እራስን መመልከት
~
እየውልህ ወንድሜ! ህሊና አልባ በድን ማሽን አትሁን። የምትገባው ከራስህ እንጂ ከኡስታዝህ ቀብር አይደለም። ሲራጥን የምትሻገረው በራስህ ስራ መጠን እንጂ ኡስታዝህ እጅህን ይዞ አያሻግርህም። ያለ አስተርጓሚ ራቁትህን ከጌታህ ፊት ለምርመራ ስትቆምም ኡስታዝህ ከጎንህ አይቆምልህም። ይህንን ሁሉ የምልህ ማንንም በጭፍን እንዳትከተል ነው። በአሁኑ ሰዓት በየሰፈሩ ያሉ ሸይኾችና ኡስታዞች አብይ መታወቂያ ጭፍንነትን ሥራዬ ብለው የሚግቱ፣ ተማሪዎቻቸውን በጭፍንነት የሚኮተኩቱ መሆናቸው ነው። የወደዱትን በጭፍን እንድትወድላቸው፣ የጠሉትን በጭፍን እንድትጠላላቸው እስከ ደም ጠብታ ይታገሉሃል። ቁርኣን፣ ሐዲሥ፣ የዑለማእ ንግግር ተንኮለኛ በሆነ መልኩ ከአውድ ውጭ እያገናኙ የሃሳብ ሽብር ይነዙብሃል። እዚህ ላይ "ለምሳሌ እነ እንትናን ብንወስድ… " ብዬ ባጣቅስ የእነ እንትና ጭፍራ ጦር ሰብቆ ይነሳል። ከነሱ ውጭ ያለው ደግሞ በአመዛኙ ይደግፋል። እውነት ለመናገር ግን ጣት መቀሰሩ ስለሚቀለን እንጂ ይሄ በሽታ ይብዛም ይነስም በየቤቱ ይገኛል። ችግራችን ግን አይናችን ውስጥ ያለውን ግንድ ጥለን ከሌሎች አይን ያለን ጉድፍ ነው የምንመለከተው። የሌሎችን ጥፋት ለማጋለጥ እንረባረባለን። እሺ የራሳችንንስ ማን ያርመው? ለማነው የምንተወው? ኧረ ልባችን ፈቃጅ ተመልካች አጣ!! ድባቡ የተበከለ ሆኖ መገሳሰፅ አልቻልንም። እኛም ለራሳችን ተገቢውን ትኩረት አልሰጠንም። ግን እስከመቼ?
እና ወንድሜ ከማንም ጎጠኛ ቡድን ጋር ጭፍን ተሰላፊ አትሁን። ከዑለማእ ንግግር ውስጥ ከስሜቱ ጋር በሚገጥምለት መልኩ እየመረጠ የሚያቀርብ ሰው ስታይ በችኮላ እጅ አትስጥ። የትኛውም ቡድን ጋር የተሰለፈው ሁሉ ይህንን እያደረገ ነውና የሱ ከሌሎች በምን እንደሚለይ ረጋ ብለህ መርምር። የማይነቃነቅ ነባራዊ ሐቅ፣ የአህለ ሱና ዋና መታወቂያ አስመስሎ ያቀረበልህ ጉዳይ አብዛኞቹ ዑለማዎች ዘንድ ያለው አቋም እሱ ካወራህ ተቃራኒ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህና ከስሜት ነፃ ሆነህ በሚገባ ፈትሽ። ደግሞ ቆም ብለህ ታዘባቸው። ብዙዎቹ ቡድናዊነት የሰበሰባቸው አካላት:—
— "እነ እከሌ ጠርዘኞች ናቸው፣ ድንበር አላፊዎች ናቸው" እያለ ከፍ አድርጎ ያስተጋባል። የሚያስከነዱ ጠርዘኞችን ግን አቅፎ ያሽሞነሙናል። ምክንያቱም እነዚህኞቹ እሱ ሲስል የሚስሉ፣ ሲያነጥስ የሚያነጥሱ የገደል ማሚቶዎች ናቸውና።
— "እነ እከሌ ጃሂሎች ናቸው" ይልሃል። በምንም መመዘኛ ከነሱ የማይሻሉ ሰዎችን ግን በትልልቅ መድረክ ላይ ያስተዋውቃል። ምክንያቱ አቋማቸው ከአቋሙ ስለገጠመለት ብቻ ነው።
— "እነ እከሌ አቋም የሌላቸው ወላዋዮች ናቸው" ያለህ ስብስብ በየክስተቱ ባደባባይ የሚዋልሉ ሰዎችን ከጎናቸው አሰልፈው ታገኛቸዋለህ። ምክንያቱም መመዘኛው ርካሹ ቡድናዊ ሚዛን እንጂ ኢኽላስ አይደለምና።
