ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal


Гео и язык канала: Эфиопия, Амхарский
Категория: Новости и СМИ


The best fiction is far more true than any journalism
📢 ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ፤ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ በሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ
👉 በፌስቡክ ገፆቻችን https://www.facebook.com/simon.dereje.56
👉 https://www.facebook.com/mik0Man

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
Эфиопия, Амхарский
Категория
Новости и СМИ
Статистика
Фильтр публикаций


የሱዳን ጋዜጠኞች የፕሬስ ነፃነትን ለማፈን እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ተቃወሙ

በፖርት ሱዳን የሚገኙ ሱዳናውያን ጋዜጠኞች የሳዑዲ አረቢያ ንብረት የሆነው የአልሻርክ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሱዳን መንግስት መታገዱን ተከትሎ በፕሬስ ነፃነት ላይ እየደረሰ ያለውን አፈናና የመረጃ ተደራሽነት እያሽቆለቆለ ነው ሲሉ ተችተዋል።

የአል ሻርክ የሱዳን ቢሮ ኃላፊ ካሊድ ኦዋይስ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው የፕሬስ ነፃነት ሲምፖዚየም ላይ እንደተናገሩት ለባለሥልጣናቱ ጥያቄ ቢያቀርብም ለጣቢያው መደበኛ የመዘጋት ምክንያት እንዳልተነገረና የመዝጋት ውሳኔው ብቻ ለጣቢያው ኃላፊዎች በስልክ ብቻ እንደተነገራቸው ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ባለስልጣናት የካቲት 20 ላይ የአል-ሻርክን ተግባራት በማገድ ስርጭች እንዲያቆም አድርገዋል። እገዳው ቴሌቭዥኝ ጣቢያው በካርቱም ውስጥ ስላለው የሰራዊት ግስጋሴ የአርኤስኤፍ አስተያየትን ያካተተ ዘገባ ካሰራጨ በኋላ ነው። የውጪ የዜና ማሰራጫዎች በግጭት ውስጥ ተደጋጋሚ ችግሮች ገጥሟቸዋል። ከነዚህም መካከል በኤፕሪል 2024 አል-አራቢያን እና አል-ሃዳትን የተሰኙ ጣቢያዎች ከፍቃድ እድሳት ጋር በተገናኘ ታግደው ነበር።

የሱዳኑ የጋዜጠኞች ቡድን ሲኒዲኬትስ ኃላፊ አብደል ሞኒም አቡ ኢድሪስ፣ ይፋዊ መረጃ አለማግኘት እና ተደራሽነት ላይ ገደብ በመኖሩ አሉባልታ እና የተሳሳቱ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በህግ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የፕሬስ እና የባለስልጣናት ግንኙነት እንዲኖርም ጠይቀዋል።

የአል-አራቢያ የሱዳን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሊና ያዕቆብ አል ሻርክን የማገድ ውሳኔ ሕጋዊ መሠረት የለውም ብለዋል።  የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ በሱዳን እና በሌሎች ሀገራት መካከል ተገቢ ያልሆነ ንፅፅር ማድረጋቸውንም ኃላፊዎቹን ነቅፈዋል። በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት ጋዜጠኞች ባለሥልጣናቱ "የብሔራዊ ደህንነት" ጽንሰ-ሐሳብ ያለ ግልጽ ትርጉም እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።  “ብሔራዊ ደኅንነት” በሚለው ላይ ትክክለኛ ትርጉም እና ስምምነት እንዲደረግ እናም ፕሬስ ለዚህ መስፈርት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




ሩሲያ ባለፈው ሳምንት ግዙፍ የሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳኤል ጥቃቶች ፈፅማብኛለች ስትል ዩክሬን አስታወቀች

ዩክሬን ሩሲያ በአንድ ጀምበር 119 አጥቂ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በበርካታ ክልሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፅማብኛለት በማለት ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ መሳሪያዎችን በመጠቀም በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን ሞስኮ መሰንዘሯን ተናግራለች። የዩክሬን አየር ሃይል እንደዘገበው 73 የሻሄድ አይነት ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሌሎች ዩኤቪዎች በተለያዩ ክልሎች ጥቃት እንዳያዱርሱ ተመትተው ሲጣሉ 37 የጠላት አታላይ አውሮፕላኖች ከክትትል ራዳር ጠፍተዋል ነገርግን ምንም አይነት ጉዳት አላደረሱም ብሏል።

