👉 የነብዩን ውዴታ ለፖለቲካ ፍጆታ
ክፍል ሁለት
ነብዩን መውደድ
ኢብኑል ቀይም የተባለው ሊቅ መውደድ የሚባለው ነገር ገድቦ መልግለፅ አይቻልም ከውስጥ የሚመነጭ ለመግለፅ ቃላት የማይገኝለት ስሜት ነው ይላል ። መውደድን የሚገልፁ ሁሉ በውጤቱ እንጂ በገደቡ አይገልፁትም ።
ለዚህ ነው ብዙዎች ስለመውደድ ሲፅፉ በአብዛኛው ከተቃራኒ ፆታ ጋር ያለውን ውዴታ ትኩረት ቢያደርጉም በተለያየ አገላለፅ የሚገልፁት ። እነዚህ ውጤቱን በማየት ስለሚገልፁት ነው አገላለፃቸው የሚለያየው ።
ሰዎች ለተለያየ ምክንያት የተለያየን ነገር ይወዳሉ ። አንድ ሰው ብዙ ነገርን ለተለያየ ነገር ሊወድ ይችላል ። ሁሉም የሚወደውን ነገር ለምን እንደሚወደው ማስተዋል ይችላል ። ሰዎች የሚወደዱባቸው ባህሪያቶች ባጠቃላይና ከዛ በላይ በነብዩ ላይ ይገኛል ። እንዘርዝር ብንል እንደክማለን እንጂ ዘርዝረን አንዘልቅም ።
በመሆኑም ነብዩን መውደድ ዋጂብ ነው ። ዋጂብ መሆኑ የኢስላም ሊቃውንቶች በአንድ ድምፅ ይስማማሉ ። ውዴታቸው የሚገለፅባቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ከማየታችን በፊት ዋጂብ መሆኑን ከሚያሳዩ መረጃ ውስጥ እንጥቀስ : –
አላህ በተከበረው ቃሉ በሱረቱ አትተውባ 24ኛው አንቀፅ እንዲህ በማለት ይነግረናል : –
قُلْ إِن كَانَ آبَاؤُكُمْ وَأَبْنَاؤُكُمْ وَإِخْوَانُكُمْ وَأَزْوَاجُكُمْ وَعَشِيرَتُكُمْ وَأَمْوَالٌ اقْتَرَفْتُمُوهَا وَتِجَارَةٌ تَخْشَوْنَ كَسَادَهَا وَمَسَاكِنُ تَرْضَوْنَهَا أَحَبَّ إِلَيْكُم مِّنَ اللَّهِ وَرَسُولِهِ وَجِهَادٍ فِي سَبِيلِهِ فَتَرَبَّصُوا حَتَّىٰ يَأْتِيَ اللَّهُ بِأَمْرِهِ ۗ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ
التوبة ( 24 )
« አባቶቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም ፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም ፣ የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም ፣ መክሰሩዋን የምትፈሩዋት ንግድም ፣ የምትወዷቸው መኖሪያዎችም እናንተ ዘንድ ከአላህና ከመልክተኛው በርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደኾኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ » በላቸው ፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም ፡፡
በዚህ አንቀፅ አላህ እሱንና መልእክተኛውን መውደድ ከምንም በላይ መሆን እንዳለበት ይህም ግዴታ እንደሆነ በጣም ቅርብ የሆኑ አባት ፣ ልጅ ፣ ሚስት ፣ አጠቃላይ ዘመድ ፣ ሀብት ፣ ንግድ መኖሪያ የመሳሰሉትን ከሱና ከመልእክተኛው አስበልጦ መውደድ መጨረሻው ለቅጣት የሚዳርግ መሆኑን በመግለፅ ሰርቶ የተገኘ አመፀኛ ( ከሀዲ) መሆኑን በመንገር አረጋገጠልን ።
ግዴታ ያልሆነን ነገር መተው እንደማያስቀጣና ከዛም በላይ ከእስልምና እንደማያስወጣ የታወቀ ነው ። አንቀፁ እነዚህን ነገሮች መውደድ ከአላህና ከመልእክተኛው ትእዛዝ ወደኋላ ያስቀረውን ነው የሚመለከተው ።
ነብዩን መውደድ ግዴታ ለመሆኑ ከሳቸው ሐዲሶች ውስጥ አንዱን ልጥቀስ : –
عن أنس أن رسول الله – صلى الله عليه وسلم – قال :
“ لا يُؤْمِنُ أَحَدُكُمْ حَتَّى أَكُونَ أَحَبَّ إِلَيْهِ مِنْ وَالِدِهِ وَوَلَدِهِ وَالنَّاسِ أَجْمَعِينَ”
رواه البخاري ومسل
አነስ ባወሩት ሐዲስ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል ይላል : –
" ከናንተ ውስጥ አንዳችሁ ከልጁ ከወላጁና ከሰው ሁሉ በላይ እሱ ዘንድ ተወዳጅ ካልሆንኩ አላመነም " ።
ሐዲሱ እሳቸውን መውደድ ዋጂብ መሆኑን የሚያሳየው ዋጂብ ባልሆነ ነገር አላመነም ስለማይባል ነው ።
ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ነብዩን መውደድ ዋጂብ መሆኑ የኢስላም ሊቃውንቶች በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል ።
ነብዩን መውደድ ዋጂብ ከሆነ ውዴታቸውን እንዴት ነው የምንገልፀው የሚለውን አላህ ካለ በሚቀጥለው ክፍል እናያለን ።
https://t.me/bahruteka