✞ ጥምቀተ ክርስቶስ ✞ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ጥር ፲ ቀን፳፻፱
ክፍል አምስት (፭)እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሚዜዎችን 'ኵሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ፤ ያዘዛችሁን ዂሉ አድርጉ፤' ማለቷ
"አንቺ ሴት ከአንቺጋር ምን አለኝ? የሚለው የጌታችን መልስ እሺታን (ይኹንታን) የሚገልጽ ቃል መኾኑን ያስረዳል፡፡
ጌታችንም
"ውኃ ቅዱና ጋኖችን ምሏቸው"ባላቸው ጊዜ በታዘዙት መሠረት ውኃውን ቀድተው ጋኖችን ሞሏቸው፡፡ ውኃውንም ክብር ይግባውና በአምላካዊ ችሎታው ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው፤ ለአሳዳሪውም ሰጠው፡፡
አሳዳሪው የወይን ጠጅ የኾነውን ውኀ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፡፡ ድንቅ በኾነ አምላካዊ ሥራ እንደ ተለወጠም አልተረዳም፡፡ ያን ምሥጢር የሚያውቀው ባለ ሰርጉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ውኀውን የቀዱ ሰዎች ናቸውና፡፡
ታዳሚዎችም
"ሰው ዂሉ የተሻለውን ወይን አስቀድሞ ያቀርባል፤በኋላም ተራውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፡፡ አንተስ መናኛውን ከፊት አስቀድመህ ያማረውን ከኋላ ታመጣለህን?"በማለት አደነቁ፡፡
ቀድሞም የአምላክ ሥራ እንደዚህ ነው፤ ብርሃን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሯል፤ ከጨለማ ቀጥሎ "ብርሃን ይኹን!" በማለት ብርሃንን ፈጥሯል፡፡ መጀመሪያ ብርሃን ተፈጥሮ ኋላ ጨለማ ቢፈጠር ይከብድ ነበርና መጀመሪያ ፳፩ ፍጥረታት ፈጥሯል፡፡
በመጨረሻም በአርአያውና በአምሳሉ የሰው ልጅን ፈጥሯል፡፡ ናትናኤልንም፤- "ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ" ብሎታል፡፡ ይህንን ማለቱም የእግዚብሔር ሥራ እየቆየ ውብ፣ ያማረ መኾኑን ያመለክታል፤ ሰው ግን 'የወደዱትን ቢያጡ ያጡትን ይቀላውጡ' እንዲሉ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር ያስቀድማል፤ ያ ሲያልቅበት ደግሞ የናቀውን መፈለግ ይጀምራል፡፡
ተራውን ከፊት፣ ታላቁን ከኋላ ማድረግ የእግዚአብሔር ልማዱ ነው፡፡ ለሰው ልጅ በመጀመሪያ የተሰጠው የሚያልፈው ዓለም ነው፤ በኋላም የማያልፈው መንግሥተ ሰማያት ይሰጠዋል፡፡
ሰው መጀመሪያ ይሞታል፤ በመጨረሻ ትንሣኤ አለው፡፡ ሰው መጀመሪያ ሲወለድ ርቃኑን ነው፤ በኋላ የጸጋ ልብስ ይለብሳል፤ ሀብታም ይኾናል፡፡
ሰው ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለምን የሚያገኛት፣ የሚተዋወቃት በልቅሶ ነው፤ በኋላ ግን ይደሰታል፡፡ ተመልሶ በኀሣር፣ በልቅሶ ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡ በደስታ "መቃብር ክፈቱልኝ? መግነዝ ፍቱልኝ?" ሳይል ይነሣል፡፡ ይህን የአምላክ ሥራም አድንቆ መቀበል እንጂ መቃወም አይችልም፡፡
፪.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም"ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ የጌታ እናት ከዚያ ነበረች፤" እንዲል፡፡ የተገኘችውም እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ በደግ ሰው ልማድ ተጠርታ እንጂ፡፡
ይህም እመቤታችን በማኅበራዊ ሕይወት የነበራትን ተሳትፎ እና በሰዎች ዘንድ የነበራትን ክብር ያመለክታል፡፡
በሌላ መልኩ በቤተ ዘመድ ልማድ ማንኛውም ዘመድ እንደ ተጠራው ዂሉ እርሷም በገሊላ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ታላቅና ቤተ ዘመድ በመኾኗ በዚህ ሰርግ ተጠርታ ነበር፡፡ የተገኘችበት ሰው ሰውኛው ምክንያት ይህ ቢኾንም በዚያ ሰርግ ቤት ማንም ሊሠራው የማይችል የሥራ ድርሻ ነበራት፡፡
