አባዬ እንዴት ነህ? ይህንን ፅሁፍ አንብበህ ስትጨርስ አፍሪካዊ ሆነህ በመፈጠርህ ልትፀፀት ስለምትችል ይቅርብህ!😀
ምን መሰለህ!?
ዓለም ላይ 7.8 ቢልዮን ህዝብ አለ። ከዛ ውስጥ ከ 1 ቢልዮን በላይ የሚገመተው ሰው የሞባይል ስልክ አለው! ተንደላቀህ የምትጠቀመው ስልክ እና ላፕቶፕ፣ በየሆስፒታሉ የምትታከምባቸው ዘመናዊ ማሽኖች እና ሌሎች በቻርጅ የሚሰሩ የኤሌክትሮኒክ መሳርያዎች አንዲት የአፍሪካ ሃገር ከሌለች የሉም!
እንዴት?
"Coltan" ከሚባለው መዓድን አለ። ከዚህ ድንጋይ መሰል መዓድን ውስጥ ደግሞ "Tantalum" የሚባል "powder" (ዱቄት) ይወጣል!
ለምን?
የያዝከው ስልክ ቻርጅ ተደርጎ ጥቅም ላይ የሚውለው(የሚሰራው) ከዚህ "Coltan" ከሚባል መአድን ውስጥ በሚወጣ "Tantalum" በሚባል "powder" ነው።
ይህ መዓድን ደግሞ በስፋት ያለው "Democratic Republic of Congo(DRC)" ውስጥ ነው! 80% የሚሆነው "Coltan" የሚገኘው ከዚህች የዓለማችን እጅግ ደሃ ከሆነች እና ከቆረቆዘች ሃገር ነው!
ጌታዬ! "Apple", "Microsoft", "Vodafone","Nokia", "Samsung", "Huawei".... የፈለከውን ምርት መጥቀስ ትችላለህ ስልካቸውን የሚሸጡልህ ከ "Congo" በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ በሚያስኮበልሉት "Coltan" ሰርተውልህ ነው። አፍሪካ አይለፍልሽ የተባለች፣ በቸነፈር፣ በችጋር፣ በበሽታ፣ በድህነት፣ በስቃይ፣ በጦርነት እና በሞት የተሞላች ገፊ አህጉር ናት! "Congo" በታሪኳ ተረጋግታ የማታውቅ ትልቅ ሃገር ናት! ሃገሪቷ መረጋጋት እንኳን ብትፈልግ የውጪ ሃይሎች በተለይ ምዕራባዊያኖቹ እንድትረጋጋ አይፈልጉም!
ለምን መሰለህ! እቺህ ሃገር ተረጋግታ፣ ሰላማዊ መንግስት መስርታ፣ በየጫካው መሳርያ ታጥቀው የሚዋጉ አማፅያን ወደ ሰላም ድርድር መጥተው፣ ሙስናን አስወግዳ እና ተቋማቶቿን አጠናክራ ከመጣች አደጋው ለነሱ ከባድ ነው! እንደ "Coltan" ያለ የዓለም ቴክኖሎጂ ሳንባ የሆነ መዓድን ባለቤት የሆነችን ሃገር እንዴት ነው እንድትረጋጋ የምታደርገው? አባዬ! ነገ "....."Coltan"ን የምሸጠው በዚህ ዋጋ ነው! መደራደር አለብኝ!...ምናምን" ብላ ብታስቸግርስ?
ስለዚህ እንደልብህ እቺን ደሃ ሃገር መዝረፍ የምትችለው መቼም ሰላም እንድታገኝ ባለማድረግ፣ አማፅያኖቹን በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ መንገድ በገንዘብ እና በክላሽ እንደልብ እየረዳህ እርስ በእርስ እንዲጨራረሱ በማድረግ እና ያልተማረው ህዝቧ መቼም እንዳይሰለጥን በማድረግ ነው!
የሚያሳዝኑ ጥሬ ሃቆች!
ይህን "Coltan" የተሰኘ መዓድንን የሚያወጡ ምስኪን የኮንጎ ዜጎች በወር ጥሩ ተከፈላቸው ከተባለ እስከ "50 ዶላር" ድረስ ብቻ ነው። 40 ሺህ የሚጠጉ እድሜያቸው ከ 15 ዓመት በታች የሚሆኑ ህፃናት ትምህርታቸውን አቁመው ይህንን መዓድን ቀኑን ሙሉ ሲፈልጉ እና መሬት ሲጭሩ ይውላሉ!
