Posts filter


ስለሁሉም አመስግኑ!

ስለሆነው ስለሚሆነው ስለማይሆነው፣ ስላጣናቸው ስላገኘናቸው ፈልገንም ስላላገኘናቸው ስለተሰጠን ስለሚሰጠን፣ ስለማይሰጠን፣ ስላልተሳካልን ስለተሳካልን፣ ስለከሰርነው ስላተረፍነው ነገር በሙሉ ፈጣሪ ይመስገን። ስለሔደው በማልቀስ፣ ስለሚመጣውም በመጨነቅ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም። ሁሉ ለበጎ ሁሉ ለመልካም እንደሚደረግ ማመን ከሁሉ ነገር ነፃ ያወጣል። ስለእራሳችን በሚገባ የምናውቅ ሊመስለን ይችላል ለእኛ የሚበጀንን ግን ከእኛ በተሻለ እግዚአብሔር አምላካችን እንደሚያውቅ ማስታወስ ያስፈልጋል። በህይወታችን የሚከሰቱ እያንዳንዱ ነገሮች በምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው። ወደዳችሁም ጠላችሁም ከትናንት ጥፋታችሁና ከዛሬ ተግባራችሁ ጀርባ በቂ ምክንያት ነበረ፣ አለም።

አዎ! ጀግናዬ..! ስለሁሉም ምስጋና ይገባልና ምስጋናን አትሰስት፣ ነገሮች ሁሉ ለበጎ እንደሆኑ ለማሰብ ብዙ አትቸገር። ቅዱስ መፅሐፍ ይህን ይላል፦ "እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ሃሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡" ምንም ክፉ ነገር ቢከሰትብን፣ ምንም ለጊዜው የሚያሸማቅቅና አንገት የሚያስደፋ ሁነት ውስጥ ብንገኘ ሁኔታው ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅምና ለበጎ እንደሆነ ማሰቡ ብዙ በረከትን ይዞልን ይመጣል። በማጣት ውስጥ መረጋጋት፣ በማግኘት ውስጥ መረጋጋት። በችግር መሃል ማመስገኛ ምክንያት መፈለግ፣ በደስታ መሃልም እንዲሁ ምስጋናን ማስቀደም ተገቢ ነው። በማማረር የሚገኝ ነገር ቢኖር ሌላ ተጨማሪ የሚያማርር ነገር ነው፤ ከማመስገንም እንዲሁ ሌላ ማመስገኛ ነገር ነው። በረከትን በመቁጠር ሌላ በረከት ይገኛል፣ እርግማንን ደጋግሞ በማሰብም እንዲሁ ተጨማሪ ችግርን ወደእራሳችን እንጠራለን።

አዎ! ፈጣሪን የምታመሰግኑት ሁሉን የሚያደርግላችሁ እርሱ ስለሆነ ነው፤ ሰዎችን የምታበረታቱት፣ ሰዎችን የምታደንቁት ብሎም ደስተኛ እንዲሆኑ የምትጥሩት እናንተም ይሔ ነገር እንዲደረግላችሁ በምትፈልጉት መጠን ነው። ክፉ ሰው መልካም ነገር ከሰዎች አይጠብቅም፤ ውሸታም ሰው ማንም እውነት የሚያወራ አይመስለውም፤ አቃቂር በማውጣት የተጠመደ ሰው ምንም በጎ ስራ አይታየውም። ከእናንተ የተሻለ ህይወት የሚኖሩ የሚመስሏችሁን ሰዎች እየተመለከታችሁ ከአመስጋኝነት አትራቁ፣ የሌላችሁን እየቆጠራችሁ ለጭንቀትና ለብቸኝነት እራሳችሁን አታጋልጡ። እያንዳንዱ ችላ የምትሉት ትንሽ ልማዳችሁ እያደር ዋጋ እንደሚያስከፍላችሁ አትርሱ። ከምስጋና የራቀ ሰው ከታሰበለት በረከቱም እንዲሁ እየራቀ ይሔዳል። ስለሁሉም አመስግኑ፣ እለት እለት በልባዊ ምስጋና ውስጣችሁን አድሱ፣ በረከታችሁን ጨምሩ፣ ደስታችሁንም እራሳችሁ ፍጠሩት።


ትኩረት ይባላል!

ብዙ ውጫዊ ጫናዎች ባሉበት ሰዓት እራስ ላይ ማተኮር የስኬታማ ህይወት ቁልፍ ነው፤ ብዙ ሰው ፍረሃትና ስህተቱን በሚያስብበት ወቅት ስኬትና ለውጥን ማሰብ የወሳኙ እድገት መሰረት ነው፤ ብዙዎች ባለፈውና በሚመጣው ጊዜ ሲጨነቁ እራስን ገዝቶ ዛሬን መኖር፣ አሁን ሃላፊነትን መወጣት ዋንኛው የጭንቀት መድሃኒት ነው። ችግር በሌለበት ችግር አትፍጠር፣ ውድቀት በሌለበት ውድቀትን አትሳብ፣ ፍረሃት በሌለበትን ፍረሃትህን አትጥራው። ትኩረትህ ከባዶ ኬትም አይመጣም። ስለምትፈራው ነገር ማሰብ ባትፈልግም ፈርተሀዋልና ታስበዋለህ፣ ውስጥህ ቦታ ሰተሀዋልና ትኩረትህንም እንዲሁ እርሱ ላይ ታደርጋለህ። የአዕምሮን አሰራር ሳያውቁ በየሔዱበት እራስን ለውድቀትና ለአሉታዊነት ማጋለጥ ይዋል ይደር እንጂ የሚመጣው ውድቀት ለመቀልበስ እጅግ አዳጋች መሆኑ አይቀርም!

አዎ! ጀግናዬ..! ትኩረትህ በብዙ ነገር ይሳብ ይሆናል፣ አዕምሮህ በምትፈልገው ልክ ላይታዘዝልህ ይችላል፣ ልማድህን ባሰብከው ልክ ላትቆጣጠረው ትችላለህ፣ ከፖራዳይም (paradigm) እስራት ለመውጣት ብዙ ዋጋ መክፈል ይጠበቅብህ ይሆናል። ነገር ግን ሁሉን በአንድ የምታስተካክልበት ወሳኝ መሳሪያ አብሮህ አለ። ይህ መሳሪያህ ትኩረት ይባላል። ትኩረት! አንድን ነገር መርጠህ ትኩረት አደረክበት ማለት እድገቱን ትፈልጋለህ ማለት ነው። ምክንያቱም ትኩረት የተደረገበት የትኛውም ነገር ያለማደግ እድል የለውምና ነው። እራስህን ይሆናል፣ ስራህን ይሆናል፣ ስኬትህን ይሆናል አልያም ውድቀትን፣ ፍራቻንና ስህተትን መርጠህ አተኩረህባቸው ይሆናል። ጠቃሚም ሆኑ ጎጂ የትኛውም የትኩረትህ ገዢ ግን ማደጉ አይቀርም።

አዎ! ስኬት ላይ አተኩር፣ ለውጥህን አብዝተህ አስብ፣ ከእድገትህ ጋር በሃሳብም በተግባርም ተዋሃድ። የምርም የምትፈልገው የስኬት ደረጃ የምትደርሰው ባተኩርክበት ልክ ነው። ስኬት ላይ ማተኮር ምናብ አይደለም፣ ስኬትን አብዝቶ ማሰብ ቁጭ ብሎ የሚደረግ አይደለም። የትኛውም ትኩረት ዋጋ አለው፤ የመታገል ዋጋ፣ ጠንክሮ የመስራት ዋጋ፣ ጠቢብ የመሆን ዋጋ፣ እራስን የማሳደግ፣ እራስ ላይ የመስራት ዋጋ አለው። የሚያሳድግህ ነገር ላይ ብታተኩር ለእድገትህ ቅርብ ትሆናለህ፣ የሚያደናቅፍህ ላይ ብታተኩር ውድቀትህ ከምታስበው በላይ ፈጣን ይሆናል። ስላለህ አብዝተህ አስብ የሌለህንም አስጨምር፣ ባለህ ነገር ለውጥ ለማምጣት ሞክር ከለውጥህም ቦሃላ የሚያስፈልግህን አሟላ። አንተ ጋር ያለ ሃይልና ጥበብ ማንም ጋር የለም፣ የመጠቀሙ ሃላፊነት የእራስህ ነው። ሰበብ ማብዛት፣ በአሉታዊነት መሞላት፣ በየጊዜው ትኩረትን መረበሽ አያዋጣህምና በትኩረትህ የህይወት ፈተናህን አሸንፍ፣ ለስኬትህም እራስህ ዋስትና ሁን።


ስፍራሽን አትልቀቂ!

ብዙ ነገሮች በእጅ ላይ ሳሉ ይረክሳሉ፣ ሲሄዱ ግን ይወደዳሉ፤ አንጀት ይበላሉ፤ ይናፈቃሉ። ምርጫው ነሽና ደስ ይበልሽ፤ አክብሮሻልና ክብር ይሰማሽ፤ ወዶሻልና ተወዳጅ ሁኚለት። አምናሃለችና ታመንላት፤ በእላይዋ ላይ አንግሳሃለችና ንገስላት፤ ተማምናብሃለችና ጠባቂዋ ሁንላት። ንፁ መልካም ስሜትን ማግኘት ቀላል አይደለም፤ ከልቡ የሚወድ፣ ከአንጀቱ የሚያከብር፣ ከነክፍተቱ፣ ከነድክመቱ ማፍቀር የሚችል ሰው ማግኘት እድለኝነትም፣ መመረጥም ነው። ማንም ሰው ተፈጥሮው ደካማ ያደርገዋል፤ ሰውነቱ ያሳስተዋል፤ ማንነቱ ይፈትነዋል፤ ማስተዋልና እውቀቱ ይጥለዋል። ነገር ግን በእንደዚ አይነት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የልብ ወዳጅ፣ ተንከባካቢና አፍቃሪ አያጣም። ወዳጅሽ ያላየብሽን ክፍተት በእርሱ ውስጥ በመፈለግ አትድከሚ፤ አፍቃሪሽ የተቀበለልሽን እውነታ ለመካድ አትሞክሪ። ማንም ፍፁም ሰው ፈልጎ አይወዳጅም ምክንያቱም ቢፈልግም አያገኝምና።

አዎ! ጀግኒት..! ስፍራሽን አትልቀቂ፤ ከዙፋንሽ አትውረጂ፤ ከክብርሽ አትነሺ። የተሰጠሽን ውድ ስፍራ በሚገባ አስጠብቂ፤ ሲወዱሽ መወደዱን፣ ሲያፈቅርሩሽ መፈቀሩን፣ ሲያከብሩሽ መከበሩን እወቂበት። ወዳጅ ፍቅሩ የዋህ ያደርገዋል፤ ስሜቱን ይገዛዋል፤ ማንነቱን ይቀይረዋል። አንቺን መምረጡ በስሜትም ይሁን በስሌት ፍቅሩን ይገልፅለታል። የመረጠሽ እርሱ ቢሆንም ምርጫውን እንዳሽር የማድረግ አቅሙ ግን አንቺ ጋር ነው። የሰው ልጅ ወዳጁን መውደድ ቢችል እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን ፍቅርን በፍቅር መመለስ ባይችልም በጥፋት፣ በጥላቻና በክፋት ባይመልስ ይበጃል። ወዳጅ ውድ በሆነበት ዘመን ተወዳጅ ሆኖ መገኘት መመረጥ ነውና በሚገባ ተጠቀሚበት።

አዎ! ጀግናዬ..! ውድነትህ በቶሎ ይግባህ፤ የተሰጠህን ስፍራ በሚገባ እወቀው፤ ከነሙሉ ማንነትህ ለተቀበሉህ ሰዎች ክብር ይኑርህ። ብዙዎች የሚናፍቁትን ግንኙነት፣ ብዙዎች የሚመኙትን እንክብካቤና ፍቅር አያያዙን እወቅበት። ምርጫው ያደረገህ ሰው እንደሚወድህ ማንም እንደማይወድህ እወቅ። ክብርህ በእጅህ እያለ ፍለጋ አትውጣ። ቤትህ የመጣን ፍቅር በጥላቻ አታባረው። ፍቅርን የሚያውቅ ይፈቀራል፤ የሰላምን ዋጋ የተረዳ ሰላምን ይመርጣል፤ ወዳጅ ልብ ያለው ይወደዳል። በውስጥህ የሌለው ነፁ ስሜት ኬትም ሊመጣልህ አይችልም። አዛኝ ሳትሆን አይታዘንልህም፤ ርህራሄ ሳይኖርህ ሩህሩህ ሰው አይገጥምህም። በዚህም በዚም የሆንክው በዓካል ተገልጦ ታገኘዋለህ። ደጋግመህ ያየሀው መጥፎም ይሁን ጥሩ ምኞት ሳይውል ሳያድር በህይወትህ ይከሰታል። የተሰጠህን ስጦታ ተንከባከብ፤ በእርግጥም ፍቅር እንደሚገባህ አስመስክር፤ ከብዙዎች መመረጥህ ትክክል እንደሆነ በተግባር አረጋግጥ፤ ስትወደድ ተወዳጅ ሆነህ ተገኝ።


መጣለሁ ስላሉህ አይመጡም!

