በካፊሮች በዓል እንኳን አደረሳችሁ ማለት ይፈቀዳልን?
በበአላት ሰሞን በተደጋጋሚ እገሌና እገሌ ላይክ አድርገውታል ከሚለን ፖስቶች መካከል ከፊሎቹ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶች ናቸው። ለጌታ መወለድ፣ ለጌታ መሰቀል፣ ለጌታ ሞቶ መነሳት (ትንሳኤና) መሰል ክስተቶች እንኳን አደረሳችሁ ሲባል ሼር ወይም ላይክ የሚያደርጉ ብዙ እህትና ወንድሞችን አስተውያለው። አንዳንዴ በስህተት ሌላ ግዜም ነገሩን እንደቀላል በመውሰድ የሚፈፀም ሊሆን ይችላል። ሆኖም እጅግ ከባድና በአኼራ ዋጋ የሚያስከፍል መዘናጋት ነው!!
በካፊሮች በአል፤ እንኳን አደረሳችሁ... እንኳን ደስ አላችሁ... እንኳን አብሮ አደረሰን ማለት እነሱን ለማስደሰትም ይሁን ለመመሳሰል ከአላህ ዲን መንሸራተት እና የካፊሮችን ኩፍር የመናገር ስነልቦና መካብ ስለሆነ
ክልክል ነው። መከባበር እና አብሮነትን ለማሳየት ከእምነታችን መንሸራተት አይጠበቅብንም። ዲን ከምንም በላይ ነውና ሸሪዓን መተላለፍ ፍፁም ጥፋት ነው!!
ፈጣሪ ወለደ ተወለደ የሚለው አስተምህሮ የጥፋትነቱ ክብደት ሰማያትንና ምድርን ሊሰነጥቅ እንደሚቀርብ ቁርአን ይነግረናል። አላህን የሚያስቆጣ ተግባር በመፈፀማቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት ከሙስሊም አይጠበቅም!!
(وَقَالُوا۟ ٱتَّخَذَ ٱلرَّحۡمَـٰنُ وَلَدࣰا * لَّقَدۡ جِئۡتُمۡ شَیۡـًٔا إِدࣰّا * تَكَادُ ٱلسَّمَـٰوَ ٰتُ یَتَفَطَّرۡنَ مِنۡهُ وَتَنشَقُّ ٱلۡأَرۡضُ وَتَخِرُّ ٱلۡجِبَالُ هَدًّا * أَن دَعَوۡا۟ لِلرَّحۡمَـٰنِ وَلَدࣰا * وَمَا یَنۢبَغِی لِلرَّحۡمَـٰنِ أَن یَتَّخِذَ وَلَدًا * إِن كُلُّ مَن فِی ٱلسَّمَـٰوَ ٰتِ وَٱلۡأَرۡضِ إِلَّاۤ ءَاتِی ٱلرَّحۡمَـٰنِ عَبۡدࣰا * لَّقَدۡ أَحۡصَىٰهُمۡ وَعَدَّهُمۡ عَدࣰّا * وَكُلُّهُمۡ ءَاتِیهِ یَوۡمَ ٱلۡقِیَـٰمَةِ فَرۡدًا)
[«
አልረሕማንም ልጅን ያዘ (ወለደ)» አሉ፡፡ ከባድ መጥፎን ነገር በእርግጥ አመጣችሁ፡፡ በእርሱ (በንግግራቸው ምክንያት) ሰማያት ሊቀደዱ፣ ምድርም ልትሰነጠቅ፣ ጋራዎችም ተንደው ሊወድቁ ይቃረባሉ፡፡ ለአልረሕማን ልጅ አለው ስለአሉ፡፡ ለአልረሕማን ልጅን መያዝ አይገባውም!! በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ (በትንሣኤ ቀን) ለአልራሕማን ባሪያ ኾነው የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም]
Surah Maryam 88 - 95
ለመሆኑ አንድን ካፊር ለሀይማኖታዊ በአል እንኳን አደረሰህ ስትለው፤ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለምን?
እንኳን አደረሰህ...ጌታ ተወልዶ ተሰቅሎ ሞቷል ብለህ ለማወጅ፣ ለመስቀል ለመስገድና የፈጣሪን ክብር የሚነኩ ንግግሮችን ለመናገር እንኳን በቃህ!
እንኳን አደረሰህ...ማርያም ፈጣሪዋን ወለደችው፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው እያልክ ለመዘመር እንኳን በቃህ!
የኩፍር ተግባርን ለመከወን ከሆነ የደረሰው ለምንስ እንኳን አብሮ አደረሰን እንላለን?