ይህ በሰዎች ዘንድ የማይታወቅ በእግዚአብሔርና በእርሷ መካከል ያለ አማላጅነት ነው፡፡ ይኸውም የጎደለውን መሙላት ለሚችል ውድ ልጇ የጎደለውን እንዲሞላ ማማለድ ነው፡፡
እመቤታችን ከሰው ልጆች የተለየች ክብርት፣ ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ልዩ በመኾኗ የምታውቀው ምሥጢርም ከሰው የተለየ ነው፡፡
"ወእሙሰ ተዐቀብ ዘንተ ኩሎ ነገረ ወትወድዮ ውስተ ልባ፤ ማርያም ግን ይህንንዂሉ ትጠብቀው፣ በልቧም ታኖረው ነበር፤"ሉቃ.፪፥፲፱
የሚለው ቃልም ድንግል ማርያም አምላክን በመውለዷ ከሰው ልጆች የራቀ ምሥጢር እንደ ተገለጠላት ያስረዳል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም
"ጸጋን የተሞላሽ"በማለት የገለጠው ለእርሷ የተሰጠው ባለሟልነት ልዩ መኾኑን ለማስረገጥ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ በሰርጉ ቤት የምትሠራውን ሥራ በውል ታውቅ ነበር፡፡
፫. ቅዱሳን ሐዋርያትመምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው ተገቢ አይደለምና፤ ደቀ መዛሙርቱ ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር አብረው በሰርግ ቤት ተገኝተው ተአምራቱን ተመልክተዋል፤ በተደረገው ተአምርም አምላክቱን አምነዋል፡፡
ሐዋርያት ከዋለበት የሚውሉ፤ ከአደረበት የሚያድሩ፤ ተአምራት የማይከፈልባቸው፤ ወንጌሉን ለማስተማር የተመረጡ ናቸውና፡፡ ምክንያቱም አየን ብለው እንጂ ሰማን ብለው ቢያስተምሩ
አይታመኑምና፡፡
የሐዋርያት በሰርጉ ቤት መገኘትም ካህናት በተገኙበት ዕለት ሥርዓተ ጋብቻን መፈጸም ተገቢ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡
በሰርግ ቤት የካህናት መገኘት እና ቡራኬ መስጠት አስፈላጊ ነውና፡፡ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ የተገለጸውም ይህ ትምህርት ነው፤
"ወማዕሰረ ተዋሰቦሶ ኢይትፌጸም ወኢይከውን ዘእንበለ በሀልዎተ ካህናት ወጸሎት ዘላዕሌሆሙ፤ የጋብቻ አንድነት ካህናት ቢኖሩ እንጂ ያለእነርሱ አይጸናም፡፡ እነርሱ ጸሎት ሲያደርጉ እንጂ ያለ ጸሎት አይፈጸምም፤"እንዲል፡፡
በጥንተ ፍጥረት "ሰው ብቻውን ይኾን ዘንድ መልካም አይደለም ረዳት እንፍጠርለት፤"ዘፍ.፪፥፲፱
በማለት የተናገረ አምላክ ጋብቻ በካህናት ቡራኬና ጸሎት መከናወን እንደሚገባው ሲያስተምረን በቃና ዘገሊላው ሰርግ ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ተገኝቷል፡፡
በአጠቃላይ የቃና ዘገሊላ ሰርግ እና በሰርጉ ላይ የታዩ ተአምራት ምልጃዎች ዂሉ ሌላ ምሥጢርንም ያዘሉ ናቸው፡፡ እመቤታችን "የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም" በማለት መናገሯ ሕዝብህን (ምእመናንን) "ደምህን አፍሰህ፣ ሥጋህን ቈርሰህ አድናቸው" ማለቷ ሲኾን፣ ይህም "ወይን" በተባለው የልጇ የክርስቶስ ደም ቤዛነት ዓለም ይድን ዘንድ እመቤታችን ያላትን የልብ መሻት ያስገነዝባል፡፡
"ጊዜዬ ገና አልደረሰም" የሚለው የጌታ ምላሽም ደሙ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ የሚፈስበት ጊዜ ገና መኾኑን ያመላክታል፡፡ በሰርግ ቤት የተገኘው በሥጋው መከራ ከመቀበሉ አስቀድሞ ነውና፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡
ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡አሜን!!!
ለአባታችን ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ቃለሕይወት ያሰማልን አሜን!!!
ተፈጸመ
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈ @yemezmur_gexem
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