በጥያቄና መልስ ፕሮግራም አንድ እህታችን ለዶር ዛኪር ይህን ጥያቄ ጠይቃው ነበር።
"በዚህ ፕሮግራም መጠየቅ የምፈልገው ለእስልምና ያለኝ ክብር እንደተጠበቀ ሆኖ ጣዖት ማምለክና ከአላህ በስተቀር አምላክ አድርጎ መያዝ በእስልምና ከባድ ወንጀል እንደሆነና እነዚህን ሰዎች አላህ እንደማይምራቸው ነግረኸናል።
እንደዛ ከሆነ ከእስልምና ውጪ በሆነ ሀይማኖት ቤተሰብ የተወለዱ ልጆች ምን ሊሆኑ ነው?
ስለ እስልምና ምንም የማያውቅ ብዙ ሰው አለ። ያስተማራቸውም የለም። የነዚህ እጣ ፈንታ ምንድነው?
ምንድነው ጥፋታቸው?
ፈፅሞ ገነት አይገቡም ማለት ነው?
አላህ አይምራቸውም ማለት ነው?
ተወልደው ያደጉበት ቤተሰብ ያስተላለፈላቸውን ሀይማኖት መከተላቸው ስህተት ነውን? አላህ አያዝንላቸውም?
አመሰግናለሁ!
ዶር ዛኪር ከመቀመጫው በመነሳት ለጥያቄዋ ማብራሪያ እንደሚከተለው ሰጧት
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
"እህታችን እጅግ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅሽው። ሙስሊም ካልሆነ ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች እጣፋንታቸው ምንድነው፣ ጣዖት የሚያመልኩና የመሳሰሉት አላህ ይቀጣቸዋልን? የሚል ጥሩ ጥያቄ ጠይቀሻል።
ለዛም ነው ተወዳጁ ነብያችን(አ ሰ ወ) "ሁሉም የአደም ልጅ ሲወለድ ተፈጥሯዊ በሆነ ሀይማኖት ነው" ያሉት። ሙስሊም ሆነን ነው የምንወለደው።
በአይሁድ ቤተሰብ ይወለድ በክርስቲያን፤
በሂንዱም ይሁን በሙስሊም ቤተሰብ፤
ማንም ሰው ሲወለድ ሙስሊም ሆኖ ነው የሚወለደው።
ሙስሊም ብሎ ማለት ራሱን ለፈጣሪ ትዕዛዝ ያስገዛ ማለት ነው።
ስለዚህም ማንም ሰው ሲወለድ ራሱን ለፈጣሪ ትዕዛዝ ያስገዛ ሆኖ ነው። ከጊዜ በዃላ ግን በቤተሰቦቹ፤ በታላቆቹ ወይም በአስተማሪዎቹ ምክንያት ሊሆን ይችላል ጣዖትን፣ እሳትን የመሳሰሉትን ማምለክ ይጀምራል። በተሳሳተ መንገድ ይሄዳል።
ለዛም ነው አንድ ሰው ሲሰልም ወደ እስልምና ተቀየረ ከሚለው ቃል ይልቅ ወደ እምነቱ ተመለሰ የምንለው።
ተቀየረ የሚለው ቃል አይገልፀውም።
ተቀየረ የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ከአንድ እምነት ወደ ሌላ እምነት ሲሄድ ነው። ተመለሰ የምንለው ግን መጀመሪያ ወደነበረበት እምነት ሲመለስ ነው።
ስለዚህ ትክክለኛው ቃል ተመለሰ የሚለው ነው።
ወደ ጥያቄሽ ስመለስ፤ ከሌላ እምነት ተከታይ ቤተሰብ የተወለደን ሰው አላህ ለምን ይቀጣዋል ላልሺው።
አንድ ህፃን ለአቅመ አዳም ሳይደርስ ከሞተ በአላህ ፍቃድ ጀነት ይገባል። ምክንያቱም ማንኛውም ህፃን ሲወለድ ራሱን ለፈጣሪ ያስገዛ ስለሆነ። የሂንዱ ስም ይኑረው የክርስቲያን ስም ለውጥ አይፈጥርም።
ለአቅመ አዳም እስካልደረሰ ድረስ በህፃንነቱ ከሞተ ጀነት ይገባል። ከሙስሊም ቤተሰብ ይወለድ ሙስሊም ካልሆነም ቤተሰብ ጀነት ይገባል።
ከጊዜ በዃላ ህፃኑ አድጎ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ግን ለሚሰራው ስራ ሁሉ ሀላፍትና የሚወስደው ራሱ ነው።
ለዛም ነው ህፃን ልጅ ጥፋት ሲያጠፋ ህግ የማይቀጣው። ለአቅመ አዳም ሲደርስ ግን "አባቴ ስረቅ ስላለኝ ነው የሰረቅኩት" ቢል ከህግ ቅጣት የማይድነው።
ልጅ ካደገ በዃላ 22 አመት ሞላው ብንል እና ሲሰርቅ ፓሊስ ቢይዘው "አባቴ ስረቅ ስላለኝ ነው የሰረቅኩት" ሊል አይችልም። ይህን ማለቱ ከቅጣት ያድነዋል?
ህፃን እያለ 5 አመቱ ላይ ይህን ቢል ችግር የለውም። ህፃን ስለሆነ ይባላል። ለአቅመ አዳም ከደረሰ በዃላ ግን "አባቴ ስረቅ ስላለኝ ነው የሰረቅኩት" ቢል ነፃ ሊወጣ አይችልም።
ማንም ሰው ለአቅመ አዳም ከደረሰ በዃላ ለውሳኔው ሃላፍትና ራሱ ነው የሚወስደው። አንድ ሰው ለአቅመ አዳም ከደረሰ በዃላ እውነትን መፈለግ የራሱ ወይም የራሷ ሃላፍትና ነው።
የእስልምናን መልዕክት ሙስሊም ላልሆኑት ማድረስ የኛ የሙስሊሞች ሃላፍትና ነው። ነገር ግን መልዕክቱ ደረሳቸውም አልደረሳቸውም የሰው ልጅ በነፃነት ከተተወ ለምሳሌ እስከ 1950 ከአለም ስልጣኔ ጋር ምንም ንክኪ ያልነበራቸው ሁለት ጎሳዎች ነበሩ። አንዱ ጎሳ ከፓውኩ ሲባል ሁለተኛው አስትሮይድ አቦ ሪጅን ይባላል። እነዚህ ሁለት ጎሳዎች እስከ 1950 ድረስ ዘመናዊ ስልጣኔ የሚባል ነገር አያውቁም። ተመራማሪዎች የኑሮ ሁኔታቸውን ለማጥናት ሲሞክሩ ሁለመናቸው ኢስላም ሆኖ ነበር ያገኙት። ራሳቸውን ግን ሙስሊም አይሉም ነበር።
በአንድ አምላክ ያምናሉ
ፈጣሪ አምሳል እንደሌለው ያምናሉ
ጣዖት እንደሌለው ያምናሉ
ፈጣሪን ሱጁድ በማድረግ ይገዛሉ
ከስም በስተቀር ነገረ ስራቸው እስልምና ይመስል ነበር።
ህፃን ልጅ ውጫዊ ተፅዕኖ ባይኖርበት ራሱን ለፈጣሪ ያስገዛ ሆኖ ያድግ ነበር። በዛም መንገድ ይፀና ነበር። ለአቅመ አዳም ሲደርስ የእስልምና ሀይማኖት መልዕክትን እኛ ሙስሊሞች የማድረስ ሃላፍትና አለብን። ካላደረስን አላህ ዘንድ ተጠያቂዎች ነን።
ነገር ግን መልዕክቱን የማድረስ ስራውን ሰራንም አልሰራንም ተጠያቂዎች ብንሆንም አላህ(ሱ ወ) በተከበረው ቁርዓን ሱረቱል ፉሲለት ምዕራፍ 41 አንቀፅ 53 ላይ "እውነት መሆኑ እስኪገለፅላቸው ድረስ በአፅናፎቹ ውስጥና በነፍሶቻቸውም ውስጥ ያሉትን ተዓምራቶቻችንን በርግጥ እናሳያቸዋለን" ይላል። አላህ(ሱ ወ) ያለማንም እገዛ ለእያንዳንዱ ሰው እውነታውን ሊያሳይ በራሱ ላይ ሀላፍትና ወስዶዋል።
እኛ መልዕክቱን አደረስንም አላደረስንም ጥሩ ምሳሌ ሆንም አልሆንም አላህ ራሱ በቀጥታ በእያንዳዱ የሰው ልጅ ልብ ላይ እውነታውን ያሳየናል።
ሙስሊም ብንሆንም ባንሆንም ስለ ፈጣሪ አንድ መሆን እውነታውን ያሳየናል።
እውነታው ከተገለፅን በዃላ መቀበል አለመቀበል የኛ ምርጫ ነው። አንዳንዱ እስልምናን ከተቀበልኩ መጠጥ ላቆም ነው፤ ከሴት ጋር ልቅ መሆን፤ መጨፈር የመሳሰሉ በሀይማኖቱ ክልክል የሆኑ ድርጊቶችን ላቆም ነው በሚል መሰል ምክንያቶች እውነትን ላይቀበል ይችላል። ምርጫው የራሱ ነው፤ ከዛ ግን ይጠየቅበታል።
በተመሳሳይ አባት ለልጁ ስህተትን ካስተማረው ለምሳሌ መስረቅን ቢያስተምረው መስረቅ ወንጀል መሆኑን መለየት የልጅ ሃላፍትና ነው። ልጅ ዳኛ ፊት ቆሞ "አባቴ ስረቅ ብሎ ስላስተማረኝ ነው የሰረቅኩት" ቢል ነፃ ሊወጣ አይችልም።
በተመሳሳይ አላህ(ሱ ወ) እውነታውን በእያንዳዳችን ልብ ይገልፅልናል። ስለ ሀቅ፣ ስለፈጣሪ አንድ መሆን፣ ጣዖት ማምለክ ወንጀል መሆኑን ይገልፅልናል። እውነቱ ከተገለፀለት በዃላ ተግባሩን የቀጠለ ሰው በድርጊቱ ተጠያቂ ይሆናል።
ለዛም ነው በምፅዓት ቀን በአላህ(ሱ ወ) ፍትሃዊነት ዙሪያ አንድም ሰው ቅሬታ የሚያቀርብ እንደማይኖር አላህ የነገረን። ምክንያቱም የሰውነታችን አካል በኛ ላይ ይመሰክራሉ፣ አይናችን፤ እጃችን እኛ ላይ ይመሰክሩብናል።
በፍርዱ ቀን እሳት የገቡት ሰዎች ሳይቀሩ በአላህ ፍትሃዊነት ላይ ቅሬታ የሚያቀርብ አታገኙም። የሚሉት "ጌታችን ሆይ አንድ እድል ስጠን" ነው። አላህም "ዘግይታችዃል" ይላቸዋል። ምድር ላይ ስንኖር ብዙ እድሎች ተሰጥቶናል። ምድር ላይ የምንኖረውም አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
ስለዚህም የፍርዱ ቀን አንድም ሰው ሙስሊም ያልሆነ ይሁን ገሀነም የገባው ሳይቀር በአላህ ፍርድ ላይ ቅሬታ የሚያቀርብ ሰው የለም። "ጌታችን ሆይ ማረን" ይላሉ "አርፍዳችኳል" ይባላሉ።
ያለንበት አለም አላህ (ሱ ወ) በቁርዓን በሱረቱል ሙልክ ምዕራፍ 67 አንቀፅ 2 ላይ ይህኛው አለም ለቀጣዩ አለም የምንፈተንበት መሆኑን ነግሮናልና ነው።
ጥያቄሽን እንደመለስኩልሽ ተስፋ አደርጋለሁ።"
https://www.facebook.com/peacetvamharic/