ገና እንዘምራለን
እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ?
የተዘጋ አንደበትን ለምስጋና ሊከፍት አይደለምን?
ከተፈወሱ ድውያን መካከል ዲዳዎች ይገኙበታል። ዲዳነት ምንድነው?
ደንቆሮነትስ?
እግዚአብሔርን ካለማመስገን በላይ ዲዳነት አለ?
ቃለ እግዚአብሔር ካለመስማት የበለጠ ደንቆሮነጽ የት ይገኛል?
ሊቃውንቱ “ህሙማነ ሥጋ በተአምራት፣ ህሙማነ ነፍስ በትምህርት ተፈውሰዋል” ያሉት ስለዚህ ነው።
ደዌ ሥጋንም ደዌ ነፍስንም ሊያድን መጥቷልና አንደበቱ ተፈቶለት ከሚናገር ዲዳ በላይ ነፍሱ የዝማሬን ቃል የተናገረችለት ክርስቲያን በክርስቶስ ፊት ታላቅ ተአምራት ተደርጎለታል።
“ኤፍታህ” የተባለች ነፍስ ማለት ይህች ናት ማር. 7፥34።
የአእላፋት ዝማሬን ስመለከት እግዚአብሔር የምስጋና ስጦታን ለዘመናችን ትውልድ እየሰጠ መሆኑን ተረድቻለሁ። እልፍ ኃጢአት ተሠርቶ በሚያድርበት ዘመን እልፍ ሆነን ለዝማሬ እንድንነሣ ያደረገንን አምላክ በልቤ አመሰገንሁት።
ክርስቶስን ማዕከል አድርገን ምስጋና በጀመርንበት ቀን ዛሬም ለምስጋና መሰብሰባችን ከሰይጣን በቀር ማንንም ያስደነግጣል ብየ አላስብም።
ብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አገልግሎታቸው የተወደደ መምህራን እና ዘማርያን ሁሉ ሲሳተፉበት ስላየሁ እኔን የተሰማኝ የደስታ ስሜት ሌሎችም ዘንድ መኖሩን አውቄአለሁ። ለነገሩ እንዳለመታደል ሆኖ መቃወም የሚወዱ ወይም ጥንቃቄና ጥርጣሬ ለተቀላቀለባቸው ካልሆነ በቀር የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙበትን መርሐግብር መቃወም በራሱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለሚያምን አንድ ክርስቲያን የሚቻል አይደለም።
ምናልባት ሌላ የተለየ ጉዳይ ካልገጠመ በስተቀር እንደ አእላፋት ዝማሬ ያለ ያልተሸፋፈነ፣ ከጀርባው ድብቅ አጀንዳ የሌለው፣ ለመተቸትም ሆነ ለማመስገን ለሚፈልግ ሰው ቅኔ ሆኖ ፍቱልኝ ተብሎ የማያስቸግር መርሐግብር ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ መገኘታቸው ብቻ የቤተ ክርስቲያን መሆኑ በቂ ማስረጃ ነው። ሌላ አንቀጽ ሳንጠቅስ የቅዱስነታቸውን መልዕክት ብቻ በመስማት ልንቀበለው የሚገባ ጉዳይ ነው።
የአእላፋት ዝማሬ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር እንድትዘረጋ የሚያደርግ መርሐግብር ነው። አንድም ሰው የጭንቀት ፊት አይታይበትም ነበር ሁሉም ደስ ብሏቸው የሚዘምሩ ምዕመናንን ብቻ ነው የተመለከትሁት። ማንም ምንም ነገር ከማሰብ ወጥቶ በዚያ ሰዓት እግዚአብሔርን ብቻ በማሰብ ውስጥ እንደሆነ ይሰማኛል።
ባለፈው ዓመት የነበረው መርሐግብር ላይ የመጀመሪያው መሥመር ላይ ተሰልፌ መዘመሬን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ዘንድሮ በቦታው ባልገኝም ተጀምሮ እስከሚያልቅ ደስ ብሎኝ እያለቀስሁ ነው የተመለከትሁት። ይሄንን ያህል ቁጥሩን እንኳን የማናውቀውን ሕዝብ በዚያ ሁሉ ሰዓት ደስታን የሚፈጥር መዝሙር ማቅረቡ የደስታ መንፈስን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በመቅደሳችን ውስጥ ያልተለየ መሆኑን ይመሰክርልናል።
የአእላፋት ዝማሬ በእውነት ለአእላፋት መዳን የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው። በሌሎች ጉባኤያት እና በዚህ ጊዜ የነበረውን የሥነ ምግባር መጠበቅ እስኪ ተመልከቱት? ነጭ ለብሰን መምጣታችን አንድ ነገር ሆኖ ወንዶቹ አስበውበት ነጠላ ለብሰው ለአገልግሎት ተዘጋጅተው መምጣታቸው በራሱ የሚያዘጋጀን ካገኘን ለማገልገል ዝግጁ ነን የሚል መልዕክት አስተላልፎልኛል።