እ.ኤ.አ ከ 1998 ጀምሮ ይህንን መዓድን በማውጣት የተሰማሩ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች እስካሁን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደሞቱ ይነገራል! በወር እስከ 10 ሺህ ሰው ይህንን መዓድን ለማውጣት ሲል በሚፈጠር ግጭት ይረግፋል!
ህዝቡ ይህንን መዓድን ፍለጋ ሲኳትን ደኖቹን መንጥሮ መንጥሮ ሃገሪቷን ምድረ በዳ ሊያደርጋት ነው። የዱር እንስሳት ማደርያ አጥተው እየተሰደዱ ነው!
መዓድኑን በዋነኝነት የሚያወጡት ህፃናት እና ሴቶች ናቸው! የመዓድን ቦታዎቹ ደግሞ ወጥ በሆነ መንገድ ከሃገሪቱ መንግስት ጋር የተያያዙ አይደሉም። ወይ በመዝባሪ የውጪ ባለሃብቶች ወይ ደግሞ ሃገሪቷ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ አማፅያን የተያዙ ናቸው! ደላላዎቹ እነሱ ናቸው! አብዛኛው መዓድን በህገ ወጥ መንገድ በአማፅያኖቹ አማካኝነት ከሃገር ይወጣል። ከዛም በዚህም ሆነ በዛ ቅድም የጠቀስናቸው ግዙፍ የስልክ አምራች ኩባንያዎች ጋር ይህ መዓድን ይደርሳል!
ሚሊሻዎቹ(አማፅያኖቹ) ከዚህ መዓድን ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣብያ ወይም መንገድ አይደለም የሚያሰሩበት! ጌታዬ! የሚገራርም ጥይት ነው የሚሸምቱበት! ከዛ እርስ በእርስ ይናጩበታል!
አብዛኛዎቹ የዚህች ሃገር መሪዎች ሃገሪቷን ሊያሳድጉ ወደ ስልጣን አይመጡም! ይልቁስን ዘርፈው...ዘርፈው...ከዛም የዘረፉትን ገንዘብ አውሮፓ እና አሜሪካ አስኮብልለው ጥለዋት ይሄዳሉ!
ይህ መዓድን በ "Rwanda" የዘር ጭፍጨፋ ወቅት ሳይቀር አስተዋጽኦ አበርክቷል! መዓድኑ በህገ ወጥ መንገድ አብዛኛውን ግዜ የሚኮበልለው በጎረቤት "Rwanda" በኩል ነው! በወቅቱ የሩዋንዳ መከላከያ ይህንን መዓድን በመሸጥ ብቻ ወደ "250 ሚልዮን ዶላር" አግኝቷል! ገንዘቡን ደግሞ በወቅቱ ለምን መሸመቻነት እንዳዋሉት አንተው ታውቃለህ።
ስናጠቃልለው!
"Congo" የዓለማችን እጅግ በጣም ሃብታም ሃገር ናት! 30% የዓለማችን ዳይመንድ እዛ ነው፣ 80% የዓለም "Coltan" የሚመጣው ከዛ ነው! 33% የዓለም ኮፐር ክምችት ያለው እዛ ነው! የወርቅ፣ የነዳጅ፣ የዩራንየም እና የዚንክ ከፍተኛ ክምችት ሳይቀር አላት!
በጣም የሚዘገንን ጥሬ ሃቅ!
"Congo" 24 ትሪልዮን ዶላር የሚገመት ገና ያልተነካ(Untapped) መዓድን አላት! ጌታዬ! እንዳትረሳ! የአሜሪካ "GDP" እራሱ 22 ትሪልዮን ዶላር ነው! እቺህ ሃገር ቢያልፍላት፣ ሰላም ብትሆን እና ህዝቦቿ ቢነቁ ሙሉ አፍሪካን ቁጭ አድርጋ መቀለብ ትችል ነበር።
ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ይህንን ሁሉ የተፈጥሮ ሃብታ የያዘች ሃገር የዓለማችን እጅግ ደሃ ሃገር ሆና ህዝቦቿ ሲበዘበዙ፣ ሲራቡ እና በጦርነት ስትታመስ ከማየት በላይ የሚያበሽቅ፣ የሚያቃጥል፣ የሚያንገበግብ ሌላ ምን አለ? ይህንን ስትሰማ እቺን አህጉት ጥለህ ጥፋ ጥፋ አያሰኝህም ወይ?
መልካም ምሽት!🙏
Wendye Engida
@legacyofbooks12