ትግልህን ምረጥ!!
“ከሕይወት የምትፈልገው ምንድነው?” ብዬ ብጠይቅህና “ደስተኛ መሆን፣ ታላቅ ቤተሰብ መመስረትና የምወደው ስራ እንዲኖረኝ፡፡” ብለህ ብትመልስልኝ፣ መልስህ የተለመደና የሚጠበቅ ከመሆኑ የተነሳ ምንም ትርጉም የሌለው ይሆናል፡፡
ሁሉም ሰው ጥሩ በሆነው ይደሰታል፡፡ ሁሉም ሰው ጭንቀት የሌለበት፣ ደስተኛና ቀላል ሕይወት መኖር፤ በፍቅር መውደቅ፣ በጣም ደስ የሚል ወሲባዊ ግንኙነትና የፍቅር ጓደኝነት፣ ዘናጭ መሆንና ገንዘብ መስራት፣ ታዋቂና የተከበረ መሆን፣ በጣም የተደነቀ ከመሆን የተነሳ ወደ አንድ ቦታ ሲራመድ ሰዎች እንደ ቀይ ባህር የሚከፈሉለት ቢሆን ይፈልጋል፡፡
ሁሉም ሰው ያንን ይፈልጋል፤ ያንን መፈለግ ቀላል ነው፡፡
በጣም ደስ የሚለውና ብዙ ሰዎች በጭራሽ የማያስተውሉት መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ግን “በሕይወትህ ውስጥ ምን አይነት ስቃይ ትፈልጋለህ? ልትታገል የምትፈልገው ምንድነው?” የሚል ነው፡፡ምክንያቱም ህይወታችን እንዴት እንደሚሆን የሚወስነው ትልቁ ነገር ያ ነውና፡፡
ለምሳሌ ብዙ ስዎች አሪፍ ቢሮ እንዲኖራቸውና ብዙ ገንዘብ መስራት እንዲችሉ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን በሳምንት ስልሳ ሰዓት በመስራት፣ በረጅም ጉዞዎችና አሰልቺ በሆኑ የወረቀት ስራዎች መሰቃየት የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ አይደሉም፡፡
ብዙ ሰዎች አሪፍ ወሲብ፣ ጥሩ የፍቅር ግንኙነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ወደዚያ ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ ንግግሮችን፣ አሳፋሪ ሁኔታዎችንና የስሜት መጎዳቶችን ለማለፍ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ከዚያ ይረጋጉና፣ ጥያቄው ከ “ቢሆንስ?” ወደ “ከዛስ?” እስኪለወጥ ድረስ ለአመታት ያስባሉ፡፡
ደስታ ትግል የሚጠይቅ በመሆኑ የሚነሳው ከችግር እንጂ ልክ እንደ አበባና ቀስተደመና ከመሬት የሚነሳ አይደለም፡፡ እውነተኛ የእድሜ ልክ እርካታና ትርጉም የሚገኘው ትግሎቻችንን በመምረጥና ማስተዳደር በኩል ነው፡፡
አሪፍ የሰውነት አቋም እንዲኖርህ ትፈልጋለህ እንበል፡፡ ነገር ግን ለብዙ ሰዓታት ጂም ውስጥ በመስራት የሚያጋጥምህን ህመምና አካላዊ ጭንቀት በፅናትና በደስታ ካልተቋቋምክ፣ የምትመገበውን ምግብ መመጠን እና ማስተካከል ካልወደድክ፣ የምትፈልገውን በስፖርት የተገነባ ሰውነት አታገኝም፡፡
ሰዎች የራሳቸውን ስራ መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ያንን ለማድረግ በሚደረግ ሙከራ የሚያጋጥማቸውን አደጋ፣ እርግጠኛ ያለመሆን፣ ተደጋጋሚ ውድቀት ካልተቋቋሙ፣ ምንም ነገር ጠብ ለማይል ነገር ያጠፏቸውን ጊዜያት በደስታ ካልተቀበሉ፣ስኬታማ ስራ ፈጣሪ መሆን አይችሉም፡፡
