ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ ወንዶች በሴቶች ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፉ የሚያግድ ትዕዛዝ ፈረሙ!
ትዕዛዙ ጾታቸውን የቀየሩ አትሌቶች እንዲወዳደሩ በሚፈቅዱ ትምህርት ቤቶች ላይ ቅጣት አስቀምጧል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ ሰዎች በሴቶች ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይሳተፉ በሚያግደ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
"ወንዶችን ከሴቶች ስፖርት ማራቅ" የሚል ርዕስ የተሰጠው የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ወንድ ወይም ሴት የሚለው "ጾታ" ሲወለድ የሚያገኘው እንጂ የሚለውጠው እንዳልሆነ ይገልጻል።
ትራምፕ እግዳውን የሚደግፉ ሴት አትሌቶች በተገኙበት ፊርማቸውን ሲያኖሩ "በሴቶች ስፖርት ላይ የነበረው ጦርነት አብቅቶለታል፤ የእኔ አስተዳደር ወንዶች ከሴቶች ጋር እየተወዳደሩ ሴት አትሌቶችን ሲያሸንፉ ቆሞ አይመለከትም" ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ጾታቸውን የቀየሩ 15 ሺህ የአሜሪካ ጦር አባል ወታደሮችን ከስራ እንደሚያግዱ ተገለጸ
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ካሮሊን ሌቪት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በየአካባቢው የሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮችን የሚመለከት መሆኑን ተናግረዋል።
የስፖርት አስተዳዳሪ አካላት በተፈጥሯዊ የወንድ የእድገት ሂደት ውስጥ ያለፉ እና ፆታቸውን የለወጡ ሰዎች ዋና፣ አትሌቲክስ እና የጎልፍ ስፖርቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሴቶች በሚሳተፉባቸው የስፖርት ዘርፎች እንዳይወዳደሩ ታግደዋልም ነው ያሉት።
ትራምፕ ፊርማቸውን ያኖሩበት ትዕዛዝ ጾታቸውን የቀየሩ አትሌቶች በሴቶች ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ የአሜሪካ ትምህርት ሚኒስቴር ክትትል እንዲያደርግ ያዛል።
ጾታቸውን ወደ ሴት የቀየሩ ወንዶች ከሴቶች ጋር እንዲወዳደሩ የሚፈቅዱ ትምህርት ቤቶች ላይ ቅጣት እንደሚጣልባቸውም ያመላክታል ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
የአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ የ2028ቱን ኦሊምፒክ የምታስተናግድ መሆኑን ያወሱት ትራምፕ፥ አዲሱ ውሳኔ በዚህ ውድድርም ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የአለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውሳኔውን ማስፈጸም እንዳለበት በማሳሰብም በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ መሳተፍ የሚፈልጉ ፆታቸውን የቀየሩ አትሌቶች የመግቢያ ቪዛ እንደማይሰጣቸው አብራርተዋል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት "ሴት አትሌት ነን በማለት በማጭበርበር ወደ አሜሪካ የመግቢያ ቪዛ የሚጠይቁ ወንዶችን ማመልከቻ ውድቅ እንዲያደርግ" መመሪያ እንሚሰጡም ነው ያነሱት።
ጾታቸውን የቀየሩ አትሌቶች እንዲወዳደሩ የሚፈቅደው የአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን እንደመጡ ጾታቸውን በቀየሩ ሰዎች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
ጾታቸውን የቀየሩ ወታደሮች የአሜሪካን ጦር እንደማይቀላቀሉና አስቀድመው የለወጡ 15 ሺህ ወታደሮችም ከስራ እንደሚታገዱ መናገራቸው ይታወሳል።
የፌደራል የጤና መድህን እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችንም እንዳያገኙ የሚያግዱ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።
Via አልአይን አማርኛ
@Skysport_Ethiopia@Skysport_Ethiopia