የግል ሕልማችሁ ጉዳይ(“የተደራጀ ሕይወት” ከተሰኘው ሰሞኑን ከታተመው አዲስ የዶ/ር ኢዮብ መጽሐፍ የተወሰደ)
የተደራጀ ሕይወት ከመኖር አንጻር ሕልማችን ላይ የመስራታችንን አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥተን እንመለከታለን፡፡ በቅድሚያ ግን “የግል ሕልም” ስንል ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ በመስማማት እንጀምር፡፡
“የግል ሕልም ማለት በተለያዩ የግል ሕይወታችን ዘርፎች ስኬታማ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመኖር የሚያስችሉንን መርሆች በመከተል የልህቀት ከፍታ ውስጥ የሚከቱንን ሁኔታዎች መገንባት ማለት ነው፡፡”
በዚህ ትርጉም መሰረት በሕልም ላይ ስለመስራት ማሰብ ማለት የራስን ሕይወት መገንባትና ማሻሻል ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ራእይ የሰውን ሕይወት የመገንባትን፣ የማሳደግንና የመለወጥን ሁኔታ ሲነካ፣ ሕልም ደግሞ የራስን ሕይወት የመገንባትን፣ የማሳደግንና የመለወጥን ሁኔታ ይነካል፡፡
ይህ ሕልም ብለን የምንጠራው ጉዳይ የራሳችንን ሁለንተናዊ ሕይወት ከማሳደግ ጋር የሚገናኝ ልምምድ ሲሆን፣ ሁኔታው እንዲሁ በሃሳባችን የፈጠርነውን ነገር ሁሉ እንደሚሆን በጭፍንነት የማሰብ ጉዳይ ሳይሆን ተግባራዊ ሂደትን ተከትሎ ስኬታማ ሕይወት ውስጥ የመግባት ጉዳይ ነው፡፡
ሕልሞቻችን ቅዠት ሆነው እንዳይቀሩ መውሰድ ከሚገቡን ወሳኝ እርምጃዎች መካከል የሚከተሉትን ቀላል መርሆች ማስታወስና መለማመድ ይጠቅናል፡፡
1. አልመው - እያንዳንዱ ታላቅ ስኬት የሚጀምረው በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ ሲፈጠር ነው።
2. እመነው - ሕልም ጋር የሚደረሰው ያለምነውን ሕልም ልንደርስበት እንደምንችል በማመን ነው፡፡
3. እየው - ሕልማችንን በገሃዱ አለም ከማየታችን በፊት በአይነ-ህሊናችን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡
4. አጋራው - ሕልማችንን በውስጣችን አምቀን ከምንይዝ ይልቅ ለተገቢ ሰዎች ማጋራት ወደ ስኬት ያስጠጋናል፡፡
5. አቅደው - ያለምነውና አምነን በውስጠ-ህሊናችን ያየነውን ሕልም በእቅድ ደረጃ ማውረድ አለብን፡፡
6. ስራው - ሕልማችንን ካመንነውና ካቀድነው በኋላ ወደ እንቅስቃሴ መግባት ይኖረብናል፡፡
7. አጣጥመው - በሕልም ተጀምሮ ጠንክሮ በመስራት እጃችን የገባውን ውጤት ማጣጣምና መደሰት ያስፈልጋል፡፡
መጽሐፉን በቅናሽ ለማግኘት በ 0947930369
@revealjesus