እውቁ አሊም ኢብኑል ቀይም ረሂመሁላህ ይህ ተግባር የተከለከለ ስለመሆኑ የኡለማዎች የጋራ አቋም መሆኑን በመጠቆም እንዲህ ብለዋል፤ «ኩፍርን ብቻ በሚያንፀባርቁ የሀይማኖታቸው መገለጫዎች እንኳን አደረሳችሁ...እንኳን ደስ ያለችሁ ማለት ሀራም መሆኑ የሁሉም ሊቃውንት ስምምነት ያለበት ነው።
ለምሳሌ አንድ ሙስሊም በነሱ በዓላትና ፆም ጊዜ፤ «በአሉን የተባረከ ያድርግልህ» ወይም «መልካም የደስታ በአል ያድርግልህ» እና መሰል የደስታ መግለጫዎችን ቢያስተላልፍ፤ ተናጋሪው ከኩፍር ቢድን እንኳ ከባድ ወንጀል ነው የፈፀመው። ይህም፤ ልክ «እንኳን ለመስቀል ሰገድክ» ብሎ ደስታን እንደመግለፅ ነው!
ይህ እንደውም፤ አንድ ሰው ነብስ በማጥፋቱ፣ አልኮል በመጠጣቱ፣ ዝሙት በመፈፀሙና በመሰል ተግባራት እንኳን ደስ ያለህ ከማለት በወንጀልነት የከበደ እና አስቀያሚ ነው። ለኢስላማዊ ድንጋጌዎች ተገቢዉን ክብር የማይሰጡ ብዙ ሰዎች ይህንን ይፈፅማሉ። ምን ያክል የሚያስጠላ የግባር እንደፈፀሙም አያስተውሉም። ቢድአ፣ ኩፍር እና ወንጀሎች በመፈፀማቸው እንኳን አደረሰህ፣ እንኳን ደስ ያለህ እና መሰል የደስታ መግለጫዎችን ያስተላለፈ፤ እራሱን ለአላህ ቁጣና ጥላቻ የተገባ እንዲሆን የሚያደርግ ምክኒያት ፈፅሟል» አህካም አህሉዚማህ
የዘመናችን ፈቂህ ሸይኽ ኡሰይሚን ረሂመሁላህ እንዲህ አሉ «ካፊሮችን እንኳን አደረሳችሁ ማለት ኢብኑል ቀይም እንዳለው የዚህን ያክል ከባድ የሆነበት ምክኒያት እነርሱ የሚፈፅሟቸውን የኩፍር መገለጫዎች ማፅደቅ ስለሆነ ነው። ምንም እንኳን ለራሱ ይህንን ኩፍር መፈፀምን ባይወድም እነሱ መፈፀማቸውን ወዷልና። ሙስሊም ደግሞ የኩፍር መገለጫዎችን መውደድም ይሁን ሌሎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት አይፈቀድለትም።»
መጅሙዑ ፈታዋ ወረሳኢል አሸይኽ ኢብኑ ኡሰይሚን 3/44
በተመሳሳይ መልኩ፤ ክሪስማስም ሆነ ሌሎች በአላት ላይ ስጦታ ወይም ፓስት ካርዶችን መለዋወጥ፤ እንዲሁም ማንኛውም ደስታን መግለጫ የሆኑ ነገሮችን መፈፀም በአሉን መካፈል ስለሆነ የተከለከለ ነው!!
በዚህ ፅሁፍ መጠቆም የፈለኩት ምንም አይነት ማህበራዊ ግንኙነት ሀራም ነው የሚል መልእክት አይደለም። በተለይም ከክርስቲያን እና አይሁዶች ጋር ባለን ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ የተፈቀዱ ብዙ በመልካም የመኗኗር እሴቶች አሉን። ሆኖም ሀይማኖታዊ ወሰኖች የሉም ማለት አይደለም። የተፈቀደውን ስንተገብር እንደ ያልተፈቀደ ጋብቻ፣ በአላት ላይ መሳተፍ፣ ለሞቱት የአላህን ማርታ መለመንና ባጠቃላይ በዲን መመሳሰልን ግን በፍፁም አንፈፅምም። ይህንን የእምነትና የሀይማኖት ወሰን መናድ አይቻልም። ማንነታችንን ማክበር፣ ግንኙነታችንን በዲናዊ ገደቦች ማጠር ብሎም አለመሟሟት ለሌሎች ሞራል ዲንና ማንነት ከመጨነቅ ይቀድማል። ዲን ከምንም በላይ ነውና ከመሸማቀቅ እንውጣ። ይህ የዲናችን መገለጫ እንጂ እንደ ማክረርና ፅንፈኝነት የሚታይ አይደለም። በነገራችን ላይ የአንድ እምነት ተከታይ ከሌሎች ለመቀራረብ ብሎ ከራሱ እምነት ጋር የሚጣላበት ሁኔታ ድሮ ቀርቷል። ሌሎቹም ቢሆኑ ይህ በኛ ሀይማኖት አልፈቀድም እና ይቅርታ ይሉሀል።
(فَلَا تُطِعِ ٱلۡمُكَذِّبِینَ * وَدُّوا۟ لَوۡ تُدۡهِنُ فَیُدۡهِنُونَ * وَلَا تُطِعۡ كُلَّ حَلَّافࣲ مَّهِینٍ)
አስተባባዮችንም አትታዝዙ፡፡ ብትመሳሰላቸውና ቢመሳሰሉህ ተመኙ፡፡
[Surah Al-Qalam 8 - 10]
ወላሁ አዕለም
አላህ ከጥፋት ሁሉ ይጠብቀን!
https://t.me/IbnuSefa