ከእራስህ የሚፈልቅ ነገር እያሰብክ ዘመናት ያልፋሉ፤ ካንተ የሚወጣ ነገር እየጠበቅ ቀኑ ይጨልምብሃል፤ ፀሃይዋ ታዘቀዝቃለች፣ ጉልበትህ ይከዳሃል፤ ወኔህ ይሸሽሃል። ትክክለኛ ጊዜ አለ፤ ትክክል የመሰለህ ጊዜ ይኖራል ነገር ግን እየመሰለህ ስለቀጠለ ብቻ ትክክል አይደለም። የእራስህ የሆነ የጊዜ ገደብ አለህ፤ የምታምንበት ሂደት፣ የምትጠብቀው እርምጃ፣ የሚገባህ ውጤት አለ። በምክንያት ትንቀሳቀሳለህ፤ አስበህ ትጓዛለህ፣ መርምረህ ትራመዳለህ። ሰዎች ብዙ ነገር ያደርጋሉ ያንተ ድርጊት ግን አቅምህን ያማከለ፣ ማንነትህን ያገናዘበ፣ ፍላጎትህን የሚጠቅም መሆን ይኖርበታል። ሰዎች ሲወስኑልህ፣ ሰዎችን ስትከተል፣ የረገጡበት ስትረግጥ፣ በኮቴያቸው ስትመራ ቆይተህ ይሆናል። ወደፊት መሔደህን እንጂ ምን ለማግኘት እንደምትሔድም አላስተዋልክም ይሆናል። እራስህ ላይ መወሰን ካልቻክ አይንህ እያየ፣ የማስተዋል አቅምህ ወርዶ መሪዬ ነው የምትለው አካል እንደፈለገው እንዲጫወትብህ ትፈቅዳለህ።

አዎ! ጀግናዬ..! መጣለሁ ስላሉህ አይመጡም፤ መኖራቸው ብቻ ዋስትና አይሆንህም፤ እንዳሉህ ስለምታውቅ ብቻ አይገለጡም። ትልቅ ስራን ይፈልጋሉ፣ ፅናትን ይሻሉ፣ ያለመታከት መልፋትን፣ ያለእረፍት መጣርን ይፈልጋሉ። እርግጥ ነው ውስጥህ ያንተ ብቻ የሆነ ክህሎት አለ፤ ነገር ግን ካልወጣ፣ ካልተኖረ፣ ካልተተገበረ መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም። እጅህ ላይ ያለውን ነገር ክብደት የምታውቀው አንተ ነህ፤ ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብህ፣ ምን እንደሚጠበቅብህ፣ ኬት መነሳት እንደሚገባህም የምታውቀው አንተ ነህ። ሃሳቦችህን ያላሰበልህ ሰው፣ የጋራ ረዕይና ውጥን የሌላችሁ አካል በምንም ሚዛን ባንተ ህይወት ላይ ስልጣን ሊኖረው አይችልም። ያንተን ፍቃድ የሚፈልጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ ዋነኞቹም እራስን መሆን፣ በእራስ መመራት፣ በእራስ መንገድ መጓዝና በእራስ መተማመን ናቸው። በእራስህ ካልኮራህ ሌሎች እንድትኮራባቸው ሊያደርጉህ ይችላሉ፤ በእራስህ ካልተመራህ ሌሎች ይመሩሃል፤ የእራስህ አቋም ከሌለህ በሌሎች የውሳኔ አዙሪት መዋተትህ አይቀርም።

አዎ! ላንተ ካንተ በላይ የሚያውቅልህ፣ አንተን እንዳንተ የሚመራህ፣ ባንተ ውስጥ እንዳንተ የሚያነቃቃህ፣ ጉልበት የሚሰጥህ፣ የሚያረጋጋህ ሌላ ሰው የለም። አምላክ የሰጠህን ለእራስ አለቃ የመሆን ስልጣን ባትጠቀመው የአለቃ መዓት ሲፈራረቅብህ፣ የጫናዎች ብዛት ሲያሰቃይህ፣ የችግር መዓት ሲያስጨንቅህ ትመለከታለህ። በእራስህ ህይወት አንተ እራስህ ክስተት ካልሆንክ ማንም ክስተት ሆኖ ህይወትህን የሚቀይር፣ አላማህን የሚኖርልህ፣ ሃሳብህን የሚያሳካ፣ ለግብህ የሚያቀርብህ፣ ስኬትህን የሚያፈጥንልህ ሰው የለም። ማንም እንደሌለህም እያወክ ጥበቃህን ካላቆምክ፣ በእራስህ መንቀሳቀስ ካልጀመርክ ከጥበቃው ባሻገር ቀፅፎ የያዘህ አንዳች ከባድ ጉዳይ መኖሩን ልትመረምር ይገባል። ያንተ እቅድ የሚሰራው ባንተ ህይወት ውስጥ ብቻ ነው፤ የሌሎች እቅድም የሚሰራው በሌሎች ህይወት ውስጥ ነው። ያንተ ትልቅ ጉዳይ ለሌላው ምንም ነው፤ አንተን የማያስተኛህ፣ እንቅልፍ የሚነሳህ ነገር ለሌላው የጫወታና ስላቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል። እርምጃህን ሁሉ በእራስህ ሚዛን መለካት ጀምር፤ የምትፈልገውን ነገር እንዳቅምህ ከእራስህ ብቻ ጠብቅ፤ ሌላውን ወዳጅ እራስህንም እንደ ባዳ መመልከት አቁም። ማንም ሰው የሚያስብልህ፣ የሚቆረቆርለህ፣ የሚያዝንልህ ቢመስልህም ካንተ በላይ ላንተ እንደማያደርገው እወቅ። ለእራስህ ኖረህ፣ እራስህን አስከብር።


ፈቃድህ ፈቃዴ ይሁን!

ከራስ ጋር ንግግር፦ "ለራሴ የማውቅ ይመስለኝ ነበር ነገር ግን በፍፁም አላውቅም፤ የሚሆነኝን መምረጥ የምችል፣ የሚገባኝን የማደርግ ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን ምርጫዬ ስህተት ነበር፣ ድርጊቴ መጥፎ ነበር። እንግዲ ትናንት ተሳሳትኩ፣ ትናንት ወደቅኩ፣ በማይሆንኝ መንገድ ተጓዝኩ፣ የማይሆነኝን ተግባር ፈፀምኩ ዛሬ ግን ያንተን ፍቃድ ላስቀድም ወደድኩ፣ አሁን ግን ባንተ ቀዳሚነት ልከተልህ ወሰንኩ። ለራሴ የማስበው ትልቅ እንደሆነ አስብ ነበር አንተ ያሰብክልኝን ስመለከት ግን ምንያህል ለራሴ በትንሹ እንዳሰብኩ ተረዳው። በእውቀቷ የምትመካ ነፍስ ከእውቀቷ በላይ ጠላት የላትም፣ ለራሴ ከእኔ በላይ የሚውቅ የለም ያለ ሰው የፈጣሪውን በረከት የሚርቅ ሰው ነው። ብዙ ጊዜ "እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ፣ የእኔ ምርጫ ብቻ ነው ትክክል፣ በእኔ ህይወት ማንም አይመለከተውም" ብዬ ፎክሬ ነበር። የሆንኩትን ስሆን የደረሰብኝ ሲደርስብኝ ግን መታረምን መርጬያለሁ፣ ዳግም ላለመውደቅ ራሴን ጠብቄያለሁ። ብቻዬን እንደሆንኩ ሳስብ የመንፈስ ድካሜ ሊጥለኝ ይሞክራል፣ ያንተ ፍቃድ አለማስተዋሌ ሲታወቀኝ ተነሳሽነቴ ሁሉ ይጠፋል።

አዎ! ፈቃድህ ፈቃዴ ይሁን፤ ምርጫህ ምርጫዬ ይሁን፣ ፍላጎትህ ፍላጎቴ ይሁን። አንተ እጄን ይዘህ ምራኝ፣ በጨለማው በዱር በቀደሉ፣ አቀበት ቁልቁለቱ በአውላላው ሜዳ ላይ፣ በችግር በመከራ በምቾቱ በእጦቱ ሁሉ አንተ ከፊቴ ቅደምልኝ። ያ ፍፁም ሃሳብህ በእኔ ላይ ይደረግ፣ ያ ምስራችን የሚያመጣልኝ፣ ብርታትን የሚድለኝ፣ ውስጤን በሃሴት የሚሞላው፣ ልቤን የሚያሞቀው ምርጫህ በእኔ ላይ ይሁን። ከእቅፍህ ወጥቼ ዳግም መሰቃየትን አልፈልግም፣ ህግህን ጥሼ እንደገና ዋጋ መክፈል አልፈልግም። ምራኝ ብዬ እጄን ሰጥቼሃለሁ፣ መንገድህ መንገዴ ይሁን ብዬ ወዳንተ ቀርቤያለሁ። ውሳኔዬ ትልቅ ነውና እንዲሁ መፈፀም ቢከብደኝ እንኳን አንተ በእኔ ላይ አድረህ ፈፅምልኝ። ለዓመታት የታሰርኩበት መጥፎም ጥሩም ልማድ አለኝ። ከእሱም በአንዴ ነቅዬ መውጣት ይሳነኝ ይሆናል፣ አንተ ግን እርሱን ማድረግ ትችላለህና ነቅለህ አስወጣኝ፣ እኔንም ገፍትረህ ወደ መረጥክልኝ ጎራ ቀላቅለኝ። አቅሜ አንተ ነህ፣ ብርታቴ አንተ ነህ።"

አዎ! ጀግናዬ..! ረጅም ርቀት ሩቅ መንገድ በራስህ ምርጫ በራስህ ውሳኔ ተጉዘሃል፣ ያለማንም ጣልቃገብነት፣ ያለማንም አስገጅነት በራስህ ፍቃድ ብዙ ስህተቶችን ፈፅመሃል፣ ዛሬ ላይ ልታነሳቸው ይቅርና ልታስባቸው እንኳን የማትደፍራቸውን ተግባራት ፍፅመሃል። ምርጫና ውሳኔዎችህ ላይ የአምላክ ፍቃድ፣ የእርሱም ጣልቃገብነት ቢኖርበት ዛሬ በትናንት ምርጫዎችህ ባላፈርክ፣ ስራዎችህንም ለመናገር ባላፈርክ ነበር። ማንም ሰው መንፈሱ ሲደሀይ ስጋው መራመድ ያቅተዋል፣ ውስጡ በባዶነት ሲሞላ ሰላምና መረጋጋት ይርቀዋል። መንፈሳዊ ህይወትህን ችላ ብለህ፣ ከፈጣሪህ ጋር ያለህን ግንኙነት ረስተህ፣ ዓለምና ዓለምን ብቻ መርጠህ በፍፁም ረፍትና ሰላምን ልታገኝ አትችልም። መንፈሳዊ እድገት የሌለበት ህይወት ባዶ ነው፣ እግዚአብሔር አምላክ ያልባረከው ቤት ተስፋቢስ ነው። ያለምንም ክፍያ ያገኘሀውን ጊዜ ለሰጪው ለመስጠት አትሰስት፣ ከአምላክህ ጋር በፍቅር ውደቅ፣ የእጆችህ ስራዎችም ይባረኩልህ ዘንድ ፍላጎትህን በርሱ ፍቃድ ላይ አፅና።


በሙላት ትረፍ!

የጀምርከው መንገድ የምትኖርበትን ገቢ አያሳጣህም፤ የመረጥከው ስራ እንጀራ አይነፍግህም፤ የምታገኘው ንብረት እንደፈለክ እንዳትዝናና አይከለክልህም። ህይወት ግን ገቢ ማግኘት፣ እንጀራ መብላት፣ የእራስን ፍላጎት ብቻ ማሟላት፣ በተገኘው አጋጣሚ ገንዘብ ማጥፋት፣ መዝናናት፣ ገፅታን እያበሩ ውስጥን ሸፍኖ መመላለስ ብቻ አይደለም። ህይወት ከዚህም በላይ ነው። መኖር እስከቻልክ ድረስ የፈለከውን፣ ያመንክበትን፣ የመረጥከውን ሁሉ የመቀየር አቅሙ አለህ፤ እርካታህን ከራስህ በላይ ለሌሎች ማሳለፍ ትችላለህ። ብዙ ነገር ታደርጋለህ፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር እኩል ነፍስህን አይመዝኗትም፤ ሃሴት አይሰጧትም፤ አያረጋጓትም። ምርጫው ያንተ ነው፤ የትኛው ያድስሃል? የትኛውም ስለመኖርህ ማረጋገጫ ይሆንሃል? በየትኛው ትረካለህ? የቱስ ወደፊት ይመራሃል? አምላክህን በደስታ ለምስጋና ያስታውስሃል?

አዎ! ጀግናዬ..! በሙላት ትረፍ፤ በመትረፍረፍ ህይወትህን ሙላት። ንጋትህ ማመስገኛ ነው፤ ጠዋትህ የመቆየትህ ነፀብራቅ ነው። ዛሬ ውስጥ ምን አይነት ግሩም ህይወት እንዳለ ተመልከት፤ የፀሃይዋን ብረሃን፣ የሰውን እንቅስቃሴ፣ የተፈጥሮን ውበት ተመልከት። በአድናቆት ውስጥ ህይወት አለ፤ በደስታ ውስጥ ነፍስ ትስቃለች፣ ሃሴትን ታደርጋለች፣ አምላኳን ታወድሳለች። ምስጋና የሌለው ህይወት፣ በምሬት የተሞላ ህይወት፣ እራስን በማዳመጥ፣ አምላክን በማግኘት ያልታነፅ ኑሮ በአደጋ ብዛት እንደተዳከመ ተሽከርካሪ ነው። ሂድ ብትለው አይሄድም፤ በአግባቡ እስካልተጠገነ ድረስ የተወሰነ እርምጃም መጓዝ አይችልም። በብሶት ታመህ፣ በምሬት ታስረህ፣ በችግርህ ተውጠህ ቀናውን ላትመለከት ትችላለህ፤ ምስጋና ላይቀናህ ይችላል። ነገር ግን ህይወት በመካራ ውስጥም ለምስጋና መፋጠን ነው፤ በስቃይ መሃልም የተሻለውን ማለም ነው፤ ከችግርም በላይ ጠንክሮ መገኘት ነው።

አዎ! የህይወትን ትርጉም ትለያለህ፤ የመኖርን ገፅታ ትቀይራለህ፤ ሁኔታዋናን ታሻሽላለህ። ከምትችለው በላይ አትበላም፤ ከአቅምህ በላይም አትንቀሳቀስም፤ ከልኬትህ በላይ አትታገልም። የጭንቀትህም ምክንያት በልክህ አለማሰብህ ነው፤ የምትችለውን አለመለየትህ ነው፤ የሚያዋጣህን አለማወቅህ ነው። ህይወትን በሚገባው መጠን፣ በሚቻለው እርከን እየተንቀሳቀሰ በሙላት የሚኖራት ሰው ስለምን በብሶትና በለቅሶ ሊማረር ይችላል? ለምስጋና የሚፋጠን፣ ውስጡን የሚያዳምጥ፣ መኖርን እንደ ስጦታ፣ መሰንበትንም እንደ በረከት የሚመለከት ሰው ስለምን በጭንቀት ሊብከነከን፣ በሃዘንም ሊታወክ ይችላል? ምክንያት ከፈለክ ይኖርሃል፤ ነገር ግን አይጠቅምህም። ሁሌም በመኖር ውስጥ የተሻለ ነገር በእጅህ ላይ እንዳለ እያሰብክ፣ የተሻለውም እንደሚመጣ አምነህ በእያንዳንዱ ቅፅበታትህ መደሰትና ማመስገን ጀምር።


ምንድነው የምታደርገው?

ምንድነው የምታደርገው? መቼ? ማንም ሰው ሳያምንብህ ሲቀር፣ መቼ? ማንም ከጎንህ በሌለበት ሰዓት፣ መቼ? የሚረዳህን ባጣህበት ሰዓት፣ መቼ? በውድቀትህ ጊዜ፣ በተሳሳትክ ወቅት፣ ቀኑ በጨለመብህ፣ መሔጃ በጠፋብህ፣ ተስፋህ በተመናመነበት፣ እቅዶችህ ሁሉ በከሸፉበት ወቅት ምንድነው የምታደርገው? በእርግጥ ምን ትከውናለህ? ቁጭ ብለህ እራስህን ትወቅሳለህ ወይስ አይንህን ከፍተህ ለመጪው ጊዜ እራስህን ታዘጋጃለህ? ምክንያት እየደረደርክ ታለቃቅሳለህ ወይስ ለሆነው ሁሉ ሃላፊነትን ትወስዳለህ? ቁጭ ብለህ እራስህን ታረጋጋለህ ወይስ እራስህን መውቀስ ትጀምራለህ? ጉዞህን ትገታለህ ወይስ ይበልጥ ጠንክረህ ረጅም ለመጓዝ ትነሳለህ?

አዎ! ጀግናዬ..! ምንድነው የምታደርገው? ሁሌም ነገሮች አልጋ በአልጋ የማይሆኑበት አለም ውስጥ ነው የምትኖረው፣ ሁሉም የከበበህ ሰው መልካሙን በማይመኙልህ ሁኔታ ውስጥ ትኖራለህ፣ ሁሉም እርምጃህ ውስጥ የሚያበረታታ ነገር ላታገኝ ትችላለህ፣ በየትኛውም ሙከራህ መሃል መውደቅ፣ መሳሳትና በሰዎች መተቸት ሊገጥምህ ይችላል። ብቻህን እንደጀመርከው ብቻህን ረጅም ርቀት መጓዝ የሚኖርብህ ሰዓት አለ፤ ምናልባት ካንተ የሚያገኙትን ነገር ሲያጡ የሚለዩህም ሰዎች ሊያጋጥሙህ ይችላል። ብዙ ፈተናዎች ሲደራረቡብህ የውስጥ ጩሀትህ ከወትሮው በተለየ ያይላል፣ ሙከራህ ሲከሽፍ፣ የጥረትህ ዋጋ ሳያገኝ ሲቀር፣ የጠበከው ሳይሆን ሲቀር ጭንቀት ወዳጅህ ይሆናል። ህልምህን ጨለማ ይወረዋል፤ ተስፋህን ውሃ ይበላዋል፤ አላማህ እንዳልነበር ይቀበራል።

አዎ! ያንን ጮክ ያለ ተስፋ የመቁረጥ፣ ዋጋ የማጣት፣ ተፈላጊ ያለመሆን፣ የስብራትና የህመም ድምፅ ስትሰማ በህይወትህ ምንም እንዳልቀረህ ታስባለህ፤ ለእራስህ መሆን እንደማትችል ይሰማሃል። ነገር ግን በዚህ ሰዓት ይህን ጥያቄ እራስህን ጠይቅ፦ "ምንድነው የማደርገው? የሚያድነኝ፣ የሚያነሳኝ፣ የሚያበረታኝ፣ ተስፋዬን የሚመልሰው አይነተኛ ተግባር ምንድነው? ምንስ ባደርግ የቀድሞ ማንነቴን መልሼ አገኘዋለሁ?" ብለህ እራስህን ጠይቅ። ጊዜያዊ ውድቀትህ እንዲጫወትብህ አትፍቀድ፤ አላፊው ጨለማ ህይወትህን እንዲያመሰቃቅል አታድርግ፤ ነገ በሚረሳ ጉዳይ ዋጋህን አታሳንስ። ቆም በል፣ ተረጋጋ ሌላኛውን ውስጣዊውን የለሆሳስ ድምፅ ለማዳመጥ ሞክር። በአምላኩ እንደሚተማመን የሚነግርህን ድምፅ፣ ነገ ሌላ ቀን እንደሆነ የሚያሳውቅህን ድምፅ፣ ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ የምትወጣበት መንገድ እንዳለ የሚነግርህን እውነተኛና በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላውን ድምፅ አዳምጥ። ከአንበሶች መንጋጋ ልጁ ዳንኤልን የታደገ አምላክ ሁሌም አብሮህ እንዳለ መቼም እንዳትረሳ።


እየተሰቃየህ እደግ!

ዓለም ለማንም ምህረት የላትም። ለፋህ አልለፋህ፣ ዋጋ ከፈልክ አልከፈልክ፣ ወደክ አልወደክ፣ ተሳሳት አልተሳሳትክ፣ ተተቸህ አልተተቸህ፣ እራስህን ሰጠሃት አልሰጠሃት በማንኛውም ጊዜ ልትሰብርህ ትችላለች፣ በየትኛውም ወቅት ተረማምዳብህ ልትሔድ ትችላለች። እስከተወሰነ ጊዜ ልፋትህ ምንም አያመጣልህም፤ ስቃይህ ምንም ክፍያ አያስገኝልህም፤ ጠንክሮ መስራትህ ወዴትም ፈቀቅ አያደርግህም፤ ከፈተና ፈተናን ብትሻገር፣ ከመከራ መከራን ብታልፍ፣ ከአስቸጋሪም አስቃቂውን የህይወትህን ክፍል በአሸናፊነት ብትሻገር ምንምአይነት ሽልማት ላታገኝ ትችላለህ፤ ምንም የተለየ ውጤት ላትመለከት ትችላለህ። ከሰውም ከዚህ የተለየ ነገር አትጠበቅ። ዋጋ ብትከፍልላቸውም የሚገፉህ አሉ፤ እራስህን ብትሰጣቸው ላንተ ምንም የተለየ ነገር የማያደርጉልህ ሰዎች ይኖራሉ።

አዎ! ጀግናዬ..! እየተሰቃየህ እደግ፤ እየታመምክ ተቀየር፤ ዋጋ እየከፈልክ ማንነትህን ገንባ፤ ውጫዊ ውጤት ባትመለከትም ውስጣዊ መሻሻልህን ከልብህ ተረዳው። ጊዜያዊውን ብለጠው፤ ከሚጠፋው ደመና በላይ ሁን፤ ወቅታዊውን የውስጥ ጫጫታ፣ ውስጣዊውን ምቾት ማጣትና ጨንቀት ተሻግረህ እለፍ። ባትለፋ፣ ባትጥር፣ ባትቸገር፣ ባትሰቃይ ምን የሚፈጠር ይመስልሃል? የቁም እስረኛ ትሆናለህ፣ ነፃነትህን በፍቃድህ ታስረክባለህ፣ ትርፍ አልባውን ህይወት እስከ ፍፃሜው መኖርን ትቀጥላለህ፣ በረከቶችህን መርሳት እርግማኖችህንም መቁጠር ትጀምራለህ፣ ሰበበኝነት፣ አማራሪነትና አልቃሻነት የየለት መገለጫህ ይሆናል። ዓለምን መስማት አቁምና ልብህን አዳምጥ፤ መረጃ መሰብሰብ አቁምና በተለየ መንገድ መታገል ጀምር፤ በገዛ ሃሳብህ መሰናከል አቁምና የተሻለውን ተግባራዊ ሃሳብ አመንጭ። ጥግ ይዞ በማለቃቀስ፣ ጀርባ ሰጥቶ ምክንያት በመደርደር ቢሆን ኖር ስንቶች ባለፈላቸው ነበር፣ ስንቶች ህይወታቸው በተቀየር፣ ስንቶችስ በተሳካላቸው ነበር፤ ከአላፊው ሁኔታ በላይ ሁን።