ጥቃቶች በዶኔትስክ፣ ካርኪቭ፣ ፖልታቫ፣ ቼርካሲ፣ ሱሚ እና ዛፖሪዝሂያ አካባቢዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ባለፈው ሳምንት ሩሲያ “1,200 የሚጠጉ የአየር ላይ ቦምቦችን፣ 870 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና ከ80 የሚበልጡ ሚሳኤሎችን” በመጠቀም በዩክሬን ላይ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን” ባለፈው ሳምንት ውስጥ ብቻ እንደከፈተች ተናግረዋል። “እያንዳንዱ ሻሄድ ሰው አልባ አውሮፕላን እና ሩሲያ የምትጠቀመው እያንዳንዱ የአየር ላይ ቦምብ ማዕቀብን በመጣስ የተፈፀሙ ጥቃቶች ናቸዋ። ይህ መሳሪያ ከ 82,000 በላይ የውጭ አገር ሰራሽ ክፍሎችን ይዟል ሲል ዘሌንስኪ በቴሌግራም ጽፏል።

ዩክሬን ከአጋሮቿ ጋር በየቀኑ ተጨማሪ የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ፣በአገር ውስጥ መከላከያ ምርት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እና በሩሲያ ላይ ጠንካራ ማዕቀቦች እንዲጤል እየሰራች መሆኑን አፅንዖት ሰጥታለች። "ፍትሃዊ ሰላም ለማምጣት እና አስተማማኝ የደህንነት ዋስትናዎችን ለማረጋገጥ ስራችንን እንቀጥላለን" ብለዋል። ዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮች ወደ ሩሲያ በሚላኩ የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ ገደቦችን እንዲያጠናክሩ ደጋግማ በመጠየቅ፣ ማዕቀቡ ቢጣልባትም ከውጭ የተሰሩ ወሳኝ የጦር መሳሪያ አካላትን ሩሲያ ማግኘቷን ቀጥላለች ስትል ኬየቭ አስታውቃለች።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




ዘለንስኪ ለህጻን ልጅ ከረሜላ እንደሚገዛው ከአሜሪካ ገንዘብ ወስዷል ሲሉ ትራምፕ ተናገሩ

ባለፈው ወር በተደረገው የጦፈ የዋይት ሀውስ ሞላላው ፅህፈት ቤት ስብሰባ በኃላ ትችታቸውን የቀጠሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ስር ከአሜሪካ የእርዳታ ገንዘብ ወስዷል ሲሉ ከሰዋል። ትራምፕ እሁድ እለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ከዚች ሀገር፣ በባይደን አስተዳደር ስር፣ ልክ ህፃን ከረሜላ የሚወስደውን ያህን ገንዘብ ወሰዷል ይህ በጣም ቀላል ነበር" ብለዋል።

ትራምፕ አክለውም "ዜለንስኪ አመስጋኝ ነው ብዬ አላምንም። 350 ቢሊየን ሰጠነው እርሱ ግን ስለተዋጋ እና ጀግንነት እንዳላቸው እየተናገረ ነው።" ብለዋል።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሀገራቸው ጄቭሊን የተባለውን ፀረ-ታንክ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን የሰጣቸው ዋሽንግተን መሆኗን ደጋግመው ገልጸዋል። ሲጀመር በ2022 የዩክሬን ጦርነት ፕሬዚዳንት ቢሆኑ ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር ሲሉ አክለዋል። ትራምፕ አክለው ከአውሮጳ የበለጠ ለዩክሬን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ ያቀረቡት የእርዳታ አሃዝ ትክክል እንዳልሆነ እና አውሮፓ በጋራ ለዩክሬን ከአሜሪካ የበለጠ ገንዘብ ለግሳለች ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን እና እስራኤልን በጦር ግንባር ላይ ላለባቸው ጦርነት በተመሳሳይ መልኩ እያስተናገደች እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ "ይህ በጣም የተለያዩ ቦታዎች ናቸው፤ በጣም በጣም የተለያየ የስልጣን እርከን ላይ ናቸው" ብለዋል። ባለፈው ወር ትራምፕ ዘለንስኪን በዩክሬን ያለውን ጦርነት ማራዘሙን እና ለአሜሪካ ዕርዳታ ምስጋና እንደሌላቸው ሲወነጅሉ የትራምፕ እና የዜለንስኪ ውጥረት ተባብሷል።

