ጥር ፬
"ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ"
==========================
ቅዱስ ዮሐንስ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካልከ አንዱ ነው በመጀመሪያ ለደቀ መዝሙርነት የተመረጠው ከቅዱስ ጴጥሮስና ከቅዱስ እንድርያስ ጋር ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ብዙ ስሞች አሉት ፦
ጌታ ይወደው የነበረ ሐዋርያ ( ፍቁረ እግዚእ )
ወልደ ዘብዴዎስ
ወልደ ነጎድጓድ
ነባቤ መለኮት ( ታኦሎጎስ )
አቡቀለምሲስ
ቁጹረ ገጽ እየተባለ ይጠራል ።
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን በመከራው ሰዓት ሳይሸሽ እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ የተከተለ ፣ እኛን ወክሎ የእመቤታችንን እናትነት አደራ የተቀበለ ፣ የዕለተ ዓርቡን የጌታን መከራ እያሰበ ቀሪ ዘመኑን በዕንባ የኖረ ሐዋርያ ነው ።
ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እየጠበቀ ለ16 ዓመታት ተቀምጧል ከኢየሩሳሌም ርቆ ያልሄደው እርሷን የመጠበቅ አደራ ስለነበረበት ነው ፤ በ49 ዓ.ም እመቤታችን አርፉ እንደ ልጇ በሦስተኛው ቀን ተነስታ ካረገች በኃላ ወደ ኤፌሶን ከተማ ገብቶ አስተምሯል በዚያም በአርጤምስ ቤተ መቅደስ የሚካሄደውን አምልኮ ጣኦት በመቃወሙ በጭካኔው በሚታወቀው በንጉሥ ድምጥያኖስ ዘመን ( ከ81 - 96 ዓ.ም ) በጣኦት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ በድምጥያኖስ ፊት ቀረበ እርሱም በፈላ ውኃ በተሞላ በርሜል ውስጥ ካሰቃየው በኃላ ወደ ፍጥሞ ደሴት አጋዘው።
ቅዱስ ዮሐንስም በጠባብ ዋሻ ውስጥ ለሰባት ዓመታት ( ከ88 - 96 ዓ.ም ) ያህል በግዞት ተቀምጦ ሳለ ነው ራእዩን ያየውና የጻፈው።
በ96 ዓ.ም ድምጥያኖስ ሲገደል ቅዱስ ዮሐንስ ከግዞት ተመልሶ ነው ሦስቱን መልእክታቱንና ወንጌሉን የጻፈው።
ከሐዋርያት ሁሉ ቀድሞ ሰማዕት የሆነው ታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ያዕቆብ ሲሆን ከሐዋርያት ሁሉ ረዥም እድሜ ( 99 ዓመት ) በምድር ላይ የቆየው ሐዋርያ ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ ነው።
በመጨረሻም ጌታ በገባለት ቃልኪዳን መሠረት ዮሐ 21 : 22 እንደ ሄኖክና ኤልያስ ሞትን ሳያይ ተሰውሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን ተወስዷል።
https://youtu.be/ORm4pdwoxZw?si=32B79QH_ywcTQORBhttps://youtu.be/ORm4pdwoxZw?si=32B79QH_ywcTQORBጸሎትና በረከቱ በሁላችን ላይ ይደርብን።