አዎ! ስኬትን መፈለግ በጀመርክ ሰዓት እራስህ ላይ ጨክነህ ለስቃይ እንደተዘጋጀህ እወቀው። ወደታላቅነት ጉዞ በጀመርክ ወቅት ለመፈተን፣ ለመውደቅ ለመነሳት፣ ለመሳሳት ለመታረም ተዘጋጅተህ እንደሆነ አስታውስ። ወደኋላ የመመለስ ምርጫ ሊኖርህ ይችላል፤ የማቆም መብት ይኖርሃል፤ ያነገብከውን ትልቅ ራዕይ፣ በልብህ የያዝከውን ተስፋ አሽቀንጥረህ መጣል ትችላለህ። ነገር ግን ገዛስ ቦሃላ ምን ይመጣል? ምቾት? ደስታ? መረጋጋት? ሰላም ማግኘት? በፍፁም አይደለም። የባሰው ትርጉም አልባ ጭንቀት ካቆምክ ማግስት ከቤትህ ይገባል፤ ዋጋቢስ የመሆኑ ስሜት ገና በጠዋቱ ያሰቃይህ ይጀምራል፤ ሚዛን አልባው ህይወት በተራነት እሳቤ ሊተበትብህ ሲጥር ትመለከታለህ። እየተሰቃየህ እደግ፤ ስሜቶችህን እየተጋፈጥክ ስኬትህን አሳድ፤ እየተጨነክ ህይወትህን ቀይር፤ እየተመታህ፣ እየተገፋህ ማንነትህን ስራው።


አምላክ ይሸልምሃል!

አንዳንድ ሰዎች አሉ ፍላጎታችውን ለመፈለግ በፍፁም የማይሰንፉ፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ ምኞታቸው እጃቸው ካልገባ በፍፁም አርፈው የማይቀመጡ፣ አንዳንድ ሰዎች አሉ የጀመሩትን መጨረስ የሞት ሽረት ጉዳይ የሚሆንባቸው። እነዚህ ሰዎች በእርግጥም ፍላጎታቸውን ያገኛሉ፣ በእርግጥም ወደፊታቸውን ብሩህ ያደርጋሉ፣ የእውነትም የሚመኙትን ህይወት ይኖራሉ። ዋናው ጉዳይ ማንም ሰው "የሚፈልገውን ነገር ምንያክል ይፈልገዋል?" የሚለው ጥያቄ ነው። ሰዎች የምርም ለሚፈልጉት ነገር ዋጋ መክፈል አይከብዳቸውም፣ የምርም ለሚያስጨንቃቸው ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት አያስቸግራቸውም። ሁላችንም ስጦታ አለን፣ ስጦታችንም ልባችንን ለሚያሞቀው ነገር የሚጠበቅብንን ዋጋ ሁሉ ከፍለን የማሸነፍ ስጦታ ነው። ከሚተጉት ጋር እግዚአብሔር ይሰራል፤ የሚጥሩትን በብዙ ይደግፋል፤ ከልባቸው ዋጋ ለመክፈል ለተዘጋጁ መንገዱን ሁሉ ያመቻቻል።

አዎ! ጀግናዬ..! ላለመሸነፍ ስትሰራ፣ እጅ ላለመስጠት ስትታገል፣ የተለየውን ማንነትህን ለመገንባት ስትጥር አምላክ ይሸልምሃል፤ ፍላጎትህን አይቶ በረከትን ይጨምርልሃል፣ ብርታት ይሰጥሃል፣ ስራውን ባንተ ላይ ይሰራል። ሁላችንም ፍላጎት እንዳለን እናውቃለን፣ ነገር ግን የምርም እንደምንፈልገው ለፈጣሪ አናሳየውም። እርግጥ ነው የምንፈልገውን ለማግኘት ወደፊት መጓዝ አለብን፣ እርግጥ ነው እንቅስቃሴ ያስፈልገናል፣ እርግጥ ነው የተወሰነ ርቀት ወደፊት መጠጋት አለብን፣ ነገር ግን ባለ በሌለ ሃይላችን ብንሮጥስ፣ በምንችለው አቅም ጠንክረን ብንሰራስ፣ እለት እለት በጥልቀትና በጥራት ብንሰራስ፣ ሁሌም ዋጋችንን ለመጨመር ያለማቋረጥ ብንተጋስ ምን ይፈጠራል?  የምንፈልገውን ነገር ምንያክል እንፈልጋለን? የምር ማድረግ የምትችሉትን ሁሉ እያደረጋችሁ እንደሆነ በጥልቀት እራሳችሁን መርምሩ፤ የምር ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ አትችሉምን? ከዚህ የተሻለ ህይወት አይገባችሁምን?

አዎ! ለሚረባ ነገር መጨነቅ ካለባችሁ ተጨነቁ፣ ህይወታችሁን እስከወዲያኛው የሚቀይር ከሆነ የሚጠበቅባችሁን ዋጋ ክፈሉ፣ የምርም ከትናንት የተሻላችሁ፣ ወደፊታችሁ ያማረ፣ የተማኛችሁትን እንድታሳኩ ከፈለጋችሁ በቸልተኝነት ህይወትን መምራት አቁሙ፤ የተነገራችሁን ሁሉ ማመን አቁሙ፤ ለተጠየቃችሁት ሁሉ እሺ ማለት አቁሙ። ማንም ሰው ብዙ የሚያውቅ ቢመስለው የማያውቀው ነገር እንደሚበልጥ ግን ማስታወስ ይኖርበታል፤ ማንም ሰው ደካማና ዋጋ ቢስ የሆነ ቢመስለው የመሰለው ነገር እውነት አለመሆኑን መረዳት ይጠበቅበታል። የሚሞክር ሰው አንድ ቀን መውጫውን በር ያገኘዋል፣ ከልቡ ለሚጥር ሰው የሆነ ጊዜ ቀን ይወጣለታል፣ የምር የሚፈልገውን ነገር የሚፈልግን ሰው አምላኩ ይረዳዋል። ፈጣሪ ከሚሰሩት ጋር ነው፤ አምላክ ሽንፈትን ተጠይፈው ከእርሱ ጋር እንደሚያሸንፉ ከሚያምኑት ጋር ይሰራል።


ሲደክመኝም እሰራለሁ!

ከእራስ ጋር ንግግር፦ "የሚታየኝን የማየት ነፃነት አለኝ፣ የሚሰማኝን የማዳመጥ ሙሉ መብት አለኝ፣ በምርጫዬ እራሴን እመራለሁ፣ ፈልጌ ስራሴን እፈትናለሁ። ከእያንዳንዱ ጥቃቅን ተግባሬ ጀርባ ውጤት እንዳለ አውቃለሁ፣ ከየትኛውም እርምጃዬ ቦሃላ መዳረሻ እንደሚኖር እረዳለሁ። በማውቀው ልክ መትጋቴን፣ በገባኝ ልክ መጣሬን አላቆምም። ስሜቴን በሚገባ አዳምጣለሁ፣ የሚበጀኝን ከአምላኬ ቀጥሎ ለእራሴ እኔ አውቃለሁ። ያዋጣኛል ባልኩት መንገድ እስከጥግ የመጓዝ ብርታቱ አለኝ፣ ለውሳኔዬ እስከመጨረሻው እፋለማለሁ፣ እራሴን አከብራለሁና ለእራሴ ለገባውት ቃልም እንዳቅሜ እታገላለሁ። አላማዬ የህይወት ስንቄ ነው። ትርጉም እስከሰጠኝ ድረስ፣ ህይወቴን እስከቀየረው ድረስ፣ ውስጤን እስካረጋጋው፣ ሰላሜንም እስከሰጠኝ ድረስ እርሱን መኖሬ የውዴታ ግዴታዬ ነው።

አዎ! ሲደክመኝም እሰራለሁ! ቢጨልምብኝም ብረሃንን መፈለጌን እቀጥላለሁ፣ ሲሰለቸኝም እጥራለሁ፤ ሲደብረኝም እተጋለሁ፣ ዝቅ ብደረገ፣ ብናቅ ብገፋም ያመንኩበትን አደርጋለሁ፣ ደጋግሜ ብወድቅም ደጋግሜ እሞክራለሁ፣ ደጋግሜ ብሳሳትም ደጋግሜ እራሴን አርማለሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው ለምወደው ማንነቴ፣ ለማከብረው እኔነቴና ለምሳሳለት ስብዕናዬ ነው። በውጣውረድ ከተሞላው ህይወቴ በላይ እንደሆንኩ አውቃለሁ፣ ከሚገጥሙኝ ፈታኝ ሁነቶች የሚልቅ ብርታት እንዳለኝ አውቃለሁ። ምቾት ባይሰጠኝም ማድረግ ያለብኝን አደርጋለሁ፤ ከማይጠቅመኝ ጋር አልታገልም ይልቅ የሚጠቅመኝ ላይ እለት እለት እሰራለሁ፣ የሚበጀኝን በጥንቃቄ እመርጣለሁ፣ ላመንኩበት ዋጋ እከፍላለሁ። በጥረቴ ልክም ህይወት እንደምትከፍለኝ በሚገባ አምናለሁ።"

አዎ! ጀግናዬ..! ጨለማ ውስጥ ብትሆን ብረሃንህን የማብራት አቅሙ አለህ፣ ውድቀት ቢደራረብብህ ዳግም እራስህን የማበርታት ወኔው አለህ። ከሙከራህ ከውጤት በላይ የምትጓዝበት መንገድ ላይ አተኩር፣ ከምትደርስበት መዳረሻ በተሻለ ለሚያደርስህ እቅድና ተግባር ትኩረት ስጥ። በስንፍና መፈተን፣ በትርጉም አልባው መንገድ ውስጥ መውደቅ፣ ለህይወት አስከፊ ገፅ መጋለጥ የሁሉም ሰው እጣፋንታ ነው። ምድርን እስካልተሰናበትክ ከየአቅጣጫው ከሚላኩብህ የህይወት እንቆቅልሾች ልታመልጥ አትችልም። እጣፈንታህን ከማማረር በላይ ለመቀየርር በየጊዜው አጥቂ መሆን ይኖርብሃል። መርከቧን ስታቃጥል የሚኖርህ አንድ አማራጭ ስኬት ብቻ ይሆናል፤ ምርጫ በመንሳት እራስህን ስታስጨንቅ ባለህ አንድ ወይም ሁለት የተገደበ አማራጭ ማንነትህን የመገምባት ብቸኛ አማራጭ ይኖርሃል። የምኞት ህይወትህ ከእራስህ ጋር ከምታደርገው አዎንታዊ ንግግር ቦሃላ ያለ ነውና እራስህን አበርታ፣ እራስህን አጠንክር፣ ለእራስህ ታመን።


አደጋውን ትቀንሳለህ!