አንዳንዴ እኮ የሴቶችን ነጠላ ቀምተው ከበሮ ለመምታት ወደ መድረክ የሚወጡ አገልጋዮችን አይተን እናውቃለን። የአእላፋት ዝማሬ ሰውን ወደ ልብሱ የመለሰ መርሐ ግብር ነው።
በጣም የገረመኝ የአእላፋት ዝማሬ ሁሉም መሣሪያውን ጥሎ ለዝማሬ ብቻ እንዲሰለፍ ያደረገ መሆኑ ነው። እረኛ ዋሽንቱን፣ ንጉሥ ዙፋኑን ጥሎ በዘመረበት ቀን ማን ለዝማሬ የማይጠቅም መሣሪያ ይዞ ይመጣል? ብለው መሰለኝ ሌላ ጊዜ ፕሮግራም ሊሠሩ የሚመጡ ሁሉ ከምስጋና በቀር ምንም የማይሠሩበት ቀን አድርገውት አይተናል።
መርሐ ግብሩን በመላው ዓለም ለማስተላለፍ ከተዘጋጁ ካሜራዎች በቀር ሌላ ማንም ካሜራውን አንጠልጥሎ የመጣ ሰው እኔ አላየሁም። በካሜራ ቀርጸው በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች ለዓለም የሚያዳርሱ የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች ሁሉ ከካሜራ ጋር መታገሉን ትተው በተመስጦ ሲዘምሩ አይተናቸዋል።
እግዚአብሔር ከዚህ ሌላ ከእኛ ምን ይፈልጋል?
አንድ ሆነን በፍቅር እንድንዘምር አይደለምን?
በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ስም የተሰየመው የጃንደረባው ትውልድ ሊመሰገን ይገባዋል።
በዓለም ፊት የሚያስደንቅ ውበታችንን የገለጠ ጩኸት ሳያበዛ፣ እዩልኝ ስሙልኝ ሳይል የሚያገለግሉ ወንዶችና ሴቶችን ካህናትንና ዲያቆናትንም ያካተተ ኅብረት ነው። በዘመኔ ምድር በምስጋና ስትሞላ በማየቴ ደስ ብሎኛል። ለዚያውም የዕርጋታ መንፈስ በተሞላበት መንፈስ የሚዘምሩ መዘምራንን ማየት እጅግ በዘመኔ ትውልድ እንድመካበት አድርጎኛል።
በስም ብጠራ ብዙ ናችሁ በዚያውም ላይ እኔ ያየሁት ካሜራው ያመጣልኝን ነው እንጅ ከካሜራ ዐይን ያልገባችሁ አገር የሚያውቃችሁ መምህራንና ዘማርያን በእውነት ታኮራላችሁ።
ከመድረክ በታች ሆኖ ማገልገል ምን ያክል ፈታኝ እንደሆነ ነጭ መጋረጃ ከጀርባችን፣ ወርቀ ዘቦ ግምጃ ከወንበራችን የማይለየን ሰዎች እናውቀዋለን።
ታላላቆቼ! ክርስትና እንዲህ አንድ ሆነን የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት ሕይወት ነውና ከሰበካችሁበት ቀን ይልቅ ዛሬ ብዙ አስተምራችሁኛል። በተለይ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ብርሄ ያንተስ ይለያል ባለፈውም ዓመትም ዘንድሮም ሳይህ የምስጋና ተመስጦህ ተለይቶብኛል። ካወቅሁህ ጊዜ ጀምሮ እንዲሁ ሳልወድህ የቀረሁበት ቀን አልነበረም ዛሬ ደግሞ ለመውደዴ ምክንያት የሚሆን ነገር ጨመርህልኝ።
የቤተ ልሔምን እረኞች ለምስጋና የጠራቸውን መልአክ አስታውሱት ሉቃ. 2፥9 ዲያቆን ሄኖክ ማለት ያ መልአክ ነው። ሄኖኬ አንተን ለመንቀፍ ነው የምንቸገር እንጅ ለማመስገን ብዙ ምክንያት አለን። እኔ በበኩሌ ዝም የምለው ባመሰገንሁህ ቁጥር ፈታኝ እየጋበዝሁብህ ወይም ለሰይጣን ጥቆማ እየሰጠሁብህ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ነው። “ቤተ ክርስቲያንን አንተውም ከቶ፤ የሰጠንን አምላክ በደሙ መሥርቶ” ብለህ ግጥምና ዜማ ሠርተህ የለ? በል ይሄንን ቃልህን እንዳትረሳ የሚቀጥለው ዓመት ናፍቆኛል።
ከአእላፋት ወደ ትእልፊት እየተሸጋገርን ገና እንዘምራለን።
በአንድ ከተማ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ይሄ መርሐ ግብር ተጀምሮልን ገና እንዘምራለን።
ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like, Subscribe እና Share ያድርጉ :-
ዩቱብ
https://www.youtube.com/@12Samualቴሌግራም
https://t.me/tsidqስምዐኮነ መልአከ
29/04/2017