"የቅድመ ክፍያ (Pre-Paid) ቆጣሪዎች ቅያሪ አደርጋለሁ" - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በያዝነው አመት ከጥር ወር ጀምሮ አውቶሜትድ የሆኑ የቅድመ ክፍያ (Pre-Paid) ቆጣሪዎች ቅያሪ እንደሚያደርግ ገልጿል።
አዲሶቹ ቆጣሪዎች ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ሲውሉ የነበሩ በካርድ የሚሰሩ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን የሚያስቀር ነው ተብሏል።
በዚህም ደንበኞች በስልካቸው በኦላይን በሚፈጽሙት (በቴሌብር ወይም በሞባይል ባንኪንግ) የኤሌክትሪክ ግዢ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እንደሆነ ነው የተገለጸው።
ቆጣሪዎቹን የመቀየር ፕሮጀክት የሚካሄደው ዝቅተኛ የሃይል ተጠቃሚ በሆኑ እና ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ የሲንግል ፌዝ(Single Phase) ቆጣሪዎች ላይ እና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት ላይ በሚውሉ የስሪ ፌዝ (Three Phase) ቆጣሪዎች ላይ መሆኑን
የፕሮጀክቱ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን አበበ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል። በሲንግል ፌዝ ቆጣሪዎች ቅየራ የመጀመሪያ ዙር ትግበራ 10ሺ በሁለተኛ ዙር ትግበራ 15 ሺ በአጠቃላይ 25 ሺ ቆጣሪዎች ላይ ቅያሪ ይከናወናል ተብሏል።
የሙከራ ትግበራው ባልደራስ አካባቢ በመቶ ቆጣሪዎች ላይ መሞከሩን የገለጹት አቶ ዘሪሁን ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ወደሙሉ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።
የሲንግል ፌዝ ቆጣሪ ቅያሪው በተመረጡ አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሏል።
በፕሮጀክቱ 125ሺ ለሚሆኑ የስሪ ፌዝ ቆጣሪዎች ቅያሪ የሚከናወን ሲሆን ይህም መሬት ላይ የሚገኙትን የስሪ ፌዝ ቆጣሪዎችን ሙሉ በሙሉ የሚተካ ይሆናል ብለውናል።
በፕሮጀክቱ 600ሺ ተጨማሪ ቆጣሪዎችን ወደ ሃገር ውስጥ ለማስገባት በእቅድ መያዙን ሃላፊው ተናግረዋል።
ከጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው የቆጣሪ ቅየራው የሚያስፈልጉ እቃዎችን ወደሃገር ውስጥ የማስገባት፣ አስፈላጊ የሆኑ የኔትወርክ እና የመገናኛ ገመዶችን የመዘርጋት እና ዳታ ቤዝ የመትከል ሥራዎች እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል።
አቶ ዘሪሁን የቆጣሪ ቅየራው የሚከናወነው ሙሉ በሙሉ በነጻ መሆኑን አጽንኦት የሰጡ ሲሆን በቅየራው ሂደት ላይ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰራተኞች ቢኖሩ ጥቆማ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ከሚያዚያ 2015 ዓም ጀምሮ በሁለት ዙር ተጀምሮ የነበረው ከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ወይም የሃይል ፍጆታቸው ከ 25 ኪሎ ዋት(KW) በላይ በሚጠቀሙ የማሕበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚገኙ ቆጣሪዎችን በዲጂታል ቆጣሪዎችን የመቀየር ሂደት መጠናቀቁን ተገልጿል።
በመጀመሪያው ዙር ትግበራ 5ሺ በሁለተኛው ዙር ትግበራ 39 ሺ ቆጣሪዎችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ዲጂታል ቆጣሪ የቅያሪ ሂደቱ በመጠናቀቁ ከአሁን በኋላ አዳዲስ ደንበኞች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት ብቻ ቅያሪ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።
ዲጂታል ቆጣሪው በየቤቱ በሰው አማካኝነት የሚከናወኑ ቆጠራዎችን የሚያስቀር ሲሆን በተጨማሪም ደንበኞች የሃይል ፍጆታቸውን ለማወቅ ያስችላቸዋል የተባለ ሲሆን ይህንን የሚያሳውቅ አፕሊኬሽን በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል።
ዲጂታል ቆጣሪው ሃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የሚጠቁሙ ጠቋሚዎች ያሉት ሲሆን አዲስ ደንበኞች ሲጠይቁ ለማቅረብ እንዲቻል ተጨማሪ 7 ሺ ዲጂታል ቆጣሪዎችን ለማስገባት በእቅድ መያዙን አቶ ዘሪሁን አበበ ተናግረዋል።
#TikvahEthiopiaFamilyAddisAbaba
@tikvahethmagazine