ሞቅ ባለ የኦቫል ኦፊስ ስብሰባ ላይ ትራምፕ ዘሌንስኪን በመተቸት እና በኋላም ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ በሙሉ በማገድ ኪየቭ ከሩሲያ ጋር እንድትደራደር ግፊት አድርገዋል። ርምጃው ከአውሮፓውያን አጋሮች ተቃውሞ የቀሰቀሰ ሲሆን ሩሲያ ውሳኔውን በመቀበል የአሜሪካ እና የዩክሬን ግንኙነት የበለጠ እንዲሻክር አድርጓል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




በቤተ ሙከራ የሚዘጋጅ ስጋና ወተት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእንግሊዝ እንደሚሸጥ ተነገረ

በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚመረት ሥጋ፣ወተት እና ስኳር ከተጠበቀው ጊዜ ቀድመው በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ ውስጥ ለሰው ልጅ ፍጆታ ሊሸጥ ይችላል ተባለ።

የምግብ ደረጃዎች ኤጀንሲ (FSA) በላብራቶሪ የሚበቅሉ ምግቦችን የማጽደቅ ሂደቱን እንዴት እንደሚያፋጥን እየተመለከተ ይገኛል ተብሏል። እንደነዚህ ያሉ ምርቶች በትናንሽ ኬሚካላዊ ተክሎች ውስጥ ከሚገኙ ሴሎች ውስጥ ይበቅላሉ። የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያዎች በሳይንስ መስክ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነዋል ነገር ግን አሁን ባለው ደንቦች መስራት ከሚችሉት በላይ እንዳይሰሩ እንደተያዙ ይሰማቸዋል ።

ከስጋ የተሰራ የውሻ ምግብ ባለፈው ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ባለፈው ወር ለገበያ ቀርቧል።እ.ኤ.አ. በ 2020 ሲንጋፖር በላብራቶሪ ውስጥ የሚመረተውን ስጋ ለሰው ልጅ ፍጆታ ለመሸጥ ፍቃድ የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር ስትሆን አሜሪካ ከሶስት አመት በኋላ እና እስራኤል ባለፈው አመት ይህንኑ ውሳኔ አሳልፈዋል። ሆኖም ጣሊያን እና የአሜሪካ ግዛቶች አላባማ እና ፍሎሪዳ እገዳ ጥለዋል።

ከፍተኛ የቴክኖሎጂ የምግብ ድርጅቶች ባለሙያዎች እና የአካዳሚክ ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር አዲስ ደንቦችን ማዘጋጀት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። የሁለት የላቦራቶሪ ምግቦችን ሙሉ የደህንነት ግምገማ ለማጠናቀቅ ያለመ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ነገር ግን ተቺዎች አዲሶቹን ህጎች በማውጣት የተሳተፉ ኩባንያዎች መኖራቸው የጥቅም ግጭትን እንደሚያመለክት ይናገራሉ።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል


አዲስ አበባ ባለፋት ሰባት ወራት ፓርኮቿን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ ባለፋት ሰባት ወራት ፓርኮቿን ከጎበኙ የተለያዩ ቱሪስቶች ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቷን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ባለፋት ሰባት ወራት 598 ሺህ 821 ቱሪስቶች የአዲስ አበባን ዋና ዋና ፓርኮች ጎብኝተዋል።

በ2017 በጀት አመት ሰባት ወራት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር ገልፀው ከዚህ አኳያ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ተመዝግቧል።ባለፈዉ ዓመት ከተሰበሰበው በእጥፍ የሚበልጥ ገቢ ማግኘት ተችሏል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ጊዜ ውስጥ 64 ሚሊዮን 222 ሺህ 515 ብር ገቢ ተገኝቷል።በዚህም የእቅዱን 88 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉ አስረድተዋል።