ወንድሜ ሆይ! አላህን አስበህ ስለምትሰራው ነገር የማንንም ጭብጨባ አትጠብቅ። የማንም ተቃውሞም አይጠፍህ። ይልቅ ውስጥህን አዳምጥ፣ ኢኽላስህን ፈትሽ። ያለ ኢኽላስ ጩኸትህ የቁራ ጩኸት ነው። ልፋትህም ከንቱ ድካም። በደዕዋህ ቀዳሚው ትኩረትህ ሰፊው ህዝብ ይሁን። አትዘንጋ! ዛሬም አብዛኛው ወገናችን ከተውሒድ ግንዛቤ የራቀ ነው። ሺርክ ላይ የሚማቅቀው ብዙ ነው። ከባባድ አጥፊ ወንጀሎች ላይ እስከ አፍንጫው የተነከረው ቀላል አይደለም። ቀዳሚው ጥረትህ የዚህን ወገንህን ሸክም ለመቀነስ ይሁን። ይህንን መሰረታዊ ጉዳይ ገሸሽ በማድረግ ውሃ ቀጠነ፣ ከሰል ጠቆረ ብሎ ለሚነታረክ ጀርባህን ስጠው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም አረፋ ነው።
በኢኽላስ እስከሰራህ ድረስ የማንም ጫጫታ ቅስምህን አይስበረው። ሰዎች እንቅፋት ሲያበዙ አንተ ፅናትህን ጨምር። ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አትበል።
የሌሎችን ጩኸት ሳታጣራ የምታስተጋባ በቀቀን አትሁን። በጭፍን አትደግፍ። በጭፍን አትንቀፍ። እወቅ! እውር ጥላቻና እውር ውዴታ ነገ ከአላህ ፊት ያሳፍርሃል። ማንንም በእውር ድንብር አትከተል። ጭፍን ወገንተኝነት በቃላት ቢያሸበርቅም፣ በሱና፞ ስም ቢቀርብም የተወገዘ ነው። የአሳማ ስጋ በወርቅ ሰሀን ስለቀረበ አሳማነቱ አይቀየርም። አሳማ አሳማ ነው። የመዝሀብ ሰዎች ዘንድ የምናውቀው ጭፍን ወገንተኝነት ተቀባብቶ ተከሽኖ በሱና፞ ዑለማዎች ስም ሲቀርብ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ይበልጥ የሚያሳፍረው ደግሞ አንዳንዶች በየሰፈሩ በየመንደሩ እየተቧደኑ ‘ወላእ’ እና ‘በራእ’ የሚቋጥሩባቸው አካላት መመደባቸው ነው።
ደግሞም በልክ እንሁን። በሌሎች ሃገራት ወይም አካባቢዎች ያየነውን ወይም የሰማነውን ኺላፍ ሁሉ ሰበብ እየፈለጉ እየጎተቱ ማምጣት ግልብነት ነው። ወላጆችህ ወገኖችህ በሺርክ እየተጨማለቁ አንተ በሸይኽ እንትናና በሸይኽ እከሌ መካከል ስለተፈጠረው ኺላፍ ጧት ማታ እያቦካህ በአካባቢህ ያሉ ዱዓቶችን ለመፈረጅ አድፍጠህ ብትጠባበቅ የፊትና ጥማትህን እንጂ ንቃትህን አያሳይም። በአካባቢህ ይሄ ነው የሚባል የደዕዋ ተሳትፎ ሳይኖርህ እንዳቅማቸው እየደከሙ ያሉ አካላትን ትንሽዬ ጥረት አይኗን ለማጥፋት ጦር ብትሰብቅ ጥሬነትህን ብቻ ነው የሚያሳየው። ወንድሜ ከቻልክ አግዝ። ክፍተት ካየህ አርም። አቅሙ ከሌለህ ባላቸው አስመክር። በምትችለው ከጎናቸው ቁም። ለሰፈርህ ለአካባቢህ የደዕዋ እንቅስቃሴ አጋዥ እንጂ አፍራሽ አትሁን። ለደዕዋ እንቅፋት በመሆን ሌሎች እንዳይለወጡ መሰናክል አትፍጠር። ሰዎች የሚተላለፉበት መንገድ ላይ አስቸጋሪ ነገሮችን መጣል ፀያፍ ጥፋት ነው። ወደ ኣኺራ በሚወስደው የደዕዋ መንገድ ላይ እንቅፋት መጣል ግን እጅግ አደገኛ ወንጀል ነው። እንዲህ አይነቱን የወንጀል ሸክም የምትቋቋምበት ጫንቃው የለህምና ዛሬውኑ ሚናህን ለይ። ዛሬውኑ ለደዕዋ ያለህን አስተዋፅኦ ገምግም።
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ የካቲት 07/2013)