ሰዎች የትዳር አጋር፣ ወይም የፍቅር ጓደኛ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ከሚያጋጥሙህ ተደጋጋሚ አለመፈለጎች የተነሳ የሚመጣብህን የስሜት መዋዠቅ በትዕግስት ካላለፍክ፣ ማስተንፈስ የማትችለውን ወሲባዊ ውጥረት ካልተቋቋምክና የማይደወል ስልክ ላይ ማፍጠጥን ካልተጋፈጥክ ማራኪ አጋር ማግኘት አትችልም፡፡ ይህ የፍቅር ጨዋታ ክፍል ነው፡፡ ካልተጫወትክ ማሸነፍ አትችልም፡፡
ያንተን ስኬት የሚወስነው “በምን መደሰት ትፈልጋለህ?” በሚለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ወደ ደስታ የሚወስደው መንገድ በሚያንሸራትቱ ነገሮችና በእፍረት የተሞላ በመሆኑ ተገቢ የሚሆነው ጥያቄ “ምን አይነት ስቃይን መቋቋም ትፈልጋለህ? የሚል ነው፡፡
ሕይወት ሁልጊዜ በፅጌረዳ ያሸበረቀ ሊሆን አይችልም፡፡ ስቃይ አልባ ሕይወት ሊኖርህ የማይችል ከሆነ ደግሞ የሆነ ነገር መምረጥ አለብህ፡፡
በጣም አስፈላጊውና ከባዱ ጥያቄ፣ “መቋቋም የምትፈልገው ምን አይነት ስቃይ ነው?” የሚለው ነው፡፡ የሆነ ቦታ የሚያደርስህና ለሕይወት ያለህን እይታ ሊለውጥ የሚችለውም ጥያቄ ይህ ነው፡፡ እኔን እኔ፣ አንተን አንተ ያደረገን እንዲሁም እኛን የሚገልፀንና የሚለያየን በመጨረሻም አንድ ላይ የሚያደርገን ጥያቄ ይህ ነው፡፡
በአብዛኛው በጉርምስናና በወጣትነት ዘመኔ ሙዚቀኛ በተለይም የሮክ ሙዚቃ ኮከብ ስለመሆን አልም ነበር።የትኛውንም በጊታር የታጀበ ሙዚቃ ስሰማ አይኖቼን ጨፍኜ በምናቤ ራሴን መድረክ ላይ በአድናቆት
ለሚጮኹ ብዙ ሰዎች ጊታር ስጫወት፣ ሰዎች በእኔ ጊታር አጨዋወት ተማርከው ራሳቸውን ሲስቱ እመለከት ነበር፡፡ ሀሳቡ ለእኔ ቢሆንስ? የሚል ጥያቄ ስላልነበረ ይህ ህልም ለሰአታት ይዞኝ ይቆይ ነበር፡፡ በአድናቆት በሚጮኹ ተመልካቾች ፊት እንደምጫወት እርግጠኛ ነበርኩ፤ ግን መቼ? ሁሉንም ማቀድ ነበረብኝ፡፡ እዚያ ደርሼ አሻራዬን ለማሳረፍ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን ኃይልና ጥረት መስጠት ከመቻሌ በፊት ጊዜዬን መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ በመጀመሪያ ትምህርቴን መጨረስ፣ ከዚያ ጊታር ለመግዛት ተጨማሪ ገንዘብ መስራት፣ ከዚያ ደግሞ ለመለማመድ በቂ ነፃ ጊዜ ማግኘት፣ ቀጥሎ የመጀመሪያ ፕሮጀክቴን ማቀድ ያስፈልገኝ ነበር፡፡ ከዚያ... ከዚያ. . . በቃ፡፡
ይህንን ነገር የእድሜዬን ግማሽ ያህል ሳልመው የኖርኩ ቢሆንም ምኞቴ ግን ለፍሬ አልበቃም፡፡ በመጨረሻ ለምን ለፍሬ እንዳልበቃ እስክረዳ ድረስ ረጅም ጊዜና ረጅም ትግል ወስዶብኛል፡፡ ለካ ለፍሬ ያልበቃው ከልቤ ስላልፈለግኩት ነበር፡፡
በምናቤ ራሴን መድረክ ላይ ሆኖ ሳየው፣ ሰዎች በአድናቆት ሲጮሁ፣ እኔ ፍፁም ከልቤ ሆኜ ጊታር ስጫወት ሳልም ፍቅር የወደቅኩት ከውጤቱ ጋር እንጂ ከሂደቱ ጋር አልነበረም፡፡