እርምጃ ካልወሰድክ አሰልቺው ህይወት ይቀጥላል፤ በእራስህ ላይ ካልጨከንክ፣ ደፋር ካልሆንክ ሸክሞችህ እየጨመሩ፣ ጫናዎችህ እየተደራረቡብህ ይመጣሉ። ከባድ እንደ ሆነ ግልፅ ነው፤ ባሉበት ተቀምጦ ከምንም ላይ የሆነ ነገር እንዲፈጠር ከመጠበቅ በላይ ግን አይከብድም። ተስፋ የሚኖርህ ይብዛም ይነስም በአቅምህ መንቀሳቀስ ስትችል ብቻ ነው። አቅሙን ሰቶህ፣ ብርታቱን አድሎህ፣ በሰውነትህ ፈልገህ የምታገኘውን ጥበብ ጨምሮለህ ያለምንም ጥረትና ድካም እንደመና ፈጣሪ ከሰማይ የሚያወርድለህ የተመቻቸ ስኬታማ ህይወት የለም። መቼም ሊኖር የማይችል ነገር ቢኖር ክፍያውን ሳይከፍሉ ውጤቱን ማጣጣም ነው። እርምጃ ለመውሰድ በዘገየህ ቁጥር፣ ህልምህን ከመኖር በጥቂቱ ባፈገፈክ ልክ፣ በህይወትህ ዙሪያ ቸልተኛ በሆንክ መጠን በቁጪት ወደተሞላው፣ አስፈሪና አስጨናቂ ህይወት እየተጠጋህ ትመጣለህ። ተስፋህ የሚለመልመው፣ የተሻለ ነገር የምታስበው፣ መልካም ክስተቶች በህይወትህ የሚከሰቱት የቻልከውን ያክል ስትሞክር ብቻ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! አደጋውን ትቀንሳለህ! እራስህን ታዳምጣለህ፤ ውስጥህን ታሳርፋለህ፤ ሰላምህን ታረጋግጣለህ። እንደመጣልህ ለመኖር ሳይሆን በእቅድ ለመመራት፣ አላማህን ለመያዝ፣ ውጥንህን ለመገንባት ትጥራለህ። አሁን "ከሰው ያነስክ፣ የማትረባ፣ ለማንም የማትጠቅም፣ ከሚገባህ በታች የምትኖር" እንደሆንክ የምታስብ ከሆነ በመጪዎቹ ጊዜያት ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስተውል? እነዚሁ ሃሳቦችህ በእጥፍ ይጨምራሉ፤ ጫናዎችህ ይበዛሉ፤ የተለያዩ ማህበራዊ ግዴታዎች ይታከሉበታል። ከአመታት በፊት መቀየር በምትችለው የወረደ አስተሳሰብ ምክንያት ቀጥለው ባሉ አመታት የወረደው ሃሳብ እውን ሆኖ፣ የህይወት ክብደት ጨምሮ፣ ተስፋህ ተሟጦ፣ ስጋት ወርሶህ እራስህን ታገኘዋለህ። ሲሰጡህ የነበሩትን መልካም ሃሳቦች፣ በቅንነት ስትመከር የነበሩ ምክሮችን ባለመቀበልህ በእራስህ ታዝናለህ፤ እራስህን በቁጪት መውቀስ ትጀምራለህ።

አዎ! ምንም ብታስብ፣ ተስፋ ብታደርግ ተስፋ ብትቆርጥ፣ ብታማርር ባታማርር፣ ብታመሰግን ባታመሰግን ጊዜ መሔዱን አያቆምም። አትራፊውን ድርጊትህን አንተ ታውቃለህ፤ አዋጩን ምርጫህን በሚገባ ትገነዘባለህ፤ ለህይወትህ የትኛው እንደሚጠቅምህም ግልፅ ነው። እድሜ ልክህን አዲስ ነገር ለመሞከር፣ ከአዲስ ከባቢ ለመቀላቀል፣ አዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ ፈርተህ፣ በሌለ አደጋ ስጋት ታጥረህ ትቆያለህን? ፈራህም አልፈራህም እድሜህ መጨመሩ አይቀርም፤ ተመችቶህም ይሁን ሳይመችህ መኖርህ አይቀርም። ከተፈጠሩት አስደንጋጭ ክስተቶች በላይ ገና የሚከሰቱት እንደሚበዙ ባሰብክ ቁጥር በእርግጥም ህይወትህ በሙሉ ስጋትና ሽበር በሚፈጥሩ አስደንጋጭ ክስተቶች መሞላት ይጀምራል፤ ማድረግ የምትችለውን ነገር ሳታደርግ ትቀራለህ፤ ተስፋ ታጣለህ፤ አቅም ያንስሃል። አንዳንዴ እርምጃም በትክክለኛው ሰዓት ካልተወሰደ ቦሃላ ቢፈለግም ወኔው ሊጠፋ ይችላል። ማስተካከል የሚገባህን ነገር ከስር ከስር እያስተካከልክ ተጓዝ፤ ረጅም የህይወት ስንቅ ይኑርህ፤ በማይወላውል አቋም ተመራ፤ ተስፋህን በእራስህ ፍጠር፤ በእራስ መተማመንህን በድፍረት ገንባ፤ በጊዜ ህይወትህን አንድ እርምጃ ወደፊት ማስኬድ ጀምር።


ህይወትህ ያንተ ነው!

ለትውስታ፦ አውቀህ ፈልገህ እራስህን እየፈተንከው ነውን? ሁን ብለህ እራስህን ጫና ውስጥ ከተሃልን? ወደህ ወዳጆችህን ለይተሃልን? ፈቅደህ እራስህን የለውጥ ሂደት፣ የእድገት ጉዞ ውስጥ ከተሃልን? ውሃ ያጠጣሀው ተክል መሬት ይይዛል፣ ያድጋል፣ ፍሬም ያፈራል። የሰራህበት ማንነት፣ ለአዲስ ክስተት ያጋለጥከው፣ የፈተንከውና ለከባድ ሁነት ያጋለጥከው አንተነትህም የተሻለ ሰው ሆኖ ታገኘዋለህ፣ ጠንካራና ብርቱ ሰው ሆኖ ታገኘዋለህ። በህይወትህ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ጉዳይ ውሃ አጠጣው፣ አጥብቀህ ስራበት፣ ዋጋ ክፈልበት፣ የሚገባውን ትኩረት ስጠው። ህይወትን እየቀለድክ አታሸንፈውም፤ ህይወትን ችላ እያልክ፣ ትኩረት እየነፈከው አታሻሽለውም። የህይወት ፈተናህ ሲያንስ፣ ጭንቀት ሲርቅህ፣ ከጫናዎች ውጪ ስትሆን በእርግጥ እያደክ እንዳልሆነ አስተውል።

አዎ! ጀግናዬ..! ህይወትህ ያንተ ነው አትቀልድበት፤ የግል ጉዳይ የእራስህ ነው፤ የሚመጣብህ እያንዳንዱ ፈተና ያንተን ጥንካሬ ይጠይቃል፤ ያንተን ብርታት ይፈልጋል። እላይ ታች፣ ወዲህ ወዲያ ማለትን በምትፈልግ አለም ውስጥ እየኖርክ ቁብነገር በሆነው ህይወትህ ብትቀልድ በተራው ህይወት በእራሱ ሲቀልድብህ መመልከትህ አይቀርልህም። አሁን አሁን ብዙዎቻችን ፋታ አጥተናል፣ ማረፍ አቅቶናል፣ ነገሮችን መረዳትና ማስተዋል ከብዶናል፣ ለማን ትኩረት መስጠት እንዳለብን፣ ምንንስ ማስቀደም እንደሚገባን ዘንግተናል። እዚም እዛም ጫወታ ያታልለናል፣ ቀልድ ማየቱ፣ ሌሎች በህይወታችን ሲያፌዙ አብሮ መሳቅን መርጠናል። በዚህ መንገድ ግን እራሳችንን ልናሸንፍ አንችልም። አንዳንዴም ቢሆን ለእራሳችን ብለን ቆምጠጥ ማለት ይኖርብናል። እየቀለድክ የምታድግበት የስራ ዘርፍ የለም፤ እያሾፍክ የሚለውጥህ ተግባርም አይኖርም።

አዎ! ቀልድም ይሁን ቁብነገር ያማረ ፍሬን ሊያፈራ የሚችለው ስራዬ ብለህ ወገብህን ታጥቀህ ስትይዘው ብቻ ነው። አንዳንዱ አንተን አይቶ፣ ሁኔታህን አንብቦ የስራህን ጥራት ያውቀዋል፤ አንዳንዱ ከጅማሬህ ተነስቶ የት እንደምትደርስ ይገነዘባል፣ ሌላው ደግሞ ተግባርህን ብቻ ተመልክቶ ለምን እንዳደረከው ይረዳል። ዘመንህን ሁሉ እየቀለድክ ብትኖር የቀልድህን ክፍያ በአመሻሹ የህይወትህ ክፍል ታገኘዋለህ፤ ዕድሜህን በሙሉ ወሬ በማመላለስና የሰዎችን ስራ በማደማመቅ ብቻ ብታሳልፍ የወጣችልህ ጀምበር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትጠልቅብህ አትጠራጠር። ህይወት በጫወታ ቢቻ የሚመራ፣ በቁብነገር ብቻም የታጠረ ጉዞ አይደለም። ሁለቱንም በማጣጣም ጎን ለጎን ማስኬድ የግድ ነው፤ ከሁሉም ከሁሉም ግን ቁብነገር በሆነው የህይወታችን ክፍል ላይ ማሾፍና መቀለድ የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍለን መረዳት ተገቢ ነው።


የሆነብህን ተቀበል!

ከባድ ያልከው ነገር የሚከብድህ አንተ አቅም ስላነሰህ፣ ደካማ ስለሆንክ ወይም የጉዳዩ ክብደት አይደለም። ነገሩን ቀለል አድርገህ መመልከት ስላልቻልክ ነው። የሆነው ሆኗልና ምንም አይደለም። its okay! ሆኖብህ ከተጎዳሀው በበለጠ ከመጎዳትህ ምን እንዳተረፍክ ለማወቅ ሞክር። የእኔ የምትላቸው፣ እንዲቀየሩና ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ የምትመኝላቸው የቅርብህ ሰዎች ሲያጠፉ ታያለህ፣ የማይመለከታቸውን ሲተነትኑ፣ በማያገባቸው ሲገቡ፣ ሰዎችን በመውቀስና በመስደብ ጊዜ ሲያጠፉ ትመለከታለህ። አንዴ የእኔ ናቸው፣ ወዳጆቼ ናቸው ብለህ አምነሃልና ወዳጅነታቸውን ባትፍቅ፣ ቅርበታቸውን ባታሻክር እንኳን እንዲሁ እንዳሉ መቀበልን ተለማመድ። ስንቶቻችን እንሆን በእራሳችን ጥፋት ሌሎችን ለመውቀስ የምንሮጥ? በእኛ በደል ሌሎችን ለመክሰስ የምንጣደፍ? ማንነታችን ሳንቀበል ሰዎች ለሆኑት ማንነት ለትቺት የምንፋጠን? ቅዱስ መፅሐፍ ይህን ይላል "የባልንጀራህን ጉድፍ ከማየትህ በፊት አይንህ ውስጥህ ያለውን ምሰሶ አውጣ።" ምሰሶ የሚያክል ድክመትና ሸክም ተሸክሞ ጉድፍን የምታክል ኢምንት ነገር አጉልቶ ለማየት መሞከር በእርግጥም ትልቅ ጥፋት ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! የሚያስተችህ፣ የሚያሰድብህ፣ የሚያሳንስህ፣ ክብርህን የሚያወርድ ቢሆን እንኳን የሆነብህን ተቀበል፤ እንዳለ ውሰደው፤ ቢመርህም ዋጠው። የቤተሰቦችህ የኑሮ ደረጃ ያሳስብሃል? ለምን ከዚህ ቤተሰብ ወጣው ብለህ ትቆጫለህ? ምናለ ከተሻለ ቤተሰብ ብወለድ ብለህ ትመኛለህ? አንድ ነገር አስታውስ፣ ይህን ሁላ ሃሳብ ማሰብ የቻልከው ከየትኛው ቤተሰብም ቢሆን ስለተወለድክ ነው፤ እንዴትም አድርገው ቢሆን አሳድገው ለዚ ስላበቁህ ነው። አንተ የመሆንህ ሚስጥር በሆኑ ማንኛውም ክስተቶች ማንንም ለመውቀስ አትቸኩል። የትም ብትወለድ፣ ከማንም ብትወለድ፣ ማንንም ብትተዋወቅ በምድራዊ ፈተናና ስቃይ በማታስበው አቅጣጫ መጠቃትህ አይቀርም፤ ያልጠበከው ዱብዳ እላይህ ላይ መውረዱ አይቀርም።

አዎ! እውነታውን የምታሸንፈው ታግለህ ሳይሆን ተቀብለህ ነው። የሌለህን ነገር የለህም፤ ያልተሰጠህ ነገር አልተሰጠህም፤ የማይገባህ ነገር አይገባህም፤ የማይመጥንህ ነገር አይመጥንህም። ለምን እያልክ መልስ በሌለው የማይረባ ጥያቄ እራስህን ከምታዞር፣ የምፈልገውን ነገር ግን ለጊዜው በእጅህ ላይ የሌለውን ነገር እንዴት ላገኘው እችላለሁ ብለህ እራስህን ጠይቅ። የስኬት ጅማሮ የት እንዳለህ ከማወቅ፣ ምን እንደምትፈልግ ከመለየት፣ ምን እንደሌለህ ከመረዳት ይጀምራል። አለም ሁሌም እንድታስደስትህ አትጠብቅ፤ ነገሮች በሙሉ ምቹና አልጋ በአልጋ እንዲሆኖ አትመኝ። ገና መኖር ስትጀምር ስቃይህ ጀምሯል፤ የምድርን ፍሬ ስትቀምስ ምሬቷንም አብረህ ቀምሰሃል። ሁሌም እየሳቁ፣ እየጨፈሩ፣ እየደነሱ፣ እየተዝናኑ፣ እየጮሁ፣ እያሙ፣ እየሰደቡ መኖር የለም። ምቾትን ብቻ ማሳደድ ስትጀምር መኖርህን ታቆማለህ፤ ምክንያቱም የቱንም ያክል ብትፈልገው አታገኘውምና። ባይሆን ስቃይህንም ተቀበለው፤ ለችግሮችህም እሺ በል፤ እውነታውን ለመቀየር አትታገል። የሆነውን አሜን ብለህ ተቀበል፤ እራስህን አረጋጋ፤ ትንፋሽ አስወጣ ንፋስ አስገባ። አለቀ፤ ህይወትን በውድነቷ ልክ ኑራት።


የሚታየው ይገልፅሃል!

አጥንት መጋጥን ሸሽተህ ወተት ብቻ እየተጋትክ፣ የሚያታግልህንና የሚያለፋህን ተግባር ተጠይፈህ በምቾት እየተመላለስክ፣ የምትችለውን ትተህ የሚቀልህን ብቻ እያደረክ፣ ብርታተህን ዘንግተህ ድካምህን ብቻ እያጎላህ፣ ጥንካሬህን ጥለህ ጉድለትህን እያሰብክ ከፍታን አታገኝም። የትም ብትሔድ፣ ሃገር ብትቀይር፣ ለቤተሰብህ ጀርባ ብትሰጥ፣ ከጓደኞችህ ብትነጠል፣ አዲስ መንገድ ብትመርጥ ለእራስህ የሰጠሀው ግምት እስካልተቀየረ ሌሎች የተቀየሩ ነገሮች በሙሉ ድካም ብቻ ይሆናሉ። ውስጥህ የተቀመጠው የደካማነት ስሜት ጥንካሬህን ሊገልጠው አይችልም፤ በእራስህ ተስፋ ቆርጠህ የሚታይህ ተስፋ የለም፤ በእራስ መተማመንህን አጥተህ ብርታትህ ኬትም አይመጣም። ነገሮች ሁሉ ከውስጥ እምነትህ፣ ከፅኑ ማንነትህ፣ ከአይበገሬው አንተነትህ ጋር የተያያዙ ናቸው። ውስጥህ ስትመለከት የሚሰማህ ስሜት ምንም ያክል ውጪ ሲወጣ ብትጨነቅለት፣ ብትጠነቀቅለት፣ ብታተኩርበት አፈትልኮ መውጣቱ የማይቀር ነው። ያመንከው ነገር ከውስጥ ነውና ምንም ውጫዊ ጫናና ሽክም ብታበዛበት ከማታገልና አቅመ ቢስ ከማድረግ ውጪ አንዳች የሚጨምርልህ ነገር አይኖርም።

አዎ! ጀግናዬ..! የሚታየው ይገልፅሃል!  እውነታው ዘወትር ደጋግመህ የምታደርገው፣ ሁሌም እራስህን ውስጡ የምታገኘው፣ ሳታስበው እየኖርክ የምትገኘው፣ ካለምንም ጫና ዝም ብሎ ወደውጭ የሚፈሰው፣ ያንተን መገደብና ለማስቀረት መሞከር የማሰማ እውነተኛው ማንነትህ ነው። አንድ እውነት አስታውስ ማንም ሰው ከዓይኑ በተሻለ ጆሮውን አያምንም፤ በተግባር ካየው በተሻለ የተነገረውን አይቀበልም፤ ቀጥታ ከተመለከተው በላይ በአሉባልታና በወሬ ደረጃ የተነገረውን አያምንም። ያንተም የሚታይ ተግባርና ስራ አንተነትህን የሚገልፀው ለዚህ ነው። ምንም ተዓምር የሚሰራ ሃሳብ ቢኖርህ ተገልጦ ካልታየ አንተ ማለት የተዓምራት ባለቤት ሳትሆን የተንሿ ማንኛውም የሚያደርጋት ተራ ልማድ ባለቤት ናት። ልትወደው ላትወደው፣ ሊያኮራህ ሊያሳፍርህ፣ ሊያሳድግህ ሊያሳንስህ ይችላል ነገር ግን ማስረዳት ሳይጠበቅብህ ብዙዎች በማየት ብቻ ሊረዱህ የሚችሉት ነገር ያንተ ጥልቅ ማንነት ነው።

አዎ! በማሰብ፣ በመጨነቅ፣ እራስን በማሳነስ አቅምህን አትግደል። ለእራስህ ነፃነት መስጠት ተለማመድ፤ በእራስ መተማመንህን አዳብር፤ ከሚያዩህ ሰዎች በተሻለ እራስህ ላይ አተኩር። "ማየት ማመን ነው።" በሚል መርህ የሚመራ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖርክ በሃሳብና እውቀትህ ብቻ ተቀባይነትና አመኔታን ማግኘት አትጠብቅ። ተጨባጭ፣ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚነካ፣ ውጤት የሚያመጣ፣ በሂደት የሚያድግ ነገር ያስፈልግሃል። በሔድክበት ሁሉ የሚገልፅህ፣ የሚያስጠራህ፣ ካንተ ጋር የሚወሳው ሃሳብህ ሳይሆን ስራህ ነው። የማያስብ ሰው አታገኝም፤ የማይመኝ፣ የማያልም ሰው አይኖርም፤ ሃሳቡን የሆነ ሰው ግን ብዙ አታገኝም። እራስህን ሁን ማለት በውጥህ የሚመላለሰውን እውነተኛ ማንነት አውጥተህ በገሃድ አሳየው፣ ከከባቢው ጋር አለማምደው፣ የተጫነበትን የፍራቻ ቀንበር አስወግድለት ማለት ነው። ማንም ሰው ይፈራል፣ ይሰጋል፣ ይጨነቃልና ያንተ በዚህ ሂደት ማለፍ አዲስ አይደለም። የዚህ ሸክምና ጭንቀት ማብቂያው ደግሞ በእርግጥም ተጋፍጠህ ስታሸንፍ ብቻ ነው። ትልቅነትን እያሰብክ፣ ከፍታን እየተመኘህ፣ ስኬትን እያለምክ ተለይቶ የመታየት፣ እራስህን የመሆን፣ በእራስህ መንገድ የመጓዝ ፍረሃት ካለብህ አይንህን ጨፍነህ፣ ጆሮህን ዘግተህም ቢሆን ከፍራቻው አጥር ለመውጣት በፅናት ታገል።


ሁሉም አለው!

ሁሉም ሰው የሚያፍርበት ታሪክ አለው፤ ሁሉም የሚያስጨንቀው፣ የሚያሳምመው ጉዳይ አለው። እንዲ ለብሶ ዘንጦ ሲታይ ምንም ችግር የሌለበት ይመስላል፤ ሰው ላይ ጣቱን ለመቀሰርና ለመፍረድ ሲፈጥን እርሱ ንፁና ነውር የሌለበት ይመስላል። ነገር ግን ችግሩን እርሱና አምላኩ ያውቁታል። ሰው ፊት ጨዋና ምንም የማያውቁ ይመስላሉ ነገር ግን ልባቸው ሌላ ነው፤ ውስጣቸው የተለየ ነው። በማስመሰል ድግግሞሽ ስንተ የሚሰቃይ ሰው አለ። አንተ ብቻ ሰነፍ እንደሆንክ፣ እንደማትችል፣ ትልቅ ቦታ እንደማትደርስ ይነግሩሃል እራሳቸው ግን ካንተ በታች መሆናቸው አይገነዘቡትም። አብዛኛው ሰው ያንተን ድክመትና ችግር አጉልቶ በማውራት የእራሱን ድክመትና ችግር ለመሸፈን ይሞክራል። ነገር ግን ህይወት እንደዚህ አትገፋም። ሁሉም ሰው የገዛ ሸክም አለው፤ አንተም አንዱ የእራስህ ሸክም ያለብህ ሰው ነህ።

አዎ! ጀግናዬ..! ሁሉም አለው! የትም ብትሔድ ከችግር የፀዳ፣ ድክመት የሌለበት፣ ክፍተት የማይታይበት ሰው የለም። የልቡን በልቡ ይዞ፣ ጭንቀቱን በጉያው ሸክፎ ያንተን ችግር ለማጉላት ቢሞክር አትገረም። አንተን እያየ ባንተ ለመፅናናት በሚያደርገው ጥረት ካንተ ተወዳድሮ አንድ ቀን መውደቁ አይቀርም። የእራሱን እሾህ ትቶ በባልንጀራው ላይ ያለውን ጉድፍ የሚመለከት ሰው ከማንም በላይ እራሱን ጠልፎ ለመጣል የተዘጋጀ ሰው ነው። ለእራስህ መሰናክል ካልሆንክ እንቅፋቶችህን ማስወገድ አይከብድህም፤ እራስህን ካወክ፣ ያለህበትን ከተረዳህ መዳረሻህ አይጠፋህም። ሸክምህን ለማውረድ፣ ችግርህን ለመቅረፍ፤ ክፍተትህን ለመሙላት በምታደርገው ማንኛውም ጥረት ምክንያት በሚደርስብህ ተፅዕኖ እንዳትሰበር፤ አንገትህን እንዳትደፋ።

አዎ! ይህን ያክል ውስብስብ አይደለም። ውድቀትህን ስለፈለጉ ብቻ አይጥሉህም፤ ዘወትር ችግርህን ደጋግመው ስላወሩ ብቻ ችጋራም አያደርጉህም፤ ተከታትለው ክፍተትህን ብቻ ስለነገሩህ ጠንካራ ጎንህን አያጠፉትም። እራስን በማወቅ አለም ውስጥ ከሚሉህ በተሻለ የሆንከውን ተቀበል፤ ከሚለጠፍብህ አሉታዊ ስም ባሻገር የሚገልፅህን አዎንታዊ ማንነት አጉልተህ አሳይ። እንደ ማነፃፃሪያና እንደ ሚዛን ስለተወሰድክ ብቻ ከደረጃህ ወርደህ፣ ቀለህ አትገኝ። ብቻህን ፈተና እንደተደራረበብህ፣ መፈናፈኛ እንዳጣህና ዋጋ እንደሌለህ አታስብ። ያንተን ጉዳይ ለእራስህ እንዲተዉት አድርግ። የእራሱን የማያልቅ ችግር ይዞ ያንተን ጉዳይ አጉልቶ ለመተንተን የሚሞክርን ሰው አትስማ። ሁሌም ቢሆን ያንተ ጉዳይ የሚፈታው ባንተና ባንተ ብቻ እንደሆነ ተረዳ።


ብዙ ታጣለህ!

አንዳንዶች ሁን ብለው አንዳንዶችም በልምድ ደጋግመው እራሳቸውን ይወቅሳሉ፣ ባላቸው ነገር ደስተኛ አይደሉም፣ እራሳቸው ላይ ህፀፅ ማውጣት ይወዳሉ፣ አብዝተው በበታችነት ስሜት ይዋጣሉ፣ ማንነታቸውን ለመቀበል አብዝተው ይቸገራሉ፣ በትንሹም በትልቁም በቀላሉ ይበሳጫሉ። ከእነዚህ አይነት ሰዎች ውስጥ አንደኛው ከሆንክ የእራስ ግንዛቤህን ደጋግመህ ማጤንና ለራስህ የምትሰጠውን ዋጋ መገንዘብ ይኖርብሃል። ሰዎች እንዲያዝኑልህ ምስኪን፣ ተጎጂ፣ ደካማና ብዙ ችግር የተደራረበበት ሰው መምሰል ትችላለህ ነገር ግን ከሰዎች ልታገኝ የምትችለው ከዘላቂው እርዳታ በላይ የአንድ ሰሞን ከንፈር መጠጣ ብቻ ይሆናል። ላንተ ለራስህ ካልሆነ ሁሌም ያንተ ዋጋቢስነትና ደካማነት ለማንም አጀንዳ እንደሆነ አይቀጥልም፣ ያንተ ደስታ ማጣት፣ ያንተ በአቃቂሮች መሞላት ለገዛ እራስህ እንጂ ለማንም የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይሆንም።

አዎ! ጀግናዬ..! የዋህ መስሎ ለመታየት፣ እንዲታዘንልህ፣ ተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት፣ ይበልጥ ለመወደድና እንክብካቤ ለማግኘት አስበህ ለራስህ የሆነውንከውንም ሆነ ያልሆንከውን የወረደ ስም እየሰጠህ ከቀጠልክ ብዙ ታጣለህ፣ ብዙ ዋጋም ትከፍላለህ። ውጪውን ታያለህ ከራስህ ህይወት ጋር ታነፃፅራለህ ለእራስህ ያነሰ ስፍራንም ትሰጣለህ፣ ድከመትህን ትቆጥራለህ፣ ካለህ በላይ የሌለህን ለሰዎችም ሆነ ለእራስህ ደጋግመህ ታወራለህ፣ የምትወደውን ነገር ስትጠየቅ የማትወደውን መዘርዘር ይቀናሃል፣ በተረጂነት ስሜት እራስህን የበታች ታደርጋለህ፣ ባለህ መርካትን አታውቅም፣ በትክክለኛው ማንነትህም ነገሮችን ማስተካከል እንደማትችል ታምናለህ። በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፍክ ከሆነ በእርግጠኝነት እውነተኛው ማንነትህን እየገደልከው ነው፤ ክብርህን እያወረድክ ነው፤ ደስትህን በፍቃድህ እያጣህ ነው፤ የህይወት አላማህን ከግብ ከማድረስ ወደኋላ እየቀረህ ነው።

አዎ! ለእራስህ የምትሰጠውን ቦታ አስተካክል፣ እራስህን የምትመለከትበትን መነፅር ቀይር፣ ለእራስህ ማዘንህ እራስህን በእራስህ እንድትቀይር እንጂ በሰዎች ሃዘኔታ ለመቀየር እንድትጥር አያድርግህ፣ ስለእራስህ በሚገባ እወቅ፣ ባወከው ልክ እለት እለት እራስህ ላይ ስራ። ከራስ ጋር ድበብቆሽ አይሰራም፤ ራስን እያሳነሱ የሚገኝ ክብር የለም፤ ለራስ የወረደ ቦታ እየሰጡ የተሻለ ስፍራ መድረስ አይቻልም። የሁሉም ጅማሮ እራስን ከድክመትና ክፍተቱ ጋር መቀበል ነው፣ ህይወትን ቀለል አድርጎ ለመኖር ወሳኙ አማራጭ እራስን መውደድ፣ ከራስ ጋር በማይቋረጥ ፍቅር መውደቅ ነው። ማንም ያጠፋልና ታጠፋለህ፣ ማንም በሃጢአት ይወድቃልና በሃጢአት ትወድቃለህ፣ ማንም ይበድላልና ትበድላለህ። ነገር ግን እራስህን ነፃ ማውጣት ከፈለክ የሆነውን ተቀብለህ፣ እራስህን በይቅርታ አድሰህ፣ ለእራስህ ማዘንህን እራስህን በማሳደግ እየገለጥክ ወደፊት ተጓዝ። ስለራስህ የምታስበውን መጥፎ ሃሳብ ቀይር፣ ህይወትህም በሂደት ሲቀየር ተመልከት።


ማጣትን ልመዱ!

በህይወታችሁ በአጋጣሚም ሆነ በምክንያት ብዙ ነገር ልታጡ ትችላላችሁ። ያላችሁን ሁሉ ከማጣትም በላይ የሆነ ጊዜ ባዶ እጃችሁን ልትቀሩ ትችላላችሁ። የእኔ የምትላቸውን ሰዎች ታጣላችሁ፣ ለዓመታት የደከማችሁበትን ሀብትና ንብረት ታጣላችሁ፣ ለረጅም ጊዜ የገነባችሁትን ስም በማይረባ ምክንያት ታጣላችሁ፣ ከራሳችሁ ጋር ሰጣገባ ውስጥ ገብታችሁ ራሳችሁን ታጣላችሁ። ነገር ግን ምንም እንኳን ማጣት አብዝቶ ቢጎበኛችሁ፣ ባዶነት ደጋግሞ ቢፈትናችሁ እናንተ ግን በባዶነትም ሆነ በማጣት ውስጥ መኖር እንደምትችሉ ራሳችሁን ማሳመን ይኖርባችኋል። የገነባችሁት ትልቅ ህንፃ ቢፈርስ እንኳን ዳግም ከዜሮ ተነስታችሁ ልትገነቡት እንደምትችሉ ከልባችሁ እመኑ። ምንም ነገር የሚሆነው በምክንያት ነው። ምክንያቱንም ለበጎ ወይም ለመጥፎ ማዋሉ የእናንተ ድርሻ ነው። "ከዛሬ ነገ ልወድቅ ነው፣ ያፈራውትን ንብረት አጣለው፣ የቀረበኝ ሰው ይርቀኛል፣ ሰው አጣለሁ፣ ብቻዬን ቀራለሁ" ብላችሁ ማድረግ ያለባችሁን ነገር ሳታደርጉ እንዳትቀሩ። በዓለም ልታሸንፉ የምትችሉት ከማጣት ቦሃላ ዳግም ቀና ማለት ስትችሉ፣ ከወድቀት ቦሃላም ዳግም ራሳችሁን መገንባት ስትችሉ ብቻ ነው።

አዎ! ማጣትን ልመዱ፣ እርዛቱን፣ ችግሩን፣ ውድቀቱን፣ ባዶነቱን፣ ብቸኝነቱን እያንዳንዱን አሉታዊውን የህይወትን የፈተና ገፅ ልመዱት። የችግር ብዛት ልባችሁን እንዲያስጨንቅ አትፍቀዱ፣ የአንድ ሰሞን ውድቀት ልባችሁን እንዲሰብር አትፍቀዱለት። ወዳጅና ጠላታችሁን ስታገኙ ሳይሆን ስታጡ እንደምትለዩ አስተውሉ። ችግርን መላመድ ጥበብ ነው፣ እስከ ህይወት ፍፃሜ ተቀበሎት መኖር ግን ሞኝነት ነው። ምንም ቢሆንባችሁ ከሁኔታው ጋር አትጋጩ፣ ምንም ቢደርስባችሁ የደረሰባችሁን ለመካድ አትታገሉ። ውስጣችሁ ያርፍ ዘንድ፣ ልባችሁ እንድትረጋጋ፣ አዕምሯችሁ በሚገባ እንዲያስብ ከተፈጠረው ክስተት ጋር ሰላም ፍጠሩ። ወደቀኝም ዞራችሁ ወደ ግራ፣ ወደላይም አላችሁ ወደታች የማይናጥ ፅኑ አቋም ካላችሁ ምንም ሁኔታ ሊያሸብራችሁ አይችልም። ዛሬ ታጣላችሁ ነገ ግን ታገኛላችሁ፣ ዛሬ ትታመማላችሁ ነገ ግን ፈውስን ታገኛላችሁ፣ ዛሬ ትራባላችሁ ነገ እናንተ ጠግባችሁ ብዙዎችን ታጠግባላችሁ፣ ዛሬ ውስጣችሁ ይረበሻል፣ የሚያስደነግጥ ክስተት ይፈጠርባችኋል፣ ከባባድ ክስተቶች ይፈጠሩባችኋል ነገ ግን ሁሉም ይቀየራል ውስጣችሁ ያርፋል፣ ሰላማችሁ ይመለሳል፣ ክስተቶቹም ጥሩ የህይወት ትምህርት ይሆኗችኋል።

አዎ! ጀግናዬ..! አሉልኝ ብለህ የተመካህባቸው ነገሮ ሁሉ ፊታቸውን ቢያዞሩብህ፣ ማንም አይንህን ለአፈር ብልህ እንኳን ለራስህ የሚያዝን ልቦና ካለህ የትኛውንም ነገር ከመሬት አንስተህ መገንባት እንደምትችል እመን። እምነትህም የሚወራ ሳይሆን የሚኖር፣ ማስረጃ የምትፈልግለት ሳይሆን ማስረጃው ፈልጎህ የሚመጣ ነው። በሰው መገፋት፣ መከዳት፣ ከሰው መጣላት፣ ሰው ፊት ክብርና ቦታ ማጣት ሁሉም በአንዴ በህይወትህ ሊከሰቱ ይችላሉ። ለክስተቶቹ የሰጠሀው ቦታና እነርሱን የምትረዳበት መንገድ ግን ሊያስተካክላቸውም ሊያጠፋቸውም ይችላል። "የሆነብኝ ነገር ከአቅሜ በላይ ነው፣ በሆነብኝ ላይ እኔ ስልጣኑ የለኝም።" ከሚለው የውሱንነት ገደብ ራስህን አውጣ። ዓለም ሁሌም ስኬትን አትሰጥህም፣ ምድር ላይ ሁሌም በምቾት አትመላለሱም። ታገኛለህ ታጠላህ፣ ስኬታማ ትሆናለህ በዛው ልክ ደጋግመህ ትወድቃለህ። ስታገኝ በደስታ ጮቤ የምትረግጥ ስታጣም ጥግ ይዘህ የምታለቅስ፣ ሲሳካልህ እዩኝ እዩኝ የምትል ስትወድቅም ደብቁኝ ደብቁኝ የምትል ከሆነ የገዛ ጠላትህ ራስህ እንደሆንክ አስተውል። ከሁኔታዎች ጋር ተስማማ፣ በማጣትም በማግኘት ውስጥ ትክክለኛ ማንነትህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ።


ፕሪማክ መርህ

የምንጊዜውም ድንቁ መፅሐፍ የልማድ ኃይል (Atomic Habits) ቀጣይነት ስላላቸው ትናንሽ ለውጦች ሃይልና ስለሚያመጡት አመርቂ ውጤት በጥልቀት ሲያትት እንመለከታለን። አያይዞም የምንፈልገውን ውጤታማ ልማድ ለመገንባት ልንተገብራቸው የሚገቡትን ህግጋቶች በግልፅ ያስቀምጣል። በመፃፉ ላይ ከተጠቀሱት አራት ህግጋት ውስጥ አንዱ የምንፈልገውን ልማድ ሳቢ የማድረግ ህግ ነው። በዚህም ውስጥ ፕሪማክ መርህ /Premack Principle/ ስለተባለው የስነልቦና ፅንሰ ሃሳብ በመጥቀስ ሁኔታውን ያብራራል። ይህም መርህ ምን ይላል "ብዙ ጊዜ የመደረግ እድል ያላቸው ባህሪያት ብዙ ጊዜ የመደረግ እድል የሌላቸው ባህሪያትን ያፀናሉ" የሚል ነው።

አዎ! የዚህ መርህ ውጤት እጅግ አስገራሚ ነው። በተለተለት የህይወት ምልልሳችን ዘወትር የምንደጋግማቸው አስደሳች ልማዶች ይኖሩናል። ይህም ክስተት ዶፓሚን (Dopamine) የተሰኘውን የሚያስደስተንን ነገር በማድረግ የምናገኘውን ውጤት በማሰብ የሚመነጨውን ኬሚካል (Chemical) ሰውነታችን እንዲላመደው ያደርጋል። ስለዚህ ሰውነታችን የለመደውን ተግባር ለመፈፀም በተዘጋጀን ሰዓት ውጤቱን እያሰብን እንደሰታለን፤ የተደጋገመውን ደስታ የለመደው ሰውነታችንም ሁሌም ተግባሩን እንድንከውን ይገፋፋናል። በሂደትም ተግባሩ ልማድና የደስታችን ምንጭ ሆኖ ይቀመጣል። በዚህም ሰዓት መገንባት፣ ማዳበር የፈለግነውን ባህሪ ከዚህ የደስታችን ምንጭ ከሆነው ልማዳችን ጋር በማቆራኘት ሳቢና ስሜት ሰጪ በማድረግ መገንባት እንችላለን።

አዎ! ጀግናዬ..! የፈለከውን አዲስ ልማድ መገንባት ትችላለህ። የፈለከው ልማድ መፅሐፍ ማንበብ ሊሆን ይችላል፤ በመንፈሳዊ ህይወትህ መጠከር ሊሆን ይችላል፤ በጠዋት መነሳት፣ በምስጋና ቀንህን መጀመር፣ የየለት ውሎህን እቅዶች ማስቀመጥ፣ የግል ክህሎትህን ማደበር ሊሆንም ይችላል፤ እነዚህንም በሚገባ መገንባት ትችላለህ። የተግባሩን ባህሪ ሳቢ፣ ውጤቱንም አስደሳች ማድረግ ብቻ በቂ ነው። ሁሌም ስታደርገው የሚያደስትህ ተግባር ካለ ከእርሱ በፊት አዲሱን ልትገነባው ያሰብከውን አዲስ ባህሪ ታስቀድማለህ። የሚያስደስትህን ተግባር ለመፈፀም ግዴታ አዲሱን ስራህን ማከናወን እንዳለብህ ለእራስህ ህግ ታስቀምጣለህ።

ፊልም ማየት የምትወድ ከሆነ ከእርሱ በፊት ቢያንስ አስር ገፅ መፅሐፍ ማንበብ እንዳለብህ ትወስናለህ፤ ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ከተመቸህ እነርሱን ለማግኘት ግዴታ የተወሰኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለብህ እራስህን ታሳምናለህ። በቀላሉ ከእያንዳዱ ከምትወደው ተግባር በፊት የፈለከው ነገር ግን እስካሁን ያልገነባሀውን ልማድ ታስቀድማለህ፤ በመደጋገም ትከውነዋለህ። ምቾት ባይኖረውም ማራኪና ሳቢነቱ ግን ሁኔታውን ቀለል ያደርገዋል። በመጨረሻም አስገራሚ ውጤት አምጥቶ ትመለከተዋለህ፤ በእራስህም ትዝናናለህ፤ በስኬትህም ትኮራለህ።


እራስህን አትጣ!

ፍቅር ይጎዳል? አዎ ይጎዳል፤ ፍቅር ያቆስላል? አዎ ያቆስላል፤ ፍቅር ያጃጅላል? አዎ በሚገባ ያጃጅላል። ፍቅር ያበረታል? አዎ ያበረታል፤ ፍቅር ይፈውሳል? አዎ ይፈውሳል፤ ፍቅር ያስተምራል? አዎ በሚገባ ያስተምራል። የትኛውም የፍቅር ግንኙነት ከሁለቱ ተቃራኒ መገለጫዎች የተለየ ትርጉም አይኖረውም። ግማሾቻችሁ ከፍቅር አትርፋችኋል፣ ግማሾቻችሁም ተጎድታችሁበታል፤ አንዳንዶቻችሁ በግንኙነታችሁ ተጠቅማችኋል፣ አንዳንዶቻችሁ ብዙ ተሰቃይታችኋል። ይሔ ሁኔታችሁ ግን የፍቅርን ትርጉም ሊቀይረው አይችልም። ልብሽ በፍቅር ቢሰበር የሚጠገነው በፍቅር ነው፤ ውስጥህ መረጋጋት ያጣው በፍቅር ከሆነ ዳግም የሚረጋጋው በፍቅር ነው። በችኮላ የምትመሰርቱት ጤነኛ ግንኙነት የለም፤ በጥድፊያ የምትገቡበት ትክክለኛ ፍቅር አይኖርም። በብዙ ያልተሳካ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ባለፋችሁ ቁጥር ወደፊት በሚኖራችሁ ግንኙነት ደስተኛና ስኬታማ የመሆን እድላችሁ እየቀነሰ ይመጣል።

አዎ! ፍቅር መልካም ነውና አፍቅሩ፣ ውደዱ፣ ተወዳጁ ነገር ግን በቅድሚያ ይበልጥ እራሳችሁን እንደምትወዱ እርግጠኛ ሁኑ። ለማንም የምትሰጡት ፍቅር ከእናንተ የተረፈ መሆን ይኖርበታል። ለእራሳችሁ ሳትሰጡ ለሰዎች የምትሰጡት ክብርም ሆነ ፍቅር ከልብ ሊሆን እንደማይችል እወቁ። ማንም ለእራሱ ሳይሆን ለሌላ ሰው ሊሆን አይችልም፤ ማንም እራሱን ሳያድን ማንንም ሊያድን አይችልም። ሁላችንም ያለንን እንሰጣለን፣ ልባችን ያነገበውን እናካፍላለን። አስቀድመህ በእራስህ ደስተኛ ሳትሆን ሌላ ሰው መጥቶ ደስተኛ ሊያደግህ አይችልም፤ መጀመሪያ ባለሽ ነገር ሙሉ እንደሆንሽ ሳይሰማሽ ማንም መጥቶ ሙሉ ሊያደርግሽ አይችልም። እናንተ ከምትወዷቸው በላይ የሚወዷችሁን ሰዎች በመጠበቅ ጊዜ አታጥፋ። ሰው እንዲወድህ በምትፈልገው ልክ እራስህን ውደድ።

አዎ! ጀግናዬ..! በፍቅር ሰበብ፣ በመውደድ፣ በመዋደድ ምክንያት እራስህን አትጣ፤ እንዲሁ በምናብ አትነዳ፤ በፍፁም በስሜትህ ቁጥጥር ስር አትውደቅ፤ እንዴትም የወደፊት ህይወትህን የሚያበላሽ ተግባር አትፈፅም። እራስህን ተቆጣጠር፣ ህልምህን አስብ። በፍቅር ውስጥ ጭልጥ ብለህ አትጥፋ፣ በግንኙነትህ ምክንያት ከአላማህ አትራቅ፣ ከቤተሰብህ አትቃረን። በሚቀያየር አለም የትም ብትሔድ የማይቀየረውን ማንነትህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ። ፍቅር የምትጀምረው እራስህን ልትጥልና ወዳጅህን ብቻ ልትንከባከብ አይደለም፤ የግንኙነትህ ዋና ጉዳይ የወዳጅህ ደስታ ብቻ ሳይሆን ያንተም ደስታና መረጋጋት ጭምር ነው። ለግንኙነትህ ግድ ይኑርህ፣ ለምትወደውና ለሚወድህ ሰው እንዲሁም ለግንኙነትህ ዋጋ ለመክፈልና ሃላፊነትህን ለመወጣት ዝግጁ ሁን።


በውሸት አትደልለው!

ካንተ የተሰወረ ነገር ያለ ይመስል የማያሳምኑ ምክንያቶችን እየደረደርክ እራስህን የበታችና አቅመቢስ አታድርገው። ለእራስህ የምትናገረው እያንዳንዱ ነገር ቀጥታ ከውስጣዊ ሃይልህና ተነሳሽነትህ ጋር እንደሚገናኝ እወቅ። ለተወሰነ ጊዜ እራስን መዋሸት ወይም ለአጭር ጊዜም እራስን መደለለ ይቻል ይሆናል ነገር በፍፁም እስከመጨረሻው እራስን እየዋሹና እያስመሰሉ መኖር አይቻልም። ምንም ነገር ከማድረግህ በፊት በነገርየው ዙሪያ ያለህን ግንዛቤ ከአንተ አቅም ጋር ማስማማት ይኖርብሃል። የማያውቁትን ስራ መጀመር በአየር እንደ ተሞላች ፊኛ አየር ላይ ያንሳፍፋል። ማስመሰል በማንኛውም ሰው ህይወት ውስጥ ይኖራል። የሌለውን እንዳለው፣ ያልደረሰበትን እንደደረሰበት፣ ያላሳካውን እንዳሳካው፣ ያልያዘውንም እንደያዘው አድርጎ የሚያዋራው ሰው ጥቂት አይደለም። እውነታውን ልቡ ያውቀዋል ነገር ግን ለሰዎች ብሎ እውነታውን ይክዳል፣ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ለእርሱ ግልፅ ነው ነገር ግን ሌሎችን እያምታታ መኖርን ይፈልጋል። ሌሎችን በማታለል ምኞቱን ለማሳካት ይጣጣራል።

አዎ! ጀግናዬ..! በውሸት አትደልለው! ያልሆነውን ማንነት እየሰጠህ ለከፋው ውድቀት አታመቻቸው፣ ለሰው ብለህ የገዛ እራስህ ጠላት አትሁን። እራስህን ክደህ፣ ትክክለኛ ማንነትህን ንቀህ፣ መገለጫዎችህን ጥለህ የምታገኘው ክብርም ሆነ ፍቅር ምንህ ነው? ሁሌም ከራስ ጋር ድብብቆሽ መጫወት አይሰለችምን? በየጊዜው ሁን ብሎ እራስን ማጥቃት አያሳምምን? ማንም የተቀባባ ማንነትህን ቢቀበልህ ከልቡ እንደማያደርገው ውስጥህም ያውቀዋል። እንኳን ሰውን ለማስደነቅ ለመኖር ይቅርና በቅጡ እራሳችንን ለማስደሰት ለመኖር እንኳን ያለችን ጊዜ አጭር እንደሆነች አስታውስ። ካልዋሸህ የማይወድህ፣ ካላስመሰልክ የማይቀበልህ ማህበረሰብ ያለ ይመስል በየሔድክበት የውሸት ቅባትህን መቀባት አቁም፤ ያገኘሀውን ሁሉ በማይመስል ታሪክ ማምታትህን አቁም። ለእራሱ ያልታመነ ሰው በምንም መንገድ በህይወቱ እምርታን ሊያመጣ አይችልም።

አዎ! ድብብቆሹ ይብቃህ፣ ለእራስህ ባዳ መሆን ይብቃህ፣ እራስህን መደለል አቁም። በማስመሰል ሰዎችን ልትገዛ ትችላለህ እራስህን ግን መግዛት አትችልም፤ በውሸት ብዙዎችን ልትማርክ ትችላለህ እራስህን ግን ልትማርክ አትችልም። እራስን ሳያሸንፉ ዓለምን ለማሸነፍ መሯሯጥ ትርፉ የውስጥ ስብራትና ባዶነት ነው። ማንም ከሚያውቅህ በላይ እራስህን ታውቀዋለህ፣ ማንም ከሚረዳህ በላይ እራስህን ትረዳዋለህ። ከእያንዳንዱ ያልተገባ እርምጃ ጀርባም ምን እንደሚመጣብህ ጠንቅቀህ ታውቃለህ። በማታለል ገፅህ ሊያሸበርቅ ይችላል ውስጥህ ግን መረጋጋት ይርቀዋል፣ በማስመሰል ንብረት ልታፈራ ትችላለህ ሰላምን ግን ታጣለህ። ስለራስህ የምታውቀውን እያወክ እንዳላዋቂ መኖር አቁም፤ የሚሰማህን ስሜት መግፋት፣ የእራስ ግንዛቤህን ችላ ማለት፣ ከእራስ በላይ ሌሎችን በእራስህ ላይ ማንገስ አቁም። ለእራስህ ታመን፣ ከነእንከኑ እውነተኛው ማንነትህን ተቀበል፣ እንዳቅምህም በሂደት እያሻሻልከው ተጓዝ።

20 last posts shown.