የእንጦጦ ፓርክ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ጎብኚዎች በብዛት የሚጎበኝ እንደመሆኑ በርካታ ቁጥር ባላቸው ጎብኚዎች ከተጎበኙት ፓርኮች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ብሄረፅጌ፣ ፒኮክ፣ ኢትዮ ኩባ የመናፈሻ ስፍራዎች በበርካታ ቱሪስቶች ከተጎበኙት መካከል ይገኙበታል።ኮርፖሬሽኑ ከከተማ ልማት ቢሮ  ከዚህ ቀደም ከነበሩት ተጨማሪ 12 ፓርኮችን እንዲሁም በኮሪደር ልማት እየለሙ ያሉ 33 ቦታዎችን መረከቡን የገለፁት አቶ ዋለልኝ ይህም የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይም በኮሪደር አካባቢ የተሰሩት ፓርኮች ለመኖሪያ ቦታ ቅርብ በመሆናቸው እና በውስጣቸውም  የተለያዩ የአገልግሎትና የመዝናኛ ስፍራዎችን የያዙ በመሆናቸው ለጉብኝት ተመራጭ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በቀጣይ እነዚህ ፓርኮች የጎብኚዎችን ቁጥር ይበልጥ በመሳብ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዲቻል ከግሉ ሴክተር ጋር በመተባበር ይህን እውን ማድረግ የሚያስችሉ  ስራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል።

በቅድስት ደጀኔ
#ዳጉ_ጆርናል




በባለሀብቶች የታሪፍ ፍራቻ የተነሳ የነዳጅ ዋጋ እየቀነሰ ነው ተባለ

ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ በአለም ኢኮኖሚ እድገት እና በነዳጅ ፍላጎት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ፣ እንዲሁም ከኦፔክ የነዳጅ አምራች ሀገራት የነዳጅ ምርት እየጨመረ በመምጣቱ፣ ባለሃብቶች ላይ ስጋትን አሳድራል። ያልተጣራው ድፍድፍ ነዳጅ አርብ እለት 90 ሳንቲም በ6 ሳንቲም ቀንሶ ወደ 70.30 ዶላር ዝቅ ብሏል። የዩናይትድ ስቴትስ ዌስት ቴክሳስ ገበያ ድፍድፍ በ ነዳጅ በ66.96 ዶላር በበርሚል የተሸጠ ሲሆን በስምንት ሳንቲን ቀንሷል።

ለሰባተኛ ተከታታይ ሳምንት ነዳጅ ቀንሷል፣ ይህም ከህዳር 2023 ወዲህ ረጅሙ የኪሳራ ጉዞ ተደርጎ ተወስዷል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ግብር መጣላቸው እንዲሁን በዋና ዘይት አቅራቢዎቻቸው ላይ ካናዳ እና ሜክሲኮ የዘገየ ታሪፍ ከጣሉ በኋላ ድፍድፍ ነዳጅ ለሶስተኛ ተከታታይ ሳምንት ቀንሷል። ቻይና በአሜሪካ እና ካናዳ የግብርና ምርቶች ላይ የአፀፋ ታሪፍ መጣሏ ይታወሳል።

ትራምፕ ሞስኮ ከዩክሬን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻለች ዩናይትድ ስቴትስ በሩስያ ላይ የምትጥለውን ማዕቀብ እንደምትጨምር ከተናገረች በኋላ አርብ እለት የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል። ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም ከተስማማች ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያ የኃይል ማመንጫ ዘርፍ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማርገብ የሚያስችል መንገድ እያጠናች ነው ሲሉ ጉዳዩን የሚያውቁ ሁለት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦፔክ ፕላስ በመባል የሚታወቀው ሩሲያን ጨምሮ የነዳጅ ላኪ ሀገራት ድርጅት እና አጋሮቹ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በዘይት ምርት ጭማሪ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ እንዳሉት ኦፔክ ፕላስ የገበያ ሚዛን በሚኖርበት ጊዜ ውሳኔውን ሊቀይር ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል




"ክህሎት ስለ ኢትዮጵያ " የተሰኘ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ክህሎት ስለኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ እና ፓናል ውይይት በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተከፍቷል።

የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ በአዲስ አበባ የተከፈተ ሲሆን በዚህም ጥንታዊ የክህሎት አጀማመር መሠረቶች፣ በሰመር ካምፕ እና በስታርት አፕ የተሰሩ ሥራዎች፣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ተማሪዎች የተሰሩ ማሽኖች እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ የተገኙ ውጤቶች ለእይታ ቀርበዋል።

በመክፈቻው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ፣ አቶ ዳንኤል ተሬሳ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፀዳለ ተክሉ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) በምዕራፍ አንድ ስለኢትዮጵያ መድረኩ በ14 የተለያዩ ከተሞች በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ምክክር ማካሄዱ ይታወሳል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በቡታጅራና በሐረር ተካሄዷል። ይህ በአዲስ አበባ የሚካሄደው መድረክ የሁለተኛው ምዕራፍ ሶስተኛ ዙር ነው። በድምሩ "ስለኢትዮጵያ" የተሰኘው መድረክ የዛሬውን ጨምሮ ለ17ተኛ ጊዜ ተካሄዷል።

የኢፕድ ስለኢትዮጵያ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት የሁለተኛ ምዕራፍ የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩና የፓናል ውይይቱ በቀጣይም በተለያዩ ከተሞች  እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

#ዳጉ_ጆርናል


የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ 20 በመቶ ቀረጥ ቢቀንስም በሱቆች ላይ እየተሸጠ ያለበት ዋጋ እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ

በኢትዮጵያአሁንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ታዳጊ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ፓድ በማጣት ከትምህርት  ገበታቸው ለመቅረት እና ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡

በገጠርም በከተማም ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ሴቶች ከትምህርት ከመቅረት ጀምሮ እስከ ስነልቦና ጫና ድረስ  እንደሚደርስባቸው ተገልጿል ።  ኤ ኤች ኤፍ ኢትዮጵያ  የንጽህና መጠበቂያ  መግዛት ለማይችሉ እንዲሁም በትምህርት ቤት በድንገት የወር አበባ ለሚመጣባቸው ተማሪዎች ነጻ የንጽህና መጠበቂያ ፓድ አቅርቦት እያደረገ እንደሚገኝ የኤ ኤች ኤፍ ኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ  መከላከል እና ምርመራ አገልግሎት  አድቮኬሲ ፕሮግራም  ማናጀር  አቶ ቶሎሳ ኦላና  ለብስራት ሬዲዮ  እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ካለፈው አራት እና አምስት ዓመት ጀምሮ መንግስት በንጽህና መጠበቂያ ፓድ ላይ የቀረጥ  ቅነሳ  ማድረጉ አንስተዋል። ይሁን እና ግን  የቀረጥ ቅነሳውን በተመለከተ ብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የንጽህና መጠበቂያ ፓድ  ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመረ እንጂ መሻሻል እያሳየ አለመሆኑ ምክንያቱ ምንድነው በማለት ላነሳው ጥያቄ በአከፋፋዩ እና በነጋዴው መካካል አለመግባበት መኖሩን  እና የታክስ ቅነሳ ሲደረግ ከታች ሆነው  ክትትል የሚያደርጉ  አካላት ሊኖሩ እንደሚገባ ገልጸው ይህ ባለመሆኑ የዋጋ መሻሻል እየታየ አለመሆኑ አንስተዋል።

ታክስ ቅነሳውን በተመለከተ አምራቹ ያለበትን ችግር እየፈታ የሚሄድበት  አግባብ  በሚፈለገው ልክ አለመኖሩ ተጠቁሟል። በመሆኑም ታክሱ በተቀነሰው ልክ ምርቱ በተጠቃሚዎች ዘንድ በአነስተኛ ዋጋ እየቀረበ አለመሆኑ ተነግሯል።  በፊት ላይ 30 በመቶ ቀረጥ ይከፈልበት የነበረው የንጽህና መጠበቂያ ፓድ አሁን  ላይ ወደ አስር በመቶ የቀነሰ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን እንዲሁም ደግሞ ለተጠቃሚው የሚሸጥበት ዋጋው ከሚገባበት የቀረጥ ዋጋ አንጻር  አግባብነት የሌለው መሆኑን አቶ ቶሎሳ ኦላና  ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል




ፈረንሳይ ሁለት ቁልፍ መገልገያዎችን በማስረከብ ከሴኔጋል ወታደራዊ ኃይሏን ማስዉጣት ጀመረች

ፈረንሳይ ከሴኔጋል ወታደራዊ ኃይሏን አርብ ዕለት ማስለቀቅ የጀመረች ሲሆን ሁለቱን ቁልፍ መገልገያዎችን ለምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር በማስረከብ በቀጣናዊ ስትራቴጂዋ ላይ ሰፊ ለውጥ አድርጋለች። በሴኔጋል የሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ በሰጠው መግለጫ አርብ ማርች 7 ቀን 2025 የፈረንሣይ ወገን በማርቻል እና ሴንት-ኤክሱፔሪ ወረዳ ውስጥ ያሉትን መገልገያዎች እና መኖሪያ ቤቶች ለሴኔጋል ወገን አስረክቧል ብሏል።

"በሀን ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙት እነዚህ ወረዳዎች ከ2024 ክረምት ጀምሮ ወደ ሴኔጋል ለመመለስ ዝግጁ ነበሩ።" ይህ እርምጃ ላይ የተደረሰው የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ የውጭ ኃይሎችን ከአገሪቱ ለማስወጣት ያደረጉትን ግፊት ተከትሎ በምዕራብ አፍሪካ ፈረንሳይ መገኘቱን የሚቃወሙ ሰፊ ዘመቻ መከፈተን ያሳያል። የፈረንሳይ በአካባቢው ያለው ተጽእኖ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጥቷል።

በአካባቢው ሀገራት እየጨመረ በመጣው ተቃውሞ የተነሳ ፈረንሳይ ጦሯን ከቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር እና ቻድን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል። የፈረንሳይን መውጣት ተከትሎ ባለፈው ወር የጋራ ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን የፈረንሳይ ጦር በቅርቡ በዳካር የሚገኙ 162 የሴኔጋል ሰራተኞችን አሰናብቷል። የፈረንሳይ ኤምባሲ ግን በሴኔጋል ምን ያህል ወታደሮቹ እንደቀሩ አልገለጸም።

ፈረንሳይ የአፍሪካ ወታደራዊ አሻራዋን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ማቀዷን ያስታወቀች ሲሆን፥ ጅቡቲ በአህጉሪቱ ብቸኛ የፈረንሳይ ቋሚ መቀመጫ ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ፓሪስ እንደገለጸችው የመከላከያ ስልጠና ወይም ወታደራዊ ድጋፍን ከዚህ በኃላ በሀገራት ጥያቄ መሰረት ብቻ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፋለች።

በስምኦን ደረጄ
#ዳጉ_ጆርናል


የአፋርና ሶማሊ ክልል ርዕስ መስተዳድሮች በተገኙበት በጅግጅጋ የኢፍጣር መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው

ዛሬ ምሽቱን የአፋር እና ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦች ታላቅ የጋራ የኢፍጣር መርሐ ግብር በጅግጅጋ እያካሄዱ ነው።

ሁለቱ ክልሎች በተደጋጋሚ በቦታ ይገባኛል ከንትርክ አልፈዉ የሰዉ ህይወት የቀጠፈ ግጭት ዉስጥ ገብተዉ ነበር። ዛሬ ጾሙን በማስመልከት በርዕሰ መስተዳደሮቻቸዉ የተመራ የኢፍጣር ስነስርዓት አካሂደዋል።

#ዳጉ_ጆርናል


የእናቶች ወግ ስለልጆች አስተዳደግና አመጋገብ የፌስቡክ ግሩፕ ለመቄዶንያ ከ325 ሺህ ብር በላይ ብር ድጋፍ አደረጉ

የእናቶች ወግ ስለልጆች አስተዳደግና አመጋገብ የፌስቡክ ግሩፕ ከግሩፑ ቤተሰቦች በማሰባሰብ 325,300 ብር ድጋፍ አድርገዋል።

#ዳጉ_ጆርናል


በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት አልፏል  

በኦሮሚያ ክልል ከየካቲት 24  እስከ የካቲት 30  ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናቶች በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ15  ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ፣ በ14 ሰዎች ላይ ከባድ እና በ12 ሰዎች ላይ ቀላል አካል ጉዳት ደርሷል፡፡

በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን ከ150 ሺ ብር በላይ የሚገመት ሲሆን የሞት አደጋዎቹ በተለያዩ  ዞኖች እና  ከተሞች የተከሰቱ ናቸው።በአንድ ሳምንት ውስጥ በደረሰው አደጋ ከ16 እስከ 55 ዓመት  የእድሜ ክልል ላይ  የሚገኙ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የኦሮሚያ ክልል የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል ባለሙያ የሆኑት ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራትሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ  አደጋዎቹ የተከሰቱት በቀኑ  ክፍለ ጊዜ ሲሆን  አደጋውን ያደረሱት ወንድ  አሽከርካሪዎች ናቸው። የሞት አደጋዎች የደረሱት በጭነት፣ በህዝብ ማመላለሻ ፣በባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) እና በሞተር ሳይክል የተከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአደጋዎቹ መንስኤዎቹ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እና ለእግረኛ ቅድሚያ  አለመስጠት፣ የቴክኒክ ችግር ፣ለተሽከርካሪ ቅድሚያ አለመስጠት እና ርቀትን ጠብቆ አለማሽከርከር   መሆኑን  ኢንስፔክተር መሰለ አበራ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል::

በሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል


በሰሜን ዳርፉር በተፈፀመ የድሮን ጥቃት ሁለት ሰዎች ተገደሉ

በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (አርኤስኤፍ) ተከፈተ የተባለው የአውሮፕላን ጥቃት እሁድ እለት በሰሜን ዳርፉር ግዛት አል-ማሊሃ አካባቢ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ሁለት ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድል አራት ሰዎችን አቁስሏል። ከኤል ፋሸር በስተሰሜን 210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እና ሱዳን ከሊቢያ በሚያገናኘው ድንበር ላይ የምትገኘው አል-ማሊሃ ከሱዳን ጦር ጋር በመተባበር እየተዋጉ ባሉት የታጠቁ ቡድኖች የጋራ ሃይል ቁጥጥር ስር ነች።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከተማዋ ወደ ኤል ፋሸር ከተማ ለማምራት እንደመነሻ አድርጎ በማሰብ ከሰራዊቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ማጠናከሪያ እያገኘችም ነው።በሰሜን ዳርፉር የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂም ካቲር ለሱዳን ትሪቡን እንደተናገሩት “ፈጣን የድጋፍ ሰጪ ሃይሎች በአል-ማሊሃ ከተማ በፈፀሙት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 4 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ አረጋግጠዋል። ወታደራዊ ምንጮች እንደተናገሩት ከሆነ ደግሞ አንድ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ቡድን በአካባቢው ወታደራዊ ቦታዎችን ጨምሮ በርካታ ቦታዎች ላይ ኢላማ አድርጎ መቷል ብለዋል።

የፀረ-አውሮፕላን መከላከያ የተወሰኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጥለፍ እንዲወድቁ ያደረገ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ የጋራ ሃይሉ ያለባቸውን ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ጉዳት ሳያደርሱ በተሳካ ሁኔታ መውደቃቸውን ጠቁመዋል። ከሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ወደ ከተማዋ የሸሹ ተፈናቃዮች መኖርያን ጨምሮ በአንዳንድ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ እና የእሳት ቃጠሎ መፈጠሩን እነዚሁ ምንጮች ጠቁመዋል።

በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ በሆነችው በኤል ፋሸር፣ ጦር ሰራዊቱ እና የጋራ ኃይሉ ቀደም ሲል በከተማዋ ደቡባዊ እና ደቡብ-ምስራቅ ሰፈሮች ውስጥ በRSF ወደተያዙ አካባቢዎች መግፋታቸውን ቀጥለዋል። ሰራዊቱ እና አጋሮቹ ባለፉት ወራት ሲቆጣጠሩት የነበሩት የ RSF ታጣቂዎችን ከነዚህ ቦታዎች ካባረሩ በኋላ “አል-ፍርዳውስ፣ አል- ሂጅራ፣ አል-ጀዋማአ፣ አል-ዋህዳ፣ አል-ሰላም እና አል-ዋህዳ” የተባሉትን ሰፈሮች እንደገና መቆጣጠር ችለዋል።

ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ የዳርፉር ግዛት ታሪካዊ ዋና ከተማ የሆነችው ኤል ፋሸር በሰራዊቱ እና በተባባሪዎቹ መካከል በአርኤስኤፍ ላይ በተነሱት የትጥቅ እንቅስቃሴዎች መካከል ኃይለኛ ግጭቶች ታይተዋል።  አርኤስኤፍ በዳርፉር ክልል የመጨረሻው የቀረው የሱዳን ጦር ይዞታ ለመቆጣጠር ይፈልጋል።

በሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ በተካሄደው ጦርነት የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ የተዘገበ ሲሆን ከዚህ ባሻገር ከ500ሺ በላይ ሰዎች ወደ ታዊላ፣ ጀበል ማርራ እና በሰሜን ሱዳን በሚገኙ አካባቢዎች አንደተፈናቀሉም ተዘግቧል። የተራዘመው ጦርነት እና ከበባ ከፍተኛ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት አስከትሏል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል



Показано 20 последних публикаций.