ያልተሳካልኝም በዚያ ምክንያት ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ወድቄያለሁ፡፡ በበቂ ሁኔታ አለመሞከር ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አልሞከርኩም ማለት ይቻላል፡፡ የየእለቱ አሰልቺ ልምምድ፣ የሙዚቃ ቡድን መፈለጉና አብሮ መለማመዱ፣ ሰዎችን የመጠበቁ ስቃይ፣ የጊታሬ ክሮች መበጠስ፣ እቃዎቼን ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የመኪና አለመኖር ህልሜን ተራራ የሚያክል አድርጎብኝ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ለመድረስ ደግሞ ተራራውን መውጣት ያስፈልግ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የወደድኩት ውጤቱን በምናቤ ማየት ብቻ ስለነበር፣ ብዙም ተራራ መውጣት እንደማልወድ ለመረዳት ብዙ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡
የተለመደው ባህላዊ ትረካ ያቋረጥኩ ወይም ተሸናፊ መሆኔ፣ “ያላገኘሁ” መሆኔ፣ ህልሜን በመተው እና ምናልባትም በህብረተሰቡ ጫናዎች እንድሸነፍ በማድረግ በሆነ መንገድ ራሴን እንድወድቅ ያደረግኩ እንደሆንኩ ይነግረኛል፡፡
እውነቱ ግን ከእነዚህ ገለፃዎች በተሻለ ደስ የሚል አለመሆኑ ነው፡፡ እውነቱ የሆነ ነገር እንደምፈልግ አስቤ ነበር፡፡ ግን አልፈለግኩም ነበር፡፡ አለቀ፡፡ የፈለግኩት ሽልማቱን እንጂ ትግሉን አልነበረም፤ የፈለግኩት ውጤቱን እንጂ ሂደቱን አልነበረም፡፡ ፍቅር የያዘኝ ከድሉ እንጂ ከትግሉ አልነበረም፡፡
ሕይወት ደግሞ በዚያ መንገድ አይመራም፡፡ማንነትህ የሚታወቀው ልትታገልለት ፈቃደኛ በሆንከው ነገር ነው፡፡ ስፖርት የመስራትን ትግል በደስታ የሚቀበሉ ሰዎች የሚፈልጉትን ስፖርታዊ አቋም ያገኛሉ፡፡ ረጅም የስራ ሳምንትንና ቢሮክራሲ መቋቋም የሚችሉ ሰዎች የአመራር መሰላል ጫፍ ላይ መድረስ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡
ይህ ስለ ቆራጥነት ወይም ጥርስን ስለመንከስ አይደለም፡፡ ይህ “ህመም ከሌለ ማግኘት የለም” የሚለው አይነት ሌላ ግሳፄ አይደለም፡፡ ይህ ትግላችን ስኬታችንን ይወስናል፡፡ ችግሮቻችን የደስታዎቻችን መፈጠሪያ ናቸው የሚል የሕይወት በጣም ቀላሉና መሰረታዊ አካል ነው፡፡
አየህ ይህ መጨረሻ የሌለው ቀጥ ብሎ የቆመ ጠመዝማዛ ብረት ነው፡፡ የሆነ ነጥብ ላይ መውጣት ማቆም እንደሚፈቅድልህ ካሰብክ፣ ነጥቡን ስተሃል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም ደስታው ያለው በራሱ በመውጣቱ ላይ ነውና!!
📚The subtle art of not giving a fuck
✍️Mark Manson
የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence