለ ጥልቅ ጥያቄ ነው:: ነቢያቱ "የጥበብ ሀገርዋ ወዴት ነው? ማደሪያዋስ ወዴት ነው?" ብለው የተጨነቁለት የጥበብ ክርስቶስ ማደሪያ የት እንደሆነ ማወቅ የነፍስ ዕረፍት ነውና ተራ ጥያቄ አይደለም?
ይህ ጥያቄ ዳዊት ለዓይኖቹ እንቅልፍ ለሽፋሽፍቶቹ ዕረፍት ያልሠጠበት "የያዕቆብ አምላክን ማደሪያ እስኪያገኝ ድረስ" የለመነበት ጥያቄ ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? የሚለው ጥያቄ እንድርያስና ዮሐንስ በአንድ ቀን ብቻ የሚመለስ ጥያቄ መስሎአቸው አብረውት ሔደው አብረውት ዋሉ እንጂ የጌታ መኖሪያ ግን ያን ቀን የዋለበት ብቻ አይደለም::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
"ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ" መዝ. 43:3
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? "ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ ነህ፤ ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ። እንደ ንስር የንጋትን ክንፍ ብወስድ፥ እስከ ባሕር መጨረሻም ብበርር፥ በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ ቀኝህም ትይዘኛለች" መዝ. 139:8 ለአድራሻ የሚያስቸግረው የረቢ መኖሪያው ብዙ ስለሆነ የት ትኖራለህ ለሚለው ጥያቄ መልሱ "መጥታችሁ እዩ" ብቻ ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ብለው ለጠየቁት ደቀ መዛሙርቱ ቦታውን ከመናገር ይልቅ "መጥታችሁ እዩ" ያለው ጌታ እርሱን ጸንተው እስከተከተሉ ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ አልፎም ከሞቱ በኋላ የሚያዩት ብዙ መኖሪያ ስላለው ነበር::
የረቢ መኖሪያው ብዙ ነው:: "የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፡ ወደ እርሱም እንመጣለን፡ በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን" እንዳለ ቃሉን የሚጠብቅ ሰው ሰውነትም የእርሱ ማደሪያ ነው:: (ዮሐ. 14:23)
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? " በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና" ስትል ሰምተንህ ነበር:: (ዮሐ. 14:2) የአንተ መኖሪያ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? ቅዱስ ጳውሎስ "ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" ሲል እንደሰማነው እስከ ዐሥር ሰዓት ድረስ እንደመዋል ዐሥሩ መዓርጋት ላይ የደረሱ በጽድቅ መንገድ የሔዱ የሚያዩት ማደሪያህ መንግሥተ ሰማያት አይደለምን? መጥተን ለማየት "እናንተ የአባቴ ቡሩካን ወደ እኔ ኑ" እስክትለን በተስፋ እየጠበቅን አይደለምን?
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ካሉት ጠያቂዎች መካከል አንዱ ዮሐንስ መሆኑን ሳስብ ደግሞ ዮሐንስ ያያቸው የረቢ መኖሪያዎች ከገሊላ እስከ ታቦር ተራራ ፣ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ፣ ከወንጌል እስከ ራእይ እጅግ ብዙ እንደነበሩ ታየኝ::
"ወዴት ትኖራለህ?" ብሎ ጠይቆ ጌታን የተከተለው ዮሐንስ "መጥተህ እይ" በተባለው መሠረት የጌታን መኖሪያ የእርሱን ያህል ያየም ሰው የለም::
ዮሐንስ "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" ለሚል ጥያቄው ግን አንጀት የሚያርስ ልብ የሚያሳርፍ መልስ ያገኘው አርብ ዕለት መስቀሉ ሥር ነበር:: ወዴት ትኖራለህ? ላለው ዮሐንስ የዘጠኝ ወር ከተማውን የዘላለም ማረፊያውን "እነኋት እናትህ" ብሎ ሲሠጠው መጥቶ ካያቸው የረቢ መኖሪያዎች ሁሉ የምትበልጠውን መኖሪያ አየ:: "እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ" ብሎ የመረጣትን ማደሪያ ከማየት በላይ ምን ክብር አለ? (መዝ. 132:13)
ዮሐንስ ይህችን የረቢ መኖሪያ ወዲያው ወደ ቤቱ ወሰዳት:: ዮሴፍ ሊወስዳት ስላልፈራ ምን እንዳገኘ ያውቃልና እርሱም ይህችን የዕንቁ ሳጥን ወደ ቤቱ ወስዶ ቢዝቁት የማያልቅ ጸጋን ተጎናጸፈ::
ጌታ እናቱን ለዮሐንስ መሥጠቱ የሁለት ድንግልናዎች ማስረጃ ሆነ:: የድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልናም የዮሐንስ ድንግልናም በጌታ ንግግር ታወቀ::
አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ድንግል ማርያም ከጌታ ሌላ ልጆች ቢኖሩአት ኖሮ "እናቴን ከልጆችዋ ነጥለህ ወደ ቤትህ ውሰዳት" "አንቺም ልጆችሽን ይዘሽ ወደ ሰው ቤት ሒጂ" ብሎ ለዮሐንስ አይሠጣትም ነበር:: ድንግል ማርያም የአብን አንድያ ልጅ አንድያ ልጅዋ አድርጋለችና አምላክ ባደረበት ዙፋን ሌላ ፍጡር ያላስቀመጠች የአምላክ ብቸኛ ዙፋን ፣ እግዚአብሔርን አስገብታ በርዋን የዘጋች ዘላለማዊት ድንግል መሆንዋ ለዮሐንስ በመሠጠትዋ ታወቀ:: ዮሐንስም ቤት ንብረት የሌለው መናኝ ባይሆንና ሚስት ድስት ያለው ሰው ቢሆን ድንገት ወደ ቤቱ ይዞአት እንዲሔድ እናቱን ባልሠጠው ነበር::
የሰው ልጅ ድኅነት ታሪክ በሁለት "እነሆ"ዎች መሃል መከናወኑ እጅግ ይደንቃል:: የሰው መዳን የተጀመረው "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ብላ ራስዋን ለፈጣሪ በሠጠችው ድንግል ቃል ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ "እነኋት እናትህ" ብሎ በደም በታጠበ አንደበቱ በነገረን የኑዛዜ ቃል ነው::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ? ለእኛም አታሳየን ይሆን? እስከ ዐሥር ሰዓት መዋል ፣ ዐሠርቱን ትእዛዛትህን ፣ ዐሥሩን የቅድስና ደረጃዎችን መውጣት ላቃተን ለእኛስ መኖሪያህን ታሳየን ይሆን? መጥታችሁ እዩ የሚለውን ጥሪ ሰምተን ለማምጣት አቅም ላነሰን መጻጉዕዎች ፣ ዓይን ላጣን በርጤሜዎሶች ተነሡ እዩ ብለህ መኖሪያህን አታሳየን ይሆን? መቅደስህን እንመለከት ዘንድ ፣ መኖሪያህን መንግሥትህን እናያት ዘንድ ፣ ዮሐንስ ያያትን መኖሪያህ እናትህን እናይ ዘንድ እንመኛለን::
ረቢ ወዴት ትኖራለህ?
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ የኤፌሶን ወንዝ
💚
@ortodoxmezmur 💚
💛
@ortodoxmezmur 💛
❤️
@ortodoxmezmur ❤️